Saturday, 05 December 2015 11:31

የቁጥር ‘ፎቢያ’ እና የቁጥር ‘ጨዋታ’

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(7 votes)

“ቁጥሮችን መደርደር ይወዳል”፣ “በቁጥር ይጫወታል” ሲባል የነበረው ኢህአዴግ፤ ዘንድሮ በድርቅ እና በረሃብ አደጋ ሳቢያ፣ “የቁጥር ፎቢያ” የያዘው ይመስላል። ወደ ጭፍን ደጋፊዎቹም፤ ተዛምቷል እንጂ። ቁጥር ሲሰሙ፣ ይሸማቀቃሉ።    
ለነገሩማ፣ ጭፍን ተቃዋሚዎችም፣ ገና ስለ ኢኮኖሚ እድገት በመቶኛ ሲሰሙ... እሪ ይላሉ። ፎቢያ ይነሳባቸዋል። ‘ገዢው ፓርቲ የሚያቀርባቸው መረጃዎችና ቁጥሮች ስህተት ናቸው። ትክክለኛው መረጃና ቁጥር፣... ይሄውና” ብለው አይከራከሩም። በቃ፤ በቁጥር የተገለፀ ነገር ያስጠላቸዋል።
እናም፤ ‘ኢኮኖሚው በአስር በመቶ አደገ’ የሚል ሪፖርት ሲሰሙ፤... “ቁጥር... ትርጉም የለውም። የዜጎች የኑሮ ችግርና ድህነት ነው መታየት ያለበት” ይላሉ።
ከዚያስ?
“4 ሚሊዮን ሰው ተራበ፤ 8 ሚሊዮን ደረሰ፤ ወደ 15 ሚሊዮን ተባባሰ”... የሚል መረጃ ሲመጣ፤ የቁጥር ወዳጅ ይሆናሉ። የመጫወቻ ካርድ ተገኘ ማለት ነው። ይሄኔ፤ ገዢው ፓርቲና መንግስት፣ የቁጥር ፎቢያ ይነሳባቸዋል። የቁጥርን ነገር ለማጥላላት መከራቸውን ያያሉ።
“ትኩረታችን በቁጥር ላይ አይደለም። ቁጥሩ... ምንም ሊሆን ይችላል። ዋናው ነገር፤ ሰዎች በረሃብ እንዳይሞቱ ማድረግ ነው” በማለት ይከራከራሉ። በቁጥር የሚገለፁ መረጃዎችን የማጣጣልና የማንቋሸሽ ተራ፤ የገዢው ፓርቲና የመንግስት ሆነ ማለት ነው።
ግን፣ ዞር ብለው፣ ቁጥሮችን እንደ መጫወቻ ካርድ ለመጠቀም ይጣጣራሉ። “ከሁለት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ስንዴ፣ ከውጭ ወደ አገር እየገባ ነው። ተጨማሪ 6 ሚሊዮን ኩንታል ተገዝቶ እንዲመጣም ወስነናል” በማለት መግለጫ ይሰጣሉ - ገዢው ፓርቲና መንግስት።
ስንት ሚሊዮን ኩንታል? ለነገሩ፣ ‘ዋናው ነገር፣ ቁጥር አይደለም። ቁጥሩ ምንም ቢሆን ለውጥ የለውም’ ተብሎ የለ! ቁጥር ሳይጠቅሱ፣ በደፈናው፣ “ስንዴ ተገዝቶ እየመጣ ነው” ማለት ነበረባቸው።
“ዜጎች በረሃብ እየተሰቃዩ፣ መንግስት... ስድስት ሚሊዮን ኩንታል፣ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል እያለ ቁጥር ቢደረድር ትርጉም የለውም” የሚል ተቃውሞ እንደሚፈጠርስ ምን ይጠረጠራል? ቁጥርን የማጣጣል ተራው፣ ወደ ተቃዋሚዎች ዞረ ማለት ነው። ታዲያ፣ “ከ50ሺ ሰዎች በላይ በረሃብ ተፈናቅለዋል። በድርቁ ከ200ሺ በላይ የቤት እንሰሳት ሞተዋል” የሚል መረጃ ሲያዩ ግን ደስታቸው ነው። በቁጥር የተገለፀው መረጃ፤ ጥሩ የማጥቂያ መሳሪያ (የመጫወቻ ካርድ) ይሆንላቸዋል። በተራው፣ መንግስት በቁጥር ፎቢያ ይንገሸገሻል። አዙሪት ነው።
ጤናማ ሆነን ስናየው፤ እንዲህ አይነቱ የፓርቲዎች ባሕርይ አስገራሚ ነው። እንደ እርግማን በጭፍን ፍርሃት የቁጥር መረጃን ማጥላላት... ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ፣ የቁጥር መረጃን እንደ ትንግርተኛ የማጥቂያ መሳሪያ መጠቀም... እነዚህን ተቃራኒ ነገሮች ማቀላቀል፣ የፓርቲዎች ‘ኖርማል’ ባህርይ መሆኑ፤ አስገራሚ ነው። ግን፣ በፓርቲዎች ላይ ብቻ የተከሰተ፣ ያልተለመደ እንግዳ ባሕርይ ነው ማለት አይደለም። በጭራሽ!
የማይጥማቸውን መረጃ መስማት የማይፈልጉ... መረጃው፣ ሙሉ ለሙሉ እውነተኛ ቢሆንም እንኳ፣... መረጃው በይፋ እንዳይነገርና ሰው እንዳይሰማ ለመከልከል የሚመኙ ሞልተዋል። የመረጃ ፎቢያ እንደማለት ነው።    

Read 4413 times