Saturday, 11 February 2012 10:43

ለባለሥልጣናት በነፍስ ወከፍ የታደለ መጽሐፍ

Written by  ሰሎሞን አበበ ቸኮል (Saache43@yahoo.com)
Rate this item
(0 votes)

የአፍሪካ አገሮች ነፃ በወጡ ማግሥት ካሉት የአፍሪካውያን መጻሕፍት አንዱን በአፍሪካ ኀብረት ጉባዔ ሰሞን ለማግኘት መቻል ምን ዓይነት ስሜት ውስጥ እንደሚጨምር አስቡት፡፡ በአሮጌ ተራም ብዙም ከማይገኙት የአፍሪካን ራይተርስ ሲርየስ መጽሐፎች አንድ ሁለቱን እዚሁ አገራችን ውስጥ ታትመው በገበያው ላይ ይገኛሉ፤ “ቲንግስ ፎል አፓርት” ከታተመ ሰንበትበት ያለ ይመስለኛል፡፡ አሁን በቅርቡ ደግሞ ሌላ ተጨመረ፡፡ ከነዚህ መፅሃፎች ጋር ቀድሞ የሚታሰበውን ናይጄሪያዊው ደራሲ ቺኑዋ አቼቤ፣ የሃያኛው መቶ እኩሌታ አለፍ እንዳለ የጻፈውን “ኤ ማን ኦፍ ዘ ፒፕል” መጽሐፍም በገበያው ውስጥ እንዲገባ አድርገውታል፡፡ መፅሃፉ የሚያስተላልፈውን መልእክት እንዲያገኙ የደራሲው ጓደኛ የሆነ አንድ ሰው፣ ለአገሩ ሚኒስትሮችና ሌሎች ሹማምንት ገዝቶ በነፍስ ወከፍ ያደላቸው መጽሐፍም ይኼው ነበር፡፡

ይህን መጽሐፍ በገበያው ውስጥ እንዲህ ሊያቀርቡልን የቻሉትንም ማመስገን ሳይገባ አይቀርም፡፡ በ 30.00 ብር ማግኘት ራሱ ቀላል ነገር አይደም፡፡ ቢያንስ አቅሙና ፍላጐቱ ላላቸው አንባቢዎች፡፡ እነዚህን መጽሐፎች ፈላጊም እንደ አዲስ ሳይነሳ አልቀረም፡፡ በልጅነቴ እነዚህን ብርቱካንማ ልባስ መለያቸው የነበሩ የአፍሪካ ጸሐፊዎችን መጽሐፍ በአንድ የሰፈሬ ወጣት ጥቆማ ከብሪቲሽ ካውንስል ቤተ መጻሕፍት በየሳምንቱ እወስድ ነበር፡፡ ያኔ ተማሪው መምህሩ ይዟቸው እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ከቺኑዋ አቼቤም “ቲንግስ ፎል አፓርት”፣ “አሮው ኦፍ ጐድ” እና “ኖ ሎንገር አት ኢዝ” የተባሉትን ያኔ ነበር ያየኋቸው፡፡ እነሆ አሁን ደግሞ ይህን ከተጻፈ ሃምሳ ዓመት የሞላውን መጽሐፉን አገኘሁ፡፡ የመሪዎች ስብሰባ ወሬ ጦፎ የነበረበት ሰሞን መሆኑም ተጨምሮ ይህን ከአቸቤ ሥራዎች ፖለቲካዊ መልእክትን የያዘ ነው የሚባለውን መጽሐፍ ይዤ ነበር የጉባዔተኞቹንም ነገር የተመለከትሁት፡፡ (በአፍሪካ ኅብረት ያሉት የአፍሪካ መሪዎች ኅብረት ወደመሆኑ እየገባ ከሚያስመስሉበት እንደ አንዱ ሊታሰብ የሚችለውን የአፍሪካ ፍ/ቤት የማቋቋም ነገርም በዚህ ጉባዔ ላይ ያነጋገረ ጉዳይ ነበር፡፡)

በነዚያ የቅኝ ግዛት ማግሥት የነበረውን የአፍሪካውያን መሪዎች ሁኔታ፣ በቺኑዋ አቼቤ መጽሐፍ ታሪክ እንደታሰበው “ተስፋው የት አለ?” ብቻ ሳይሆን ያ እነ አቼቤም ተስፋ የጣለባቸው የተማሩት ወጣቶቹ መሪዎችም ቢሆኑ የአፍሪካ ቀን ዐውጭዎች እንዳልሆኑ ጭምር እምናስብበት ጊዜ ላይ ነው እንግዲህ ይህን እምናነብበው፡፡ በአጠቃላይ በአፍሪካውያን ፖለቲከኞች ብቻ ሳይሆን፣ በደራሲዎችና ምሑራኑም ዘንድ የሚኖረው ሚናም ጭምር ያን ጊዜ በቅን ተቆርቋሪነት በነቺኑዋ አቼቤ ሲታሰብና ሲለፋበት ከነበረው ውጭ መሆኑን፣ እንዲያውም አላስፈላጊ እንደሆነ የሚሞገትበት ዓለማቸው ውስጥ እንዳለንም አሳስቦ ልብን ስብር የሚያደርግ ነገርም ነበረው፡፡ ያን ጊዜ እንዲያ መቀንቀኑ ጊዜው ነበር ልንል ቢዳዳንም አፍሪካ ግን ዛሬም በመጽሐፉ ውስጥ እንደተተረኩት ሚኒስትር ናንጋን የመሳሰሉ ባለሥልጣናት የሞሉባት ምድር ናት፡፡

ቺኑዋ አቼቤ መቶ ሃምሳ ገጾች ባሉት በዚህ መጽሐፉ ውስጥ ሊያስተላልፍ የፈለገው መልእክት የቅኝ ገዢዎች ሰንኰፍ በአፍሪካ ተነቅሎ ያልወጣ መሆኑን፣ የነፃነት ፋኖዎችና ተከታዮቻቸው ሆነው በወጡት ጭንቅላት ውስጥ በተቀበረው አስተሳሰብና አኗኗር የአፍሪካውያን መሪዎች እና ባለሥልጣናት በገዛ ሕዝባቸው ላይ የተቀመጡ መዥገሮች እንዳደረጋቸውና እነዚያ ተወግደው ለሕዝብ የሚያስቡ የተማሩ ሰዎች አፍሪካውያንን እንዲመሩና እንዲያስተዳድሩ መመኘትን ነው፡፡ ምናልባት በሽፋኑ (የጀርባ) ላይ የ”ኤክስፔክቴሽን” የተባለው መልካሙን የአመራር ሥርዓት ተስፋ የማድረግና የመጠበቅ ጉዳይ አንዱ ዐቢይ ጭብጡ ተደርጐ መቅረቡም ከዚህ አንፃር ይሆናል፡፡ በእርግጥም በወጣቱ የዩኒቨርሲቲ ምሩቅ በኦዲል ሳሞሉ በኩል ቺኑዋ አቼቤ ይህን ማሳየት ፈልጐ ነበር - ምን እንደተሳካለት ዛሬ ላይ ቢጠየቅ ምን ይል ይሆን?

“ኤ ማን ኦፍ ዘ ፒፕል” የባሕል ሚኒስትሩን ቺፍ ናንጋን የመሰለውን ባለሥልጣን የቅኝ ገዢዎቹ መንፈስ ቤቱን የሠራባቸው ምሣሌ አድርጐ አቅርቧል፡፡ ብዙ ጥንቃቄን በሚጠይቀው በአንደኛ መደብ የተተረከው መጽሐፍ፤ ወጣቱን ኦዲል ሳሞሉን ተራኪውና ባለድል ተቃዋሚ አድርጐ፣ ከልጅነት መምህሩ ከሚስተር ናንጋ ጋር ያፋጥጠዋል፡፡

አዲል ከአንደኛ ደረጃ ትምሕርቱ ጀምሮ ጥይት ተማሪ እንደሆነ የዩኒቨርሲቲ ትምሕርቱን አጠናቅቆ መምሕር ሆኖ ተቀጥሯል፡፡ በተቀጠረበት ት/ቤት አንድ ዝግጅት ይዘጋጅና የባሕል ሚኒስትሩ እንዲገኙ ይደረጋል፡፡ መምሕራኑ የባሕል ሚኒስትሩን ተሰልፈው እንዲቀበሉ ሲደረግ፣ ሚኒስትር ናንጋ ከአዲሱ ወጣት መምሕር ጋ ሲደርሱ  እጁን እንደጨበጡ፣ “ሚር ሳሞሉ?” ብለው ይጠይቁታል፡፡

አልተሳሳቱም፡፡ ኦዲልን አውቀውታል፡፡ እሱም በአንደኛ ደረጃ ት/ቤት ትምህርቱን ሲጀምር  አስተማሪው የነበሩትን ሳር ናንጋ አውቋቸዋል፡፡ ግና በየት ሾልከው እንደወጡ ባያውቅም የአገሪቱ የባሕል ሚኒስትር ሆነዋል፡፡

አዲል ዩኒቨርሲቲ ሳለ፣ የአገሪቱ ቡና ገበያ ይወድቅና ይህን ሁሌ የሚገጥም ችግር እንዴት አድርገው ቢይዙት እንደሚበጅ ያቀረቡትን መፍትሔ ብዙ ጥቅም የሚነካባቸውና ፖሊሲም የሚነካ ዕቅድ ስለሆነ ያገሪቱን መሪ እና ንኪኪዎችን አስቆጣ፡፡ “ሃገር ከሃዲዎች፣ የቀድሞ ቅኝ ገዢዎች ቅሪቶች፣ …”  እየተባሉ አንድ ባንድ ተለቅመው ተብጠለጠሉ፡፡ ተወነጀሉም፡፡ በሰልፍ ሕዝብ እንዲያወግዛቸው ብቻ ሳይሆን እንዲገደሉም ሲጠየቅ የነበረበትን ጊዜ ኦዲል ያስታውሳል፡፡

ኦዲል ባደገበት አካባቢ አገሪቱን ይመራ የነበረው ፓርቲ ተወካይ ሆነው እኝህን አስተማሪውን ያውቃቸዋል፡፡ እንግዲህ እንደምንም ብለው መምሕር ናንጋ በእነዚያ በተወገዱት ፈንታ (ለመሪውና ለፓርቲው እስከታመኑ ይልቁንም ራሳቸው መሪውንና ፓርቲውን  እስካመኑ) ከተሠየሙት አንዱ ሆነዋል፡፡

ናንጋ ኦዲልን የመሠለ ተማሪ “ኤክስፐርት” መሆን ሲችል እንዴት አስተማሪ እንደ ሆነ ሁሉ ይጠይቁታል፡፡ እንዲያውም ለቅቆ ወደርሳቸዉ ቤት እንዲመጣና ሌላ ሥራ እንደሚያገኙለት ቢነግሩትም እሱ የውጭ ትምሕርት ዕድልን እየፈለገ መሆኑን ገልጾ አይቀበላቸውም፡፡

የእርሳቸውን ሥራ አለመፈለጉን በቀጥታ ቢነግራቸውም፣ ለማንኛውም በገና ዕረፍቱ ጊዜው እርሳቸው ቤት መጥቶ እንዲያርፍ ይነግሩታል፡፡

ሰውዬው በብዙዎች ዘንድ ከምር የሕዝቡ ልጅ (ኤ ማን ኦፍ ዘ ፒፕል) ሆነው መታየት የቻሉ አፈ ቅቤ ናቸው፡፡ እንደ አየሩ ፀባይ ማውራት የሚችሉ፣ “የሕዝብ ሰው” መስለው ሊታዩ የቻሉ ናቸው፡፡ በአንድ “ግራመር ስኩል” በሚካሄደው አንድ ዝግጅት ላይ መገኘታቸው ሁሉ ከዚያ የተነሣ ነው!

አብራቸው የመጣች የርሳቸው ልጅ ልትሆን የምትችል እጅግ ውብ የሆነች ልጃገረድም ነበረች፡፡ የኦዲል ልብ ስለርሷ ማንነት፣ ምናቸው ልትሆን እንደምትችልም ጊዜ ሰጥቶ ሲያሰላስል ከመቆየትም ዐልፎ ማንነቷን እስከ ማጣራትም ድረስ ወጥቷል፡፡ በኋላ ላይ ቀስ እያለ ያውቃታል፡፡ የቼፍ ናንጋ (ረዳት) ሚስት ወይም በመጀመሪያዋ ሚስታቸው በወ/ሮ ናንጋ “አዲሷ ሚስታችን” ተብላ የምትጠራው ውቧ ወጣት ኤድና ናት፡፡ የኦዲል ልብ በርሷ እንደደነገጠ፣ በልቡ አምቋት ይኖራል፡፡

አንድ ሰው በአጠገቧ ካለፈ በኋላ አንገቱን ዞር አድርጐ እንደገና ከኋላዋ ካላያት፣ “ያ ሰው አንገቱ ግትር ብሎ የቀረበት” በሽተኛ መሆን እንዳለበት ተራኪው (ኦዲሊ) እስከ መግለጽ የደረሰበት የኤድና ውበት ገና እንዳያት ጀምሮ በልቡ ተተክሏል፡፡ ደሞ በእድሜያቸው አባትዋ የሚሆኑ፣ በዚያ ላይ ሌላ ሚስት ያላቸው ቺፍ ናንጋ በመዘበሩት ኃብታቸውና ባላቸው ሥልጣን ብዙ ፓውንድ ከፍለውባት ሊያገቧት የመሆኑ ነገር ሆዱን እንደበላው ኖረ፡፡

ገና ላይ በሚ/ር ናንጋ ቤት ቀምጠል ያሉ የዕረፍት ቀኖችን ባገኘባቸው  ጊዜያት ከተለያዩ ሴቶች ጋር መቀራረብም  የጀመረው ኦዲል፤ ወጣቱ አስተማሪ ኤልሲ የተባለች የሚያውቃትን ወጣት ከምትሠራበት ሆስፒታል ድረስ ሄዶ ያገኛታል፡፡ ቀጠሮ ይዘው በቀጠሮ ቀን ቦሪ (የሚ/ር ናንጋ ዋና ቤት የሚገኝበት) ትመጣለች፡፡ ሚኒስትሩም  የልጆቹን እናት ወ/ሮ ናንጋን አናታ በተባለው አገር ባላቸው ቤታቸው ሄደው እንዲቀመጡ አድርገው ለቅብጠታቸው ቤቱም ግቢውም ነፃ ነበር፡፡ እሳቸውም አያርፉም፡፡ በመሃል የርሳቸውና የቀድሞ ተማሪያቸው የዛሬ እንግዳቸው መ/ር ኦዲል ፀብ የመጣው ኤልሲ በተባለችው ሴት ነበር፡፡

ነርስ ኤልሲን ወዳረፈበት መኝታ ክፍል ይዟት ሊያድር፣ በሚ/ር ናንጋ ካዲላክ መኪና ይዘዋት ገቡ፡፡ ሚኒስትሩ አሽከራቸውን የባለሥልጣን ቀጭን ትዕዛዝ ዐዘዙት፡፡ የልጅቱን ሻንጣ በሚስዝ ናንጋ ክፍል ውስጥ እንዲያስገባው ነገሩት፡፡ አሽከር የእንግዳዋን ሻንጣ ከመኪና አውጥቶ እንደታዘዘው ፈፀመ፡፡ ልብሷን ልትቀያይር ሻንጣዋ ወዳለበት ክፍል ገባች፡፡  እንደምትመጣለት ነገሩ ሁሉ ያልጣመው ኦዲል ሌሊቱን ቢያጋምስም አልመጣችለትም፡፡ ወጣቲቱን ሚኒስትሩ ተኝተዋት አደሩ፡፡ ኦዲል  ተቀብለውት ለሳምንቶች ያህል በተቀናጣ መስተንግዶ ካስተናገዱት ያገሪቱ ባሕል ሚኒስትር ጋር ንጋት ላይ ክፉና ደግ ተነጋግሮ ግቢያቸውን ጥሎ ወጣ፡፡…

ከዚያን ዕለት ጀምሮ እሱም የሚበቀልበትን ያውጠነጥን ጀመር፡፡ አብሮት በዩኒቨርስቲ ይማር የነበረና ኩል ማክስ በሚል ብዕር ስም ይጽፋቸው በነበሩ ግጥሞቹ ይታወቅ የነበረ የሕግ ባለሙያውና እንደሱ ሕግ ያጠናች ሚስቱ ዩኒስ ከሌሎች ጋር በመሆን የፖለቲካ ፓርቲ ምሥረታ ሐሳብ አቀረቡለት፡፡ ተስማምቶ ከመሥራቾቹ አንዱ ሆነ፡፡ በቀጣዩ ምርጫም ተወዳዳሪ ሊሆንና በሚ/ር ናንጋ የምርጫ ቦታ ተፎካካሪ ሊሆን በፓርቲው ይታጫል፡፡ ኦዲል በፖለቲካው እንዲህ ተፎካካሪያቸው ሆኖ ሊበቀላቸው ተነሳ፡፡

በሴት በኩልም ሊያገቧት ያጯትን ኤድናን የራሱ አድርጐ ሚ/ር ናንጋን በድርቡ ሊበቀለው ወጥኖ ይቆማል፡፡ ሰበብ ተገኘ እንጂ ወትሮውንም ከልቡ ዐይቷታል፡፡ ከዚያም ሳይጣሉ በፊት ከወ/ሮ ናንጋ ቤት በሄደ ጊዜም የኤድና ሚኒስትር ናንጋን ማግባት እንዲቀር ራሷን ወጣቲቱን ሊያሳምናት ጥረት ሲያደርግም ቆይቷል፡፡ በዚህ ረገድ የታሪኩ ግጭቱ መንታና ከዚያም በላይ እንዲሆን ተደርጐ የቀረበ ነው፡፡ የምርጫው ጊዜ ደርሶ ዛሬም በአፍሪካ ምድሮች የሚታዩትን ዓይነት ሹክቻዎች እየተደረገ ይፋጠጣሉ፡፡  በዚሁ ጊዜ ኦዲል መገኘት በማይገባው የምርጫ ቅስቀሳ ላይ ተደብቆ ሊገኝ ይሄድና አንዱ አይቶት ይጠቁማል፡፡ ራሱን እስኪስት ተቀጥቅጦ ሆስፒታል እስከመግባት ይደርሳል፤ በወንጀልም ተጠያቂ ይሆናል፡፡ በሕክምና ወቅት በሁለት ፖሊሶች እየተጠበቀም ነበር፡፡ እሱ ራሱን ስቶ ሳለ ባለሥልጣናቱ በፈፀሙት የለየለት ጥፋት (ማክስ ተፎካካሪያቸው ሆኖ በመቅረቡ የተነሳ ሌላው ኮኮ የተባሉ ሚኒስትር ያስገድሉታል) ቀድሞውኑም ሕዝቡ የተንገፈገፈበት እምቅ ብሶትና ጥላቻ አጋጣሚውን በመጠቀም ወደ ብጥብጥና ነውጥ ይደርሳል፡፡

እነ ኦዲልም ወደማሸነፉ ይደርሳሉ፡፡ ኤድናም ልታገባቸው ከነበሩት ናንጋ ተርፋ፣ ገንዘብ የማይበቃቸው መንጠቆው አባቷም ከተገቢውም በላይ የሆነ የገንዘብ ጥሎሽ ተቀብለው  የኦዲል ሳሞሉ ሚስት ወደመሆን ትመጣለች፡፡

“ኤ ማን ኦፍ ዘ ፒፕል” የሚለው ርዕስ ማንን እንደሚጠራ የማያጠያይቅ መስሎ ይታያል፡፡ አንባቢዎች ናንጋን እያሰቡ ንባባቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ዛሬም ለሃምሳ ሁለት ፈሪ ዘመኖች በኋላም ናንጋን በመሳሰሉ  ሹማምንትና መሪዎች ተጠፍንጋ የተያዘችውን የአፍሪካን ዕድልና መጨረሻ እየጠየቀ ያነብባል፡፡ በአርዕስቱ የተጠሩም የተከበሩ ቺፍ ናንጋ፤ ባሕልን የማያውቁት የባሕል ሚኒስትሩ ናቸው፡፡ ደራሲውም እንዲሁ ነው ያሰበው፡፡

“የተከበሩ፤ ሚ/ር፣ ኤም ኤ፣ ቺፍ ፒ ኤም” የተባሉ የማዕረግና ሌሎች የሥልጣን መጠሪያዎች የነበሯቸው፣ ጭራሽ በምርጫ ቅስቀሳ ሰሞን “ዶክተር” የሚል መጠሪያም የጨመሩት ናንጋ፤ በእርግጥም በአፍሪካውያን ላይ በአፍሪካውያን መሪዎች የተጫነባቸውን “አገዛዝ” እንዲያሳዩ ሆነው የተመሰሉ ባለታሪክ ናቸው፡፡ በናይጄሪያ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ሁሉ የሰፈነውን አገዛዝ ይወክልልኝ ብሎ እንዳቀረበውም ገልጾ ነበር፡፡  “እሱ (ናንጋ) በናይጀሪያ ወታደራዊው ደርግ በፖለቲካው ሳይገባ በፊት የነበረውን “አመራር” የሚወክል፤ እናም፣ ወታደሩ ወደ ሥልጣን ባልወጣባቸው ሌሎች የአፍሪካ አገሮችም ያለውን አመራር የሚወክል፣ ብሎ ነበር ቺኑዋ አቼቤ መጽሐፉ በወጣ በ8ኛው ዓመቱ ባደረገው ቃለ ምልልስ የተናገረው፡፡ በዚያ ዓይነት አገዛዝ ሥር የሚገኙትንም “አያስፈልግም እንጂ” አንድ - ሁለት ብሎ በስም ጭምር ሊጠራቸው እንደሚችልም ነበር የገለፀው፡፡

“የአፍሪካን ፖለቲካ ብትመለከቱ ልክ በዚህ መጽሐፍ እንደቀረበው ሆኖ የሚገኝባቸው ሌሎች አፍሪካ አገሮችንም ታገኛላችሁ” ሲል ቺኒዋ አቺቤ የዛሬ 43 ዓመት ቢናገርም ዛሬም ቢሆን የሞሉ መሆናቸውን ከመጽሐፉ በሚተረከው መገንዘብ ይቻላል፡፡ እንዲያውም በተገላቢጦሹ እንደ ናንጋ ያሉት ስለ ሕዝብ የቆሙ መሳይ መሪዎችና ባለ ሥልጣናት የሚገኙባቸውን ሳይሆን የማይገኙባቸውን መፈለጉ የሚቀልበት ጊዜ ላይ በመገኘታችን፣ መጽሐፉ ይህንን የማሳየት ብቃት እንዳለው ለማጤንም ጊዜውም የራሱን ድርሻ አክሎልናል እንላለን፡፡

የደራሲው ጓደኛ የሆነ አንድ ምሥራቅ አፍሪካዊ ሰውዬ፣ ይሄን መጽሐፍ በብዛት ገዝቶ፣ በአገሩ ለነበሩ ሚኒስትሮችና መሪዎች በነፍስ ወከፍ እንዳደላቸውም፣ ቼኑዋ በኦስቲን ዩኒቨርሲቲ ቃለ መጠይቁ ገልጾ ነበር፡፡ “የትኛይቱ ምሥራቅ አፍሪካዊት አገር እንደሆነች” አልገልጽም” ብሎ አገሪቱን ባይጠቁምም፣ እንዲያ የታደላቸውን አንብበው ራሳቸውን እንዲያገኙት ተቆርቆሪው ምሥራቅ አፍሪካዊ የበኩሉን አድርጐ ነበር፡፡ ለዛሬዎቹስ፣ ከጉባዔያቸው ሰፈር ተገኝቶ የሚያድላቸው ቢኖር …በጭራሽ!

ዛሬ ላይ ያሉ የምሥራቅ አፍሪካም ይሁኑ የሌላ አፍሪካ መሪዎች አቼቤን አይደለም ሌሎች ብዙዎችንም ያነበቡ፣ የተማሩዋቸውና ምናልባት፣ በፓርላማዎቻቸው ብንጠራጠር በኦዲሊ አፍ ምሑራን ያልሆኑ የተባሉትን ናንጋን መሳይ መሪዎች አይደሉምና፡፡ ገዢዎቻችንና አንዳንድ ሹማምንቶቻቸው ይህን ባይሆን እንኳ ሌሎችን መሰል መጽሐፎች አጣጥመው ያነበቡ ናቸው፡፡ ጭራሽ እንኩ ይህን አንብቡ ለማለት  ፈራ ተባ የምንልባቸው ናቸው፡፡ የተማሩ፣ ዓዋቂዎች፣ አንዳንዶችም የመጽሐፍ ቀበኛነታቸው የሚወራላቸው ናቸውና ከዚህ አንጻር እንኳ ከናንጋም በላይ መሆናቸው አይቀርም…

በዚህ ረገድ ሲታሰብ ነው ከናንጋ ይልቅ ወደ ኦዲል ጐራ የምንስባቸው፡፡ “ኤ ማን ኦፍ ዘ ፒፕል” ብሎ መጽሐፉ የጠራው ማንን እንደሆነ መልሰን እስከ መጠየቅም የሚያደርሰን ነው፡፡ ኦዲል ራሱን ከምሑር ጐራ የመደበ በመሆኑ፣ በምርጫው ወቅት “ናንጋን በመሰሉ” መሃይሞች “ከመመራት በምሑራን” አገራቸው ልትመራ እንደሚገባት ይገልፃል፡፡ ቺኑዋ አቼቤም በነኦዲል ሥልጣን ላይ መውጣት በኩል ተስፋ ያደረገው የመጽሐፉ አንድ ጉዳይም ይሞግታል፡፡ የኦዲል ማንነት ሲጤን ያን ያህል “እሱን ጥሩ ደረጃ አድርሼ መጽሐፉን ፈጸምኩት፣” ያለውንም ጥያቄ ውስጥ ይከትተዋል፡፡

ኦዲል ዲግሪ አለው፡፡ ከዚህም በላይ ሊማር - ሊመራመር የሚያስብ፣ ሊማር ወደሚችልበት ቀጣይ ደረጃም እየወጣ ያለ “ምሑር” ነው፡፡ ያም ሆኖ የሃገሪቱ  ጉዳይ ደንታ አይሰጠው የነበረ፣ ወደ ፖለቲካው የግዱን የሚከትተው የግል ጉዳይ የርሱ ገፀ ባሕርይነት አነጋጋሪ ሆኖ እንደነበረም ጠቅሰው ራሱን ደራሲውን ጠይቀውት ነበር፡፡  በቀጥታ ወደ ፖለቲክስ የከተተው ደግሞ በግሉ የደረሰበትን ጥቃት አነሳስቶት ነው፡፡ “ብቀላ” ብሎ ዘው ያለ ነው፡፡

የኦዲል ገጽ ባሕርይነት ከዚህም በላይ የሆነ ግራ መጋባት ውስጥ ይከትታል፡፡ አቋሙ የጠራ ሳይሆን ነው ወደ ፖለቲካው የሚለው፡፡ አንድ ሁሉንም ለማንፃት የሚፈልግበት ጉዳዩ ሆኖ የሚገኘው ከጉቦና ምዝበራ የመጥራት ጉዳይ ነው፡፡ ይህንን ያልለየለት ማንነቱን ደራሲው ተጠይቆ ነበር፡፡

“ትምሕርታችን የተጠናቀቀው “ኤ ማን ኦፍ ዘ ፒፕልን” በማንበብ ነበር፡፡ ስለኦዲል ያንተ አመለካከት ምን እንደነበር አነጋግሮናል፡፡ ልምድ ያለው እና መልካም አሳቢ ልታደርገው ነው ያሰብከው ወይስ ፌዘኛ ማድረግ ነበር የፈለግኸው?”

“የርሱ ምሥል እዚያው መጽሐፉ ላይ አለ፡፡ እየጠየቅኸኝ ያለው አንተ ራስህ ምን መምሰል እንደነበረበት ያሰብከውን ምስል ነው፡፡ መልካሙን አሳቢ እና ልምድ የለሽ ተራ ሰው ነበር፤ ያንንም - ይሄንንም ነበር፡፡ እኔ ግን በዋነኝነት ልዩነትን የሚፈጥር ታማኝ ነበር ብዬ ነው የማስበው፡፡ በጣም ቅን ነበር፡፡ የራሱን ድክመቶች ያወቀ ሰው፤ ሌላው ቀርቶ ገፋፊ ስሜቶቹ እንኳ የጠሩ እንዳልነበሩ የተረዳ ነበር፡፡ ይህ እንግዲህ እርሱ ኹነኛ ቦታ ይሰጠዋል - በበኩሌ፡፡ ሌላው ቢቀር በቀጣዩ ጊዜ ጥሩ ነገር ይሠራል፡፡

በዚያ ጨካኝና ምሕረት የለሽ ማህበረሰብ ውስጥ ስለነበረ ተሰቃይቷል፡፡ ግና በቶሎ መማር የሚችል ነበር፡፡ በመጨረሻም ሲያስባቸው የነበሩትን የመሥራት፣ አገልጋይ የመሆን እድሎቹን ሁሉ እያሳደገ እንደነበር ነው የማስበው፡፡ እንዲህ ያለው ሁሉ ተይዞ፤ በኦዲል ላይ አንድ ያልታሰበ ነገር ይመጣል፡፡ ቺኑዋ አቼቤ ራሱ ባያስብበትም፣ “ኤ ማን ኦፍ ዘ ፒፕል” የሚለው ጥሪ ኦዲልንም የሚመለከት መስሎ ይታያል፡፡ እርግጥ ነው፣ ብዙ ቁጥርን ያመለከተ ርእስ አይደለም፡፡ ቢሆንም ኦዲል ሌላው ዓይነት የመሪዎች መልክ ነው፡፡ ይልቁንም በመጽሐፉ ውስጥ ካለው አነሳስ እነማን እንዴት ሆነው ወደ ፖለቲካው እንደሚደርሱ ስናይ ልብ ላለ “ኤ ማን ኦፍ ዘ ፒፕል” ለሱም ጭምር ይሆናል ብሎ ያስባል፡፡ ኦዲሎችም ሥልጣን ላይ ናቸው፡፡ ቺኑዋ አቼቤ ነገ ሊሠራ የሚችል አድርጐ እንዳሰበው ሳይሆን፤ በተግባርም ታዩ፡፡ ናንጋዎችንም የያዘችው አፍሪካ ከዚያው የነፃነት ማግሥት አመራሯ አልደዳችም፡፡ አልተገዛንም በሚሉትም ስውሩ አገዛዝ እንደፀና ይገኛል፡፡ ቺኑዋ አቼቤ እንዳለው ሰዎቹ እንጂ መንፈሳቸው እንደተጠናወተ” ኖሯል፡፡ የገዛ ሰዎቿ አዕምሮ ሆኖ አለ፡፡ የአእምሮ ቅኝ መሆኑ ደግሞ የበለጠ ጐጅ ይሆናል፡፡ አንድ ፀሐፊ “አንዳች ማኅበራዊ ወይም ፖለቲካዊ መልእክት” በሥራው ማስተላለፍ እንዳለበት የተናገረው የቼንዋ አቼቤ “ኤ ማን ኦፍ ዘ ፒፕል” እንዲህ የምናይበትና የምንረዳበት መጽሐፍ ነው፡፡ እንደዚህ ያሉትን ያፍሪካውያን መጽሐፎች መውጣትም ያላየንባቸውን እንድናይባቸው ያደርጋል፡፡ ያ ጊዜ እንደዚያ ያሉ ሥራዎች የሚያስፈልጉበት ጊዜ ነበር ተብሎ ቢታሰብ እንኳ፤ የደራሲያኑ ምኞት ምን ያህል ልክ ነበር ብለን ለመጠየቅም ቢሆን ያለፉት ጊዜያቶች ጭምር ስለሚረዱ የመነበባቸው ጥቅም ይጨምራል፡፡ መጽሐፍ “አንዳች ማኅበራዊ ወይም ፖለቲካዊ መልእክት መያዝ አለበት” የሚለውን ቺኑዋ አቼቤን የመሳሰሉ ሌሎችም አሉ፡፡

 

 

Read 2560 times Last modified on Saturday, 11 February 2012 10:49