Saturday, 11 February 2012 10:25

የጌታና ባሪያ ወግ

Written by  ስብሃት ገ/እግዚአብሄር
Rate this item
(0 votes)

ባርያ ሲባል ወንዱም ሴቱም ያው ነው፣ ባርያ ነው በቃ! ክብር አይወድለትም፡፡ ይህን የሚሉት ጌቶቹና እመቤቶቹ ናቸው፣ ያውም ወላጆቹ ያወጡለትን ስም እንኳ ሊጠሩት ሰብአዊ በጎ ፈቃድ ስለሌላቸው፡፡ ባርያ ምስጢርና ተራ ወሬ አይደለም፣ የመጣለትን ወሬ ሳያመዛዝን መዘርገፍ ነው በዚያ በገመድ አፉ ይላሉ እንግዲህ፡፡ ባሮችስ ምናቸው ሞኝ ነው? ሊደበቅ የሚገባውን መዘክዘክ! እርባና የሌለው ወሬ ቢሆንም መዘክዘክ! እዚህ ክፍታፍነት ሽፋን ስር ተደብቀው የሚኖሩ፣ በጮካ-ብልጥነት ጌቶቹንም እመቤቶቹንም በእፍረት የሚገርፉ ባሮችም አሉ፡፡ ለቅምሻ ያህል በምሳሌነት የሚከተሉትን ታሪኮች እጠቅሳለሁ፡፡ በዚች አብዛኛው ሰው ቢያንስ ሁለት ሶስት ጊዜ ሰምቷት በሚያውቅ ልጀምርላችሁ፡፡ ጌቶች ለአስር ቀን ያህል እውጪ ሰንብተው፣ ዛሬ ፀሀይ ስትጠልቅ እቤት ገቡ፡፡ ከገብሬ ሌላ ሰው የለም (እሱ ቤት እየጠበቀ ነው) ጌቶች ተቀምጠው፣ እሱ እግራቸውን አጥቦ፣ ከድካማቸዉ ለማረፍ ገና “እፎይ” ከማለታቸው፣ ገብሬ ከሳቸዉ ፈንጠር ብሎ ከተቀመጠበት ሰውነቱን በሀዘን እያወዛወዘ የብቸኛ ወንድ ልጃቸውን እየደጋገመ ይጠራል፡፡

“እፎይ ለዬ! እፎይ ለዬ! እፎይ ለዬ!”

“አንተ ገብሬ፣ ምን ሆነህ ነው ምታላዝንብን? ለዬ ምን ሆነ?”

“ነብር ቧጠጠ”

“ነብር ቧጠጠው?!” ብለው ጮሁ “ጐዳው?”

“ጐዳም አልጐዳ፣ ትላንት ቀበርኔ!”

(ገብሬ’ኮ ጌቶች ድክም እንዳላቸውና ራብ እንደሚሞረሙራቸው አሳምሮ ያውቃል፡፡ ግን ባርያ ጅል ነው ብለው ስለሚያምኑ፣ ምንም ያጠፋ ሳይመስለው ጌቶችን እራት እንዳይበሉ፣ ረሀብና ሀዘን እንቅልፍ እንደሚነሱዋቸው ከእቅዱ ውስጥ በማስገባት ነው …

… ይሄኛው ገብሬ ቀልደኛ ሰውዬ ነው፡፡ እኚህኛው ጌቶች ደሞ ለአስር ቀን ያህል ውጪ ሰንብተው፣ ዛሬ ወደ እኩለ ቀን ላይ ወደ ቤት ተመልሰው፣ ገብሬ እግራቸውን ካጠባቸው በኋላ ከሳቸው እልፍ ብሎ ተቀምጦ፣ በትዝብት አይነት ራሱን እየነቀነቀ፡-

“ወይ ትላንትና’! ወይ ትላንትና!” እያለ ይደጋግማል

“አንተ ገብሬ፣ ምን ሆነህ ነው ራስክህ ‘ምትነቀንቅብኝ?”

“ጉድ ፈላ ብዬ ነው”

“የምን ጉድ ነው የፈላው?”

“ማታ በኩራዝ ብርሀን እሜቴ ፈስ አምልጧቸው ስንጨነቅ አደርኔ!” …

.. አመቴ የአእምሮ ዘገምተኛ ኰረዳ ናት፣ እና ብቻዋን ነው፤ አንዲት ጠባብ ክፍል ውስጥ የምትተኛው፡፡ ቅድም እንደተናገርነው፣ የሰፈሩ ጐረምሶች የቅንዝር ማብረጃ ናት፡፡

ቤቷን ዘግታ ልትተኛ ስትል፣ አድፍጦ ሲጠብቅ የቆየ ጐረምሳ በትንሽ ድምፅ ያንኳኳል፡፡

“ማን ነህ?” ትላለች በዚያው ሹክሹክት

“እኔ ነኝ!”

“ታውቀኛለህ?”

“አዎን አውቅሻለሁ”

“እስቲ አመቴ ነሽ በለኝ”

“አመቴ ነሽ”

“እውነትም ታውቀኛለህ፡፡ በል ግባ” ብላ ትከፍታለች …

… ይሄ አራተኛው ገብሬ ከሌሎቹ ገብሬዎች የበለጠ ብልህ ስለሆነ የሱን ተንኰል ለመጨረሻ አስቀመጥኩላችሁ (ፍርዱን ለአንባቢ ለመተው እንዲያመቸኝ ብዬ፡፡)

እኚህ አራተኛው ጌቶች ደግሞ ለጦርነት መርሸው፣ በዘመቱ በሰባት አመታቸው ወደ ቤታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ ወደ እኩለ ቀን ይሆናል፣ ገብሬ ከሩቅ ሲያያቸው እንደ ነፋስ እየሮጠ መጣ፣ የፈረሳቸዉን ልጓም ገቱ፣ ገብሬ በደስታ እያለቀሰ እግራቸውን ተሳለመ፡፡

“እህ ገብሬ፣ ምነው ቡቺ አብሮህ የለም?”

“ቡቺማ ሞተ”

“ውይ፣ ቡቺዬ! ምን ሆኖ ሞተ?”

“አጥንት ሲግጥ በጉሮሮ ተቀርቅሮ አነቄ”

“አዬ ጓዴ፣ አጫዋቼ! የምን አጥንት ነው እሱ?”

“የሳልገኝ”

“ሳልገኝ የልብ ጓደኛዬ ሞተ? ያ ሲያርስ ውሎ የማይደክመው ጀግና!? ምን ሆኖ ሞተ?”

“ለተዝካር ታረዴ”

“የማን ተዝካር ነው እሱ?”

“የሜቴ ተዝካር ኖ”

“የቆረብኩላት የኑሮ ጓደኛዬ! ደጋፊዬ አለኝታዬ!! ምን ሆና ሞተች?”

“በወሊድ ሞቴ”

“ሰአሊ ለነ ቅድስት! አባቱስ ማን ነው ይላሉ?”

“አባቱ ገብሬ ነው ይላሉ፡፡ እኔ ግን እሳቸው ያረገዙት ከሌላ ባርያ ነው እላለሁ”

ከዚህ የባሰ ዘግናኝ ቅጣት ከየት ይመጣል? አይ ገብሬ ጀግናው! …

ከዚህ በላይ የተፃፉት ታሪኮች፣ ጌታና ባሪያ በቅራኔ ሲኖሩ ያሳያሉ፡፡ በጌትየው እይታ ባሪያ ከሰው በታች ነው፡፡

እቺ የምትከተለው ታሪክ ግን ጌታና ባሪያ ሰውና ሰው ሆነው በወዳጅነትና በመከባበር ሲኖሩ ታሳየናለች፡፡

ጊዜው በአጤ ምኒልክ ዘመነ መንግስት ማብቅያ አካባቢ ላይ ነው፡፡ አቶ ስመኝ ሴት ባሪያ ሊገዙ ገበያ ሄዱ፡፡ በለስ ሲቀናቸው አንዲት ገጽታዋም አኳኋኗም የደስ ደስ ያላት፣ በሃያ አምስት አመት የምትገመት ሴት አገኙ፡፡ ውቃቢያቸው ወደዳት፡፡ እንደ ሌሎች ገዢዎች ገላዋን ሳይደባብሱ፣ እኝ በይ ጥርስሽን ልየው ሳይሉዋት

“ስምሽ ማን ነው?” ጠየቁዋት

“ስሜ ጆርጌ ነው” አለቻቸው

“ስሚኝ ጆርጌ” አሉዋት “ሚስቴ አምስት ህፃናት ጥላብኝ ሞተች፡፡ እንጀራ እናት ብታሳድጋቸው ውድ ልጆቼን ትጐዳብኛለች ብዬ ፈራሁ፡፡

አንቺ ከኔ ጋር መጥተሽ አብረን ብናሳድጋቸው ጥሩ ይመስለኛል፡፡

ፈቃደኛ ነሽ?”

“ታዛዥ ነኝ”

ቤታቸው ደርሰው ከልጆቻቸው ጋር ሲያስተዋውቁዋት “እቺ ጆርጌ ናት፡፡ እንደ ባሪያችሁ ሳይሆን እንደ እናታችሁ እየተንከባከበች ታሳድጋችኋለች፡፡ ፈቃደኞች ናችሁ?”

ልጆቹ በጣም ፈቃደኛ መሆናቸው ከሁኔታቸውና ከፈገግታቸው ያስታውቅ ነበር፡፡ በሁለት ሶስት ቀን ውስጥ ተለማመዱ፡፡ አማርኛ ስትናገር በአፍ መፍቻ ቋንቋዋ ቅላፄ ስለሆነ በጣም ያስሰቃቸዋል፡፡

እሷ ደሞ “አማራ ያገኘውን እህል እያግበሰበሰ ሆዱ እስኪወጠር ስለሚበላ፣ ፈሱ ሲቆንስ እንደ መርዝ ነው፤ ንፋሱ ከሚመጣበት በኩል አትቁሙ አትቀመጡ፡፡ ፈሳቸው አንዴ ካመለጠ ቶሎ አይጠፋም፡፡ ራስ ምታት ያስይዘኛል፡፡” ይህን ሁሉ የምታወራው ዝብርቅርቅ ባለ አማርኛ ስለሆነ ሲስቁባት አያባሩም፡፡ ድምጿ ግን ደስ የሚል ወፍራምና ልዝብ ነው፡፡ በተለይ ስትስቅ ሲያምርባት ልጆቹ ሲጠሩዋት “እማ ጆርጌ” እያሉ ሆነ፡፡

ይሄ ሁሉ ሲሆን፣ አቶ ስመኝ የወጥ ቤት ሙያዋ ለሳቸውም ለልጆቻቸውም በጣም ስለተስማማቸው እንደ ልጃቸው ያስቡላት ጀመር፡፡

“እኔ በሌለሁ ጊዜ ቤቱን እንድትጠብቂ” ብለው ጠመንጃቸውንም ሽጉጣቸውንም መተኮስ፣ እና ፈታትቶ ዘይት ቀብቶ መልሶ መገጣጠም አስተማሯት፡፡

እንደዚህ የሞቀ ደስተኛ ቤተሰብ ሆነው ጥቂት አመት አብረው ኖሩ፡፡ ዳሩ ምን ይሆናል፣ አቶ ስመኝ ለአንድ ሳምንት ያህል ቤቱን እንድትጠብቅ ለእማ ጆርጌ በአደራ ትተውላት ሄዱ፡፡

መሄዳቸውን ያወቁ ባሪያ ፈንጋዮች በድንገት ተከሰቱ፡፡ ልጆቹን አስፈራርተው እማ ጆርጌን ዘርፈው ወሰዷት፡፡ አቶ ስመኝ ሲመለሱ ከልጆቻቸው ጋር በሀዘንና በናፍቆት ተሰቃዩ፡፡ ቢያፈላልጉ ቢያጠያይቁ እነ ጆርጌን የበላ ጅብ አልጮህ አለ፡፡ ወራት አለፉ፡፡

ተስፋ ቆርጠው መኖሩን እየተለማመዱት ሄዱ፡፡

እና አንድ ቀን ወደ ማታ ላይ ሽለላና ፉከራ ሰሙ “ዘራፍ እኔ ጆርጌ የስመኝ ባሪያ” እያለች ጠበንጃ ደጋግማ ተኩሰች፡፡ ግቢያቸው ስትደርስ ከጥቁር ፈረስ ላይ ዘልላ ወርዳ እየሮጠች መጥታ ሁሉንም አንድ ላይም በየተራም ሳመቻቸው፡፡

እየተሳሳቁ እራት እየበሉ ታሪክዋን ነገረቻቸው፡፡ የፈንጋዮቹ አለቃ እንድታገለግለው ወደ ቤቱ ወሰዳት፡፡ ምንም እንደማያውቅ ተራ ባሪያ መስላ ተቀመጠች፡፡ የመንደሩን ሰዎችና ከብቶቻቸውን በጥንቃቄ እያስተዋለቻቸው ኑሮዋን ተላመደችው፡፡

አንድ ቀን ጌታዋ ቤቱን በአደራ ትቶላት ከሳምንት በኋላ እመለሳለሁ ብሏት ሄደ፡፡ ጠበንጃው የተለመደው ቦታ ተሰቅሏል፡፡ ጠበንጀውንም ከነዝናሩ፣ ጥቁር ሀር የመሰለ ፈረሱንም ከነኮርቻው ዘርፋ፣ በግልብያ ወደ ስመኝ ቤት ተመለሰች፡፡

አቶ ስመኝ ልባቸው ተነካ፡፡ ጆርጌን ሊክሱዋት ፈለጉ፡፡ አንድ ቀን ለብቻዋ ጠርተው አነጋገሩዋት፡-

“ከእንግዲህ ወድያ የኔ ባሪያ አይደለሽም” አሉዋት “ነፃነትሽን ሰጥቼሻለሁ፡፡ ግን ብቻሽን ብትሄጂ፣ ሩቅ ሳትደርሺ ፈንጋዮች አፍነው ይወስዱሽና ወደ ባርነት ይመልሱሻል፡፡ ስለዚህ ስንቅ አዘጋጂልንና ወደ ቤተሰቦችሽ ላድርስሽ”

እንባው እየተናነቃት እጃቸውን ወስዳ ሳመችው፡፡ “አባቴ የጐሳችን መሪ ነው፣ ባለ ሙሉ ስልጣን፡፡ ታናሽ ወንድሙ “አባትሽ ይፈልግሻል፡፡ አምጣልኝ ብሎ ልኮኝ ልወስድሽ መጣሁ” አለኝ፡፡

“አመንኩት፣ ወስዶ ለፈንጋዮች ሸጠኝ፡፡ ዛሬ ወደ አገሬ ብመለስ፣ አባቴ ይህን ከሀዲ ሰይጣን ወንድሙን በህግ ያስፈርድበትና በሞት ያስቀጣዋል፡፡ እንዲህ ቤተሰቤም ጐሳዬም ሀዘን ከሚደርስባቸው፣ ካንተ ጋር መኖርን እፈቅዳለሁ፡፡ ከልጆቼም ጋር ከምለያይ፣ ባርነቴን እመርጣለሁ ከፈቀድክልኝ፡፡”

አቶ ስመኝ ደስታውን አልቻሉትም “እመ ብርሃንን እያመሰገንኩ በሙሉ ልቤ ፈቃደኛ ነኝ” አሉዋት “የሚቀጥለው ስራችን ልጆቻችንን መዳር ይሆናል”

አሜን ብላ ተቀበለች፡፡ ይህ ታሪክ ልቦለድ ቢሆን ኖሮ ከዛሬ ጀምሮ የጭን ገረዳቸው ያደርጉዋት ነበር፡፡ አቶ ስመኝ ግን እንዲህ አይነት ርካሽ ድርጊት በሀሳባቸው እንኳ መጥቶ አያውቅም፡፡ እማ ጆርጌን የላከላቸውን ፈጣሪ አመሰገኑ፡፡ ይህን ታሪካቸውን የነገሩኝ እሳቸው ራሳቸው ናቸው፡፡ እሳቸው ሲተርኩልኝ ግን አማርኛዋ ቅላፄው የጐሳዋ ልሳን ሆኖ የቃላትና የሀረግ አሰካኩ በጣም የተዘበራረቀና አስቂኝ ነበር፣ በጽሑፍ መግለፁ አልሆንልህ ስላለኝ በራሴ አማርኛ አቅርቤላችኋለሁ፡፡

እስከሚቀጥለው ቸር ይግጠመን አሜን!!

 

 

=====================================================================================የትጋት እመቤት!

ትውልዷና እድገቷ በሰሜናዊው የአገሪቱ ክልል መቀሌ ከተማ ውስጥ ነው፡፡ ተወልዳ ካደገችበትና እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ትምህርቷን ከተከታተለችበት የመቀሌ ከተማ በ1979 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ መጣች፡፡ እዚሁ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ በመግባትም በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽንና በማርኬቲንግ ሙያዎች ትምህርቷን ተከታትላ በዲፕሎማ ተመረቀች፡፡

የሥራውን ዓለም የተቀላቀለችው ግን በጠብታ መስኖ ቴክኖሎጂ ላይ ለሚሰራና “አማረኤፍሞይ” ለተባለ እስራኤላዊ ድርጅት ፀሐፊ በመሆን ነበር፡፡ ይህ ድርጅት የጠብታ መስኖን (Dip irrigation) ቴክኖሎጂን በኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት ለማስተዋወቅ የመጣ ቢሆንም በወቅቱ ቴክኖሎጂው በህብረተሰቡ ዘንድ እምብዛም ባለመለመዱ የድርጅቱ ሠራተኞች አብዛኛውን ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት ያለስራ ነበር፡፡

ሆኖም ግን ወርሃዊ ደመወዛቸውን በወቅቱ ከመቀበል የሚያግዳቸው ነገር አልነበረም፡፡ ይህ ሁኔታ ለሥራ ወዳዷ አስቴር ፈጽሞ ሊዋጥላት አልቻለም፡፡ ከወር እስከ ወር ያለ ሥራ ተቀምጦ የሚወሰድ ወርሃዊ ደመወዝን ህሊናዋ አልተቀበለውምና ከራሷ ጋር መክራ ወሰነች፡፡ ሥራዋን በፈቃዷ ለመልቀቅ መወሰኗን የነገረቻቸው የድርጅቱ የሥራ ኃላፊዎች ግን ሃሳቧን ፈጽሞ ሊቀበሏት አልፈለጉም፡፡ ለሥራ መልቀቋ ምክንያት የሆናትን ነገር መለወጥ እንደምትችል አሳምነው፣ ደንበኛ እንድታመጣና ከሚገኘው ገቢ ተካፋይ እንድትሆን አደረጓት፡፡ አሁን ሁኔታው ለአስቴር በጣም ተመቻት፣ ደንበኞች ፍለጋ በምታደርገው ሩጫ ስለ ጠብታ መስኖ የበለጠ እውቀት እያዳበረችና ሙያውን እየወደደችው ሄደች፡፡ ግን ወቅቱ ስለጠብታ መስኖ ቴክኖሎጂ በቂ ግንዛቤ ያልነበረበት ጊዜ ስለነበር ቴክኖሎጂውን ለማስተዋወቅ በምታደርገው ጥረት ሰዎች ይሳለቁባት ነበር፡፡ ምን ማለት ነው? በዓመት ሁለቴ ዝናብ ላላት አገር ለዚያውም ተንጠባጥባ በምትገኝ ውሃ ምን አይነት ሰብል ሊመረት ይችላል?... በሚል፡፡

ግን ተስፋ አልቆረጠችም፡፡ ዕለት ከዕለት የምታየው ለውጥና እንቅስቀሴም ተስፋዋን አለመለመው፡፡ እ.ኤ.አ እስከ 2000 ዓ.ም በዚህ ሁኔታ ቀጠለች፡፡ የእስራኤላውዊ ድርጅት ኃላፊዎች ወደአገራቸው ሲመለሱ ወ/ሮ አስቴርን በኢትዮጵያ የድርጅቱ ወኪል አደረጓት፡፡ የጠብታ መስኖ ቴክኖሎጂው ቀስ በቀስ እየታወቀና እየተለመደ በመምጣቱም ሥራዎች ይመጣሉቸው ጀመር፡፡ የተለያዩ የአበባ እርሻዎች፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ማሳዎች ቴክኖሎጂውን ለመጠቀም ጥያቄ ማቅረብ ጀመሩ፡፡ ሁኔታው ለሥራ ወዳዷ እንስት ትልቅ ደስታ ነበር፡፡ ደከመኝ፣ ሥራ በዛብኝ፣ እረፍት እፈልጋለሁ ሳትል የደንበኞቿን ጥያቄ ለመመለስና በአግባቡ ለማስተናገድ ደፋ ቀና ማለቱን ተያያዘችው፡፡ መናገሻ ፍላወርስ፣ ድሬ ሃይላንድ፣ አርሲ አበባ የወ/ሮ አስቴር ተስፋሚካኤልን ዝናባማ እጆች ያገኙና የጠብታ መስኖ ቴክኖሎጂውን ተጠቅመው ውጤት ካስገኙ የእርሻ ማሳዎች ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ለአምስት አመታት የድርጅቱ ወኪል ሆና ከቀጠለች በኋላ ራሷን ችላ ለመቆምና ባለሙያዎችን ይዛ በግሏ ለመስራት ወስና “አስቱኔት ቢዝነስ ኢንተርፕራይዝ” የተባለ ድርጅት አቋቋመች፡፡ ድርጅቱ እስራኤል አገር ከሚገኝ የጠብታ መስኖ ቴክኖሎጂ መሥሪያ ዕቃዎችን ከሚያመርት ድርጅት ጋር ግንኙነት እንዲፈጥር በማድረግ ሥራዋን ቀጠለች፡፡ በሙያው የሰለጠኑ ባለሙያዎችን በመያዝ የተጀመረው እንቅስቃሴ ቀስ በቀስ እድገት ማሳየት ጀመረ፡፡ የደንበኞቹ ቁጥር ዕለት ከዕለት እያደገ፣ ትላልቅ እርሻዎችንና የልማት ሥራዎችን እንዲሠራ ትዕዛዝ መቀበል ያዘ፡፡ በዚህ ድርጅት ከተሰሩና በስፋታቸው ከሚጠቀሱ የእርሻ ማሳዎች መካከል የካስትል ዋይነሪ (የካስትል የወይን እርሻ) ዋንኛው ነው፡፡ በ125 ሄክታር ላይ ያረፈውን የዚህን እርሻ የጠብታ መስኖ ቴክኖሎጂ የሠራው የዚህችው ትጉ ሴት ድርጅት ነው፡፡ ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት ሥራውን በማስፋፋት በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎችና በገጠራማ አካባቢዎች ላይ ለመሥራት ከፍተኛ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ነው፡፡ የወ/ሮ አስቴር የቴክኖሎጂ ሥራ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ለተማሪዎች ማሳያ ቀርቧል፡፡

ሙያዋን የበለጠ ለማሳደግ ዘወትር የምትጥረው ወ/ሮ አስቴር፤ ወደ እስራኤል አገር ሄዳ ትምህርቷን ተከታትላለች፡፡ የጠብታ መስኖ ቴክኖሎጂ ያለውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታም አስመልክታ ስትናገር፤ “በዚህ ቴክኖሎጂ በመጠቀም በአመት ሁለትና ሶስት ጊዜ ምርት ማግኘት ይቻላል፡፡ ውሃን ለመቆጠብና በርካታ ሥፍራዎችንም ለማዳረስ ቴክኖሎጂው ከፍተኛ ጠቀሜታ ይሰጣል” ትላለች፡፡

የጠብታ መስኖ ቴክኖሎጂ በከተማ ውስጥም የቤተሰብ መስኖንና የግቢ ማስዋብ ሥራን ለመሥራት እንደሚያገለግልና Landscape የተባለው ግቢን ለማስዋብ የምንጠቀምበት የዚህ ቴክኖሎጂ ሥራ ግቢው ሁሌም አረንጓዴ እንደሆነ በማቆየት፣ ተክሎችን በየዕለቱ ውሃ ለማጠጣትና ለመንከባከብ የሚውለውን የሰው ጉልበትና ጊዜ በመቆጠብ ረገድ ከፍተኛ ጥቅም ያለው መሆኑን ትናገራለች፡፡ ለጠብታ መስኖው ቴክኖሎጂ መሥሪያ የሚሆኑ ዕቃዎችን ከእስራኤል አገር እንደምታስገባ የምትናገረው ወ/ሮ አስቴር፤ ዓላማችን እነዚህን ዕቃዎች እዚሁ አገር ውስጥ በማምረት ለዕቃዎቹ መግዣ የምናውለውን የውጪ ምንዛሪ ከማስቀረቱ ጐን ለጐን የቴክኖሎጂው ተጠቃሚዎች በተመጣጣኝ ዋጋ አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ ማድረግ ነው በማለት አስረድታለች፡፡ ሕይወቷና ሥራዋ ከእርሻ ጋር የተያያዘው ወ/ሮ አስቴር፤ ምርቶች ከእርሻ ማሣ ላይ ተቀጥፈው ወደሚፈለጉበት ቦታ ከመጓጓዛቸው በፊት በሙቀትና በፀሐይ እንዳይበላሹ በማድረግ ለማቆየት የሚያስችል Cold Store (ቀዝቃዛ መጋዘን) የሚሰራ “ጌርሎፍ” የሚባል የደች ኩባንያ ሥራ አስኪያጅም በመሆን እየሰራች ትገኛለች፡፡ ኩባንያው በመቀሌ አየር መንገድ ውስጥ የሰራው ትልቅ መጋዘን ሥራው በመጠናቀቁ በቅርቡ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል፡፡ መጋዘኑ የሚቀመጡት ፍራፍሬዎችና ተክሎችም ሆኑ አበቦች በሚያስፈልጋቸው የአየር ሙቀት መጠን እንዲጠበቁና ወደሚፈለጉበት ሥፍራ እስከሚጓዙ ድረስ በጤና እንዲቆዩ ለማድረግ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለውም ወ/ሮ አስቴር ታስረዳለች፡፡ በኤሌክትሪክና በጄኔሬተር ኃይል የሚሰራውን ይህንን መጋዘን በሶላር ሲስተም እንዲሠራ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑንና ቴክኖሎጂውን ወደ ሁሉም የአገሪቱ ክልሎች ለማዳረስ እየተሰራ መሆኑን ወ/ሮ አስቴር ገልፃልናለች፡፡ የጠብታ መስኖ ቴክኖሎጂውም ሆነ የቀዝቃዛ መጋዘን ሥራው በአገራችን ብዙም ያልተለመዱ እንደሆኑ የምትናገረው ወ/ሮ አስቴር፤ መንግስት ቴክኖሎጂዎቹ ያላቸውን ጠቀሜታና አገልግሎት ተገንዝቦ እያደረገ ያለውን ድጋፍ በመቀጠል የጐደለውን ቀዳዳ እያየ ሊደፍንልን ይገባል ትላለች፡፡ ቴክኖሎጂውን ሁሉም አውቆትና በስፋት ተሰርቶበት አገሪቱ አረንጓዴ ሆና የማየት ጽኑ ምኞትም እንዳላት ትናገራለች፡፡

“አስቱኔት ኢንተርፕራይዝ” የተባለው ድርጅት በአሁኑ ወቅት ለሁለት ኢሪጌሽን ኢንጅነሮች፣

ለአስራ አራት ቋሚ ሠራተኞችና ለ12 ጊዜያዊ ሠራተኞች የሥራ እድል ከፍቶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡

 

 

Read 2960 times Last modified on Saturday, 18 February 2012 13:08