Saturday, 14 November 2015 09:44

ቲቢን የማስቆም ንቅናቄ ተካሄደ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ metijossy@gmail.com
Rate this item
(2 votes)

በዓለማችን ባለፈው ዓመት ብቻ 9.6 ሚሊዮን ሰዎች በቲቢ ተይዘዋልኢትዮጵያ በበሽታው ከተጠቁ ግንባር
ቀደም አገራት አንዷ ናትኢትዮጵያ በበሽታው ከተጠቁ ግንባርቀደም አገራት አንዷ ናት

   በማደግ ላይ ባሉ አገራት የሚኖሩ ህዝቦች ግንባር ቀደም ገዳይ ከሚባሉት በሽታዎች አንዱ የሆነውን የቲቢ በሽታ ለማስቆም የሚያስችል ”EndTB” የተሰኘ ንቅናቄ ተካሄደ፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ባለፈው ረቡዕ በሒልተን ሆቴል በይፋ ያስጀመረው ቲቢን እናስቁም ንቅናቄ እ.ኤ.አ በ2032 በበሽታው የሚያዙ ሰዎችን ቁጥር ከ100 ሺህ አስር ብቻ ለማድረስ የታለመ ነው፡፡ ከአዳሱ የፈረንጆች ዓመት እስከ 2032 ዓ.ም ይደረጋል በተባለው በዚሁ “ቲቢን እናስቁም” ንቅናቄ፤ አገራት ሁሉ፤ ተሳታፊ በመሆን በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ፍጥነት እየተሰራጨ ያለውን የቲቢ በሽታ ለመግታትና በበሽታው የሚያዙ ሰዎችን ቁጥር ለመቀነስ በትጋት እንደሚሰራ ተገልጿል፡፡
በሒልተን ሆቴል በተካሄደው ፕሮግራም ላይ ጥናታዊ ፅሁፍ ያቀረቡት የግሎባል ቲቢ ፕሮግራም ዳይሬክተር ዶ/ር ማርዮ ራቨግሊዮን እንደገለፁት፤ በሽታው በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ስርጭት 133 ሰዎች ከ100 ሺህ ሰዎች ሲሆን በኢትዮጵያ ቁጥሩ 200 ሰዎች ከ100 ሺህ ሰዎች ይደርሳል ብለዋል፡፡ በሽታውን ለማስቆም በተያዘው ዕቅድ መሰረትም፤ እ.ኤ.አ ከ2016-2032 ዓ.ም ድረስ በበሽታው የሚያዙ ሰዎችን ቁጥር ከ100ሺ አስር ለማድረስ መታቀዱንም ተናግረዋል፡፡ ዕቅዱ እንዲሳካም አገራት ከፍተኛ ሥራ እንደሚጠበቅባቸውና ለተግባራዊነቱም የመንግስታቱን ቁርጠኝነት የሚጠይቅ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በተጠናቀቀው የፈረንጆች ዓመት ብቻ 9.6 ሚሊዮን ሰዎች በበሽታው የተያዙ ሲሆን ከእነዚህም መካከልም 1.5 ሚሊዮን የሚሆኑት በበሽታው ህይወታቸውን ማጣታቸውን ገልፀዋል፡፡ በበሽታው ከተከሰተው ሞት 95 በመቶ የሚሆነው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ አገራት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ በሽታው በህፃናት ላይም በስፋት እየታየ ሲሆን ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ብቻ አንድ ሚሊዮን ህፃናት በበሽታው መያዛቸውና ከእነዚህ መካከልም 140ሺ የሚሆኑት በበሽታው ህይወታቸውን ማጣታቸውንም ተናግረዋል፡፡ ቲቢ ኤችአይቪ በደማቸው ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን ገዳይ ከሆኑ በሽታዎች አንዱ ሲሆን ከሦስት የኤችአይቪ ህሙማን ሞት አንዱ የሚከሰተው በቲቢ መሆኑም በዚሁ ወቅት ተገልጿል፡፡
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ከሰተብርሀን አድማሱ፤ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በቲቢ ህሙማን ቁጥርና በበሽታው ስርጭት ያለችበት ከፍተኛ ደረጃ በሽታውን ለማጥፋት የተቀመጠውን ግብ ልታሟላ የሚያስችላት ይሆናል ወይ በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፤ “ከአስራ አምስት ዓመታት በፊት ስርጭቱ 400 ሰዎች በአንድ መቶ ሺህ ሰዎች የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ቁጥሩ በግማሽ ቀንሶ፣ 200 ሰዎች በ100ሺ ሰዎች ደርሷል፡፡ ይህ ደሞ ተስፋ ሰጪ ጅምር ነው፡፡ አሁን በሄድንበት ፍጥነት ከተንደረደርን በተባለው ጊዜ የበሽታውን ስርጭት ለመግታት የሚያስችልና የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት የሚያስችል ደረጃ ላይ እንደርሳለን” ብለዋል፡፡ በዓለም ጤና ድርጅት ዓለም አቀፍ ቲቢ ፕሮግራም አዘጋጅነት የተካሄደው ይኸው ጉባኤ በትናንትናው ዕለት ተጠናቋል፡፡

Read 3885 times