Print this page
Monday, 11 January 2016 11:12

“የመንግሥትና የግል ሌቦች” ይበልጥ፤ ተግተዋል!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(19 votes)

     የህዝብና የመንግስት ሃብት እንደሆነ በሚነገርለት ኢቢሲ፤ ሰሞኑን የቀረበው ዘገባ አስደንጋጭ ነው፡፡ (አገሬ ወዴት እየሄደች እንደሆነ ሹክ ለሚለኝ ወሮታውን እከፍላለሁ!) መቼም “ጃካራንዳ” ምናምን ሲባል ሳትሰሙ አትቀሩም ብዬ እገምታለሁ (የመገመት መብት ተከብሯል ብዬ ነው!) “ጃካራንዳ” ምን ይሁን? አትሉም? አዎ… “ጃካራንዳ” በአትክልትና ፍራፍሬ እርሻ ላይ የተሰማራ አክሲዮን ማህበር ነው። እናላችሁ… በሺዎች የሚገመቱ ሰዎች ላባቸውን ጠብ አድርገው በቋጠሯት ጥሪት እንደየአቅማቸው አክሲዮን በመግዛት የ“ጃካራንዳ” ባለድርሻ ሆኑ፡፡ (የህዝብ ሃብት ማለት ይሄ ነው!)
ኢቢሲ እንደዘገበው ታዲያ፤ ከ3 ወይም ከ4 ዓመት በፊት በ20 ሚ. ብር ካፒታል ነበር  ማህበሩ የተቋቋመው፡፡ በእርግጥ ተቋቋመ ከተባለ በኋላ ስለ ሥራ እንቅስቃሴው ብዙም ሲነገር አልሰማም። (የአክስዮኖች ባህርይ ነው እንዴ?) ከዚህ ሁሉ በኋላ… ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ የ“ጃካራንዳ”ን አስደንጋጭ ዜና ኢቢሲ አረዳን። (“መርዶ ነጋሪ” አልወጣኝም!…) በ20ሚ. ብር የተቋቋመው ማህበሩ፤ በቀድሞ የዳይሬክተሮች ቦርድ ተመዝብሮ፣ በባንክ ሂሳቡ ውስጥ 300 ብር ብቻ እንደተገኘም ተገልጿልም፡፡ (በአስማት መመዝበር ተጀመረ እንዴ?!)
በምዝበራው ዜና የደነገጥኩት ሳያንሰኝ ሌላ አፍ የሚያሲዝ መረጃ ደግሞ ከጓደኞቼ ሰማሁ፡፡ የአክስዮን ማህበራት ጉዳይ ይመለከተዋል የተባለው የመንግስት ተቋም፤ የማህበሩን ገንዘብ የመዘበረውን የቀድሞ ዳይሬክተሮች ቦርድ ለህግ እንዳያቀርብ አባላቱ በህጋዊ መንገድ የተመረጡ አለመሆናቸው እንቅፋት ሆኖብኛል ብሏል አሉ፡፡ በቃ … ይኸው ነው?
እኔ የምለው … በህጋዊ መንገድ ያልተመረጠ የዳይሬክተሮች ቦርድ፣ ገንዘብ ዘርፎ ማምለጥ ይችላል ማለት ነው? (ይሄ እኮ ለግል ሌቦች መንገድ መክፈት ነው!)
በዚሁ ሳምንት የደረሰኝ ሌላው መረጃ ደግሞ ከራስ ጋር የሚያስወራ ነው፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው ዋና ምንጩ ከየት እንደሆነ ያልታወቀ 800 ኪ.ግ የአሳማ ሥጋ በህገ-ወጥ መንገድ አዲስ አበባ ሊገባ ሲል አቃቂ ኬላ ላይ ይያዛል፡፡ ከዚያም ይወገድ ተብሎ ወደ አዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ይላካል - ከእነ መኪናው፡፡ በነጋታው ግን ቄራ ግቢ ውስጥ የተገኘው መኪናው ብቻ ነበር፡፡ ስጋው የገባበት አልታወቀም ተብሏል፡፡ ይታያችሁ… 800 ኪ.ግ የዓሳማ ሥጋ በአንድ ሌሊት ተሰወረ፡፡
እስካሁንም እምጥ ይግባ ስምጥ የታወቀ ነገር የለም፡፡ (“የመንግሥትና የግል ሌቦች” የተሳተፉበት ድራማ ይመስላል!) በነገራችን ላይ “የመንግስትና የግል ሌቦች” የሚለው አጠራር የቀድሞውን ጠ/ሚኒስትር (ነፍሳቸውን ይማረውና) ያስታውሰኛል። ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁት ከእሳቸው አንደበት ነው። አሁን ግን የሌቦቹ ስፋታቸውና ግዝፈታቸው፣ ቁመታቸውና ወርዳቸው… በእጅጉ ስለጨመረ… ስሙ የሚበቃቸው አይመስለኝም፡፡ (“ስሙ በዝቶበት ሞተ” የሚል ታሪክ አውቃለሁ!) እስቲ ይታያችሁ… ሞባይል የሰረቀና 20ሚ. ብር ጠራርጐ የበላ በምን ሚዛን እኩል “ሌባ” ይባላል? (እነሱም እኮ “አይመጥነንም” ብለው ሊከሱ ይችላሉ!)
አሁን ደግሞ በቀጥታ ወደ አማካሪ እሻገር። በነገራችን ላይ በ8 ዓመት የፕሬዚዳንትነት የስልጣን ዘመናቸው እንጦሮጦስ ከተዋል በሚል በሪፐብሊካን እጩ ተፎካካሪዎች የሚብጠለጠሉት ባራክ ኦባማ፤ ሰሞኑን በአንድ ለየት ያለ ነገር የዓለም አቀፉን ሚዲያ ትኩረት ስበዋል፡፡ ይሄ ለየት ያለ ነገር ምን መሰላችሁ? ለመጀመሪያ ጊዜ በአደባባይ፣ እንባ አውጥተው ማልቀሳቸው ነው፡፡ ሁሉም የቴሌቭዥን ጣቢያዎች ካሜራዎችም ፊታቸው ተደግነው ሲቀርፁ ውለዋል - እንባቸውን!  (የፀጋዬ ገ/መድህንን “ወንድ የሚያለቅሰው ብቻውን ነው” የሚል ግጥም አያውቁትም!) ፕሬዚዳንቱ የዛሬ 3 ዓመት በጅምላ ስለተጨፈጨፉት የሳንዲ ሁክ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት የ1ኛ ክፍል ተማሪዎች መናገር ሲጀምሩ ነበር ስሜት ፈንቅሏቸው ያለቀሱት፡፡
የቀድሞ የአላስካ ገዢ ሳራ ፖሊን የኦባማን ማልቀስ በተመለከተ በሰጠችው አስተያየት፤ “እሱ ምኑ ተነክቶ ያለቅሳል፤ እኛ እናልቅስ እንጂ” ሲሉ በአሜሪካ ለተፈጠረው ውንብድና እና ሥርዓት አልባነት ኦባማን ተጠያቂ አድርገዋል። (ለቅሶአቸውንም “የአዞ እንባ ነው” ብለውታል!) “ኦባማ አንድ ጊዜ ነው ያነባው፤ የቀረነው ግን ለአገራችንና ለሰለጠነው ዓለም ማንባታችንን እንቀጥላለን” ብለዋል - ሳራ ፓሊን፡፡ (“ዕድሜ ለኦባማ” ማለታቸው ነው!)
በነገራችን ላይ ኦባማ በአሜሪካውያን መሳሪያ የመታጠቅ መብት ላይ ቁጥጥር እንዲደረግ የጀመሩት እንቅስቃሴ ያሰቡትን ያህል አልተሳካላቸውም። ዘንድሮ በሚካሄደው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሪፐብሊካንን በመወከል የሚወዳደሩት ቢሊየነሩ ዶናልድ ትረምፕ፤ የኦባማን የመሳሪያ ቁጥጥር ደንብ ከሚቃወሙት ወገኖች ቀንደኛው ቢሆኑም እንደ ሳራ ፖሊን ለቅሶአቸውን የአዞ እንባ ለማለት አልደፈሩም። “የኦባማ እንባ ከልብ የመነጨ ይመስለኛል” ብለዋል - ትረምፕ፡፡ የዲሞክራት ፓርቲ እጩ ተወዳዳሪዋ ሂላሪ ክሊንተን ላይ ግን ትረምፕ ጨከን ያሉ ይመስላል (ዘንድሮ ማን በሂላሪ ላይ ያልጨከነ አለ?)
“ሂላሪ ክሊንተን በመሳሪያ ቁጥጥር ጉዳይ ላይ ከኦባማም ሳትብስ አትቀርም” ያሉት የሪል እስቴት ከበርቴው ትረምፕ፤ “እውነቱን ለመናገር ሂላሪ የእያንዳንዱን ሰው ጠብመንጃ ለመንጠቅ ትፈልጋለች” ብለዋል - ሰሞኑን ለፎክስ ኒውስ በሰጡት አስተያየት፡፡ እኔ የምላችሁ … በሩቅም ሆነ በቅርብ ታሪካችን ለህዝባቸው ያለቀሱ ወይም ያነቡ መሪዎች ነበሩን እንዴ? (“ያስለቅሱናል እንጂ አያለቅሱልንም” ብላችሁ ሆድ እንዳታስብሱኝ!)
ሰሞኑን ከኢንተርኔት መረጃ ስበረብር… አንድ አስገራሚ ያልተዘመረላቸው የአፍሪካ ጀግና ማግኘቴን ስነግራችሁ በታላቅ ደስታ ነው፡፡ ሰውየው ማን መሰሏችሁ? የአሁኑ የሴኔጋል ፕሬዚዳንት ማኪ ሳል ናቸው፡፡ እኚህ መሪ ባለፈው ዓመት ማንም ሳይጎተጉታቸው በራሳቸው ተነሳሽነት ያደረጉት ነገር በአፍሪካ ላይ ከእነ አካቴው ተስፋ እንዳንቆርጥ የሚያነቃቃ ነው፡፡ (እነ ሙጋቤን እያየንማ ተስፋችን ሊበራ አይችልም!)
እናላችሁ … ፕሬዚዳንቱ የአገር ውስጥና የውጭ ሚዲያዎችን ሰብስበው፣ ህገ መንግስቱ ከሚፈቅድላቸው 7 ዓመት የሥልጣን ዘመን ሁለቱ እንዲቀነስ ሃሳብ አቅርበዋል! (እልልል … በቅምጤ … አትሉም!) እንዲህ ያለው ተዓምር … እንዲህ ያለው ብስራት … በአፍሪካ ተሰምቶ አያውቅም!! ብዙዎቹ የአፍሪካ መሪዎች ሥልጣንን የሙጥኝ ብሎ በመያዝ ክፉኛ በሚነቀፉበት በዚህ ዘመን ይሄን ድፍረት መስማት መንፈስን ያድሳል፤ በተስፋ ይሞላል፤ ሌሎች የአፍሪካ ጀግኖችን አስሶ ለማግኘትም ያስመኛል፡፡
ይታያችሁ … እንደ እነ ቤኒን፣ ሩዋንዳ፣ ቡሩንዲና ኮንጎ ብራዛቪል ጨምሮ ሌሎችም መሪዎቻቸው ለ3ኛ ዙር በስልጣን ላይ እንዲዘልቁ ለማድረግ የህገ መንግስት አንቀፆች እስከመለወጥ (መሰረዝ፣ መደለዝ፣ ኤዲት ማድረግ፣ መቅደድ፣ አዲስ ማውጣት … ወዘተ) መድረሳቸውን አሳምረን እናውቃለን፡፡ የሴኔጋሉ ፕሬዚዳንት ግን … ጭራሽ ህገ መንግስቱ ከፈቀደላቸው ሥልጣን ላይ ቆንጥረው በመመለስ የማይታመን የጀግንነት ታሪክ ሰርተዋል - እንኳን ለአፍሪካ ለምዕራባውያንም ጭምር!!
“የሥልጣን ጊዜዬን እቀንሳለሁ ያለ ፕሬዚዳንት ሰምታችሁ ታውቃላችሁ? እኔ ግን አደርገዋለሁ” ያሉት እኚህ መሪ፤ ለአፍሪካም ጭምር አርአያ መሆን እንደምንችል መረዳት አለብን፤ ሥልጣን በራሱ ግብ አይደለም” ብለዋል፤ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፡፡ (“አፌ ቁርጥ ይበልልዎ” ማለት እኚህን ነው!)
በ2012 ዓ.ም (እኤአ) በፕሬዚዳንትነት የተመረጡት ሚኪ ሳል፤ ከሥልጣን ዘመናቸው ላይ ሁለት ዓመት እንዲቀነስ ስለጠየቁ የአገሪቱ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ከሁለት ዓመት በኋላ ሳይሆን በ2017 ዓ.ም እንዲደረግ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡ በህገ - መንግስቱ የተፈቀደውም ለሁለት ዙር የሥልጣን ዘመን (term) የመወዳደር መብት ባለበት እንዲፀና እፈልጋለሁ ብሏል። አያችሁልኝ … አንዳንዴ በአንድ መሪ ባለራዕይ መሆን ብቻ፣ ሙሉ የአገር ታሪክ ሊለወጥ ይችላል፡፡ (የአገር ታሪክ የህዝብ ታሪክ ነው!!)
ከሴኔጋል ስንወጣ ደግሞ ሌላ ታሪክ እናገኛለን፡፡ የተለመደውን የአፍሪካ አምባገነኖች አሰቃቂ ታሪክ፡፡ በአልጀርያ፣ አንጎላ፣ ቻድ፣ ጅቡቲና ኡጋንዳ በመሳሰሉት የአፍሪካ አገራት የአምባገነን መሪዎችን የሥልጣን ዘመን ለማራዘም … ህግና ህገ መንግስት ሲለውጥ ኖሯል፡፡ (አሳፋሪ ታሪክ ነው!!)
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎስ ምን ተከሰተ? አገሪቷን ለ14 ዓመታት የገዟት የፕሬዚዳንት ጆሴፍ ካቢላ የሥልጣን ዘመን እንዲራዘም ለማስረዘም የወጣውን ማሻሻያ በመቃወም አደባባይ የወጡ ከ40 በላይ ዜጎች ተገደሉ፡፡ (40 ዓመት ለመግዛት 40 ሰው መግደል!?)
ያልታደለችው አፍሪካችን… ይሄን የመሳሰለ የጨለማና የሥልጣን ጥመኝነት ታሪክ ሞልቶ የተረፋት ናት፡፡ ለዚህ ነው የሴኔጋሉ ፕሬዚዳንት ያልተለመደ የሥልጣን ይቀነስልኝ ጥያቄ ብርቅና ድንቅ የሚሆንብን፡፡ በእርግጥም እሳቸው … ለአፍሪካ ያልተዘመረላቸው ጀግና ናቸው!! (ይኼኔ እኮ እነ ሙሴቪኒ ጥርስ ነክሰውባቸዋል!)
የሴኔጋሉ መሪ ማኪ ሳል፣ በፈፀሙት ትውልድ ተሻጋሪ ተግባር እነ ሙጋቤ፣ ኢሳያስ አፈወርቂና ካጋሜ ፈፅሞ… ሊደሰቱ እንደማይችሉ ሳይታለም የተፈታ ነው። (የኢህአዴግን አላውቅም!) እንደውም ሁለት አምባገነን መሪዎች አንድ ላይ ሆነው ስለእኚህ መሪ ወሬ ቢጀምሩ እንዲህ የሚሉ ይመስለኛል፡-
አምባገነን 1፡- “ወገኛ በለው፤ ይሄኔ ሃኪም ከሁለት ዓመት በላይ አትኖርም ብሎት ነው!” (ሁሉም እንደነሱ በሽተኛ ይመስላቸዋል!)
አምባገነን 2፡- “ጀብዱ ሰራሁ ብሎ ስልጣን ሲለቅ ወህኒ ቤት በወረወሩልኝ!”
(አምባገነን መጨረሻው እስር መሆኑን ያውቁታል!)

Read 7569 times