Saturday, 17 October 2015 08:52

ኢፕሊፕሲ - የሚጥል በሽታ

Written by 
Rate this item
(6 votes)

• በዓለማችን ከ50 ሚሊዮን በላይ የኢፕሊፕሲ ተጠቂዎች አሉ
• ከነዚህ መካከል 1 ሚሊዮን የሚሆኑት በአገራችን ይገኛሉ
• ከህሙማኑ መካከል 85% የሚሆኑት ህክምና አያገኙም

    በአገረ እንግሊዝ ለሃያ አምስት አመታት ቆይታ ወደ አገሯ በተመለሰችውና የኢፕሊፕሲ (የሚጥል በሽታ) ታማሚ በነበረችው ወ/ሮ እናት የእውነቱ የተቋቋመው Care Epilepsy Ethiopia ህብረተሰቡ ስለበሽታው ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግና በህሙማኑ ላይ የሚደርሰውን የአድልኦና የመገለል ችግር ለማስወገድ የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራም ሰሞኑን በጁፒተር ሆቴል አካሂዶ ነበር፡፡ በእለቱም በሽታው በአሁኑ ወቅት በአለም አቀፍ ደረጃ ያለበትን ሁኔታና እንዲሁም በአገራችን ያሉ የበሽታው ተጠቂዎች ቁጥርና የሚደርስባቸወን ስቃይ ለማሳየት ተሞክሯል፡፡ በሽታው ጊዜና ቦታን ሳይመርጥ በማንኛውም ሁኔታ ታማሚውን ስለሚጥለው ህሙማኑ አሳት ላይ በመውደቅ፣ ከፎቅ ላይ በመከስከስና መሰል አደጋዎች ገጥመዋቸው በአሰቃቂ ሁኔታ ጉዳት እንደደረሰባቸው የሚያሳዩ የተለያዩ ፎቶግራፎችም ለፕሮግራሙ ታዳሚዎች ቀርበዋል፡፡የኬር ኢፕሊፕሲ ኢትዮጵያ መስራችንና ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ እናት የእውነቱ፤ ድርጅቱን ለማቋቋም ያነሳሳቸውን ነገር አስመልክተው ሲናገሩ፤ በኢፕሊፕሲ በሽታ ተይዤ ለአመታት ስሰቃይ ብቆይም እድለኛ ሆኜ ጥሩ ህክምና በሚሰጥበት አገር በመኖሬ ምክንያት ህክምናውን አግኝቼ ከበሽታዬ ለመዳንና በህይወቴ የምፈልገውን ለመሆን ችያለሁ፡፡ በአሁኑ ወቅት በፐብሊክ ሄልዝ ስፔሻላይዝድ አድርጌአለሁ፡፡ ማስተርሴንም ያገኘሁት በዚሁ ነው፡፡ ይህንን እድል ሳያኙ ቀርተው በበሽታው የተያዙና እጅግ የከፋ ስቃይና እንግልት የሚደርስባቸወ ኢትዮጵያዊ እህት ወንድሞቼ ግን መድሃኒትና ህክምና እንኳን ለማግኘት ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ ከዚህ በከፋ ሁኔታ ደግሞ በህብረተሰቡ የመገለል ሁኔታ ይደርስባቸዋል፡፡ ስለዚህም ይህንን ነገር ለመቀየርና በበሽታው የሚሰቃዩ እህትና
ወንድሞቼን ለመርዳት፣ ህክምናውን ለማግኘት የሚችሉበትን ሁኔታ ለማመቻቸት፣ ህብረተሰቡም በበሽታው ላይ ያለውን አመለካከት ቀይሮ ለህሙማኑ ተገቢውን ፍቅርና እንክብካቤ እንዲሰጣቸው ለማድረግ በማሰብ ድርጅቱን አቋቁመናል፡፡ ከተቋቋመ ቅርብ ጊዜ ቢሆንም በዚህ ዙሪያ በርካታ
የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ስንሰራ ቆይተናል፡፡ አሁን ደግሞ የበለጠ ወደ ህዝቡ ውስጥ ለመግባትና በሽታው በህሙማኑ ላይ እያደረሰ ያለውን ችግር ለማስወገድ ጥረት በማድረግ ላይ ነን ብለዋል፡፡
የሮማውን ገዡ ጁሊየስ ቄሳርን፣ የመቄዶኒያውን ንጉስ ታላቁ እስክንድርንና የፈረንሳዩን የጦር መሪ ናፖሊዮን ቦናፓርት ሲያሰቃይ የኖረው ኢፕሊፕሲ፤ በተወሰኑ የአንጐል ነርቭ ሴሎች ውስጥ በሚከሰት ጊዜያዊ የኤሌክትሪክ ንዝረት ሳቢያ የሚፈጠርና አንጐል ለአጭር ጊዜ የወትሮ ስራውን እንዳይሰራ የሚያደርግ በሽታ ነው፡፡ ሁለት ዋና ዋና የኢፕሊፕሲ አይነቶች እንዳሉና Generalized እና focul በሚል ስያሜ እንደሚጠሩ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ Generalized የምንለው የኢፕሊፕሲ አይነት ታማሚውን መሬት ላይ የሚጥል፣ የሚያንቀጠቅጥና ሰውነትን የሚያግተረትር ሲሆን Focul የሚባለው ደግሞ በዝምታ በመዋጥ፣ ለጥቂት ሰከንዶች አካባቢንና ራስን በመሳት የሚገለፅ ህመም ነው፡፡ በሽታው ከሰው ወደ ሰው የመተላለፍ ባህርይ የለውም፡፡ ህብረተሰቡ በሽታው ከሰው ወደ ሰው እንደሚተላለፍ ስለሚያምን፣ ብዙውን ጊዜ የበሽታው ተጠቂዎች ራሳቸውን ስተው በማወድቁበት ጊዜ ለመርዳትና ጉዳት እንዳይደርስባቸው ለማድረግ ፍርሃት ያድርበታል፡፡ የውስጥ ደዌ ህክምና እና የነርቭ ህክምና ስፔሻሊስቷ ዶክተር ሞህላ ዘበንጉስ ይህንኑ ጉዳይ አስመልክተው ሲናገሩ፤ “ኢፕሊፕሲ በተለያዩ ምክንያቶችና መነሻዎች ሳቢያ
በአንጐላችን ነርቮች ውስጥ በሚከሰት ድንገተኛና ጊዜያዊ የኤሌክትሪክ ንዝረት ምክንያት የሚፈጠር በሽታ ሲሆን ከታማሚ ወደ ጤነኛ ሰው በንኪኪ፣ በትንፋሽና መሰል ሁኔታዎች ፈፅሞ የማይተላለፍ
ነው፡፡ ለበሽታው መነሻ ምክንያቶች ይሆናሉ ተብለው ከሚታሰቡ ነገሮች መካከል በወሊድ ወቅት ከአስቸጋሪ ምጥ ጋር ተያይዞ በአንጐል ላይ የሚሰት አደጋ፣ የአንጐል ኢንፌክሽን፣ አንጐል ውስጥ
የሚያድጉ እጢዎች፣ በጭንቅላት ላይ የሚደርሱ የተለያዩ ጉዳቶች፣ ስትሮክና የደም ውስጥ የስኳር
መጠን በጣም ዝቅ ማለት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ በአገራችን በሽታው ወደ አንድ ሚሊዮን በሚጠጉ ሰዎች ላይ የሚታይ ሲሆን ከእነዚህ ህሙማን መካከል ህክምናውን የሚያኙት ከ5-10 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው ብለዋል፡፡ በሽታው በህፃናትና በእድሜ በገፉ ሰዎች ላይ በስፋት እንደሚታይም ሃኪሟ ተናግረዋል፡፡
የኢፕሊፕሲ በሽታን 70% በመድሃኒት መቆጣጠር እንደሚቻል የሚገልፁት ዶክተር ምህላ፤ ታማሚዎች ህክምናውን በአግባቡ ከተከታተሉት በሽታውን ተቆጣጥረው መደበኛ ህይወት ለመምራት እንደሚችሉና በሽታው እንደ ስኳር፣ ደም ግፊት ህመም የሃኪም የቅርብ ክትትል የሚያስፈልገው ተናግረዋል፡፡ህክምናው በሽተኛው እንዴት እንደሚያደርገው መረጃ ከተሰበሰበ በኋላ በምልክቶቹ ተለይቶ ለሚታወቀው በሽታ መድሃኒት በመስጠት ምክንያታቸው የሚታወቁትን የኢፕሊፕሲ በሽታ ለመንስኤው ምክንያት የሆነውን ነገር ነጥሎ በማውጣትና በማከም ለመከላከል እንደሚቻልም ሀኪሟ ገልፀዋል፡፡ ህክምናው ረዘም ያለ ጊዜን የሚወስድ ሲሆን የጭንቃላትን ኤሌክትሪክ ንዝረት በሚለኩ መሳሪያዎች በመለካት ህመሙ ያለበትን ደረጃ በመከታተል፣ ታማሚው መድሃኒቱን በአግባቡ እንዲወስድና ከህመሙ ነፃ በሚሆን ጊዜ መድሃኒቱን እንዲያቆም በማድረግ፣ ጤናማና ሰላማዊ ህይወት እንዲመራ ማድረግ መቻሉንም ሃኪሟ አስገንዝበዋል፡፡
ኢፕሊፕሲ (የሚጥል በሽታ) በህክምና ቁጥጥር ስር እስካልዋለ ድረስ ምን ጊዜና የት ቦታ ህመምተኛውን እንደሚጥለው ማወቅ ስለማይቻል ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል፡፡ የእሳት፣ የመብራት ወይንም የቴሌቭዥን ማንፀባረቅና ማብለጭለጭ በሽታውን ሊቀሰቅሰው እንደሚችል አንዳንድ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በሽታው ድንገት የሚቀሰቀስና ታማሚውን እጅግ ለከፋ አደጋ የሚዳርግ በመሆኑ የሚጥል በሽታ ያለባቸው ሰዎች መኪና ከማሽከርከር፣ ሳይክል ከመንዳት፣ ከዋና፣ ፈረስና በቅሎ ከመጋለብ፣ ከፍታ ቦታዎች ላይ ከመስራትና እንደ አልኮልና ጫት ካሉ ሱሶች በእጅጉ መቆጠብ እንደሚኖርባቸው ዶክተር ምእላ አስገንዝበዋል፡፡   

Read 9336 times