Saturday, 11 February 2012 11:02

እስራኤል የኢራንን ኒውክለር ልትመታ ነው ቻይናና ሩሲያ ከኢራን ጎን ተሰልፈዋል

Written by  ጥላሁን አክሊሉ
Rate this item
(13 votes)

በመካከለኛው ምሥራቅ ቀጠና ኃያል አገር እንደሆነች የምትታወቀው እስራኤል፣ በተደጋጋሚ ከአረቦች ጋር ባካሄደችው ጦርነት ማሸነፏ ይታወቃል፡፡ እስራኤል ጠንካራ በሆነው ወታደራዊ ኃይሏ፤ ከፍልስጤሞች ነፃ አውጭ ድርጅት ከነበረው ከፒ.ኤል.አ እስከ ኢንቲፋዳ ድረስ፣ ከሀማስ እስከ ሂዝቦላና ያሉት ፀረ-ጽዮናዊያን አቋም ያላቸዉን ኃይሎች በተለያየ ጊዜያት ያሉበት ስፍራ ድረስ በመሄድ በአውሮፕላንና በሮኬት ደብድባለች፡፡ በ2004/05 በሊባኖስ የሚገኘውን ሂዝቦላን እንዲሁም በ2008 በጋዛ ሰርጥ ሃማስን መደብደቧ አይዘነጋም፡፡ በተጨማሪም ሞሳድ የተባለው የስለላ ድርጅቷና ሺቤት የተባለው በህቡዕ የሚንቀሳቀሰው የደህንነት ተቋሞች ለአለም አቀፍ ሚዲያ ጆሮ ሳይደርስ በተለያየ ጊዜያት የወሰዱትና አሁንም እየወሰዱ ያሉት እርምጃ የትየለሌ ነው፡፡

እስራኤል ከግብጽ ጋር የሰላም ስምምነት ከተፈራረመች በኋላ፣ ከአብዛኞቹ የመካከለኛው ምሥራቅ ሙስሊም አገራት ጋር የነበራት ግጭት ወደ ሰላማዊ ደረጃ ሲቀየር፣ ከኢራንና ከሶሪያ ጋር ያላት ግንኙነት ግን እስካሁንም የሻከረ ከመሆኑም በላይ ከሁለቱም አገራት ጋር ቀን ጠብቆ ሊፈነዳ የሚችል ጠላትነት አላት፡፡ እ.ኤ.አ በ1973 ዓ.ም አረቦች ለሶስተኛ ጊዜ ጦርነት ከፍተውባት ሽንፈት ከገጠማቸው በኋላ፣ እስራኤልን ለማጥቃት በሕብረት ባይንቀሳቀሱም፣ ሶሪያ ሃማስን በመርዳት እንዲሁም ኢራን የሂዝቦላ ሚሊሺያዎችን በገንዘብና በጦር በመሣሪያ በመደገፍ በእስራኤል ላይ ጥቃቶች እንዲካሄዱ አድርገዋል፡፡ እስራኤል በበኩሏ ከዓመታት በፊት በሶሪያ፣ በኢራቅ፣ በቱኒዚያ፣ በሊባኖስ በተለያየ ጊዜያት ጥቃት ፈጽማለች፡፡ በተለይም እንደቆቅ ነቅቶ በሚጠብቀው የስላለ ድርጅቷና የጦር ሃይሏ ጥምረት 8 ሚሊዮን የማይሞላ ሕዝብ ይዛ በድምሩ 186,614,858 በሚደርሱ ተቀናቃኞቿ ተከባ ሉዓላዊነቷ አስከብራ ትኖራለች፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ከወራት በፊት በአሜሪካና በኢራን መካከል በኒውክሊየር ጦር መሣሪያ ግንባታ ዙሪያ የተጀመረው ውዝግብ የአለም አቀፍ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ (IAEA) ኢራን ዩራኒየምን 20 በመቶ በማበልጸግ የኒውክሊየር ጦር መሣሪያ ባለቤት ለመሆን የሚያስችል ደረጃ መድረሷን ከገለፀ በኋላ፣ አሜሪካ ኢራንን በዲፕሎማሲ ለማግባባት ያደረገችው ሙከራ በመክሸፉ የኢኮኖሚ ማዕቀብ መጣሷ ይታወቃል፡፡ በተጨማሪም አሜሪካ ኢራንን ላይ የምታሳድረው ጫናና ማስፈራራት ኢራንን እጅ ከመስጠት ይልቅ ተመሳሳይ የአይበገሬነት ምላሽ በተደጋጋሚ በመስጠቷ ሁለቱንም አገራት የጦፈ የቃላት ጦርነት ውስጥ አስገብቷል፡፡

በእርግጥ፣ አሁን የኒውክሊየር ጦር መሣሪያ ባለቤት ብትሆን፣ አትላንቲክ ውቅያኖስን አሻግራ አሜሪካ ላይ ጥቃት ትፈጥራለች ተብሎ ባይታሰብም ባላንጣዋ የሆነችው ጎረቤቷ እስራኤል ላይ አደጋ ለመጣል እንደማይከብዳት ግልጽ ነው፡፡ የዋይት ኃውስ ባለስልጣናት በዋነኛነት ኢራን ኒውክሊየሩን በእጇ ካስገባች ወዳጃቸው እስራኤል ላይ የተነጣጠረ ጥቃት ልትከፍት ትችላለች የሚል ስጋት ያላቸው ሲሆን በተጨማሪም ኃላፊነት የማይሰማት አገር በመሆኗ ለሰው ዘር እልቂት የሆነውን የኒውክሊየር መሣሪያ በመጠቀም በመካከለኛው ምሥራቅ የማይባራ ሃይማኖታዊ ግጭት እንዲፈጠር ምክንያት ልትሆን ትችላለች ብለው ያምናሉ፡፡ ይሁንና ጠላቶቿን ቀድማ በማጥቃት የረጅም ጊዜ ልምድ ያላት እስራኤል፣ የኢራንን የኒውክሊየር ማብለያ ለመምታት መዘጋጀቷ እየተነገረ ነው፡፡ እስራኤል ኢራንን ልትመታ እንደምትችል ከባለፈው ሕዳር ወር ጀምሮ ከአካባቢው ሲናፈስ የነበረው ዜና፣ አሁን እውን ሊሆን እንደሚችል ተገልጿል፡፡ የሚገርመው እስራኤል ኢራንን ለመምታት መዘጋጀቷን በተመለከተ ለወዳጇ ለአሜሪካ እንኳን ፍንጭ ያልሰጠች ሲሆን የአሜሪካ ባለሥልጣናት የእስራኤልን ጥቃት የተረዱት በስለላ ድርጅታቸው በኩል ነው፡፡

የአሜሪካው የመከላከያ ሚኒስትር ሊዮን ፓኔቲ፤ እስራኤል እስከሚቀጥለው ሚያዝያ ወር ድረስ በኢራን የኒውክሊየር ሀይል ማብላያ ላይ ጥቃት ትሰነዘራለች በማለት ለዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ተናግረዋል፡፡ ሲ.ኤን.ኤን ቴሌቪዥን በበኩሉ፤ ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የኦባማ ከፍተኛ ባለስልጣንን ጠቅሶ፤ እስራኤል ኢራንንን ለመምታት መዘጋጀቷን ዘግቧል፡፡

በአሜሪካ ሚዲያዎች የተሰራጨውን ዘገባ ተከትሎ፣ የኢራን መንፈሳዊ መሪ የሆኑት አያቶሎ አሊ ካሚኒ፤ ባለፈው ሳምንት ለኢራን ሕዝብ መንግስታዊ በሆነው የአገሪቱ ቴሌቪዥን ባስተላለፉት መልዕክት፣ የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ሊዮን ፓኔቲ፣ እስራኤል እስከሚቀጥለው ሚያዝያ ወር ድረስ የኢራን የኒውክሊየር ሀይል ማብላያ ላይ ጥቃት ልትሰነዝር ትችላለች በማለት ያስተላለፉት ማሳሰቢያ ምንም ስጋት አይፈጥርብንም ብለዋል፡፡

“ኢራንን፣ ማስፈራራት፣ ኢራንን ማጥቃት የሚጎዳው አሜሪካንን ነው፡፡ ማዕቀብ በሀገራችን ላይ ምንም የሚያሳድረው ተፅዕኖ የለም፡፡ እኛ ፅዮናዊቷን እሥራኤልን ለማጥቃት ለሚፈልግ ማንኛውም መንግሥትና ቡድን ድጋፍ ለመስጠትና ለመርዳት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለን ስንገልጽ ምንም ፍራቻ አይሰማንም” የሚል ጠንከር ያለ ምላሽ ሰንዝረዋል፡፡

ካሚን ይህንን በድፍረት የተሞላ ምላሽ ይስጡ እንጂ እስካሁን በተደጋጋሚ የሆርሙዝን የባህር ወሽመጥ እንዘጋለን በማለት የሚሰነዝሩትን ማስፈራሪያ ወደ ተግባር ለመለወጥ አንድም እርምጃ አልወሰዱም፡፡ እንዲያውም የአሜሪካ የጦር መርከብ በዓለም ሁለት ሶስተኛ ነዳጅ የሚጭኑ መርከቦች የሚተላለፉበትን የኢራን የባህር ወሽመጥ ለማቋረጥ ከወሰነ የጥቃት ሰለባ ይሆናል ባሉ በማግስቱ 5ኛው የአሜሪካ የጦር ኃይል ምድብ ሊንከን የተባለችው የጦር ጀት ተሸካሚ መርከብ ወሽመጡን ስታቋርጥ “የዛሬን አልፈናቸዋል ሁለተኛ ቢደግሙ ግን ይቅርታ አናደርግላቸውም” በማለት መናገራቸው በብዙ የፖለቲካ ተንታኞች ትዝብት ውስጥ ከቷቸዋል፡፡

በተመሣሣይ ከአንድ ወር በፊት የኢራን የባህር ኃይል ኮማንደር አድሚራል ሃቢቦላ ሳያሪ “የሆርሙዝ የነዳጅ ማስተላለፊያን መዝጋት በብርጭቆ ውሃ የመጠጣት ያህል ቀላል ነው” ብለው ማለታቸው አይዘነጋም፡፡

ቻይናና ሩሲያ

ኢራን አሜሪካን እንድትገዳደርና በእስራኤል ላይ ስጋትን እንድትፈጥር ያደረጋት ከምዕራባዊያን በተቃራኒ በመቆም ለኢራንና ለሶሪያ ጥብቅና የቆሙት ቻይናንና ሩሲያን ተመክታ እንደሆነ የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡

ቀዝቃዛው ጦርነት ካከተመ በኋላ ሩሲያ በመካከለኛው ምሥራቅ የነበራትን ወታደራዊ ይዞታ ለቅቃ የወጣች ሲሆን፤ ከዚያ በኋላ ቀጠናው በአሜሪካ ተጽእኖ ሥር ሊወድቅ ችሏል፡፡ ሩሲያ ቻይናና ሩሲያ ድምጽን በድምጽ የመሻር ሥልጣናቸውን በመጠቀም በአለም አቀፍ ደረጃ ተሰሚነታቸው ጐልቶ እንዲሰማ የሚያደርግ የፖለቲካ ቁማር መጫወት የጀመሩት የአረብ አብዮት ከፈነዳ በኋላ ነው፡፡

ሩሲያና ቻይና እ.ኤ.አ በ1991 ዓ.ም እና በ2003 አሜሪካ መራሹ ጦር ኢራቅን ሲወርና በሊቢያ የፀጥታው ምክር ቤት ከበረራ እግድ ቀጠና ሲወስን በምክር ቤቱ ያላቸውን ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ተጠቅመው ውሳኔው ከመቃወም ይልቅ በድምጽ ተአቅቦ ማለፋቸው ይታወቃል፡፡

ይህንን ውሳኔያቸውን በተመለከተ በቤይሩት የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ የመካከለኛው ምሥራቅና የአረብ ፖለቲካ ጥናት ዳይሬክተር ዋሊድ ሂዝቡን በሰጡት ሙያዊ አስተያየት፤ ቻይናና ሩሲያ በሊቢያ ላይ የፀጥታው ምክር ቤት ያስተላለፈውን ነፃ ዕግድ የበረራ ቀጠና በድምጽ ተአቅቦ በማለፍ በድምጽ ብልጫ እንዲያልፍ ያደረጉት ምዕራባዊያን መጨረሻ በሌለው ጦርነት ውስጥ ይዘፈቃሉ በሚል ፖለቲካዊ ግምት ነበር፡፡

ለዚህ ስህተት የዳረጋቸው ከሊቢያ ጋር በነበራቸው ጥብቅ ወዳጅነት ሸቀጦቻቸውን እየቸበቸቡና ነዳጅ እየሸመቱ እስከ አፍንጫቸው መሣሪያ ያስታጠቋቸው ጋዳፊ በቀላሉ እጃቸውን አይሰጡም፡፡ ቢበዛ ሊቢያ እንደ ሶማሊያ በማያልቅ የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ትዘፈቃለች አሊያም ጦርነቱ እንደ አፍጋኒስታንና ኢራቅ ጦርነት ምዕራባዊያንን ለመቶ ቢሊዮን ዶላር ወጪ የሚዳርግ አመታት የሚዘልቅ ጦርነት ይዳርጋል ከሚል ግምታቸው የተነሳ ነበር፡፡

ቻይናና ሩሲያ አለምአቀፍ ሰላምን እያወኩ እንደሆነ ሮይተርስ ሰሞኑን “China and Russia:- Drivers of Instability” በሚል ርዕስ ባቀረበው ዘገባ ላይ የአለም አቀፍ የፖለቲካ ግጭት ተንታኝ የሆኑትን ፕሮፌሰር ፒተር አፕስን አስተያየት አቅርቧል፡፡

ፕሮፌሰሩ ሲያብራራ፣ ቻይናና ሩሲያ ይህንን ፖለቲካ የቆመሩት ቻይናና ሩሲያ ዜጐቻቸውን ከሊቢያ ሳያስወጡ የፀጥታው ምክር ቤት ንፁሀንን ከአየር ጥቃት ለመከላከል የሊቢያ አየር ከበረራ ጥቃት ቀጠና በመቀየር እንግሊዝና ፈረንሳይ ከኔቶ ፊታውራሪ ሆነው በሰዓታት ልዩነት የጀት ጥቃት መፈፀም ጀመሩ፡፡

ጥቃቱ ከተጀመረ በኋላ ሩሲያና ቻይና የኔቶ ጥቃት ከፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ ውጭ የሚፈፀም ነው የሚል ተደጋጋሚ ወቀሳ ቢሰነዝሩም ሰሚ አጥተው ትሪፖሊ በመመላለስ ጋዳፊን ለማግባባት ያደረጉት ሙከራ እሳት ውስጥ የገባ ሆኖባቸው፣ ጉድጓዷ እንደጠፋበት አይጥ ወዲህና ወዲያ ዳክረው ጋዳፊን የእሳት እራት ካደረጉ በኋላ፣ መርዶ ነጋሪ የሚያልቅ ሌት ካባ ተከናንበው አጨብጭበው ተቀመጡ፡፡

በዚህ አቋማቸው ክብራቸውን እንደተነጠቁ የቆጠሩት ሩሲያና ቻይና አሁን የዘየዱት መላ ከምዕራባዊያን የሚተላለፉ ውሳኔዎችን ሥር ሥር እየተከታተሉ ያለ አንዳች ማቅማማት ማውገዝና በፀጥታው ምክር ቤት ያላቸውን ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት በመጠቀም ውድቅ ማድረግ ነው፡፡

የአሜሪካ ጦር ከቴህራን ጋር በጦርነት ቢዘፈቅ ቻይና በእስያ የጀመረችውን አዲስ የጦር ቤዝ ግንባታ ስለሚያስተጓጉል በኢራን ላይ የሚደረገውን ማንኛውንም ጫና ከኢራን ጐን በመቆም ለመጋፈጥ አስባለች፡፡

ሌላው ቻይና ቀደም ሲል በሊቢያ የሽግግር መንግስቱን ሊቢያን አይወክልም በማለት በያዘችው አቋም ጋዳፊ ከተገረሰሱ በኋላ፣ ከሊቢያ ታገኘው የነበረው የነዳጅ አቅርቦት መቋረጡና ከ3000 የሚበልጡ ዜጐቿ ተጠራርገው በመውጣታቸው ያደረሰባት የፖለቲካና የኢኮኖሚ ኪሣራ በኢራን እንዲደገም አትፈልግም፡፡

ቻይና ከሩሲያ ጀርባ ሆና እያበጣበጠች ከአሸናፊው ወገን ካልተቀለቀለች የነዳጅ ፍላጐቷ በመካከለኛው ምሥራቅ የተመረኮዘ በመሆኑ ከሩሲያም ከመካከለኛው ምሥራቅም እንዳትነጠል በፖለቲካ ዥዋዥዌ መጓዙን ተያይዛዋለች፡፡ የጀርመኗ መሪ አንጌላ መርኬል ያለፈው ሳምንት የቻይና ጉብኝት አላማም ቻይና በኢራን ላይ የተጣለውን የነዳጅ ማዕቀብ በመደገፍ ከአውሮፓ ህብረት ጐን እንድትቆምና የነዳጅ ፍላጐቷንም ከሳውዲ አረቢያ የምትሟላበትን መተማመኛ ለማመቻቸት ነው፡፡

የአውሮፓ ሕብረት ባለፈው ወር ባስተላለፈው ውሳኔ አባል አገራቱ ከኢራን የሚገዙትን ነዳጅ እስከ መጪው ሀምሌ 1 ቀን 2012 ዓ.ም ሙሉ ለሙሉ እንዲያቋርጡ የሚያሳስብ ነው፡፡ ህብረቱ ይህንን ውሳኔ ያስተላለፈው ኢራን ለውጭ ገበያ የምታቀርበውን ነዳጅ ብታቋርጥ ሳውዲ አረቢያ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ሙሉ በሙሉ እንደምትሸፍን ከመግለጽ በተጨማሪ ቀደም ሲል በቀን የምታቀርበውን 9 ሚሊዮን በርሜል ወደ 900 ሺህ በርሜል ማሳደጓን ከገለፀች በኋላ ነው፡፡

ሳውዲ አረቢያ፣ ቱርክና ህንድ ምዕራባዊያን በኢራን ላይ ጠንከር ያለ ማዕቀብና ጥቃት እንዲሰነዝሩ የሚፈልጉት ኢራን የኒውክሊየር ቦንብ ከታጠቀች ጡንቻዋ ይፈረጥምና እነርሱ የሚፃረሩትን የሺያት ሙስሊም ሃይማኖት በማስፋፋት የሱኒ ሙስሊሞች የበላይነት ያከትማል በሚል ፍራቻ ነው ይባላል፡፡

ምዕራባዊያን ኢራን እንድትገለል ጫና እያደረጉ ባለበት በዚህ ሰዓት ሶሪያ ላይ የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ በሽር አል አሳድ ሥልጣን እንዲለቁ ግፊት እያደረጉ የሚገኙት፣ ሶሪያ ከተረጋጋች ከኢራን ጐን ወግና እስራኤል ላይ ጥቃት ሊሰነዝሩ ይችላሉ የሚል ዕምነታቸው የጐላና የማያጠራጥር በመሆኑ ነው፡፡

ኢራን፣ ቀደም ብሎም ከኩዌት፣ ከዮርዳኖስ፣ ከሳውዲአረቢያና ከሌሎች የአረብ አገራት ጋር ያላት ግንኙነት የሻከረ በመሆኑ የበሽር አል አሳድ መንግስት ከተሽመደመደ በኢራን ላይ የሚገባው ሸምቆቆም እየጠነከረ መሄዱን የሚያውቀው የኢራን መንግስት፤ የሶሪያን መንግስት በመሣሪያ ከመደገፍ በላይ የኢራን እስላማዊ አብዮት ጦርን በሶሪያ የተቀሰቀሰውን ሕዝባዊ አመጽ በኃይል እንዲጨፈልቁ ወደ ደማስቆ ልኳል፡፡

በተጨማሪም ኢራን በሶሪያ መንግስት ላይ ሕዝባዊ አመጹ እንደተቀሰቀሰ 5 ቢሊዮን ዶላር ለግሳለች፡፡

በመካከለኛው ምስራቅ በኢራን ላይ እየተካሄደ የሚገኘው ጫናና ተጽእኖ ኃያላን አገራትን በሁለት ጐራ ከፍሎ በሚገኝበት በዚህ ጊዜ፣ ራሷን ለመከላከል እርምጃ ከመውሰድ ውጭ ስለ አለም አቀፍ ሕግም ሆነ የኃያላን ለሁለት መከፈል ደንታ የማይሰጣት እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት ከሰነዘረች፣ በአካባቢው ላይ ሌላ  ውጥረት እንደሚሰፍን እየገለፀ ይገኛል፡፡

 

 

 

Read 17120 times Last modified on Saturday, 11 February 2012 11:07