Saturday, 10 October 2015 16:15

አንከር ወተት በዓመት 2.5 ሺህ ቶን ወተት ያመርታል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

በቅርቡ ምርቱን ወደተለያዩ የአፍሪካ አገራት ለመላክ አቅዷል

       በዓለም በወተት ምርቷ ታዋቂ በሆነችው ኒውዝላንድ ውስጥ የሚገኘው ፎንቴራ የተባለው ወተት አምራች ድርጅት በፋፋ የህፃናት ምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ውስጥ እየተመረተ ለገበያ የሚቀርበው አንከር ወተት፤ በዓመት 2.5 ሺህ ቶን ወተት እያመረተ ለገበያ እያቀረበ እንደሆነ ተገለፀ፡፡ ድርጅቱ ባለፈው ረቡዕ በፋፋ የህፃናት ምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ውስጥ የሚገኘውንና በ600 ሺህ ዶላር ወጪ ያሰራውን የወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ለጋዜጠኞች ባስጐበኙበት ወቅት የአንከር ወተት ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዚኮ ሰይድ እንደተናገሩት፤ ፋብሪካው በዓመት 6ሺህ ቶን ወተት በማምረት ለገበያ ለማቅረብ የሚያስችል አቅም ቢኖረውም በአሁኑ ወቅት 2.5 ሺህ ቶን ምርት እንደሚያቀርብ ተናግረዋል፡፡ በዓመት 20 ቢሊዮን ሊትር ወተት የሚያመርተውና በ140 አገራት  ቅርንጫፎች ያሉት ፎንቴራ፤ ከፋፋ የህፃናት ምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ጋር የ30% ድርሻ ይዞ አንከር ወተትን በማምረት እያሸገ በማቅረብ ላይ ሲሆን በቅርቡ ወደተለያዩ የአፍሪካ አገራት ምርቶቹን ለመላክ እቅድ እንዳለው ተገልጿል፡፡ ከሁለት ዓመታት በኋላ ከውጪ አገር የሚመጣውን የዱቄት ወተት ግብአት እዚሁ በአገር ውስጥ ለማምረት መታቀዱን የጠቆሙት ሥራ አስኪያጁ፤ ይህንኑ ለማድረግ የሚያስችሉ ቅደመ ዝግጅቶችም በመደረግ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ህብረተሰቡ ወተት የመጠጣት ባህሉ አነስተኛ በመሆኑ ይህንኑ ለማሻሻል የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ በስፋት መሰራት እንደሚገባው አቶ ዜኮ ገልፀዋል፡፡
ፎንቴራ በአለም 25 ቢሊዮን ዶላር አመታዊ የገንዘብ ዝውውር ያለው ሲሆን በአገራችን በአፍሪካ የመጀመሪያው የሆነውን የአንከር ወተት ማቀነባበር ስራ በፋፋ የምግብ ፋብሪካ ውስጥ በመስራት ለገበየ እያቀረበ የሚገኝ ግዙፍ ድርጅት ነው፡፡ አንከር ወተት ከ30 በላይ ሚኒራሎችና ኢንዛይሞች ተጨምረውበት እንደማዘጋጅም ታውቋል፡፡

Read 5628 times