Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 11 February 2012 09:53

የአዲሱ ሚካኤል አስተዳዳሪ በምዕመናን ተቃውሞ ገጠማቸው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ወደ 1ሺህ የሚጠጉ ምዕመናን ለፓትርያርኩ አቤቱታ አቅርበዋል

የደብረመዋዕ ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል (አዲሱ ሚካኤል) አስተዳዳሪ ሊቀሊቃውንት ዕዝራ ተክለ ጊዮርጊስ ከአስተዳደርነታቸው እንዲነሱና ሰበካ ጉባኤው የመረጣቸው አዲስ አመራሮች ሹመት እንዲፀድቅላቸው ወደ 1ሺህ የሚጠጉ ምዕመናን ከትናንት በስቲያ በጠቅላይ ቤተክህነት አቤቱታቸውን አቀረቡ፡፡ በዕለቱ አቤቱታቸውን ያቀረቡት ምዕመናኑ የቤተክርስቲያኑ አስተዳዳሪ ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ፤ ምዕመናኑን ስለሚዘልፉ፣ ተገቢ ያልሆኑቃላትንስለሚናገሩና የቤተክርስቲያኒቱን ሐብትና ንብረት ለግል ጥቅማቸው ስለሚያውሉ ከአስተዳዳሪነት እንዲነሱላቸው ጠይቀዋል፡፡ ምዕመናኑ በተጨማሪም ከዚህ ቀደም ተቋቁሞ የነበረው አጣሪ ኮሚቴ ያቀረበው ሪፖርት ከምን እንደደረሰም ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

አያይዘውም የሪፖርቱ ውጤት ምንም ይሁን ምን አስተዳዳሪው መነሳት ስለሚገባቸው ፓትርያርኩ አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጡና ምዕመናኑ የመረጣቸው አዲስ አመራሮች  ሹመት ፀድቆ ሥራ እንዲጀምሩ ጠይቀዋል፡፡ አቤቱታውን የሰሙት የጠቅላይ ቤተክህነቱ ሥራ አስኪያጅ አቡነ ፊሊጶስ፤ አቤቱታውን ሲሰሙ የመጀመሪያቸው በመሆኑ በዕለቱ መልስ ለመስጠት ስለሚያስቸግር ምላሹን ለሌላ ጊዜ አስተላልፈውታል፡፡ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ንቡረዕድ ኤልያስ በበኩላቸው፤ የአዲሱ ሚካኤል ቤተክርስቲያ ምዕመናን አስተዳዳሪ ሳይኖራቸውም ቢሆን በጥምቀት በዓል አከባበር ያሳዩት በጎ ተግባር የሚያስመሰግናቸው መሆኑን ጠቅሰው ሀገረ ስብከቱም በሚፈለገው ሰዓት ምላሽ ያልሰጠው ከጥምቀት በዓል አከባበር ጋር በተያያዘ በተፈጠረ የጊዜ መጣበብ እንደሆነ  አስረድተዋል፡፡ በመጨረሻ ለአቤቱታው ምላሽ የሰጡት አቡነ ጳውሎስ፤ ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ከተወነጀሉባቸው ነገሮች ነፃ መሆናቸውን ከገለፁ በኋላ ቢሆንም ግን ቤተክህነት ችግሩን ለመፍታት እንደምትሞክር ቃል ገብተዋል፡፡ በፓትርያርኩ ምላሽ ያልተደሰቱት ምዕመናኑ፤ ለተጨማሪ አቤቱታ እጃቸውን ቢያወጡም ፓትርያርኩ ትተዋቸው ወደ ውስጥ ገብተዋል፡፡ ከስብሰባው በኋላ ያነጋገርናቸው ተወካዮች  ጉዳዩ መፍትሄ እንዲሰጠው ለአራት ወራት ያህል ሲከታተሉ መቆየታቸውን ጠቁመው ከዚህ በኋላ መፍትሔ የማይሰጠው ከሆነ በቂ መረጃ ስላላቸው ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት እንደሚወስዱት ገልፀውልናል፡፡

 

 

Read 12723 times Last modified on Saturday, 11 February 2012 12:24