Saturday, 12 December 2015 11:18

የአውሮፓ ህብረት ጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስወገድ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገለጸ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

      በሴቶችና በልጃገረዶች ላይ የሚፈፀሙ ጐጂ ባህላዊ ድርጊቶችን በተለይም የሴቶችን ግርዛት ለመከላከል አገሪቱ እያደረገች ላለው ጥረት ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የአውሮፓ ህብረት አስታወቀ፡፡
በየዓመቱ ህዳር 30 ቀን የሚከበረውን የሰብአዊ መብት ቀን ምክንያት በማድረግ ህብረቱ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል በአዋሣ ዙሪያ ወረዳ፣ ጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስቀረት የተደረጉ ድጋፎችንና የማህበረሰብ አቀፍ ሥራዎችን ለጋዜጠኞች ባስጐበኘበት ወቅት በህብረቱ የሲቪል ማህበረሰብና የጾታ ጉዳዮች ፕሮግራም መሪ ስቴፋን ካሬት እንደተናገሩት፤ በወረዳዎቹ የሴት ልጅ ግርዛት፣ ያለዕድሜ ጋብቻ፣ ጠለፋንና የውርስ ጋብቻን ለማስቀረት አገሪቱ የምታደርገውን ጥረት ህብረቱ ሲደግፍ ቆይቷል፡፡
በክልሉ በተለይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ እናቶች፣ ህፃናትና ልጆችን መሠረታዊ ችግር በመቅረፍ ለነዋሪዎች የጤና እና የትምህርት እድል ለማስገኘት ለሚሰራው ሴንተር ኦፍ ኮንሰርን የተባለ ማዕከል ድጋፍ የሚያደርገው ህብረቱ፤ በእነዚሁ ወረዳዎች ውስጥ ለሚገኙና ቀድሞ በግርዛት ሥራ ላይ ለተሰማሩ 60 ሴቶች 1500 ብር መቋቋሚያ በመስጠት፣ ከጐጂ ልማዳዊ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ መደረጉም በዚሁ ወቅት ተገልጿል፡፡
ዞኑ በተለይም ከሴት ልጅ ግርዛትና ከውርስ ጋብቻ ጋር በተያያዘ በርካታ ችግሮች የነበሩበት ሥፍራ እንደነበር የገለፁት የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር አቶ አሰፋ ጌታነህ በበኩላቸው፤ የጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶቹ ሰለባ የሆኑ ሴቶችን መልሶ በማቋቋም ኑሮአቸውን ለማሻሻል ጥረት መደረጉን ጠቁመው፣ በወረዳው ሥር ባሉ ትምህርት ቤቶችና መንደሮች ማህበረሰቡን ለማስተማር ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

Read 3256 times