Saturday, 11 February 2012 14:45

ከሰሞኑ የፓርላማ ወግ ጀርባ “ሌላ ወግ”

Written by  ናርዶስ ጂ.
Rate this item
(0 votes)

እንዴት ሰነበታችሁ? አገር አማን ነው? የገበያውም ሆነ የፓርላማው ውሎስ እንዴት ነው?... አይነት አሰልቺ ሠላምታ ማዳመጥ ካቆመች ቆይታለች - አያቴ፡፡ ባስ ሲላትም፣ “ሦስት ጊዜ እንዴት አደራችሁ አንዱ ለጠብ ነው አሉ” ብላ ትተርታለች፡፡ እኔንም የአያቱ ልጅ እንዲሉኝ፣ ሠላምታ መስጠት አቁሜያለሁ፤ ሠላም የምልበት ሀይል እያነሰኝ፡፡ “ፓርላማው እንዴት ሰነበተ?” የሚል ጥያቄ ለአያቴ ሲቀርብላት ግን፣ “እሱ ምን ይሆናል የሚመክርለት ሳይሆን የሚመክርበት የኢትዮጵያን ያህል ሙሉ ህዝብ እያለለት” ትላለች፡፡ እናም፣ የፓርላማ ወግ አያመልጣትም፡፡ 
በተለይ፣ “የፓርላማው ፊታውራሪ ካቡ…” በምንም ታምር አታልፈውም፡፡ ከትላንት በስቲያ፣ ማለትም የጥር ወር መዝጊያ ላይ የፓርላማው ወግ ሲደራ፣ በቴሌቪዥን ለማየት ብሞክር፣ በወግ አምጣው ገበታ (ዲሽ) እንዳይተላለፍ በሰማይ ላይም የፌደራል ፖሊሲ ቁማል መሰል፣ “ወይ ፍንክች የአባ ቢላዋ ልጅ” አለኝ፡፡

የአፍሪካና የኢትዮጵያ ዋና ከተማ የምትባለው አዲስ አበባ፣ መቼም ለጉድ ነው የፈጠራ፣ ከአራት ኪሎ ቤተመንግስት 3 ኪ.ሜ እርቀት ላይ ጠላታችሁ ጥፍት ይበልና የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጭራሽ በጄ አይልም፣ አይታይም…ብላችሁ ምን ትሉ 

ይሆን?ለዚህ ነው ወግ አምጣ ገበታውን ተበድሬ የገዛሁት! አንዳንድ ሰዎች እንደሚሉት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዝግጅት “ላለመቃጠል”አይደለም ወይም የውጭ ሀገር ወጐችን ለመኮምኮም ካለኝ ፍላጐትም አይደለም ምክንያቴ አንድ ነው - የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከኔ ቤት ሊደርስባለመቻሉ፣ በፈረንጆቹ ወግ አምጣ ገበታ አማላጅነት ለመከታተል እንጂ!የእኛን ሀገር ወግ መቼም ታውቁታላችሁ! አንዱን ይዞአንዱንአንጠልጥሎ ነው… የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በወግ አምጣው ገበታ (ዲሽ) እንዳይተላለፍ፣ ከፓርላማ ይሁን ወይም ከከነማ፣ ወይም ደግሞ ከየካድሬው አውድማ፣ ብቻ ከየት በመጣ ቀጭን ትዕዛዝ እንደሆነ ባላውቅም፣ በወግ አምጣው አማላጅነትና ቸርነት የሚተላለፈው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዝግጅት ከኔ ቤት ከተቋረጠ ይኸው ድፍን አንድ ሣምንት ሞላው፤ ሳይሉት በሦስት መስመር መተላለፍ ጀምሮ፣ ዛሬ አንዱም እንኳ የሚቀርብበት አቅም አጣ! ይሄ ለጉድ የፈጠረው አይናውጣ (እዝች ላይ የፈጠርኳትን ግጥም ልብ በሉልኝ - ስድቤ በግጥም ሂዶ ግጥም ማለቱ ማስተዋል ጥሩ አንባቢነት ነው፡፡)በነገራችን ላይ ለቴሌቪዥንም ለሞባይሌም ጦም ማደር ዋናው ተጠያቂ “የኢትዮጵያ ቴሌኮሚኒኬሽን ኮርፖሬሽን” ነው፤ ውይ ይቅርታ ብዙ ዶላር አፍስሶ ያስቀየረውን አዲስ ስሙን “ኢትዮ ቴሌኮም” ማለት ነበረብኝ፡፡ ብር አልበቃው፣ አልመጥነው ብሎ በውጭ ምንዛሪ “በዶላር” ሀይል፣ ስሙን እንጂ አሠራሩን አለመቀየሩ ሲያናድደኝ የሰማችው አያቴ፣ “ዝድቁ ቀርቶብኝ በወጉ በኮነነኝ አሉ…መሻሻሉ ቀርቶበት፣ ከድሮው ብሶ ባልተወላሸሸ፤ ወግ ነው ሲዳሩ ማልቀስ አሉ…ይልቅ በየቀኑ በፈረንጅ አፍ እየጻፈ የሚልከውን ደብዳቤ ባቆመልኝ” ስትል ሁላችንም ሳቅን - በጣም፡፡ “በሉ እንደሞላለት ሰው ከቤት በላይ አትሳቁ” ቀጭን ትዕዛዝ ሰጠችና ቴሌቪዥኗ ላይ አራጠጠች፤ እኔና የአያቴ የቤት ሠራተኛ ከትከት ብላን ሳቅን፤ “ጌታው የመጣህበትን ቴሌቪዥንህን እይ! ግብሩን እኔ ነኝ የምከፍለው… ቆይ ቆይ ዝም በሉ” ሁላችንም ዝም አልን፡፡
ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ፣ በፓርላማ ንግግር እያደረጉ ነው፡፡ አያቴ፣ “የፓርላማው ፊታውራሪ” ነው የምትላቸው፡ እሳቸው እየተናገሩ፣ ከቤት ውስጥ ማንም ትንፍሽ እንዲል አይፈቀድለትም፡አንድ ቀን ንስሃ አባቷ ቄስ መፍቀሬ እያሉ፣ አቶ መለስ በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለው መግለጫ ሲሰጡ ተመለከተች፡፡ ወዲያው፣ “አባ መፍቅሬ ፀሎቱን በኋላ እናቆየው ይንሱ ቴሌቪዥኑን ይመልከቱ” አለቻቸው፡፡ 
አባም ደንግጠው፣ “ወለተማርያም…የላይኛውን ንጉሥ ነው መስማት ያለብሽ የመንግስተ ሰማያቱን አለቃ!” ሲሉ፣ አያቴም፣ “አይ መምሬ…ወደ መንግስተ ሰማያት በየት ነው የምንገባው?...መጀመሪያ የመቀመጫዬን አለች አሉ ዝንጀሮ …መጀመሪያ የምድሩን ስቃይ ለምድሩ ንጉሥ አቤት ብለን፣ ሃጢያታችን ካልተፈታ…” እውነቴን ነው የምልዎት መምሬ!… አሁን አሁንማ ይሄ የኑሮ ውድነት እንደ ደማሚት ስጋችንን ብቻ ሳይሆን ነፍሳችንንም አመድ አድርጐ የሚያስቀራት መሰለኝ…” ስትላቸው፣አባ ተናደው ከተቀመጡበት ብድግ አሉና ሄዱ፡አያቴ እንደነገረችኝ ከሆነ አባ ከቤት ከመውጣታቸው በፊት፣ “የምድሩ ንጉስዎ!… የፓርላማ ምክር ቤትና የቃሊቲ እስር ቤት የሚገባውን ይወስን እንጂ የመንግስተ ሰማያትንማ ምን አገባው! የመላይክት አለቃ ቀልድ መስልዎታል” ብለው መናገራቸውን አውርታኛለች፡፡ የአያቴን እልኸኝነትና ደፋር ተናጋሪነት አውቀዋለሁ፤ ዝም አትልም! ቄሱ ተናግረዋት ሲወጡ፣ “እስዎስ ቢሆኑ ምን እንዲህ ያደርግዎታል መንግስተ ሰማይትን ሄደው አላዩት…ፓርላማው ፊታውራሪ በፓርላማ አስወስነው መንግስተ ሰማያትን ላለመቆጣጠራቸው ምን ማረጋገጫ አለዎት” ብላ በሆዷም ቢሆን እንደምትመልስ 
አውቃለሁ፡፡ ዛሬም ታዲያ አያቴ የፓርላማውን ወግ ታዳምጣለች፤ አቶ መለስ ስለ ኤርትራ ጠብ ጫሪነትና በተባበሩት መንግስታት እንድትቀጣ ስለማደርጋቸው በስሜት እየተናገሩ ነው፤ “ካልሆነ…” አሉ “ካልሆነ እራሳችን የመከላከል መብታችን ወደ መጠቀም መግባታችን ነው…” አይነት ማስጠንቀቂያ (ለአስመራው ንጉስ) እያስተላለፉ ሳለ በድንገት ተነፈሰች፡፡ “እየሰማችሁ ነው? ደግ አረጉ! ለነገሩ የደሃ ህዝብ መሪ ሆነው እንጂ ወኔዋንማ አያጡም! የአባታቸው ነው…” እያለች ስታደናንቅ፣ ሠራተኛዋ ከፍ ብላ ሳቀች፡፡ አሁን አያቴ ተበሳጨች፤ “አንቺ ሙጥሙጥ! ደብተርሽን አታንብቢና በማታውቂው ጉዳይ ተገለጭ“የአያቴ ነገር ይገርመኛል! እውነት ግን አቶ መለስን ስለምታደንቃቸው ነው ወይስ ስለምትፈራቸው እንዲህ የምትሆነው የሚል ጥያቄ አንስቼ እስከአሁን ምላሽ አላገኘሁም፤ በርግጥ ደፍሬ ፊት ለፊት አልጠየቅኋትም፡፡ ጥያቄዬን በገዛ አንጐሌ ቀቅዬ አማሰልኩት እንጂ!…ዛሬ ግን ደፈር ብዬ “ወኔያቸውን፣ ወንድም ከሆነው ከኤርትራው መንግስት ላይ ማሳየቱን ትተው፣ የገዛ አውሮፕላናችንን አጋይቶ ብዙ ወገኖቻችን መጨረሱ አልበቃ ብሎ፣ የተጠየቀውን በወጉ ላለማስረዳት የሚያቧትረውን የሊባኖስ መንግስት ለምን አያስጠነቅቁም?” በማለት ጠየቅኋት፡፡ አያቴ ወሬዬ እንዳላማራት ከፊቷ ላይ አነበብኩት! በቴሌቪዥኑ መስኮት ላይም አሁንም አሉ፤ የፓርላማው ወጋቸው አላለቀም፤ አያቴም ድምፃችንን ሁሉ አስጠፍታ ትመለከታለች፡፡ ልብ ብሎ ላያት፣ የቴሌቪዥን ተመልካቾች ተቆጣጣሪ ዋና የሥራ ሂደት መሪ ትመስላለች፡፡ ቶ መለስ “የሽብርተኛ ህጉ ከአሜሪካ፣ የተባበሩት መንግስታት ወዘተ…ቃል በቃል ነው የተቀዳው… 
ኮማም አልቀረም” ሲሉ፣ የአያቴ ሠራተኛ፣ “እንዴዬ ምን ማለታቸው ነው! ወንጀል እኮ ነው! መምህራችን ስታነቡ ኮማ ሳይቀር ቃል በቃል አትገልብጡ… ዋናውን ሀሳብ ነው ጨምቃችሁ መውሰድ ብለዋል” ስትል እኔ ከጣራ በላይ ሳቅሁ፡፡ አያቴም ሳቀች፡፡ ወዲያው ግን፣ “እቺ የአምስተኛ ክፍል የማታ ትምህርትሽ አቶ መለስን ለመገምገም አበቃችሽ! እኔ የምለው መምህራችሁ፣ የፀረ ሽብር አዋጁ አርቃቂ ኮሚቴ ሃላፊ ነው እንዴ?” ብላ ተሳለቀች - አያቴ፡፡ ገራገሯ የአያቴ ሠራተኛ “ኧረ አይደሉም! የእኛ የክፍል ሃላፊ ናቸው” አለች፡፡ ሁላችንም ሳቅን… 
የአያቴና የአቶ መለስ ወዳጅነት ተጀመረ እንጂ አላለቀም፡፡ ገና ወጋቸው እንደ ጉድ ይወጋል!

 

Read 2887 times Last modified on Saturday, 11 February 2012 14:50