Print this page
Saturday, 03 October 2015 10:19

የወንዶች የጡት ካንሰር በሽታ

Written by 
Rate this item
(6 votes)

      የካንሰር አይነቶች በርካታ ቢሆኑም ሁሉም ካንሰሮች ግን መነሻ ምክንያታቸው በሰውነታችን ሴሎች ላይ የሚከሰተው ያልተለመደ የሴሎች እድገትና መራባት ነው፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ሴሎች ከተለመደውና ተፈጥሮአዊ ከሆነው መንገድ ውጪ ለቁጥጥር በሚያዳግት መጠን እየተባዙ ይመጣሉ፡፡ በዚህ መንገድ ከሚከሰቱ የካንሰር አይነቶች መካከል የጡት ካንሰር አንዱ ነው፡፡ የጡት ካንሰር ከተፈጥሮአዊ ሁኔታዎች፣ ከጡት ሴሎችና ቲሹዎች መብዛት አንፃር በሴቶች ላይ በስፋት የሚታይ በሽታ ቢሆንም ወንዶችም በጡት ካንሰር የመያዝ እድላቸው ከፍ ያለ ነው፡፡አራት አይነት የወንዶች ጡት ካንሰር በሽታዎች አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከልም ኢንቫሰይቭ ዳክታል ካርሲኖማ የተባለው ወንዶች ላይ በስፋት የሚታይና የጡትን ውጫዊ ክፍል የሚወር ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት በጡት ካንሰር በሽታ የሚያዙ ወንዶች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱንና በሽታው በተለይ እድሜያቸው ከ60 ዓመት በላይ የሆናቸው ወንዶች ላይ በስፋት መታየቱን Journal of Health በቅርቡ ለህትመት ያበቃው መረጃ አመልክቷል፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃ በዚህ በሽታ የሚያዙ ህሙማን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ይኸው መረጃ ጠቁሟል፡፡ በአሜሪካ በ2013 ብቻ ከአንድ ሺህ በላይ ወንዶች በበሽታው መሞታቸውንም ገልጿል፡፡
በአገራችን በካንሰር በሽታ ላይ የተደረጉ የተለያዩ ጥናቶች ቢኖሩም በተለይ በወንዶች ጡት ካንሰር በሽታ ላይ የተደረጉና በሽታው አሁን ያለበትን ደረጃ የሚያመለክቱ መረጃዎች የሉም፡፡ ይሁን እንጂ በአገራችንም በዚህ በሽታ ተይዘው ለህክምና ወደ ሆስፒታሎች የሚሄዱ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄዱን በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ጠቅላላ ሃኪም የሆኑት ዶክተር አብርሃም ተስፋዬ ይገልፃሉ፡፡
በወንዶች ጡት ካንሰር በሽታ ተይዘው፣ ወደ ሆስፒታሉ ከሚመጡ ከአስር ህሙማን መካከል ሁለቱ በሽታቸው የጡት ካንሰር መሆኑን ሳያውቁ፣ ለዓመታት ሲሰቃዩ የቆዩና ህክምና በወቅቱ ለማግኘት ባለመቻላቸው ምክንያትም ህይወታቸውን የሚያጡ መሆናቸውንም አመልክተዋል፡፡
ከወንዶች ጡት ካንሰር በሽታ አይነቶች መካከል ኢንቫሲይቭ ዳክታል ካርሲኖማ የተባለው በሽታ በአገራችንም በስፋት የሚታይ መሆኑን እኒሁ ዶክተር ተናግረዋል፡፡
የወንዶች ጡት በተፈጥሮው አነስተኛ እና ወተት አምራች ክፍል የሌለው ቢሆንም ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው በአራቱ አይነት የጡት ካንሰር በሽታዎች ይጠቃል፡፡ እነዚህ አራት የጡት ካንሰር አይነቶች ምን ምንድናቸው? መነሻ ምክንያታቸውስ? እስቲ በአጭሩ እንያቸው፡፡
1. ኢንቫሲይቭ ዳክታል ካርሲኖማ
ይህ የጡት ካንሰር የጡት ውጫዊውን አካል በመውረር በከፍተኛ መጠን የሚባዛና በስፋት የሚከሰት የጡት ካንሰር ነው፡፡ ከ80-90% የሚደርሰው የወንዶች ጡት ካንሰርም የዚህ አይነቱ ነው፡፡
2. ኔፓል ፓጌት ዲዝዝ
ከጡት የውስጠኛው ሴል አካባቢ ተነስቶ ወደ ጡት ጫፍ በመውጣት፣ በጡት ጫፍ አካባቢ ራሱን ለማባዛት የሚሰራጭ ነው፡፡ እየበዛ ሲመጣም ጠፍጣፋና ጠቆር ወዳለው የጡት ክፍል ይዛመታል፡፡ ይህ የካንሰር አይነት ከሴቶች ይልቅ በብዛት የሚያጠቃው ወንዶችን ነው፡፡
3. ዳክታል ካርሲኖማ
ይህ የካንሰር አይነት ፈሳሽ ሊያስተላልፍ የሚችለውን የጡት አካል የሚያጠቃ ሲሆን ወደ ውጪኛው ክፍል መጥቶ የመባዛት ሁኔታው ዝቅተኛ ነው፡፡ ይህ አይነቱ የጡት ካንሰር እንደ ኢንቫሲይቭ ዳክታል ካርሲኖማ እና እንደ ኔፓል ፓጌት ዲዝዝ በብዛት የሚከሰት አይደለም፡፡ ከአስር የወንዶች ጡት ካንሰር ህሙማን መካከል አንዱ ብቻ በዚህ አይነቱ የጡት ካንሰር ህመም ተጠቂ ይሆናል፡፡ ይህ የካንሰር አይነት በቀዶ ጥገና የመዳን እድሉ ከፍተኛ ነው፡፡
4. ኢንሼሲይቭ ሎብላር ካርሲኖሚ
እጅግ አነስተኛ በሆነ መጠን የሚታይ የጡት ካንሰር ነው፡፡ በሴቶች ጡት ላይ ወተት የሚያመርቱ ክፍሎችን የሚያጠቃ የጡት ካንሰር አይነት ሲሆን በወንዶች ላይ የመከሰት እድሉ እጅ አነስተኛ ነው፡፡ 2% የሚሆኑት የጡት ካንሰር ታማሚ ወንዶች፤ በዚህኛው አይነት የጡት ካንሰር የተጠቁ ናቸው፡፡
የወንዶች የጡት ካንሰር እንደማንኛውም የካንሰር ህመም መነሻ ምክንያታቸው በግልፅ የሚታወቅ ባይሆንም ከዚህ በታች በዝርዝር የተገለፁት ነገሮች ለበሽታው መከሰት መነሻ ምክንያት ይሆናሉ ተብለው እንደሚገመት ዶ/ር አብርሃም ገልፀዋል፡፡
የእድሜ መግፋት
እድሜ እየጨመረና እየገፋ ሲሄድ በጡት ካንሰር በሽታ የመያዝ እድልም እየጨመረ ይሄዳል፡፡
በውልደት ጊዜ የX እና Yክሮሞዘሞች ተዛብቶ መገኘት
አንድ ወንድ ልጅ ሲወለድ ከአንድ በላይ የX እና አንድ የY ክሮሞዞም ይዞ መገኘት፡፡ ይህም ከፍተኛ የኤስትሮጅንና አነስተኛ የአንድሮጅን ሆርሞኖችን እንዲያመርት ያደርገዋል፡፡ ሆኖም ከአንድ ሺ ወንዶች መካከል በአንዱ ላይ ብቻ የሚከሰት ነው፡፡
የጡት ካንሰር ያለበት የቤተሰብ ታሪክ መኖር
በቤተሰቡ ውስጥ በጡት ካንሰር ህመም የተያዘ ሰው ካለ፣ ለቀጣዩ ትውልድ የካንሰር ሴል ጅኖችን የማስተላለፍ እድሉ ከፍ ያለ ነው፡፡
ለአደገኛ ጨረሮች መጋለጥ
በደረት አካባቢ በሚሰጡ የጨረር ህክምናዎች ሳቢያ አሊያም በማንኛውም የሥራ ፀባይ በጡት አካባቢ ለጨረር የመጋለጥ እድል ካለ፣ በጡት ካንሰር የመያዝ እድሉ ከፍ ያለ ይሆናል፡፡
ወንዶች በጡት ካንሰር በሽታ ሲያዙ ስለሚያሳዩአቸው ምልክቶችና ምልክቶቹ በሚታዩ ጊዜ ማድረግ ስለሚገባቸው ነገር ሃኪሙ ሲናገሩ፤
የጡት ጫፍ አካባቢ በጣም ጠጣርና ወፍራም ሲሆን የጡት ጫፍ የቅርፅ ለውጥ ሲያደርግ፣ በጡት አካባቢ ያለው ቆዳችንን ስንጫነው ጐድጐድ ብሎ የመቅረት ባህርይ ካለው፣ በጡት ጫፍና በጡት አካባቢ መሰነጣጠቅ ከታየ፤ የመቅላት፣ የማሳከክና የማቃጠል ስሜት ካመጣና አልፎ አልፎ የመድማት ወይም ፈሳሽ የማውጣት ሁኔታ ከታየበት አስቸኳይ ምርመራና ህክምና ማድረግ ይገባል፡፡ ይህም በሽታው ስር ሳይሰድ ለመግታት ይረዳል፡፡  

Read 8225 times
Administrator

Latest from Administrator