Saturday, 24 October 2015 08:58

ራስን ማጥፋት የስነልቦና ቀውስ ውጤት ነው

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(5 votes)

ባለሙያዎች ራስን የማጥፋት ምልክቶች እንዳሉ ይገልጻሉ

“ታላቅ እህቴ ከእህቶቿና ከዘመዶቿ ሁሉ እኔን መርጣ ወርቆቿን በአደራ እንዳስቀምጥላት ስትሰጠኝ፣ አደራዬን ጠብቄ ንብረቷን በፈለገችው ጊዜ እንደማስረክባት እምነቴ ፅኑ ነበር፡፡ ፈጽሞ ባላሰብኩትና
ባልጠረጠርኩት ሁኔታ ወርቆቹ ከቁምሳጥኔ ውስጥ ተሰርቀው ተወሰዱብኝ፡፡ ሁኔታው ከአቅሜ በላይ
ነው፤ አሁን ማን ያምነኛል፡፡ እሷ አረብ አገር ተንከራታ ያፈራችው ንብረት እኮ ነው፡፡ አደራ በል
የመሆኔ መርዶ ለእህቴ ከሚነገራት ይልቅ የሞቴ መርዶ ቢነገራት መርጫለሁ፡፡ ለሞቴ ማንንም
ተጠያቂ አታድርጉ፡፡ ራሴን ያጠፋሁት እኔ ነኝ፡፡”ኮልፌ ቀራንዮ ክፍል ከተማ ቤተል እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪ የነበረችውና መርዝ ጠጥታ ራሷን ያጠፋችው የ28 ዓመቷ ወጣት ጽፋ ያኖረችውና በፖሊስ እጅ የገባው ይህ ማስታወሻ፣ በሟች እጅ የተፃፈ ለመሆኑ ፖሊስ ማረጋገጡን ቤተሰቦች ይናገራሉ፡፡
በአንድ የግል ድርጅት ውስጥ በሽያጭ ሰራተኛነት ተቀጥራ ትሠራ የነበረችው ሟች፤በቤተሰቦቿና
በአካባቢዋ ማኅበረሰብ ዘንድ እጅግ ትከበርና ትወደድ ነበር፡፡
ለሞቷ ምክንያት ሆነ የተባለው ወርቅ ባለቤት የሆነችው የሟች ታላቅ እህት፣ የእህቷን  መርዶ ስትሰማ ካለችበት አገር ሳትውል ሳታድር ጓዟን ጠቅልላ ነው ወደ አገሯ የመጣችው፡፡ ሆኖም ሁሉም ነገር ጅብ ከሄደ ሆነባትና ለአመታት በአረብ አገር አስከፊ ሕይወት ተንገላታ ካፈራችው ንብረቷ አሊያም እጅግ ከምትወዳት ታናሽ እህቷ ሳትሆን መቅረቷ ሀዘኗን እጥፍ ድርብ አደረገው፡፡ የድሬዳዋ ሳቢያን አካባቢ ነዋሪ የነበረችው የ17 አመቷ ወጣት ራስን የማጥፋት ታሪክም እጅግ አሳዛኝ ነው፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ የነበረችው ወጣቷ፤ በትምህርቷ ጎበዝ እንደነበረች ይነገርላታል፡፡ የታዳጊዋ ጓደኞች እንደሚሉት፤ከቅርብ ወራት ወዲህ ታዳጊዋ ብቸኝነትን የመፈለግ፣ የመጨነቅና ለትምህርቷ ግድ የማጣት ስሜት በብዛት ይታይባት ነበር፡፡ ቤተሰቦቿ ታዳጊዋ ስለገጠማት ችግር ለማወቅ ከመሞከር ይልቅ ትምህርቷን ችላ ማለቷ አሳስቧቸው ተደጋጋሚ ቁጣና
ተግሣፅ ያደርሱባት ነበር፡፡ ጓደኞቿም ቢሆኑ በታዳጊዋ ላይ የስሜት ለውጥ ያስከተለውን ጉዳይ ተከታትሎ ለማወቅና መፍትሔ ለመፈለግ ያደረጉት ሙከራ እምብዛም አልነበረም፡፡ብዙም ሳትቆይ ግን ወጣቷ በመኝታ ክፍሏ ውስጥ አንገቷን በሻርፕ አንቃ ሞታ ተገኘች፡፡ ጽፋ ባኖረችው ማስታወሻ
ላይ እንደገለጸችው፤ ራሷን ለማጥፋት የወሰነችው፣ በፍቅር ጓደኛዋ በመከዳቷና ይህንን ችግሯንም
ቤተሰቦቿም ሆኑ ጓደኞቿ ለማወቅና መፍትሔ ለመፈለግ ባለመሞከራቸው ነው፡፡ ፋሲል ታረቀኝ (ስሙ ለዚህ ጽሑፍ የተቀየረ) እዚሁ አዲስ አበባ አለም ባንክ እየተባለ በሚጠራው
አካባቢ ነዋሪ ነበር፡፡ ከመኖሪያ ቤቱ ጥቂት ርቀት ላይ በሚገኝ ጅምር የመኖሪያ ቤት ጣራ ላይ
ራሱን በገመድ ሰቅሎ ሞቶ ተገኝቷል፡፡ ከሟቹ ኪስ የተገኘው ማስታወሻም፣ በሚተዳደርበት የንግድ ሥራ ከፍተኛ ኪሣራ ስለደረሰበትና ለመንቀሳቀሻ ተበድሮት የነበረውን ገንዘብ ለመክፈል ባለመቻሉ ምክንያት ራሱን ማጥፋቱን ይገልፃል፡፡ በአዲስ አበባ ዙሪያ ኦሮሚያ ክልል ቡራዩ ከተማ ውስጥ ተመሳሳይ የሆነ ራስን የማጥፋት ድርጊት የቤት ሠራተኛ በነበረችው የ24 ዓመቷ ወጣት ተፈጽሟል፡፡ ታዳጊዋ በሠራተኝነት ተቀጥራ በነበረበትና ህይወቷን ባጣችበት ቤት ውስጥ ለአራት ዓመታት ያህል ቆይታለች፡፡ ሠራተኛዋ ጽፋ
የተወችው ወይም ለሞቴ ምክንያት ነው ያለችው ጉዳይ ባይገኝም በዳግማዊ ምኒሊክ ሆስፒታል
በአስከሬኗ ላይ በተደረገው ምርመራ፣ የሶስት ወር ነፍሰጡር እንደነበረች ተረጋግጧል፡፡ ምናልባትም
ሞቷ ከዚሁ ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችልም ተገልጿል፡፡ የቤት ሠራተኛዋ አሠሪዎች በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለው ተገቢው ማጣራትና ምርመራ
ተደርጐላቸው ከእስር የተፈቱ ሲሆን ሠራተኛዋ በአቅራቢያዋ ከሚኖር አንድ ወጣት ጋር የፍቅር
ግንኙነት እንደነበራትና የፀነሰችውም ከዚሁ ፍቅረኛዋ መሆኑን እንደነገረቻት የሠራተኛዋ ጓደኛ
የምስክርነት ቃሏን ሰጥታለች፡፡ ከአመታት በፊት እዚሁ በመዲናችን አዲስ አበባ በንግድ ሥራቸው የተሣካ ደረጃ ላይ ደርሰዋል በሚባሉ ታዋቂ ባለሃብቶች የተፈፀመው ራስን የማጥፋት ድርጊት፣ በወቅቱ የብዙዎችን ትኩረት የሳበና አነጋጋሪ የሆነ ዜና እንደነበር ይታወሳል፡፡ በተመሳሳይ ወቅት ራሳቸውን ያጠፉት እነዚሁ
ታዋቂ ባለሀብቶች፣ ለሞታቸው መንስኤ ያደረጉትም የተበደሩትን የአራጣ ብድር መክፈል
አለመቻላቸውን ነበር፡፡ ራስን የማጥፋት ድርጊቶች በየጊዜው ቢሰሙም ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ፣ ሰዎች ራሳቸውን የሚያጠፉት ለምንድነው? ራስን ማጥፋት ከስነልቡና ችግር ጋር የሚያያዝበት ጉዳይ አለ ወይ?
ችግሩን ለመከላከል መወሰድ የሚገባው ቅድመ ጥንቃቄስ ይኖር ይሆን ----- የሚሉ ጉዳዮችን የሚከታተል አካል የለም፡፡ ይሄ ደግሞ ድርጊቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንዲሄድና በቀላሉ ሊፈቱ በሚችሉ ተራ ችግሮች ሳይቀር ሰዎች ክቡር ህይወታቸውን እንዲያጡ ምክንያት ሆኗል፡፡  በእርግጥ ራስን ማጥፋት በሰለጠኑት አገራትም እንግዳ ጉዳይ አይደለም፡፡ እንደውም በብዛት የተለመደ ተግባር ነው፡፡ ራስን የማጥፋት ድርጊት አፈፃፀም የተለያዩ መንገዶች አሉት፡፡ መታነቅ፣ መርዝ መጠጣት፣ ከፎቅ ላይ መውደቅ፣ በጦር መሳሪያ መጠቀም፣ ራስን ማቃጠል፣ ደም በብዛት እንዲፈስ ማድረግ፣ በስለታም ነገሮች መጠቀም ---- ዋንኞቹ ራስን የማጥፊያ መንገዶች ናቸው፡፡ ራስን ለማጥፋት በምክንያትነት ጐልተው ከሚጠቀሱ ጉዳዮች መካከል ደግሞ ከስራ መፈናቀል፣
ብድርን መክፈል አለመቻል፣ ተገድዶ መደፈር፣ ያልተፈለገ እርግዝና፣ ፍቺ፣ ግብረሰዶማዊነት፣ ከህግ
ተፈላጊነት ለመሸሽና የእፅ ሱሰኝነት ዋንኞቹ ናቸው፡፡  በድሬዳዋ ከተማ አብዛኛውን ጊዜ ራሳቸውን የሚያጠፉት ወጣቶች ሲሆኑ ለድርጊቱም ሴልፎክስ
የተባለውን የትኋን መግደያ መድሃኒት እንደሚጠቀሙ ከድልጮራ ሆስፒታል ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡ የድሬደዋ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ዲቭዥን ኃላፊ ኢንስፔክተር ገመቹ ካቻ እንደገለፁት፤በከተማው ባለፈው አመት ብቻ 19 ሰዎች በተለያዩ መንገዶች ራሳቸውን ያጠፉ ሲሆን
ዘንድሮ ሶስት ሰዎች ህይወታቸውን በገዛ እጃቸው አጥፍተዋል፡፡ መታነቅ፣ ራስን ማቃጠልና መርዝ
መጠጣት ሰዎቹ ራሳቸውን ለማጥፋት የተጠቀሙባቸው ዘዴዎች ናቸው፡፡   የድርጊቱ ፈፃሚዎች የሚጠቀሙባቸው የተለያዩ መንገዶች ሁሉ ወደ ሞት የሚያደርሱ አይደሉም፡፡ ሙከራቸው ሳይሳካላቸው ቀርቶ ለከፋ የጤና ችግር የሚዳረጉ እንዳሉ ሁሉ፣ ለጊዜው ሙከራቸው ቢከሽፍም ለቀጣዩ ሙከራ የሚዘጋጁ ሰዎችም አሉ፡፡ የዕፅ ተጠቃሚዎችና የአዕምሮ ህሙማን ተደጋጋሚ ራስን የማጥፋት ሙከራ ያደርጋሉ፡፡ በጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረጉት የሥነልቦና ባለሙያው ዶክተር እሩይ ተመስገን እንደሚናገሩት፤ በአገራችን ከቅርብ አመታት ወዲህ እራስን የማጥፋት ተግባር እየጨመረ መጥቷል፣ ድርጊቱ በተለይም ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 25 ዓመት ድረስ በሚሆናቸው ወጣቶች ላይ በስፋት ቢታይም የ13 ዓመት ታዳጊና የ62 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ ራሳቸውን በተለያዩ መንገዶች አጥፍተዋል፡፡ ሁሉም የድርጊቱ ፈፃሚዎች ድርጊቱን ለመፈፀም ያስቻላቸው አንድ ምክንያት ከበስተጀርባቸው የሚገኝ ቢሆንም ይህንን ችግር ለማወቅና
ተጐጂዎቹን ለመርዳት የሚደረግ አንዳችም ሙከራ የለም፡፡ ራስን ማጥፋት ከሥነልቦና ጋር የሚያያዝበት በርካታ ምክንያቶች እንዳሉት የሚያስረዱት የህክምና ባለሙያው፤#አብዛኞቹ የድርጊቱ ፈፃሚዎች የጭንቀት፣ የድብርትና ራስን የመጥላት ስሜት ተጠቂዎች ናቸው፤ይህ ሁኔታ ደግሞ ሰዎቹ ከችግሮቻቸው እፎይታን የሚያገኙት ራሳቸውን ሲያጠፉ ብቻ እንደሆነ እንዲሰማቸው ያደርጋል፡፡ በዚህ ምክንያትም በራሳቸው ላይ እርምጃውን ለመውሰድ ይገደዳሉ፡፡” ብለዋል፡፡ በሰለጠኑት አገራት አንድ ሰው ስሜቱ በተለያዩ መንገዶች ሲጐዱና ህይወቱን መጥላት ሲጀምር፣ህክምናና የባለሙያዎች የቅርብ ክትትል እንዲያገኝ በማድረግ፣ ወደ ሰላማዊና ደስተኛ ህይወቱ እንዲመለስ የሚደረግበት አሠራር መኖሩን የጠቆሙት የሥነልቦና ባለሙያው፤ይህም ቅድመ ጥንቃቄ በርካታ የድርጊቱ ፈፃሚዎች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ገልፀዋል፡፡ በአገራችን በእንዲህ አይነት ጉዳዮች ላይ አተኩሮ የሚሰራና መፍትሔ የሚሰጥ አካል ባለመኖሩ  በተለያዩ ምክንያቶች ራሳቸውን ጠልተው፣ ሞታቸውን የተመኙ ሰዎች ነፍሳቸውን በቀላሉ ያጠፋሉ፡፡ ደካማ የሆነ ማህበራዊ ህይወት ያላቸው ሰዎች ራሳቸውን የማጥፋታቸው ዕድል ሰፊ መሆኑን የሚገልፁት ዶክተሩ፤እንደነዚህ አይነት ሰዎች ብቸኝነት የሚያጠቃቸው፣ ችግራቸውን
ለሰው ከማማከር ይልቅ በራሳቸው ለመፍታት የሚጥሩ በመሆናቸው ለችግራቸው መፍትሔ ማግኘት ሲሳናቸው ራሳቸውን ወደማጥፋት ድርጊት ይገባሉ፤ብለዋል፡፡  አንድ ሰው ራሱን ለማጥፋት ፍላጐት በሚያድርበት ወቅት የሚያሳያቸው የተለያዩ ምልክቶች እንዳሉ የጠቆሙት ዶክተር እሩይ፤ ግለሰቡ ምልክቶቹን በሚያሳይበት ወቅት ወደዚህ ድርጊት የገፋፋው ጉዳይ ምንድነው? በማለት ችግሩን ለማወቅና መፍትሔ ለመፈለግ መሞከር እንዲሁም ግለሰቡን ከሥነልቡና ባለሙያ ጋር በማገናኘት የምክር አገልግሎት እንዲያገኝ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ራስን የማጥፋት ምልክቶች እንቅልፍ ማጣት፣ እረፍት የለሽ መሆን፣ ከሥራ መቅረት፣ መልካም ነገሮችን አለመፈለግ፣ ከቤተሰብ ጋር አለመግባባት፣ ብቸኝነትን አብዝቶ መፈለግ፣ መከፋትና ማልቀስ፣ የምግብ ፍላጐት ማጣት፣ መደበትና የድብርት ስሜት ውስጥ መግባት ዋንኞቹ ናቸው፡፡ እነዚህ ምልክቶች በሚታዩ ጊዜ አፋጣኝ እርምጃ በመውሰድ ግለሰቡ ሊፈጽመው ካሰበው ራስን የማጥፋት ድርጊት ልንታደገው
እንደሚገባም የሥነልቦና ባለሙያው ይመክራሉ፡፡

Read 7955 times