Saturday, 11 February 2012 10:15

ላሊበላ ገባን

Written by  ነቢይ መኰንን
Rate this item
(2 votes)

የላሊበላው የጉዞ ማስታወሻ

የናኩቶ ለአብን ቤተክርስቲያን ከጐበኘን በኋላ አስፋልቱ ዳር ወደቆመው አውቶብሳችን ስንመለስ እዚያው አካባቢ ወደሚገኝ አንድ ቤት ጐራ አልን፡፡ ውሃ ጠምቶናል፡፡ እንጀራ በድቁስ ይሸጣል እዛ ቤት፡፡ ጠላም አለ፡፡ እንጀራ በድቁስ በርበሬ በላን፡፡ የመጀመሪያ ጊዜዬ ነው እንደዚያ ያለ ድቁስ ስበላ፡፡ ጠላው እንዲያው ሰለክለክ ብሎ የሚገባ ጠላ ነው፡፡ ውሃ ጥም ይቆርጣል፡፡ አንዲት ከእኛ ጋር የሚሄዱ መነኩሲት በሃይላንድ አስሞልተው ወደ አውቶቡሱ ገቡ፡፡

የአውቶብሳችን መንገደኞች በሙሉ ሲመጡ መንገድ ጀመርን፡፡

እስካሁን ስለአቀማመጣችን አልነገርኳችሁም፡፡ ሁለት ሰው በሚይዘው ወንበር ላይ እኔና ባለቤቴ ተቀምጠናል፡፡ በዚያው መስመር ሦስት ሰው በሚይዘው መቀመጫ ላይ አንድ ወጣት አጭር፣ ቀጭን ልጅ አለ፡፡ ከጐኑ ትንሽ ጐልመስ ያለ ወጣት አለ፡፡ ከሱ ቀጥሎ እትዬ ፀሐይ አሉ፡፡ እትዬ ፀሐይ በኋላ ስናውቃቸው ደስ የሚሉ ተጨዋች ሴት ናቸው፡፡ ከወጣቱ ልጅ ጋር በጣም ስንግባባ እትዬ ፀሐይ ያጫወቱትን አጫወተኝ፡፡ ከዚህ ቀደም እንደተረኩላችሁ 47 የማይተዋወቅ ሰው የተጫነበት አውቶቡስ 47 አለመግባባት ይዞ ነው የሚጓጓዘው፡፡ የየሰው ፍላጐት እንደየፍጥረቱ የተለያየ ነው፡፡ በዚህ መለያየት ምክንያት የሚፈጠረውን ጥቃቅን አለመግባባት እልባት መስጠት በቀላሉ የሚቻል ነገር አይደለም፡፡ አባው አንድ ነገር ያዝዛሉ፡፡ ተጓዡ ሌላ ሀሳብ ያቀርባል፤ ውዝግብ ይፈጠራል፡፡ ይህንን አለመግባባት እትዬ ፀሐይ እንደሚከተለው ይገልፁታል፡፡

“በአንድ ቤት ውስጥ፣ በገጠር፣ አራት ሰዎች ይኖራሉ” አሉ፡፡ “ባል ሚስት፣ ሴት ልጅ እና አንድ አራሽ ዘመዳቸው ናቸው፡፡ ሁሉም መስማት የተሳናቸው ናቸው፡፡ እስከዛሬ ማናቸውንም ነገር ከጐረቤት ጋር እየተዋዋሱ ነው የሚጠቀሙት፡፡ አራሹ ይሄ መዋዋስ እስከመቼ ይቀጥላል? በማለት፤ ገበያ ይወጣና በሬ ገዝቶ ይመጣል፡፡ በሬውን ይዞ ሲመጣ፤

“አባወራው - “ይሄ አራሽ በቃችሁኝ የራሴን በሬ ይዣለሁ ማለቱ ነው” ይላል፡፡ ሚስት - “አሃ ሌላ የሚታረስላት ሴት አለች ማለት ነው” ትላለች አዲሱን በሬ ስታይ፡፡

ልጅ - “እኔ ሳላውቅ እናንተ በፈለጋችሁት መንገድ ልትድሩኝ? በጭራሽ አይሞከርም” ትላለች፡፡

አራሽ ያሰበው ሌላ፤ ሌሎቹ ያሰቡት ሌላ!

ከናኩቶ ለአብ አካባቢ ጉዟችን ወደ ላሊበላ ሆነ፡፡

ላሊበላ ከተማ ገባን፡፡ የምናርፈው በሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቱ ቅጽር ግቢ ነው፡፡ አንድ ክፍል እንድናድር የተዘጋጀ መሆኑን ነግረውን ክፍሉን አየነው፡፡

በጭራሽ 47 ሰው ሊያድርበት አይችልም፤ የሚል ክርክር ተነሳ፡፡ “ሁለት ክፍል መዘጋጀት ነበረበት የሚልና፤ ተበቃቅቶ መተኛት ይቻላል” በሚል ብዙ አጨቃጨቀ፡፡ በመጨረሻ የተወሰኑ ሰዎች “እኛ ተለይተን ለት/ቤቱ የሚከፈለውን ገንዘብ አዋጥተን ከፍለን፤ ለብቻ እናድራለን፤ መጨናነቅ የለብንም” አሉ፡፡ ተለያይቶ ማደሩ ግድ ሆነ፡፡ 13 ሰዎች ናቸው፡፡

እዚህ ውስጥ እኔም አለሁ፡፡ ከ47 ሰዎች መካከል 13 የሚግባቡ ሰዎች ማግኘት ከባድ ነበር፡፡ ብዙ ጊዜ ፈጀ ውዝግቡ፡፡

የላሊበላን ከተማ ዘወር ዘወር ብለን ለማየትና መታጠቢያ ለመፈለግ ወደ ከተማ ወጣን፡፡ እያጠያየቅን ስንጓዝ ፀሐዩ በረታብን፡፡ መታጠቢያውን ገና አላገኘንም፡፡ አንድ ቡና ቤት ጐራ አልን፡፡ አብረውኝ ያሉት ያ ወጣቱ ቀጭን አጭር ልጅና ጐልመስ ያለው ወጣት ናቸው፡፡ ወጣቱ ልጅ አሁን የገባንበትን ቡና ቤት ከዚህ ቀደም የሚያውቀው መሰለኝ፡፡ ቢራ፣ ጠጅና ጠላ አንድ ላይ የሚሸጥበት ቦታ ነው፡፡ ወደ መፀዳጃ ቤቱ ስሄድ የሰው አቀማመጥ አስገርሞኛል፡፡ ወደ ጓሮ መውጫው አካባቢ ጠላ ጠጪ ነው ያለው፡፡ መካከለኛው ቤት በብዛት ጠጅ ጠጪ ነው ያለው፡፡ ደጅ፣ ከፊት ለፊት፣ ቢራ ጠጪው አለ፡፡ በመሠረቱ ወጣቱና ወጣቱ ጐልማሳ እዚህ ቤት እንድንገባ የፈለጉት የገናን ፆም እስከዘጠኝ ሰዓት የሚፆሙ ስለሆነ እስካሁን ምንም እህል በአፋቸው አልዞረም፡፡ ስለዚህ ምግብ ለመቅመስ ፈልገዋል፡፡

“እዚህ ቤት ብርዛቸው ቆንጆ ነው ጋሽ ነቢይ” አለኝ ወጣቱ፡፡

“በጣም ጥሩ እንሞክረዋ፡፡ ጠጅ መሸጡ ገርሞኛል” አልኩት፡፡

“አሃ የማር አገር’ኮ ነው፡፡ ላሊበላ እኮ እንደምንጠራው አይደለም ስሙ፡፡ ላልይበላል ነው ትክክለኛው አጠራር፡፡ ይህም “ንብ ሊበላው” ማለት ነው፡፡ ታሪኩ እንዴት መሰለህ ጋሽ ነቢይ፤ ቅዱስ ላል ይበላል፡፡ በተወለደ ጊዜ ሰዎች በላዩ ላይ ንቦች ሰፍረውበት እንደማር ሲልሱት አይተው ያወጡለት ስም ነው ይባላል፡፡ “ላል” ማለት በአገውኛ ቋንቋ “ንብ” ማለት ነው፡፡ “ይበላል” ሲጨመርበት ላልይበላል የሚል ስም ይሰጠናል፡፡” አለኝ፡፡

ዕውነትም ብርዙ አሪፍ ነው፡፡ የማር አገር ለመሆኑ ይመሰክራል፡፡ ስለላልይበላል ከተማና ስለራሱም ስለላልይበላል ታሪክ ያነበብኳቸው ጽሑፎች በአብዛኛው የሚከተለውን አማካይ ታሪክ ያካተቱ ናቸው፡፡

“ላስታና ቅዱስ ላሊበላ የሚገኘው በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል በመኪና ከአዲስ አበባ ደሴ ወልዲያ ጋሸናን አድርጐ 700 ኪ.ሜ፤ ወይም ወልዲያ ሲደርሱ ከወልዲያ እስከ ድልብ ተጉዘው፣ በኩል መስክ በገነተ ማርያም ወደ ቅ/ላሊበላ ከተጓዙ፣ በጋሻና ካለው መንገድ 60 ኪሎ ሜትር ቀንሶ 640 ኪ.ሜ ያህል ተጉዘው ነው፡፡

ሁለኛው የመኪና መንገድ ከአዲስ አበባ - ባህር ዳር ወረታ ደብረታቦር - ጋይንት - ገረገራ - ጋሻና ቅ/ላሊበላ 865 ኪ.ሜ ነው፡፡ በአየር ለመሄድ ላሻም፣ ከአዲስ አበባ፣ ከባህርዳር፣ ከጐንደር፣ ከአክሱም ወደ ላስታ ቅ/ላሊበላ መምጣት ይቻላል፡፡”

ከላይ በተጠቀሱት መንገዶች የተመጣበት ቦታ የቅዱስ ላሊበላን ታሪክ ያቀፈ ድንቅ ቦታ ነው፡፡

ቅዱስ ላልይበላል ታህሳስ 29-1100 ዓ.ም ከዣን ስዩምና ከወ/ሮ ኬረወርና ተወለደ፡፡ ኬረወርና ተወለደ፡፡ ኬረወርና በአገውኛ ቤተክርስቲያን ማለት ነው፡፡

ላልይበላል ቡግና እየተባለ በሚጠራው በአባቱ በዣን ስዩም ቤተመንግስት ውስጥ ለነገሥታት ልጆች የሚሰጥ መንግሥታዊ የአስተዳደር ሥርዓትና የቤተክርስቲያን ትምህርት እየተማረ አደገ፡፡

ላልይበላል በ22 ዓመቱ ወንድሙ አፄ ገ/ማርያም እንደተመቀኘውና አንድ ቀን በነገረ- ሠሪዎች ምክንያት ከሦስት እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ እንዳስገረፈው ዜና ገድለ ላልይበላል ይገልፃል፡፡

አፄ ገብረማርያም ወንድሙን ካስገረፈው በኋላ የሞተ መስሎት አውጥተው እንዲጥሉት አዘዘ፡፡ ቅዱስ ላልይበላል ግን እግዚአብሔር ከግርፋትና ከጥፋት ከልሎታልና እንኳንስ ሊሞት ግርፋቱም አልተሰማውም፡፡ ስለዚህም ከጊዜያት በኋላ አፄ ገብረማርያም የወንድሙን የላልይበላልን በህይወት መኖር ሰማ፡፡ አስጠርቶት መጥቶ ፊቱ ሲቆም ከባድ ሀዘን ተሰማው፡፡ ቅዱስ ላልይበላልን በህዝቡ መካከል ከዛሬ ጀምሮ መንግሥት ላንተ ይገባል፡፡ በግፍ አስገርፌሃለሁና ይቅር በለኝ በማለት ከጫማው ሥር ወድቆ ይቅርታ ከጠየቀ በኋላ መንግሥቱን አስረክቦት መንኖ ለመሄድ ወሰነ፡፡ ቅዱስ ላልይበላልም “ለይቅርታው ይቅር ብዬሃለሁ፤ ነገር ግን መንግሥት የእግዚአብሔር ገንዘብ ናትና መንግሥትህን የምቀበለው ከእግዚብሔር እንጂ ካንተ አይደለም፡፡ አንተም በዙፋንህ መቆየት አለብህ፡፡ እኔም መልስም ሆነ ፈቃድ ከእግዚአብሔር እስካገኝ ድረስ በትዕግስት እጠባበቃለሁ” በማለት የአፄ ገ/ማርያምን ጫማ ስም በፍቅር ተሰናብቶ ወጣ፡፡

በዚህ ጊዜ ሕዝቡ - መንግሥትን ያህል ነገር እንደቀላል ነገር ቆጥሮ፤ አልነግሥም አንተ በመንግሥትህ ቆይ፤ ብሎ ትቶ መሄዱ እንዴት የእግዚአብሔር መንፈስ ቢያድርበት ነው? በማለት፤ በችሎት ተቀምጦ ሁኔታውን በግብር ሲከታተል የነበረው ሁሉ እያለቀሰ፤ ቅዱስ ላልይበላልን ተከትሎ ወጣ፡፡

… ቅዱስ ላልይበላል ወደ እየሩሳሌም ለመሄድ ወሰነ፡፡ አክሱም ቆይቶ፤ በሱዳን ምድር አቋርጦ ወደ ግብፅ ሄደ፡፡ በግብፅ ብዙ ክርስቲያኖችን አገኘ፤ ተዋወቀ፡፡ … ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ መጥቶ “በአሁኑ ጊዜ አንተ ወደ እየሩሳሌም ለመሄድ አልተፈቀደልህም፡፡ ይልቁንስ እነዚህ በግብፅ ምድር የተበተኑትን በጎቼን ወደመጣህበት ወደ ኢትዮጵያ ይዘህ ተመለስ” ብሎ ስለነገረው፤ ስልሳ ሺህ ክርስቲያኖችን ይዞ ከግብፅ ወደ ኢትዮጵይ ተመለሰ፡፡

አፄ ገ/ማርያምም ወንድሙ ቅዱስ ላልይበላል ሕዝበ - ክርስቲያንን ይዞ የኢትዮጵያን ምድር እንደረገጠ በሰማ ጊዜ በክብር የሚቀበለው ቁጥር ሥፍር የሌለው ሠራዊት አሰልፎ ወደ ቤተመንግሥቱ እንዲመጣ ላከበት፡፡ ቅዱስ ላልይበላልም የእግዚብሔር ፈቃድ እንደደረሰ አውቆ ልዋል ልደር ሳይል ወደ ቡግና ቤተ መንግሥት መጥቶ ከወንድሙ ከአፄ ገ/ማርያም ጋር ተገናኘ፡፡ አፄ ገ/ማርያምም ወንድሙን ቅዱስ ላልይበላልን ባየ ጊዜ በፍቅር እንባ ተቀበለውና ሕዝቡን ሰባስቦ “አሁን የእግዚአብሔር ፈቃድ ደርሷል፡፡ መንግሥት ለዚህ ሰው ይገባል፤” ብሎ ዙፋኑን ለቅዱስ ላይይበላል አስረክቦና ተሰናብቶ ዛሬ ቅዱስ ሀርቤ እየተባለ ወደሚጠራው ገዳም ሄደ፡፡ በዚያም ዘግቶና በፆም በፀሎት በቀኖና ሰውነቱን ለእግዚአብሔር አስገዝቶ በክብር አርፏል፡፡

ቅዱስ ላልይበላል ከዚያን ጊዜ ጀምሮ መንግሥቱን ተቀብሎ ሕዝቡን በሰላም በሃይማኖት ይመራ ጀመር፡፡  ቅዱስ ላልይበላል በዘመነ መንግሥቱ ሁሉ እንደሌሎች ነገሥታት ርስት፣ ጉልት ፈፅሞ አልነበረውም፡፡ ከሕዝቡም በንጉሥነቱ ምክንያት የሚቀበለው ግብርም ይሁን ሌላ ምንም አልነበረውም፡፡

ቅዱስ ላልይበላል ንጉሥ ነኝ ብሎ ሥልጣኑን ጨብጦ አስተዳደሩን ጨቁኖ አልያዘም፡፡ ሥልጣኑን ለህዝቡ ሰጥቶ በሕዝቡ ይመራ እንደነበር ታሪከ-ነገሥት ይመሰክራል፡፡ ከሁሉ የሚያስደስተው፣ የሚያስቀናውና የሚያስደንቀው ደግሞ ለዕለት ምግቡ እንኳ ከችሎት ሲመለስ በስውር ሰሌዳ እየሠራ ያንንም ለታማኝ አሽከሩ ሰጥቶ እየሸጠ፣ ከዚያው ገንዘብ ጥሬም ሆነ ቁራሽ እንጀራ ለቁመተ - ሥጋ ያህል ይቀምስ ነበር እንጂ እንደ ሌሎቹ ነገሥታት ጮማ በመቁረጥ፣ ጠጅ በማማረጥ ልብሰ-መንግሥት ለብሶ በመሽሞንሞን አልኖረም፡፡

… ሕዝቡም የቅዱስ ላልይበላልን የሃይማኖት ፅናትና ደግነት እያየ ይህን ሃይማኖታዊ ንጉሥ ዕድሜውን አርዝምልን እያለ ይፀልይለት እንደነበር ይነገራል፡፡

ቅዱስ ላልይበላል መዋዕለ - ዘመኑን በሰላምና በፅኑ ዕምነት ያሳለፈ ንጉሥ ነበር፡፡ ሰኔ 12 ቀን 1172 ዓ.ም በነገሠ በ40 ዘመኑ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡ ንጉሥ ላልይበላል የሚያስቀና ንጉሥ ነው፡፡ ምነው ቢሉ፤

ወንድሙን - እኔ አልነግሥም አንተ በመንግሥትህ ቆይ ማለቱ! (ዛሬ ይሄን ማን ያደርጋል?)

ወንድሙም - የእግዚአብሔር ፈቃድ ደርሷል፡፡ መንግሥት ለዚህ ሰው ይገባል ማለቱ ና ማስረከቡ! (ዛሬ ይሄን ማን ያደርገዋል?)

ህዝቡን በሰላምና በሃይማኖት መምራቱ

ርስት ጉልት አለመፈለጉ (ይህን ዛሬ ማን ሊያደርገው ይችላል?)

ሥልጣኑን ጨብጦ፣ አስተዳደሩን ጨቁኖ አለመያዙ (ዛሬ ይሄን ማን አደረገ?)

ሥልጣኑን ለህዝቡ መስጠቱ (ዛሬ ይህን ማድረግ ከቶ ማን ይቻለዋል?)

ጮማ አለመቁረጡ፣ ጠጅ አለማማረጡ፣ በልብሰ መንግሥት አለመሽሞንሞኑ (ከቶ ይሄንስ ዛሬ ማን ሊያደረገው ቻለ?)

ይህን ቅዱስ ንጉሥ ዕድሜው እንዲረዝም ህዝቡ መፀለይ (ይህን ከቶስ ማን ሊታደለው ይችላል?)

ከሁሉም በላይ ግን ጥበብን የታደለ ቅዱስ ንጉሥ መሆኑ፤ ታላቅ ፀጋ ነው፡፡

ላይይበላል

“ሃያ ሶስት ዓመት ሙሉ ቆፍሮ

ሃያ ሶስት ዓመት ሙሉ ወቅሮ

ድንጋይ በድንጋይ ጠፍሮ

በመንፈስ ቁግ ሐብል አሥሮ

ታሪክ ሠርቶ ታሪክ ነገሮ -

የሚቀረፅ የሚዳሰስ፤

አገር ያቆየ ንጉሥ

አገር ያፈራ ቅዱስ!

ማሩን በማማር ያሳየ

ተፈጥሮን ፈጥሮ የለየ

ከዓለም ባሻገር አለም፣ ጥበብ በአለት ያፀኸየ!

አገር ያቆየ ንጉሥ

አገር ያፈራ ቅዱስ!

ላልይበላል ነው እሱስ

ላልይበላል ነው መቅደስ!!” እላለሁ፡፡

የላልይበላልን ውቅር አብያተ-ክርስቲያናት ለማየት ፊታችንን ወደ ነገ አዙረን እንተኛ!

(ይቀጥላል)

 

 

Read 4553 times Last modified on Saturday, 11 February 2012 10:25