Saturday, 18 February 2012 10:10

ከአውሮፓ 5 ታላላቅ ሊጎች የቱ ይልቃል?

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(3 votes)

ፕሪሚዬር ሊግ፤ ላሊጋ፤ ቦንደስ ሊጋ፤ ሴሪኤ ...ሊግ 1

አውሮፓ 5 ታላላቅ ሊጐች የ2012 -13 የውድድር ዘመን ተጋምሦ ያለፈ ሲሆን በየሊጉ ሻምፒዮኖች በቀረቡ ዋንጫዎች ከ1 በላይ ክለቦች ተናንቀውበታል፡፡ አምስቱ ታላላቅ ሊጐች ባላቸው የዋጋ ግጭት፤ በገቢ አቅማቸው እና በሌሎችም መስፈርቶች መነፃፀራቸው ቀጥሏል፡፡ የስታድዬም ታዳሚ ፡ የጀርመን ቦንደስሊጋ በየጨዋታው በአማካይ በሚያገኘው የስታድዬም ተመልካች ብዛት ቀዳሚ ነው፡፡ አንድ የቦንደስ ሊጋ ግጥሚያ በአማካይ 42637 ተመልካች አለው፡፡ ለዚህ ዋና ምክንያት በጀርመን የሚገኙ ስታድዬሞች ግዝፈትና የትኬት ዋጋ ማነስ ነው፡፡ ጀርመናዊያን ለቦንደስ ሊጋ አንድ ጨዋታ የሚከፍሉት የትኬት ዋጋ 22 ዩሮ ሲሆን ዋጋው የባስ ወይም የባቡር ትራንስፖርትን ያካትታል፡፡ በርካሽ የቲኬት ዋጋ ሊግ 1 በ26 ዩሮ 2ኛ ነው፤ የጣሊያኑ ሴሪኤ በ27 ዩሮ የስፔኑ ላሊጋ በ36 ዩሮ እንዲሁም የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ በ43 ዩሮ የትኬት ዋጋቸው ተከታታይ ደረጃ አላቸው፡፡

በዓመታዊ ገቢ ፡ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ 20 ተወዳዳሪ ክለቦች ባንድ የውድድር ዘመን እስከ 2.5 ቢሊዮን ዩሮ ገቢ በማስገባት ይመራሉ፡፡ የጀርመን ቦንደስ ሊጋ ደግሞ በየዓመቱ 1.664 ቢለዮን ዩሮ ገቢ በመስራት ሁለተኛ ደረጃ አለው፡፡ የእንግሊዙ ፕሪሚዬር ሊግና የጀርመኑ ቦንደስ ሊጋ አምስቱ ግዙፍ ሊጎች በየዓመቱ ከሚያገኙት ገቢ 50 በመቶውን ድርሻ ይወስዳሉ፡፡  የስፔኑ ላሊጋ 1.622 ቢሊዮን ዩሮ፤ የጣሊያኑ ሴሪኤ 1.532 ቢሊዮን ዩሮ እንዲሁም የፈረንሳዩ ሊግ 1 1.072 ቢሊዮን ዩሮ ዓመታዊ ገቢ በማስመዝገብ ተከታታይ ደረጃ ይሰጣቸዋል፡፡ የአውሮፓ 5 ታላቅ ሊጎች ዋና ገቢ ከቴሌቭዥ የስርጭት መብት የሚያገኘው ነው፡፡ ከ5ቱ ሊጎች ከፍተኛውን የቲቪ  ገቢ ይዞ የሚመራው በየዓመቱ 1.15 ቢሊዮን ዩሮ የሚገኝበት የእንግሊዙ ፕሪሚዬር ሊግ ነው፡፡ የጣሊያኑ ሴሪኤ በ892 ሚሊዮን ዩሮ ሁለተኛን ደረጃ ሲወስድ የስፔኑ ላሊጋ በ560 ሚሊዮን ዩሮ፣ የፈረንሳዩ ሊግ 1 በ517 ሚሊዮን ዩሮ እንዲሁም የጀርመኑ ቦንደስ ሊጋ በ422 ሚሊዮንዩሮ ዓመታዊ ገቢ ተከታታይ ደረጃን ወስደዋል፡፡

በክለቦች የዋጋ ግምት ፡ ብራንድ ፋይናንስ የተባለ ተቋም በሰራው ሪፖርት ክለቦች ባላቸው የብራንድ የዋጋ ተመን ከ1 እስከ 4 ያለውን ደረጃ የወሰዱ አራት ክለቦች ከሶስት ሊጎች የተወከሉ ናቸው፡፡ ደረጃውን በ412 ሚሊዮን ዩሮ የዋጋ ተመን የሚመራው የእንግሊዙ ማን ዩናይትድ፤ በ401 ሚሊዮን ዩሮ የሚተመነው ሪያል ማድሪድ እና በ392 ሚሊዮን ዩሮ የተገመተው ባርሴሎና ከስፔን ላሊጋ፣ እንዲሁም በ308 ሚሊዮን ሚሊዮን ዩሮ የብራንድ ዋጋ የተሰጠው ባየር ሙኒክ ናቸው፡፡ በደረጃው የጣሊያንን ሴሪኤ የወከሉት ሁለቱ የሚላን ከተማ ክለቦች ኤሲ ሚላንና ኢንተርሚላን 7ኛና ስምንተኛ ደረጃ የያዙት በ170 ሚሊዮን ዩሮ ተተምነው ነው፡፡ የፈረንሳዩ ኦሎምፒክ ሊዮኔስ በ76 ሚሊዮን ዩሮ የዋጋ ተመኑ 16ኛ ነው፡፡ በሊግ ደረጃ ተወዳዳሪ ክለቦች ባላቸው ድምር የብራንድ ዋጋ የሚመራው 1.18 ቢሊዮን ዩሮ በ20 ክለቦች ያስተመነው የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ሲሆን ላሊጋ በ898 ሚሊዮን ዩሮ 2ኛ፤ ቦንደስ ሊጋ በ647 ሚሊዮን ዩሮ 3ኛ፤ ሴሪኤው በ617 ሚሊዮን ዩሮ 4ኛ እንዲሁም የፈረንሳዩ ሊግ 1 በ198 ሚሊየን ዩሮ 5ኛ ናቸው፡፡

ያንድ ጨዋታ ዋጋ ፡ በአንድ ጨዋታ ከፍተኛውን ገቢ በማስገባት የሚመራው 6 ሚሊዮን 579ሺ ዮሮ የሚገመተው የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ 5 ሚሊዮን 444ሺ ዩሮ የሚያወጣው የቦንደስሊጋ ጨዋታ ሲቀመጥ፤ የጣሊያኑ ሴሪኤ አንድ ጨዋታ በ4 ሚሊዮን 32ሺ ዩሮ እንዲሁም አንድ የስፔን ላሊጋ ጨዋታ በ4 ሚሊዮን 269ሺ ዩሮ ዋጋ ተተምነው 3ኛና 4ኛ ደረጃን ያገኛሉ፡፡ የፈረንሳዩ ሊግ 1 ጨዋታ 2 ሚሊዮን 321ሺ ዩሮ የሚያስገኝ ነው፡፡በአውሮፓ ውድድሮች ዋንጫ ብዛት ፡ በአውሮፓ ውድድሮች በዋንጫ ውጤት ከፍተኛውን ደረጃ የተናነቁበት የጣሊያኑ ሴሪኤ እና የስፔኑ ላሊጋ ክለቦች ናቸው፡፡ በአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ስር በሚዘጋጁ ውድደሮች 17 ዋንጫ በመሰብሰብ ኤሲ ሚላን ሲመራ የስፔኖቹ ሪያል ማድሪድ በ17 እንዲሁም ባርሴሎና በ12 ዋንጫዎች ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ ይኖራቸዋል፡፡ ጁቬንትስ እና ሊቨርፑል በ11 ዋንጫዎች አራተኛ ደረጃን ሲጋሩ የሆላንዱ አያክስ በ10 እንዲሁም የጀርመኑ ባየር ሙኒክ በ 8 ይከተላሉ፡፡በአገር ደረጃ በአውሮፓ ትልልቅ የክለብ ውድድሮች ከፍተኛ የዋንጫ ስብስብ በማስመዝገብ አንደኛ የሆነው የጣሊያን ሴሪኤ ሲሆን ተወዳዳሪ ክለቦቹ 48 የዋንጫ ድሎች አሳክተዋል፡፡ የስፔኑ ላሊጋ ክለቦች 44 ዋንጫ በመሰብሰብ ሁለተኛ ደረጃ ሲሰጣቸው የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ክለቦች በ37 ዋንጫዎች 3ኛ ደረጃን ይይዛሉ፡፡ የጀርመን ክለቦች በ27 የዋንጫዎች ስብስብ አራተኛ ደረጃን ሲወስዱ የሆላንድ ኤርዲቪዜ ክለቦች በ18 እንዲሁም የፈረንሳዩ ሊግ 1 ክለቦች በ14 ዋንጫዎች ስብስብ 5ኛ እና 6ኛ ደረጃ ይሰጣቸዋል፡፡ በሻምፒዮንስ ሊግ የዋንጫ ብዛት የስፔን ክለቦች 12 በመውሰድ የሚመሩ ሲሆን የጣሊያን ክለቦች በ12 እንዲሁም የእንግሊዝ ክለቦች በ11 የሻምፒዮንስ ሊግ ድሎች ይከተላሉ፡፡ የጀርመንና የሆላንድ ክለቦች እኩል ስድስት የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችንወስደው ተከታዩን ደረጃ ሲይዙ የፈረንሳይ ክለቦች 1 ግዜ ብቻ ድሉ ቀንቷቸው የበታች ናቸው፡፡በ57ኛው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ከ52 አገራት የተወከሉ 76 ክለቦች ያሳተፈው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ 16 ክለቦችን በያዘው የጥሎ ማለፍ ምዕራፍ ሰሞኑን የቀጠለው ከ3 ወራት ቆይታ በዃላ ነው፡፡ በጥሎ ማለፉ የመጀመርያ ዙር ጨዋታዎች ሰሞኑን አራት ግጥሚያዎች ሲደረጉ አርሰናል በሳንሲሮ በኤሲ ሚላን 4ለ0 ተሸንፎ የመውደቅ አደጋ ተጋርጦበታል፡፡ በሌሎች ጨዋታዎች ባርሴሎና ከሜዳው ውጭ ሌቨርኩዘንን 2ለ1፤ ሊዮን የቆፕሮሱን አፖል ኒኮስያ 1ለ0፤ ዜኒት ፒተርስበርግ በሜዳው ቤናፊካን 3ለ2 አሸንፈዋል፡፡

በቀጣይ ሳምንት ቀሪዎቹ 4 ጨዋታዎች ይደረጋሉ፡፡ ሪያል ማድሪድ ወደ ሞስኮ ተጉዞ ከሲኤስኬ ጋር ሲገናኝ በስታድዮ ሳን ፓውሎ ናፖሊ የእንግሊዙን ቼልሲ ያስተናግዳል፡፡ ባየርሙኒክ ከሜዳ ውጭ ከኤፍሲ ባሰል ጋር ሲጫወት ኢንተር ሚላንን በስታድዮቬልደሮም የሚያስተናግደው ማርሴይ ነው፡፡

በሻምፒዮንስ ሊጉ የጥሎ ማለፍ ምእራፍ ሲጀመር 100 ጨዋታዎች ተደርገው 268 ጎሎች ሲመዘገቡ ባንድ ጨዋታ በአማካይ 2.68 ጎሎች እየገቡ ናቸው፡፡ ኮከብ ግብ አግቢነቱን የሚመራው የባርሴሎናው ሊዮኔል ሜሲ በ7 ጎሎቹ ነው፡፡

በዘንድሮው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የስፔኖቹ ክለቦች ሪያል ማድሪድና ባርሴሎና ለሻምፒዮናነት የተሰጣቸው ግምት የላቀ ነው፡፡ ላለፉት 5 ዓመታት ከሩብ ፍፃሜ እስከ ዋንጫ ጨዋታ ቋሚ ተሰላፊ የነበሩት የእንግሊዝ ክለቦች ደግሞ ገና በጥሎ ማለፉ መፎካከር አዳግቷቸዋል፡፡ በአንፃሩ የጀርመን እና የጣሊያን፣ የፖርቱጋል እና የራሺያ ተወካይ ክለቦች በጥንካሬ እየመጡ ናቸው፡፡

20ኛው የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ፡ ባደረጋቸው 25 የሊግ ጨዋታዎች 60 ነጥብ በመሰብሰብ መሪነቱን የተቆናጠጠው ማንችስተር ሲቲ ነው የቅርብ ተቀናቃኙ ማን ዩናይትድ በ58 ነጥብ ሁለተኛ ሆኖ ይከተላል፡፡ ቶትንሃም ሆትስፐርስ በ53 ነጥብ 3ኛ ደረጃን ሲይዝ፤ አርሰናል በ43 ፤ ቼልሲ በግብ ክፍያ ተበልጦ በ43 ፤ ኒውካስትል በ42 እንዲሁም ሊቨርፑል በ42 ነጥብ ከ4 እስከ 7 ባሉ ደረጃዎች ተያይዘዋል፡፡ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ 25ኛው ሳምንት ላይ ሲደርስ በተደረጉት 250 ጨዋታዎች 713 ጎሎች ተቆጥረውበታል፡፡ በአንድ የሊጉ ጨዋታ 2.85 ጎሎች ከመረብ ያርፋሉ፡፡ ኮከብ ግብ አግቢነቱን በ22 ጎሎች እየመራ የሚገኘው የአርሰናሉ ፊትአውራሪ ቫንፒርሲ ነው፡፡ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ዋንጫን ሁለቱ የማንችስተር ከተማ ክለቦች እንደተናነቁበት ናቸው፡፡ ማንችስተር ሲቲ በታሪክ የመጀመርያውን የሻምፒዮናነት ክብር ለማንሳት መሪነቱን ይዞ ሲገሰግስ ማንዩናይትድ በበኩሉ በውድድሩ ታሪክ 20ኛውን የሊግ ዋንጫ በማንሳት ከፍተኛው የወጤት ክብረወሰንን ለመያዝ አድፍጧል፡፡ ከሁለቱ ትንቅንቅ ውጪ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ በቀጣይ የውድድር ዘመን መሰለፍ የሚያስችለውን 3 እኛና አራተኛ ደረጃ ተቀራራቢ ነጥብ የሚፈልሙበት ቶትንሃም፤ቼልሲ፤አርሰናል፤ ሊቨርፑልና ኒውካስል ናቸው፡፡81ኛው የስፔን ላሊጋ ፡ በላሊጋው ባደረጋቸው 22 ግጥሚያዎች 58 ነጥብ ይዞ መሪነቱን የተቆናጠጠው ሪያል ማድሪድ ሲሆን  ባርሴሎና በ48 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ነው፡፡  ቫሌንስያ በ40 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ሲይዝ ሌቫንቴ በ32 ነጥብ አራተኛ ነው፡፡ በላሊጋው እስከ 22ኛው ሳምንት 220 ጨዋታዎች ተደርገው 582 ጎሎች ተመዝግበዋል፡፡ ባንድ ጨዋታ በአማካይ 2.65 ግቦችን እያስተናገደ ነው፡፡ ለኮከብ ግብ አግቢ በሚሰጠው የፒቺቺ ክብር የሪያል ማድሪዱ ክርስትያኖ ሮናልዶ 27 ጎሎች በማስቆጠር እየገሰገሰ ሲሆን የባርሴሎናው ሊዮኔል ሜሲ በ23 ጎሎች ይከተለዋል፡፡ለበረኞች ኮከብነት በሚዘጋጀው የዛሞራ አዋርድ ላይ ደግሞ የባርሴሎናው ቪክቶር ቫልዴዝ 16 ጎሎች ብቻ ተቆጥረውበት 1ኛ ሲሆን  የሪያል ማድሪዱ ኤከር ካስያስ 22 ጎሎች ገብተውበት ሁለተኛ ነው፡፡

ማድሪድ በ10 ነጥብ ልዩነት ባርሴሎና አስከትሎ ላሊጋውን መምራቱ ከ4 ዓመት በዃላ ለመጀመርያ ጊዜ ሻምፒዮን ሊሆን የሚችልበትን እድል አስፍቶታል፡፡ ማድሪድ የሊጉ ሻምፒዮናነት ክብር ብቻ ሳይሆን በውድድር ዘመኑ  ብዙ ሪኮርዶችን ሊያስመዘግብ የሚችልበት ሁኔታም ይስተዋላል፡፡ ከ2 የውድድር ዘመናት በፊት ባርሴሎና ላሊጋውን በሻምፒዮናነት ሲፈፅም ያስመዘገበው 99 ነጥብ ዘንድሮ በሪያል ማድሪድ የዋንጫ ግስጋሴ 100ን ተሻግሮ ሊሰበር ይችላል፡፡ በ1990 እኤአ ሪያል ማድሪድን ባሰለጠኑት ጆን ቶሻክ ዘመን የነበረው ቡድን ባንድ የውድድር ዘመን ያገባቸው 107 ጎሎችም ሊሻሻል ይችላል፡፡49ኛው የጀርመን ቦንደስ ሊጋ ፡ ቦንደስ ሊጋውን በ21 ጨዋታዎች 46 ነጥብ በማስመዝገብ የሚመራው ቦርስያ ዶርትመንድ ነው፡፡ ባየር ሙኒክ በ44፤ ቦርስያ ሞንቼግላድባክ በ43 ሻልካ 04 በ41 ነጥብ እስከ አራተኛ ሰፍረዋል፡፡ አራቱ ክለቦች ባንድ ጨዋታ ውጤት ሊተራመስ በሚችል ደረጃ የሻምፒዮናነቱን ጉዞ ተናንቀውበታል፡፡ ቦንደስ ሊጋው 22ኛ ሳምንት ላይ ሲደርስ በተደረጉ 189 ጨዋታዎች 530 ግቦች ተቆጥረውበታል፡፡ በየጨዋታው በአማካይ 2.8 ጎሎች እየገባ ነው፡፡ የኮከብ ግብ አግቢነቱን ፉክክር የባየር ሙኒኩ ማርዮ ጎሜዝ በ18 ጎሎች ይመራዋል፡፡ የሻልካ 04 አጥቂ ክላስ ያን ሁንትላር በ15 ጎሎች ይከተላል፡፡

ቦንደስ ሊጋው እንደላሊጋውና እንደ ፕሪሚዬር ሊጉ ብዙ ትኩረት ማግኘት ባይችልም ባለው የተረጋጋ የገንዘብ አስተዳደርና በስታድዬም የተመልካች ብዛት ደምቆ ሂደቱን ቀጥሏል፡፡ በቦንደስ ሊጋው የዋንጫ ፉክክር አራት ክለቦች ተስፋ ቢኖራቸውም ዋናው ትንቅንቅ ግን በቦርስያ ዶርትመንድና በባየር ሙኒክ መካከል ነው፡፡80ኛው የጣሊያን ሴሪኤ ፡ ሴሪኤውን በ23 ሳምንት ጨዋታዎች 47 ነጥብ አስመዝግቦ በውድድር ዘመኑ ለመጀመርያ ጊዜ ባለፈው ሳምንት መምራት የጀመረው ኤሲ ሚላን ነው፡፡ ጁቬንትስ ሁለት ቀሪ ጨዋታ እያለው በ21 ጨዋታዎች 45 ነጥብ ይዞ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል፡፡ ላዚዮ በ42 ነጥብ እንዲሁም ኡዲኔዜ በ41 ነጥብ በ3ኛ 4ኛ ደረጃዎች ይከተላሉ፡፡ ኢንተር ሚላን በ23 ጨዋታዎች 36 ነጥብ በመያዝ  በ5ኛ ደረጃ ርቆ ተቀምጧል፡፡ እስከ 23ኛ ሳምንት በተደረጉት 221 ጨዋታዎች 559 ጎሎች ከመረብ ተዋህደዋል፡፡

ሴሪኤው በአማካይ 2.53 ጎሎች እየተመዘገበበት ይገኛል፡፡ ኮከብ ግብ አግቢነቱን ልማደኛው የኡዲኒዜ ግብ አዳኝ አንቶኒዮ ዲናታሊ በ17 ጎሎች ይመራል፡፡ የኤሲ ሚላኑ ዝላታን ኢብራሞቪች በ15 ጎሎች እየተከተለው ነው፡፡

የጣሊያን ሴሪኤ ለዋንጫው ክብር ያፋጠጠው ታሪካዊ ተቀናቃኞች የሆኑትን ኤሲሚላንና ጁቬንትስን ነው፡፡ ሁለቱ ክለቦች ከ2 ሳምንት በኋላ በሴሪኤው ጨዋታ ሲገናኙ የዘንድሮ ሻምፒዮናነት ወየትኛው ክለብ እንደሚያጋድል የሚለይ ይሆናል፡፡በ74ኛው የፈረንሳይ ሊግ 1፡ በተጫወተባቸው 23 ግጥሚያዎች 50 ነጥብ ያለው ፓሪስ ሴንትዠርመን ሊግ 1ን እየመራ ሲሆን  በ49 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ይዞ የሚከተለው ሞንትፕሌር ነው፡፡ እስከ 23ኛ ሳምንት 226 ጨዋታዎች ተደርገው 570 ጎሎች የተመዘገቡበት የፈረንሳዩ ሊግ 1 በየጨዋታ በአማካይ 2.52 ጎሎች እየተቆጠሩበት ይገኛል፡፡ የሊጉን ኮከብ ግብ አግቢነት የሚመራው የሞንትፕሌየሩ አጥቂ ኦሊቭር ጊር ውድ በ16 ጎሎች ነው፡፡

 

 

Read 3485 times Last modified on Saturday, 18 February 2012 10:17