Print this page
Saturday, 12 December 2015 11:17

“የዓለም ሞዴል” ካልተባልን መኖር የማንችል መሰልን!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(28 votes)

አይቻልም ወይ መኖር የማንም ሳይሆኑ” አለች የትዝታዋ ንግስት
“ኢቢሲ 50ኛ ዓመቱን በ9ሚ. ብር ሳይሆን እንደነ ብአዴን “በታሸገ ውሃ” ቢያከብርስ?
ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ ከታንዛኒያው አዲሱ ፕሬዚዳንት ምን ይማራሉ?

  የፖለቲካ ወጌን ያለወትሮዬ በጥያቄ ልጀምረው ነው (ያልተመለሱ ነገሮች በዙብና!) ቆይ ግን ሞዴል ሳንሆን ወይም ሳንባል ዝም ብለን በ “low profile” መኖር አንችልም እንዴ? (ብቻ “የአዋቂ” ትዕዛዝ ነው እንዳትሉኝ?!) በልማታዊ ገዢ ፓርቲ፣በምርጫ፣በፌደራሊዝም ሥርዓት፣ በግሪን ኢነርጂ--- ወዘተ የዓለም ሞዴል እንደሆንን እስኪሰለቸን ድረስ አንድ ለእናቱ በሆነው  ብሔራዊ ቴሌቪዥናችን እየተነገረን ነው፡፡ (ይልቅ ሴቶቻችንን በሞዴሊንግ ብናበቃ ያዋጣን ነበር!)
 ነገሩ “የዓለም ሞዴል ነን” በሚል ብቻ የሚያበቃ እንዳይመስላችሁ… በዓለም ተወዳዳሪ ለመሆን ያላለመ የመንግስት ተቋም ፈልጋችሁም አታገኙም፡፡
በ2ሺህ ምናምን ዓመተ ምህረት (ጊዜው ትንሽ ራቅ ቢል እንኳን ደግ ነበር!) በዓለም ተወዳዳሪ ለመሆን ማቀዳችንን እንደዘበት እንናገረዋለን። (በኮፒራይት አያስጠይቅማ!) በነገራችን ላይ በቅርቡ የ50ኛ ዓመት የኢዮቤልዩ በዓሉን ለማክበር በዝግጅት ላይ የሚገኘው (ጊዜው እንዴት ይከንፋል!) ኢቢሲ ሳይቀር በ2ሺ ምናምን ዓመተምህረት ላይ በዓለም ተወዳዳሪ ሚዲያ ለመሆን ራዕይ መሰነቁን በድፍረት ነግሮናል፡፡ (ራዕይ እኮ አይከለከልም!) በቅርቡ የተከፈተ አንድ የመንግስት ዩኒቨርስቲም (የመጀመሪያ ዙር እንኳን ሳያስመርቅ እኮ ነው!) የሆነ ቅርብ ዓመት ጠቅሶ፣ በዓለም ተወዳዳሪ  ዩኒቨርሲቲ ለመሆን ማለሙን በእግረ መንገድ ጠቆም አድርጓል፡፡ (የተፈጥሮ ሂደት የሚባል ነገር ቀረ ልበል?!)
በነገራችን ላይ ማለምን ወይም ራዕይ መሰነቅን እያጣጣልኩ አይደለም፡፡ ህልማችን ግን በመሬት ላይ ከምናውቀው ወይም ከተጨባጩ እውነታ፣ የሰማይና የምድር ያህል ሊራራቅ አይገባውም፡፡  (ያለዚያ እኮ ቅዠት ይሆናል!) በእርግጥ ፈረንጆቹ (ኒዮሊበራሎቹን ማለቴ ነው!) dream big የሚሉት አባባል አላቸው፡፡ (ትልቅ ትልቁን አልም ለማለት ይመስለኛል!) ይሄ አባባል ያለአግባብ ጥቅም ላይ ሲውል ግን ቅዠት ይመስላል፡፡
እስቲ ይታያችሁ…ከተከፈተ ገና ሁለት ዓመት ያልሞላውና 500 ተማሪዎች እንኳን የሌሉት ተቋም እንዴት ዘሎ በዓለም ተወዳዳሪ እሆናለሁ ይላል። (ያውም የመንግስት ዩኒቨርሲቲ!) መጀመሪያ ተወዳዳሪነቱን በአገር ውስጥ ማሳየት ያለበት ይመስለኛል፡፡ እኔ የምለው ግን --- ለመሆኑ አንጋፋው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በአፍሪካና በዓለም ያለው ደረጃ የቱ ጋ ነው?
በነገራችሁ ላይ አንድ ለማሳካት ያሰብነው ሁነኛ ዓላማ ከሌለ በቀር የዓለም ሞዴልም ሆነ ተወዳዳሪ ባንባልም እኮ ችግር የለውም፡፡ (“አይቻልም ወይ መኖር የማንም ሳይሆኑ ---” አለች በዛወርቅ!!) ይሄንን ስል ግን ከማንም ጋር መፎካከር ወይም መወዳደር አንችልም በሚል የአቅም ማጣት ስሜት ወይም ተስፋቢስነት አይደለም፡፡ ይልቁንም “ሙያ በልብ ነው” በሚል የጥንት አገራዊ ብሂል እንጂ። (እቺ አባባል Outdated ሳትሆን አልቀረችም!!)
በቀጥታ የልደት በዓሉን ወደሚያከብረው EBC ልመልሳችሁ፡፡ እናላችሁ…ባለፉት 50 ዓመታት የአገልግሎት ዘመኑ ምንም የለውጥ ፍንጭ ያላሳየን ኢቢሲ፤ (ባለቤትነቱ እንደ መሬት፣ የህዝብና የመንግስት ነው!) ድንገት ተነስቶ በዓለም ተወዳዳሪ ለመሆን ራዕይ ሰንቄአለሁ ሲለን ብንደነግጥ ይፈረድብናል? (መች አለማመደን?) እውነቴን እኮ ነው የምላችሁ ---- ከመንግስት ልሳንነት (በኢህአዴግ አጠራር “አዝማሪ ሚዲያ”) ወጥቶ መች ሚዛናዊ ዘገባ ማቅረብ ጀመረ? መቼ የህዝብ አመኔታን ተቀዳጀ? (በኢህአዴግ አባባል “ህዝባዊ ወገንተኝነቱን” መች አረጋገጠ?!) መቼስ እውነተኛ የመረጃ ምንጭነቱን አስመሰከረ? (“ከአንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች” መቼ ተላቀቀ?!) በራሱ አቅም አዝናኝና ማራኪ ፕሮግራሞችን አሰናድቶ ማቅረብ ቢያቅተው እንኳን አዘጋጅቶ የማቅረብ ብቃቱ ያላቸውን “የአየር ሰዓት ተከራዮች”፣ መች በቅጡ ማስተናገድ አወቀበት? (እንደ “ክፉ የቤት አከራይ” ተከራዮች አይበረክቱለትም!) በግል አዘጋጆች የሚቀርቡ አንዳንድ ተወዳጅ ፕሮግራሞች፤ በጣቢያው ያለ አንድ ዙር በቀር መች ዘልቀው ያውቃሉ? (ነገር ቢኖር ነው ያስብላል!)
እናላችሁ… እንዴት ነው በዚህ አቋሙ በዓለም ተወዳዳሪ ለመሆን ራዕይ ሰንቄአለሁ የሚለን? (በእርግጥ ራዕይ አይከለከልም!) እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ---- ኢቢሲ በቅርቡ ከተጀመረው ኢቢኤስ እንኳን የመፎካከር አቅም አለው? ቆይ ግን የትኛው ጣቢያ ነው ይበልጥ ተወዳጅ? (መልሱን ለራሱ ለኢቢሲ ትቸዋለሁ!) ምንጮቻችን እንደሚነግሩን ከሆነ፣ የኢቢኤስን ጣቢያ ተወዳጅና ተናፋቂ እያደረጉ ከሚገኙት ብዙዎቹ ፕሮግራሞች መካከል ቀላል የማይባሉት መጀመሪያ ኢቢሲ ሄደው የተመለሱ ናቸው፡፡ (ወይ አለመታደል አሉ!)
እኔ የምለው ግን EBC እንደ ልጅ፤ “ስታድግ ምን ለመሆን ትፈልጋለህ?” ቢባል ምን ይመልስ ይሆን? (መቼም እንደ ቻይናው CCTV አይለንም!) ቻይና እኮ በመንገድና በባቡር ሃዲድ ዝርጋታ እንጂ በሚዲያና በዲሞክራሲ ዝርጋታ በኩል የለችበትም፡፡ (ኢህአዴግ ነፍሴ፤ በኢኮኖሚ ዕድገቷ ተወስውሶ የፖለቲካ ቅኝቱን እንዳይቀይር!) እናላችሁ---- EBC የዛሬ 50 ዓመት፣ 100ኛ ዓመቱን ሲያከብር ራሱን የቱ ጋ ነው ማግኘት የሚፈልገው? (የትም እንዳይለን ብቻ!!) በነገራችን ላይ ወ/ሮ ሰሎሜ ታደሰ፣ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሥራ አስኪያጅ በነበሩ ጊዜ ጣቢያው በቢቢሲ ሞዴል ተዋቅሮ እንደነበር ሰምቻለሁ (ማን ነበር “ደግ አይበረክትም” ያለው?!) እናላችሁ --- ያን ጊዜ ነበር እነ “አውደሰብ”፣ “ስኬት”፣ “ዓይናችን” የመሳሰሉ ምርጥ  ፕሮግራሞች የተጀመሩት። ግን አላለለትም፡፡ ሥራ አስኪያጇ ኢቲቪን ሲለቁ፣ ፕሮግራሞቹም የሃላፊዋን እግር ተከትለው ከጣቢያው እመጭ ብለው ወጡ! (“ወይ ነዶ” አለ ያገሬ ሰው!)
አያችሁ----የEBC 50ኛ ዓመት በሚከበርበት ዕለት የኮርፖሬሽኑ ሃላፊዎች፣“ስኬቶቹን” እና ህልሞቹን የግዳችንን አንቀው ስለሚነግሩን፣ እኛ እንደ ተመልካች ወይም እንደ ባለቤት ድክመቶቹን ነቅሰን ማሳየታችን ከነውር እንደማይቆጠርብን እምነታችን ነው፡፡ (ኢቢሲ፤የህዝብና የመንግስት ሃብት መሆኑን ልብ ይሏል!)
በነገራችን ላይ ኮርፖሬሽኑ የ50ኛ ዓመት በዓሉን ለማክበር ከ9 ሚ. ብር በላይ መድቦ የነበረ ቢሆንም በመሃል ባጀቱ ከግማሽ በላይ እንደተቀነሰ ምንጮች ተናግረዋል፡፡ እኔ የምለው----አገር በድርቅና በረሃብ ተመትታ ባለችበት ክፉ ወቅት፣ የ9 ሚሊዮን ብር ፌሽታ ለምን አስፈለገ? ጠ/ሚኒስትሩ በቅርቡ ከግል ፕሬስ ጋር ባደረጉት የመጀመሪያው ታሪካዊ ቃለምልልስ፣ የኢህአዴግ ግንባር ድርጅቶች፣ የልደት በዓላቸውን ብዙ ሚሊዮን ብሮች እየመዠረጡ ያከብራሉ ስለሚባለው ተጠይቀው ምንድን ነው ያሉት? “እኛ በዓሉን የምናከብረው በታሸገ ውሃ ነው!” (ጠ/ሚኒስትሩ ከታች በሚቀርብላቸው ሪፖርት ተሸውደው እንዳይሆን እንጂ በአበል፣ በትራንስፖርት፣ በሆቴል በኮፍያና በቲ-ሸርት ብቻ የሚወጣው ገንዘብ የትየለሌ ነው ይባላል!)
የሆኖ ሆኖ ግን ኢቢሲ ጠ/ሚኒስትሩ እንዳሉት፣ለምን 50ኛ ዓመቱን “በታሸገ ውሃ” አያከብረውም? ባይሆን ለፌሽታው አስቦት የነበረውን ከ9 ሚ. ብር በላይ ለረሃቡ በእርዳታ ቢለግስ አገራዊ ሃላፊነትን እንደመወጣት ይቆጠርለታል፡፡ በነገራችን ላይ የታንዛኒያው አዲሱ ፕሬዚዳንት ጆን ማጉፊሊ፤በአፍሪካ መሪዎች ዘንድ እምብዛም ያልተለመደ ስልጡንና ድፍረት የተመላበት አመራር በማሳየታቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ ዝናቸው እየናኘ ነው፡፡
በአገራቸው ከተከሰተው አደገኛ የኮሌራ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ሰሞኑን በዋና ከተማዋ መንገድ ላይ ወጥተው ከህብረተሰቡ ጋር በጽዳት ዘመቻ ላይ ተሳትፈዋል፡፡
ባለፈው ወር በየዓመቱ በወታደራዊ ሰልፍና ደማቅ ስነስርዓት እንዲሁም በሙዚቃ ኮንሰርት ሲከበር የኖረውን የአገሪቱን የነጻነት ቀን በዓል ሰርዘውታል፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ ውሃ የሚያነሳ ነው፡፡ አገሪቱ በአደገኛ የኮሌራ ወረርሽኝ ተጠቅታ ባለችበት ሰዓት፣ ከፍተኛ ገንዘብ መድቦ በዓሉን ማክበር “አሳፋሪ ነው” ነበር ያሉት። ቡልዶዘር የሚል የቅጽል ስም የወጣላቸው ፕሬዚዳንቱ፤ ለአዲሱ ፓርላማ መቀበያ ፌሽታ ለማድረግ የተመደበውን 100ሺ ዶላር፣ ወደ 7ሺ ዶላር እንዲቀነስ አዘዋል፡፡ እኚሁ ጉደኛ መሪ ወደ አንድ የመንግስት ሆስፒታል የድንገቴ ጉብኝት ባደረጉ ወቅት ህመምተኞች ወለል ላይ ተኝተው በማየታቸው፣ጣጣ ፈንጣጣ ሳያበዙ የሆስፒታሉን ዋና ሃላፊ ከሥራው አስወግደውታል፡፡ እኒህን በአፍሪካ መሪዎች ዘንድ ያልተለመዱ ድንቅ ተግባራትንም አዣንስ ፍራንስ ፕሬስን የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች እየተቀባበሉት ይገኛሉ፡፡ ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝና መንግስታቸው እንዲህ ያለ ድፍረትና ውሳኔ ሳያስፈልጋቸው አይቀርም፡፡ ያለዚያ የሚፈለገው ለውጥ አይመጣም፡፡    
በመጨረሻ EBCን እንኳን ለ50ኛ ዓመት የልደት በዓሉ አደረሰው ለማለት እወዳለሁ፡፡ (ቢያደርሰው እኮ ነው ለመወቃቀስ የበቃነው!)     

Read 5354 times