Saturday, 07 November 2015 09:24

ጠ/ሚኒስትሩ ቀላል ተናገሩ!! (የሚቀረው ሥራ ብቻ ነው)

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(18 votes)

• የመንግስት ባለሥልጣናት፤ “ኔትዎርካችሁን” በደንብ ቁረጡ ተባሉ!
• በቀን 2 ሚ. ብር የሚያንቀሳቅሱ “ደላሎች” አፍርተናል!
• “ደላሎች” - የመንግስት ባለሥልጣናት የብእር ስም ቢሆንስ??

   ሰሞኑን በኢቢሲ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች (የሥልጣን ቁንጮዎቹ ቢባሉ ይሻላል!) በመልካም አስተዳደር ጥናት ዙሪያ ያካሄዱት ውይይት፣ “በዓይነቱ እጅጉ ለየት ያለ” ተብሎ የሚመዘገብ ነው፡፡ ይሄንን የባለሥልጣናት ክርክር- አከል ውይይት ያልተከታተለ ሰው፣መቆጨቱ አይቀርም፡፡ ብዙ ነገር ነዋ የሚያመልጠው፡፡ የሚገርመው ደሞ ምን መሰላችሁ? ውይይቱ ለሁሉም በእኩል ደረጃ ለየት ያለ ሆኖ መገኘቱ ነው፡፡ የእኛ ይቆይና ለራሳቸው ለኢህአዴግ ሹማምንትም ጭምር በእጅጉ ለየት ያለ ነበር፡፡ (ባይሆንማ ኖሮ ጠ/ሚኒስትሩ እንዳሉት፣ድንጋጤ ባልተፈጠረ ነበር!)  ባይገርማችሁ----ይሄ ታሪካዊ ውይይት ለኢቢሲም ጭምር በዓይነቱ ለየት ያለ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ለምን ብትሉኝ ----ኢቢሲ ይሄን የመሰለ መሬት የወረደ፣የባለሥልጣናትን---- ውይይት የማሰራጨት ዕድል ገጥሞት አያውቅማ! (ግን ታውቆት ይሆን?!) በነገራችን ላይ በዚህ ስርጭቱ ብቻ “ኢቢሲ ለምኔ!” ያሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ   ተመልካቾች፤ለአንድ ሁለት ቀንም ቢሆን ዓይንና ጆሮ ያዋሱት ይመስለኛል። (“እቺንስ ቢሆን ማን አየብኝ” ይበል!) እግረመንገዴን ግን ለኢቢሲ (የመንግስትና የህዝብ ሃብት ነውና!) አንድ  ልማታዊ ምክር ብለግሰው ደስ ይለኛል፡፡ ጣቢያው እንደ ሰሞኑ ለየት ያለ የመንግስት ባለሥልጣናት ውይይት ሲኖር ብቻ ሳይሆን በአዘቦቱም ቀን ተመልካች ያገኝ ዘንድ የህዝብ አመኔታ መፍጠር አለበት፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ በሰሞኑ ውይይት፣የመልካም አስተዳደር
ችግሮችን ለመፍታት በህዝብ ዘንድ አመኔታ የሚፈጥር እንቅስቃሴ መጀመር የግድ ነው እንዳሉት ማለት ነው፡፡   
እኔ የምለው ግን ከመንግስት ባለሥልጣናት ስንት ፐርሰንቱ ኢቢሲን እንደሚያይ የተደረገ ጥናት አለ እንዴ? (መንግስት “አዝማሪ ሚዲያ አልፈልግም” ማለቱን ዘንግቼው እኮ ነው!) እንዲያም ሆኖ የመልካም አስተዳደር ችግርን፣ ኪራይ ሰብሳቢነትና በሥርዓቱ ላይ ነግሷል የተባለውን የደላላ ተጽዕኖ (90 ሚሊዮን ህዝብ የደላላ መጫወቻ እንሁን?!) ለመቅረፍ የሚዲያ ሚና ወሳኝ ነው ከተባለ (ወይስ አልተባለም?) እነ ኢቢሲን በትክክል ማን እንደሚመለከታቸው ጥናት መደረግ ይኖርበታል፡፡ (ራሳቸው የጣቢያው ሃላፊዎች ይመለከቱት ይሆን?)  
የመንግስት ከፍተኛ አመራሮች ባደረጉት ውይይት ላይ የጀመርነውን ወግ አልጨረስንም፡፡ (#መች ተነካና” አለ የአገሬ ሰው!) እንደ ማረፊያ ግን ሰሞኑን ለሚዲያ ዘገባ የበቃ አንድ ከፍተኛ የሙስና ወንጀል እንቃኝ (ማረፊያ ብቻ ሳይሆን ማስረጃም ይሆናል!) ዘገባው
እንዲህ ይላል----  “የገቢዎችና ጉምሩክ ከፍተኛ ኦዲተርና ኦፊሰሮች በከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰሱ” (ባለፈው ረቡዕ የወጣው ሪፖርተር ጋዜጣ፡፡) ዘገባው እንደሚለው፤የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የመርካቶ ቁጥር ሁለት ቅርንጫፍ ከፍተኛ ኦዲተርና ሦስት ኦፊሰሮች ጉቦ በመቀበል ከባድ የሙስና ወንጀል ባለፈው ሰኞ ተከሰዋል፡፡  ተከሳሾቹ፤የግል ተበዳይ አቶ ዮሐንስ ጥጋቡ የተባሉትን በጨርቃጨርቅ ንግድ የተሰማሩ ነጋዴ፤“ግዢና ሽያጭ አልተጣጣመም፤በቆጠራ
የሚፈጠረውን ጉድለት ባላንስ እናደርግልዎታለን!” በማለት ሁለት ሚሊዮን ብር ጉቦ መጠየቃቸውን፣ የፌደራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት የመሰረተው ክስ ያስረዳል። ሆኖም የግል ተበዳዩ የተጠየቁትን ገንዘብ ለመስጠት ሳይስማሙ ይቀራሉ፡፡ በመጨረሻ ግን ተከሳሾች የግል ተበዳዩን በማስጨነቅና ሰነዱን ሲመረምሩ 12 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ከፍተኛ ዕዳ እንደሚመጣባቸው ማወቃቸውን በመንገር፣ በተለያዩ ቀናት ተከሳሾች ከተበዳይ 1.2 ሚሊዮን ብር መቀበላቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡
(የጦቢያ ባለሃብት ያለበትን ጭንቅ አያችሁልኝ!) ለማንኛውም ግን እንደ አንጋፋው ደራሲ አጉቾ ተረፈ የአጭር ልብወለድ ዋና ገጸ ባህሪ፣#እያስመዘገብኩ ነው” ብያለሁ፡፡   
አሁን ወደ አቋረጥነው ወግ ልመልሳችሁ፡፡ እናላችሁ ---- በዚህ የሰሞኑ የከፍተኛ አመራር ውይይት ላይ በጣም የገረመኝ አንድ ነጥብ ምን መሰላችሁ? የደላሎች ጉዳይ!! በቀን 2 ሚሊዮን ብር የሚያንቀሳቅሱ ደላሎች፣ የክልል ሃላፊዎችን ከፌደራል ባለሥልጣናት ጋር በስልክ የሚያገናኙ ደላሎች፣ በሥርዓቱ ውስጥ የነገሰው የደላላ ተፅዕኖ ወዘተ----- (ሹም ሽረት እኮ ነው የቀራቸው!) አገሪቷን ደላሎች የወረሯት ወይም የሚመሯት ነው የሚመስለው፡፡ (ለነገሩ ሥራቸውም መሬት ወረራ አይደለ?!) እኔ ግን አንድ ነገር ልቤ ጠረጠረ፡፡ ምን
መሰላችሁ--- “ደላሎች” የሚለው የባለሥልጣናትና የመንግስት ሃላፊዎች የብዕር ስም ቢሆንስ? (ለነገሩ ጎስት ራይተር በሚለውም ያስኬዳል!) ሌላው የሚያስፈራኝ ምን መሰላችሁ? የግልና የመንግስት ደላሎች ተፈጥረው እንዳይሆን የሚለው ነው፡፡ (የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር፤ የመንግስትና የግል ሌቦች አስቸገሩን ያሉት ትዝ አይላችሁም?) ይሄን ሁሉ ብዬም ግን አንድ ወሳኝ ጥያቄ ልሰንዝር፡፡ እነዚህን ደላሎች
ማን ነው የፈጠራቸው? እነዚህን ደላሎች ማን ነው ተጽዕኖ ፈጣሪ ያደረጋቸው? እነዚህን ደላሎች ማነው ጉልበት የሰጣቸው? (ችግሩን ለመፍታት ምንጩን ማወቅ ያስፈልጋል ብዬ እኮ ነው!) በእርግጥ ጠ/ሚኒስትሩ፤ በሥርዓቱ ውስጥ የነገሰውን የደላላ ተፅዕኖ በቁርጠኝነት መታገል እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡ (መታገልማ የግድ ነው!)  በነገራችን ላይ በመልካም አስተዳደር ችግሮች ላይ የተሰራው የዳሰሳ ጥናት ከቀረበ በኋላ ከአንዳንድ ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናት የተሰነዘሩ አስተያየቶች ትኩረቴን ስበውታል፡፡ (አጠቃላይ የውይይቱን መንፈስ እንድናገኘውም ያግዛል!) የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል አስተባባሪ አቶ አባይ ፀሐዬ፤ ችግሩ ሥር የሰደደ በመሆኑ በዘመቻ መፍታት ስለማይቻል በአስቸኳይ ሥርዓት የመዘርጋት ሥራ መሰራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ (እሳት አደጋ የማጥፋት ሥራ መሰለ እኮ!) “እኛ በመተማመን ነው እየሰራን
ያለነው፡፡ መሬት ላይ ያሉት ነገሮች እኛ እንደምናስባቸው አይደሉም፡፡ አመለካከት እስኪቀየር ሥርዓት ሳንዘረጋ የምንጠባበቅ ከሆነ እንበላለን” ብለዋል፡፡ (“አደጋ አለው” አለች ተዋናይዋ!!)
በፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል የኮሙዩኒኬሽንና መረጃ አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ሴኮቱሬ ጌታቸው በበኩላቸው፤“ጥናቱ የችግሩን ጥልቀት መቶ በመቶ ይገልፃል የሚል እምነት የለኝም፤ በመሬት ላይ ያለው ችግር የከፋ ነው፡፡ ሕዝቡ የሚሰማው አካል እንደሌለ ነው የሚገልፀው፡፡ ሰብስበው ቢያናግሩንም መፍትሔ የለም ነው የሚለው” ሲሉ በትግራይ ክልል ተዘዋውረው የተገነዘቡትን አቅርበዋል፡፡  
የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ሚኒስትሯ ወ/ሮ አስቴር ማሞ ግን ከወትሮው የተለየ ሃሳብ አልሰነዘሩም፡፡ “መሬት ላይ ያለውና የተጠቀሰው ችግር ስፋት አሳሳቢ ቢሆንም፣ ከገዢው ፓርቲና ከመንግስት አቅም በላይ የሆነ ችግር አይደለም” ብለዋል፡፡ መሬት ላይ ያለው እውነታ ግን እሳቸው እንደሚሉት አይመስልም!! (እኔም በኢህአዴግ ቋንቋ ልተንፍስ ብዬ እኮ ነው!)
በመልካም አስተዳደር ችግሮች ዙሪያ በተደረገው ጥናት መነሻነት የተካሄደውን የከፍተኛ  አመራሮች ውይይት ከወትሮው ፍጹም በተለየ ቆፍጣናነትና ቁርጠኝነት ሲመሩ የታዩት ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፤በእርግጥም ብዙዎች እንደታዘቡት የኢህአዴግ ዋና አቅጣጫ ቀያሽነታቸውንና የአገሪቱ መሪነታቸውን አድምቀውና አስረግጠው አሳይተዋል፡፡ (የሥልጣን ግማሽ እኮ የለውም!)  ጠ/ሚኒስትሩ
የመልካም አስተዳደር ችግርን ለመቅረፍ በስርዓት ግንባታ ላይ ማተኮር እንደሚገባ አስተያየት ለሰነዘሩ ባለስልጣናት የማያወላዳ ምላሽ ነው የሰጡት፡- “እንደ አዲስ የምንፈጥረው ነገር የለም፡፡ ምርጥ የመሬት ሪፎርም አዘጋጅተን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የተደገፈ ስርዓት ገንብተናል፡፡ … የያዝነውን ፕሮግራም ተግባራዊ ሳናደርግ ነው እንዴ ወደ ሌላ ሥርዓት የምንሸጋገረው?” ብለዋል ጠ/ሚኒስትሩ፡፡
በተለይ በውይይቱ መዝጊያ ላይ ጠ/ሚኒስትሩ ድፍረትና እርግጠኝነት በተሞላበት መልኩ የተነፈሱት ነገር እንኳንስ ባለስልጣናቱን የቴሌቪዥን ተመልካቹንም በድንጋጤ አፍ ያስያዘ ነበር፡፡ (ከተለመደው ውጭ ነዋ!) እውነት ግን ጠ/ሚኒስትሩ ይሄን ያህል ምን ቢሉ ነው የብዙዎችን ትኩረት የሳበው?
 “እዚህ አገር ያለ ከባድ ፈተና፣እዚህ እናወራለን እንጂ ከወጣን በኋላ የተለያየ የራሳችን ኔትዎርክ እንዳይነካብን እንከላከላለን፡፡ ይሄ አንድ ትልቁ በሽታ ነው፡፡ ስለዚህ መቁረጥ ከሆነ በደንብ መቁረጥ ነው የሚያስፈልገን፡፡
የእኛ ነው የምንለውን ሰው ለመደበቅና ለመሸፈን ብቻ የምንሄድ ከሆነ ለውጡ አይሰራም፡፡ በብሄር፣ በአብሮ አደግነት፣ በተለያየ ጥቅም ትስስር የምንሰራና የምንከላከል ከሆነ አይሰራም፡፡ መፍትሄው የሚመሰረተው በከፍተኛ አመራሩ ቁመና ነው፡፡ ይህን ለመለወጥ ትክክለኛ የህዝብ ተሳትፎ ላይ ሊሰራ ይገባል” ብለዋል ጠ/ሚኒስትሩ፡፡  (ላልተወሰነ ጊዜ አድናቂያቸው ነኝ!) ከምሬ ነው የምላችሁ ----- ጠ/ሚኒስትሩ የዓመቱን ምርጥ ንግግር ነው ያደረጉት፡፡ አሁን የሚቀረው ንግግሩን ወደ ሥራ መቀየር ብቻ

ነው፡፡

Read 7290 times