Saturday, 16 January 2016 10:32

የእግር ህመምና መነሻ ምክንያቶቹ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(49 votes)

      እግራችን የሰውነታችን ጠቅላላ ክብደት ተሸካሚ በመሆኑ ሁልጊዜም ጫና ይበዛበታል።  በተለይም ከፍተኛ የሰውነት ክብደት ያላቸው ሰዎች ክብደታቸው በመገጣጠሚያዎቻቸው ላይ በሚፈጥረው ተደጋጋሚ ጫና ምክንያት የነርቭ ሥርዓታቸው ስለሚዛባ የእግሮቻቸው ጤና ለጉዳት ይዳረጋል፡፡ በዚህ ወቅትም የእግር መደንዘዝና የማቃጠል ስሜት ይፈጠርባቸዋል፡፡ ቀስ እያለም ችግሩ ወደ ከፋ ደረጃ ላይ ደርሶ እንደ ቀድሟቸው ለመራመድ ይሳናቸዋል፡፡ እንዲህ ያለው ሁኔታ በስፋት የሚታየው ዕድሜያቸው በገፋ፣ ከመጠን ያለፈ የሰውነት ክብደት ባላቸውና ምንም ዓይነት የሰውነት እንቅስቃሴ በማያደርጉ ሰዎች ላይ ነው፡፡
የእግር ህመም በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰት ሲሆን በዕድሜ የገፉ ወንዶች ከሴቶች የበለጠ ለእግር ህመም የተጋለጡ መሆናቸውን ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ ለበርካታ ሰዎች የእግር ህመም መነሻ ምክንያት ሆነው ከሚጠቀሱት በሽታዎች መካከል ዋንኛው የሪህ በሽታ መሆኑን የሚገልፀው የአለም ጤና ድርጅት መረጃ፤35% በመቶ ለሚሆነው የእግር ህመም መነሻ ምክንያት እንደሆነ ይገልፃል፡፡ ካልሲየም የተባለው ንጥረ ነገር በሰውነታችን ውስጥ በመከማቸት ካልሲየም ፎስፌት ወደተባለ ጠንካራ ንጥረ ነገር ተለውጦ፣ በመገጣጠሚያዎቻችን አካባቢ በብዛት በመጠራቀሙ ሳቢያ የሚከሰተው የሪህ በሽታ፤ በሴቶችም ሆነ በወንዶች ላይ የሚታይ ቢሆንም ወንዶች በበሽታው የበለጠ እንደሚጠቁና በወጣትነት ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሰዎችንም በስፋት በማጥቃት ለእግር ህመም እንደሚዳርግ መረጃው ይጠቁማል፡፡ በቀጣይነት ለእግር ህመም መነሻ ተብሎ የሚጠቀሰው ደግሞ የኩላሊት በሽታ ነው፡፡  
በኩላሊቶቻችን ላይ በሚደርሱ የጤና ችግሮች ሳቢያ ኩላሊት መደበኛ ተግቫሩን ማከናወን ሲሳነው ሽንት ከሰውነታችን ውስጥ መወገድ ያቅተዋል፡፡ በዚህ ወቅትም በእግራችንና በመላው ሰውነታችን ላይ እብጠት ይከስትና እንደ ልባችን መራመድ ያዳግተናል፡፡ በነርቭ ስርዓችን ላይ መሰናክል የሚፈጥሩ ነገሮች በሚያጋጥሙን ጊዜም ችግሩ በእግሮቻችን ላይ መዛልን በማስከተል እንደ ልባችን ለመንቀሳቀስ እንዳንችል ያደርገናል፡፡ ይህም በአብዛኛው የሚፈጠረው በአከርካሪያችን ላይ የሚያልፈው ነርቭ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ሲጐዳ ነው፡፡ ለነርቭ ሥርዓታችን መዛባት በምክንያትነት ከሚጠቀሱ  ችግሮች መካከል የደም ቧንቧ መታወክ፣ የዲስክ መንሸራተት (በአከርካሪያችን ንብርብር ላይ የሚገኘውና ዲስክ በመባል የሚጠራው የአካላችን ክፍል ትክክለኛ ቦታውን ለቆ ነርቫችንን ሲጫነው) እና በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰቱ አደጋዎች እንዲሁም ኢንፌክሽኖች ይገኙበታል፡፡ አብዛኛውን የታዳጊ አገራት ህዝቦች የሚያጠቃው ኢንፌክሽን፣ የአከርካሪ አጥንት ቲቢ ሲሆን ይህ የጤና ችግር በአከርካሪ አጥንታችን ላይ ሲከሰት ሕክምና በፍጥነት ማግኘት ይገባል፡፡ ይህ ሳይሆን ከቀረ ግን አንዱን አሊያም ሁለቱንም እግሮቻችንን ሊያዝላቸው አሊያም ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጪ ሊያደርጋቸው ይችላል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በአከርካሪ አጥንታችን ንብርብሮች ላይ በሚፈጠሩ እጢዎች ሳቢያ በነርቮቻችን ላይ ጫናና የሥራ መስተጓጐል ሲፈጠር ሂደቱ ከተስተጓጐለበት የነርቫችን ክፍል በታች ያለው እግራችን ጤናው በእጅጉ ይቃወሳል፡፡
በጭንቅላታችን ውስጥ የሚፈጠሩ እጢዎች፣ኢንፌክሽኖችና ፈንገሶች እንዲሁም በጭንቅላት ውስጥ የፈሳሽ መጠን መብዛትና የደም ዝውውር መዛባት፣ የነርቭ ሥርዓታችንን ጤና በማቃወስ በእግሮቻችን ላይ የጤና ችግርን ያስከትላሉ፡፡ የእግሮቻችን ጤና ከደም ዝውውርና ከነርቭ ሥርዓት መታወክ እንዲሁም ኩላሊትንና ልብን ጨምሮ ከሌሎች የውስጥ ደዌ በሽታዎችና ከአደጋ ጋር በተያያዙ ምክንያቶች ሊታወክና እንደ ልብ ከመንቀሳቀስ ሊያግደን ይችላል፡፡
የእግራችን ጤና በታወከ ጊዜ በተለያዩ መንገዶች በሚሰጥ ህክምና ልንድን እንችላለን፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግን መዳን የማይችሉና ታማሚውን እስከ ዕድሜ ፍፃሜው ድረስ ህመምተኛ የሚያደርጉ የእግር ህመም አይነቶች አሉ፡፡ ለእግር ህመም የሚሰጡት የህክምና ዓይነቶች ከቀላል የነርቭ ህክምና እስከ ቀዶ ህክምና ድረስ የሚዘልቁ ሲሆን በደም ዝውውር መዘጋት ሳቢያ የተከሰተ የእግር ህመም የተዘጋውን የደም ዝውውር በመክፈት የታማሚውን ጤና ወደነበረበት ለመመለስ የሚያስችል የህክምና ዘዴ አለ፡፡
የእግር ህመም ከመከሰቱ በፊት በእነዚህ መንገዶች መከላከል እንችላለን፡፡
ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን መከተል፣
የሰውነት ክብደትን መቀነስ ቀለል ያሉና ምቾት የሚሰጡ ጫማዎችን መጠቀም፣ የኩላሊት የጉበት፣ የልብና የደም ግፊት በሽታዎችን በወቅቱ መታከም ዋንኞቹ የእግራችንን ጤና መጠበቂያ መንገዶች ናቸው፡፡

Read 36507 times