Print this page
Tuesday, 29 December 2015 07:36

የግጥም ጥግ

Written by 
Rate this item
(21 votes)

አብረን ዝም እንበል
ከሰው መንጋ እንገንጠል
ለአንድ አፍታ እንኳ እንገለል
በእፎይታ ጥላ እንጠለል
ዝም ብለን አብረን ዝም እንበል።
ምነው አዋሽ ማዶ፣ ቆቃ ሸለቆው ግርጌ ሸሽተን
የቆቃን ሰቆቃ ሰምተን
ሲቃውን ሲሰብቀው አይተን
ሰቀቀኑን ተወያይተን
የምሽት ጀምበር ቢውጠን ….
ውኃ እንደ ዱታ ሲተምም፣ በድን ሸለቆ ሲናገር
በሰማይ ፈረስ ተጭኖ ከአጽናፍ አጽናፍ
ሲንደረደር
ሲያጉተምትም ሲያስገመግም ባይነ ህሊና
ለመመስከር
ሳንጨነቅ ሳንገደር
ለምንም ምንም ሳናዋይ ሳንናገር ሳንጋገር
ከዐይንሽ ከልብሽ ከልቤ አዋሽ ማዶ አብረን
እንብረር
አዋሽ ማዶ አብረን እንውረድ
አጉል ነው ብለን ሳንፈርድ
ድንቅም ነው ሳንል ሳንወድ
ዝም ብለን አብረን ብንወርድ…
ከሰው መንጋ ተለይተን
ከጠረኑ ተነጥለን
ከጉምጉምታው ተገንጥለን፣ ከኳኳታው ብንከለል
ከላንቃው ከድምፁ ሸሽተን በእፎይታ ጥላ
እንጠለል
በቆይታ በጸጥታ ዝም ብለን አብረን ዝም እንበል።
መቼስ አይሆንም ካልሽ ቅሪ
ግዴለም አትገደሪ
ልቦናሽ በመተረልሽ ባሳደረብሽ እደሪ
ተስፋ መቀነን ነው መቼም
የሰው ልብ አይችለው የለም።
ብቻ ዳግመኛ ሞት ሳንሞት፣ አዲስ ቀን
ሳይጨልምብን
ድፍን ደመና ሳይቋጥር፣ ክረምት ውርጅት
ሳይወርድብን
ኮከባችንን ሳንጠራ፣ ሳንቆጥርባት ሳትቆጥርብን
ሞራችንን ሳናስነብብ፣ ሳናሳያት ሳታይብን
ጨረቃን መስክሪ ሳንል፣ ሳናውቅባት ሳታውቅብን
አዋሽ ማዶ ቆቃ በረን፣ እባክሽ ጀምበር
ትጥለቅብን።
ውኃ እንደ ዱታ ሲተምም፣ በድን ሸለቆ ሲናገር
በሰማይ ፈረስ ተጭኖ፣ ከአጽናፍ አጽናፍ
ሲንደረደር
ሲያጉተምትም ሲያስገመግም፥ ባይነ ህሊና
ለመመስከር
ሳንጨነቅ ሳንገደር
ለማንም ምንም ሳናዋይ፣ ሳንናገር ሳንጋገር
ከዐይንሽ ከልብሽ ከልቤ አዋሽ ማዶ አብረን
እንብረር።
ከሰው ኳኳታ እንነጠል
ለአንድ አፍታ እንኳ እንገለል
በእፎይታ ጥላ እንጠለል
ዝም ብለን አብረን ዝም እንበል።
ከሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን

Read 5715 times
Administrator

Latest from Administrator