Saturday, 10 October 2015 16:19

ከባህሉ ጋር ግብግብ የፈጠሩት የአፋር እናቶች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

የሴት ልጅ ግርዛትን በ10 አመት ውስጥ ለማስቆም ቃል ተገብቷል
                             

     ከ5 አመት በፊት በአፈር ምድር የተፈፀመ እውነተኛ ታሪክ ነው፡፡ እናት ሴት ልጇን በባህልና በወጉ መሠረት አስገርዥ ተባለች፡፡ እንደተባለችው አደረገች፡፡ የመጀመሪያ ልጇን አይኗ እያየ ለገራዦች (ብልት ተልታዮች) አሣልፋ ሰጠች፡፡ ህፃኗ ተገረዘች፡፡ በግርዛቱ ወቅት ክፉኛ ደም ፈሷት ነበርና ህፃኗ ከደቂቃዎች በኋላ ህይወቷ አለፈ፡፡ እናት አይኗ እያየ አምጣ የወለደቻትን የአካሏን ክፋይ ወደ መቃብር ላከች፡፡
እናት የመጀመሪያ ልጇን በእንዲህ ያለ ሁኔታ ማጣቷ፣ እንደ እግር እሳት እየለበለባት ሳለ ምትክ ትሆን ዘንድ ፈጣሪ ሌላ ልጅ ሠጣት፡፡ ምነው ሴት ባልሆነች እያለች ብትፀልይም ፈጣሪ የፈቀደው ሆነና ሴት ልጅ በድጋሚ ወለደች፡፡ ህፃኗ ትንሽ ከፍ ስትል እነዚያው ገራዦች (ብልት ተልታዮች)  ቢላቸውን ሞርደው ቀን ቆጥረው በቤቷ ተገኙ፡፡ ግርዛቱ ይከናወን ተባለ፡፡ የመጀመሪያ ልጇን አይኗ እያየ ወደ መቃብር የላከችው ይህች እናት፤ አሻፈረኝ አለች፡፡  የመጣው ይምጣ ብላ ባህሉን ጣሠች፡፡ የባለቤቷን ሽጉጥ መዘዘች፡፡ ለ “አራጆቹ” ሽጉጡን እንካችሁ አለች፤ ልጇን ከጀርባዋ እየከለለች፡፡
መጀመሪያ እኔን ግደሉኝ፤ከዚያ ልጄን ወስዳችሁ ያሻችሁን ትፈጽማላችሁ አለች፡፡ የመንደሩ ታዋቂ ገራዦች ደነገጡ፡፡ ወደ ኋላቸውም ተመለሱ፡፡ ያቺ እናት ልጇን በእንዲህ መልኩ ማዳኗ ዛሬ በአፋር ምድር እንደተረት ይነገራል፡፡ ታሪኩ ግን እውነት ነው፤ያውም ከ5 አመት በፊት የተፈፀመ፡፡
አብዛኞቹ የአፋር እናቶች ዛሬ አቋማቸው የዚህች እናት አይነት ነው፡፡ ከባህሉ ጋር ግብግብ የገጠሙበት ዘመን ላይ ናቸው፡፡ የሃይማኖት አባቶችም በእስልምና አስተምህሮ ሴት ልጅ ትገረዝ የሚል በቅዱሳን መጽሐፍቶች ተፅፎ አላየንም፤ ሊቃውንቶቻችንም ሴት ልጅን ግረዙ ብለው አላስተማሩንም እያሉ ነው፡፡
“እንዴት ባህላችን፣ ወግ ልማዳችን ይጣሣል” የሚሉ የሀገር ሽማግሌዎች ደግሞ በተቃራኒው ተሠልፈዋል፡፡ አብዛኛው ማህበረሰብ ዘንድም የሴት ልጅ ግርዛት ነውር መሆኑ ከግንዛቤ አልገባም፡፡ ዛሬም ለስልጣኔዎች ሁሉ መነሻ የሆነው የሰው ልጅ መገኛ በሆነችው አፋር፤ሴት ልጅ ትገረዛለች፡፡ ሌላው አለም ለልጅ ልጆቹ፣ ሴት ልጅ ድሮ ድሮ በቅድመ አያቶቻችን ዘመን ትገረዝ ነበር እያለ ሲያወራ፣በሰው ዘር መገኛዋ ምድር ደግሞ የሴት ልጅ ግርዛት ይቁም የሚለው መፈክር ቀን ከሌት ይደመጣል፡፡
ከጥቂት አመታት ጀምሮ ማህበረሰባዊ ንቅናቄ በመፍጠር በአፋር ብሎም በኢትዮጵያ ግርዛት ይቆም ዘንድ በርካታ አለማቀፍ ድርጅቶች የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ከሰሞኑም የተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ድርጅት፤ በአፋር ምድር የሚፈፀመው ግርዛት ይቆም ዘንድ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞችን ሲያከናውን ሰንብቷል፡፡  
ባለፈው እሁድ “ግርዛት በሴት ልጅ ላይ እርም”፤ በሃገሬው ቋንቋ “Saloot sayyo qiqddu” በሚል መርህ ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር በመተባበር፣ሴቶችን በስፋት ያሳተፉ የ5 ኪ.ሜ ሩጫ በሠመራ ከተማ አካሂዷል፡፡
በሩጫው ላይም “ግርዛት በሴት ልጅ ላይ እርም” የሚለው በተደጋጋሚ ተስተጋብቷል፡፡ ማህበረሰቡን የማንቃትና ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራም በተከታታይ እንደሚሠራ በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ተወካይ ጊሊያን ሜሎኮፕ ተናግረዋል፡፡
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤በኢትዮጵያ በሴት ልጅ ላይ የሚፈፀም ግርዛት በአብዛኞቹ ክልሎች ነውር መሆኑ ከግንዛቤ እየገባ መጥቷል፡፡
በአፋር እና በሱማሌ ክልል እንዲሁም በአንዳንድ የአርብቶ አደር አካባቢዎች ግን ዛሬም ግርዛት ባህል ነው፡፡ ህብረተሰቡን ከዚህ ባህል ለማላቀቅ ጠንካራ ስራ መስራትን እንደሚጠይቅም የማህበረሰብ አጥኚዎች ይገልፃሉ፡፡
በሌላ በኩል በቅርቡ በለንደን የተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ አለማቀፍ ስብሰባ ላይ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፤በ10 አመት ውስጥ ግርዛትን ከኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ለማጥፋት ቃል ገብተው ተመልሰዋል፡፡ መንግስታቸው ህብረተሰቡን በተለያዩ መንገዶች በማስገንዘብ የሰለጠነው አለም፤ “የሴት ልጅ አካልን የማጉደል ኢ-ሠብአዊ ተግባር” የሚለው ግርዛት፣ በኢትዮጵያ ምድር በ10 አመት ጊዜ ውስጥ እርም እንዲሆን ያደርጋል ብለዋል፤ ምክትል ጠ/ሚኒስትሩ፡

Read 4375 times