Print this page
Saturday, 02 January 2016 12:12

ጮማ ሱሰኛ ያደርጋል!

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(0 votes)

  “ህዝቤ ለካ ስጋ ቤት ደጃፍ የማይጠፋው …”
    ሁልጊዜ በዓል ሲቃረብ በዓሉን በዓል ለማስመሰል የተለያዩ የምግብና የመጠጥ አይነቶችን በብዛት ማዘጋጀት የተለመደ ነው፡፡ ምንም እንኳን የኑሮ ውድነቱ የህብረተሰቡን እንደልብ የመሸመት ፍላጐት ቢገድበውም ሁሉም እንደአቅሙ ደረጃ ለበዓሉ አስፈላጊ ናቸው የሚላቸውን ነገሮች መሸማመቱ አይቀሬ ነው፡፡ ከበዓል የሸመታ ዝርዝር ውስጥ ፈጽሞ የማይለይና በበዓል ማድመቂያነቱ ጐልቶ የሚጠቀሰው ደግሞ ሥጋ ነው፡፡
አብዛኛዎቻችን ከሥጋም ነጩ በዛ ያለበትን ጮማውንና የሰባውን ይበልጥ እንመርጣለን፡፡ “ስጋ ከተበላማ ነጩን ነው እንጂ ቀይማ ምን ይሰራል፡፡ ሣር ሣር ነው የሚለው፡፡ ቢያስጨንቅም ጮማ” ከሚለው አባባል አንስቶ “የጮማዬ ጌታ” እየተባለ ለምስጋናና ለማሞካሺያ እስከሚውለው ቃል ድረስ ህብረተሰቡ ለጮማ ሥጋ ልዩ ፍቅርና አክብሮት አለው፡፡ ይሁን እንጂ ጮማ ሥጋ በጤና ላይ የሚያስከትለው የከፋ ችግር ምነው ባይበላስ ሊያሰኝ የሚችል እንደሆነ ይነገራል፡፡ ሰሞኑን “ኔቸር ኒውሮ ሳይንስ” በተባለ የምርምር መጽሔት ላይ የወጣው ዘገባ ግን ከቀድሞዎቹ ለየት ያለና አዳዲስ የጮማ ሥጋን አደጋዎች የያዘ ነው፡፡ ጮማና ቅባት ነክ ምግቦች ልክ እንደ አደንዛዥ እፆች አዕምሮን ሰቅዞ የመያዝና ሱሰኛ የማድረግ ተፅዕኖን ያሳድራሉ የሚለው ዘገባው፤ እነዚህ ምግቦች ከሱሰኝነትም ባለፈ ለበርካታ የጤና ችግሮች መነሻ ሊሆኑ እንደሚችሉ አመልክቷል፡፡
መፅሄቱ ለንባብ ያበቃው ይኸው ዘገባ፤ የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት ጠቅሶ  በአንድ አመት ብቻ ከ5 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ጮማና ቅባት ነክ ምግቦች በሚያስከትሉት የኮሌስትሮል በሽታ ሳቢያ ህይወታቸውን እንደሚያጡ የገልጿል የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርትን ጠቅሶ፡፡  
ኮሮናሪ ኸሪት ዲዚዝ የተሰኘው አደገኛ የልብ ህመም ዋንኛ መነሻ ጮማና ቅባት ነክ ምግቦችን አብዝቶ በመመገብ ከመጠን ያለፈ ቅባት በደም ቧንቧዎች ውስጥ መከማቸትና ቧንቧው መዘጋት ነው፡፡ እንደሚታወቀው የትኛውም የሰውነታችን ህዋስ በህይወት ለመቆየት ኦክስጂንና ንጥረ ምግቦችን ይፈልጋል፡፡ ይህ ደግሞ ተግባራዊ የሚሆነው በደም አማካኝነት ነው፡፡ የደም ፍሰትን ወይም ዝውውርን የሚገቱ ማናቸውም ችግሮች ለከፋ የጤና እክል አሊያም ሞት ሊዳርጉ ይችላሉ። ጮማና ቅባት ነክ ምግቦች የሚያስከትሏቸውን የጤና ችግሮች አስመልክቶ የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት እንዳመለከተው፤ ጮማና ቅባት ነክ ምግቦች መጠኑ ለበዛ ኮሌስትሮል ያጋልጣሉ፡፡ በዓለም ላይ ከሚከሰቱ የጭንቅላት ቧንቧዎች ህመም - 18 በመቶውን፣ ለልብና ልብ አካባቢ ለሚገኙ የደም ቧንቧዎች ህመምና ሥራ መስተጓጐል - 56 በመቶውን የሚያስከትሉትም እነዚሁ ጮማና ቅባት ነክ ምግቦች መሆናቸውን ሪፖርት ጠቁሟል፡፡ የደም ቧንቧዎች በቅባት ጥርቅም እየጠበቡ በመምጣት በቂ ደም ወደ ጭንቅላት እንዳይደርስ በሚያደርጉበት ጊዜ ስትሮክ እንደሚያጋጥምና ይህም ለድንተገኛ ሞትና ለከፍተኛ የአካል ጉዳት ሊዳርግ እንደሚችል “ኔቸር ኒውሮ ሳይንስ” አመልክቷልል፡፡
ጮማና ቅባት ነክ ምግቦች በጤናችን ላይ ከሚያስከትሉት ጉዳት በተጨማሪ እንዲህ ሱስ አስያዥ ከሆኑና ለአዕምሮ አለመረጋጋት የሚዳርጉን ከሆነ ቀድሞ መጠንቀቅ አይበጅም ትላላችሁ። በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ ሰው በሰጠኝ አስተያየት ጽሑፌን ላጠቃል፤ “እንዴ ጮማ ሱስ አስያዥ መሆኑ ተረጋገጠ ነው የምትይኝ? ህዝቤ ለካ በሱስ ተጠምዶ ነው በየሥጋ ቤቱ ደጃፍ ወረፋ የያዘው!” እውነት ይሆን እንዴ?

Read 4302 times