Monday, 11 January 2016 12:18

የህይወት ክህሎት ስልጠና እየተሰጠ ነው

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(7 votes)

    ቅን ጤናማና የበለፀገ ትውልድን ማፍራት አላማው ያደረገውና በ2024 ኢትዮጵያን በዓለም ቁጥር አንድ አገር ማድረግ የሚል ራዕይን ይዞ የሚንቀሳቀሰው ቅን ቡድን በየሳምንቱ የህይወት ክህሎት ስልጠናን በመስጠት ላይ ነው፡፡
ከቡድኑ መሥራችና መሪ አባላት መካከል አንዱ የሆነው አቶ ሲሳይ ምህረት ለአዲስ አድማስ እንደተናገረው ቡድኑ የወጣቱን አዕምሮ በመለወጥ ለዕድገትና ለተሻለ ህይወት ማነሳሳት ላይ ትኩረት አድርጐ ይሰራል፡፡ “ዓላማችን ቅን ጤናማና የበለፀገ ትውልድ በማፍራት ኢትዮጵያን በ2024 ቁጥር አንድ አገር ማድረግ ነው፡፡ አገር የምትለወጠው ደግሞ አመለካከት ሲለወጥ ነው” ያሉት አቶ ሲሳይ ቡድኑ ትኩረት አድርጐ የሚሰራው በጭንቅላት ልማት ላይ መሆኑንና ብቁ በሆኑ አሰልጣኞች በየሳምንቱ የህይወት ክህሎት ስልጠናው በዓለም ሲኒማ እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡
የቡድኑ አባላት በሙሉ ቡድኑን በነፃ ለማገልገልና ለቡድኑ ዓላማ ተግባራዊነት ለመሥራት በፈቃደኝነት የገቡ መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ ሲሳይ ሁሉም የቡድኑ አባላት የየራሳቸው ገቢ ያላቸውና ቡድኑን በነፃ ለማገልገል ራሳቸውን የሰጡ ሰዎች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በቡድኑ ውስጥ አሰልጣኝ ለመሆን ከሚያስፈልጉ መስፈርቶች መካከል አንዱና ዋንኛው ግለሰቡ ራሱ አርሃያ ለመሆን በሚያስችል ደረጃ መለወጥና ወርሃዊ ገቢው ከ50ሺህ ብር በላይ መሆን እንደሚገባውም አቶ ሲሳይ ተናግረዋል፡፡
ከማንኛውም ፖለቲካ፣ ሃይማኖትና ብሔር ነፃ ሆኖ የሚንቀሳቀሰው ይኸው ቡድን ላለፉት አንድ ዓመት ከስምንት ወራት በዓለም ሲኒማ በየሳምንቱ ስልጠናን የሚሰጥ ሲሆን እስከአሁን 18ሺህ ለሚሆኑ ሰዎች የህይወት ክህሎት ስልጠናዎችን መስጠቱን አቶ ሲሳይ ተናግረዋል፡፡ በድሬዳዋ፣ መቀሌና አዳማ ላይ ተመሳሳይ ስልጠናዎች በቡድኑ እየተሰጡ ሲሆን ስልጠናውን በክልሎች ሁሉ ለማስፋፋት በእንቅስቃሴ ላይ መሆናቸውንና በቅርቡም የቴሌቭዥን ፕሮግራም ለመጀመር ዝግጅት በማደረግ ላይ መሆናቸውን አቶ ሲሳይ ተናግረዋል፡፡

Read 6712 times