Saturday, 18 February 2012 11:06

የእስልምና ጉዳዮች ም/ቤት ችግር ተባብሷል

Written by  ሰላም ገረመው
Rate this item
(1 Vote)

ህዝበ ሙስሊሙን ያልወከለ  አመራር ተቀምጧል - አህመዲን ጀማል

ይህንን ጥያቄ የሚያነሱት ፀረ - ዲሞክራሲዎች ናቸው - ሀጂ ሰይድ አስማረ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ም/ቤት የቅርስ ጥበቃና ዶክመንቴሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊበም/ቤቱ ላይ ቅሬታ ያቀረቡ ሠዎችን አክራሪዎችና ህገወጦች ናቸው ለማለት ያበቃችሁ ምንድነው?አንድ አካል በህጋዊ መንገድ ካልተንቀሳቀሠ ህገወጥ ነው እንለዋለን፡፡ ህጋዊ በህጋዊ ማዕቀፉ የህግ ፈቃድ ኖሮት፤ ከህዝቡ ትክክለኛ ውክልና አግኝቶ የሚንቀሳቀስ ሲሆን ብቻ ነው ህጋዊ የምንለው፡፡ ከዚህ ውጪ ካለፈ ግን ህገወጥ ድርጊት ነው ብለን ነው የምናየው፡፡

እነዚህ ሠዎች ም/ቤቱን የመቃወም መብት የላቸውም?

ማንኛውም ሙስሊም፤ በምክር ቤቱ ውስጥ ችግር ካለ የራሱ ተቋም ስለሆነ መቃወም ይችላል፡፡ በቅድሚያ ግን የእኔ ተቋም ነው ብሎ ማመን አለበት፡፡ ህጋዊ ናቸው ለመባል ጥያቄያቸውን ተደራጅተው ነው ማቅረብ ያለባቸው? በግለሠብ ደረጃ ጥያቄ ማቅረብ አይቻልም?

ጥያቄና ተቃውሞ እናቀርባለን ብለው የሚመጡ ሰዎች፣ ተወክለናል ይላሉ፡፡ ግን በትክክል ሙስሊሙ ወክሏቸዋል ወይ? ፔቲሽን አስፈርመናል ይላሉ፡፡ ግን ተፈራረሙ የተባለው ነገር ህጋዊ ነው ወይ? ማንም ተነስቶ የአንድ ሚሊዮን ህዝብ ፒቲሽን ሊያመጣ ይችላል፡፡ ነገር ግን ህጋዊ መሆን አለበት፡፡ ህጋዊውን መንገድ መከተል ይገባዋል፡፡ እንግዲህ ሰዎቹ ከመስጊድ እንደጀመሩ ይናገራሉ፡፡ ትክክለኛው ህጋዊ ሂደት፤ የመስጂድ ጀመአ መጀመሪያ ኮሚቴ ያቋቁማል፡፡ ከዛ ለወረዳ፤ ቀጥሎ ለክልል፣ በመጨረሻ ለፌደራል እያለ ሰንሰለቱን ጠብቆ ይጓዛል፡፡ ይሔ ፒቲሽን አስፈርሜያለሁ የሚለው አካል ከየትኛው ነው የጀመረው? በየትኛው መስጂድ ነው የህዝብ ውክልና የተሰጣቸው? ህገ ወጥ ናቸው የምንለውም መነሻቸዉ ሌላ ነገር ስለሆነ ነው፡፡ የአወለያ ት/ቤትን የቅስቀሳ መነሻ አደረጉት፡፡ የአወሊያ የተማሪዎች ጥያቄ ከተመለሠ በኋላ፤ ቅስቀሳ ሲያካሂዱ የነበሩት ሰዎች የጥያቄውን መልክ ቀይረው ሔዱ፡፡ እንቅስቃሴያቸውና ጥያቄያቸው ሙስሊሙን የሚመለከት ከሆነ ወደ ሙስሊሙ ተቋም ነው መምጣት ያለባቸው፡፡ የእኛ አስተያየት ሙስሊሙ መጀመሪያም ይሠራልኛል ብሎ ይህን ተቋም አቋቁሟል፡፡ ችግር ካለበት ወደዚሁ ተቋም ነበር ጥያቄው የሚመጣው፡፡ እነሱ ወደዚህ አልመጡም፡፡ የተዘበራረቀ ጥያቄ ነው የሚያቀርቡት፡፡  የተለየ ጥያቄያቸው ምን እንደሆነ አይታወቅም፡፡

የመጨረሻ የም/ቤቱ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የተካሔደው መቼ ነው?

በ1998 ዓ.ም ለቀጣይ አምስት አመታት የሚሠራ ሠው ተመርጧል፡፡ አሁን በዚህ አመት የአምስት አመት የስራ ዘመን ስለተጠናቀቀ ሌላ ምርጫ ለማካሔድ በጠቅላላ  ጉባኤው ወቅት የምርጫ ማንዋል ተሠርቶ ቀርቦ ነበር፡፡ ሆኖም በበጀትና በተለያዩ ምክንያት ምርጫው እንዲዘገይ ጠቅላላ ጉባኤው ወስኗል፡፡ የጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ ነው የሚገዛን፡፡

በ1998 ዓ.ም የተካሔደው ምርጫ ህብረተሠቡን ያሳተፈ ነበር? አሁን ያሉትን አመራሮች ማን ነው የመረጣቸው?

ህብረተሠቡ ነው የመረጣቸው፡፡ እዚህ በፌደራል ደረጃ የጠቅላላ ጉባኤ ስራ  አስፈፃሚዎች የክልል ተወካዮች ናቸው፡፡ ድሬዳዋንና አዲስ አበባን ጨምሮ በዘጠኝ ክልሎች ከወረዳ ጀምሮ የምርጫ ስራ ተከናውኗል፡፡ ከየወረዳው የተመረጡ ወደ ክልል ይወከላሉ፡፡ ከየክልሉ የተመረጡ ወደ ፌደራል ደረጃ ይወክላሉ፡፡ በ2001 ዓ.ም የነሼህ ኤልያስ ኮሚቴ ሲወገድ፣ የምርጫ ውክልና ይዘው የመጡ ናቸው አሁን በስራ አስፈፃሚነት እየሰሩ ያሉት፡፡ እነዚሁ ሠዎች ሙስሊሙን የማይወክሉ ከሆነ፤ የክልሉ ህዝብ እኛ አልመረጥናቸውም አልወከልናቸውም ብሎ ማንሳት ይችላል፡፡ ይሔ ጥያቄ ግን በየትኛውም ክልል ከሚገኝ ሙስሊም እስካሁን አልቀረበም፡፡

ጅማና አዳማ ላይ የሚገኙ ከ60 በላይ መስጂዶች ስራ አስፈፃሚዎች አይወክሉንም እንዳሉ ሲነገር ቆይቷል፡፡ ም/ቤቱም አያዘንም ብለዋል፡፡ ይሔ ተቃውሞ አይደለም?

በእኛ ስር አልተዳደርም ያሉ መስጂዶች የሉም፡፡ እኛ እስላማዊ ተግባርን ለማጠናከር በሚል ጅማ ላይ ውይይት ስናደርግ አንዳንድ አለመግባባቶች ነበሩ፡፡ እሱ ደግሞ በእስላማዊ አስተምሮ እንዲፈታ በሚል የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ ስለዚህ ያፈነገጡ መስጂዶች አሉ የሚባለው ውሸት ነው፡፡

ናዝሬትና ጅማ፤ በኦሮምያ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ውስጥ ናቸው፡፡ እነሱንም ማነጋገር ይቻላል፡፡

ከዞን የጀመረው ቅሬታ ወደ እናንተ እንዳይደርስ ጣልቃ ለመግባት የሠራችሁት ነገር አለ?

እኛ ማንንም መስጂድ ማጣት አንፈልግም፡፡ በአስተዳደር ደረጃ አንድም ሠው መበደል የለበትም፡፡ በሁለቱ ዞኖች ችግር ሲኖር እኛን ይጐዳናል፡፡ ነገር ግን ችግሮቹን ለመፍታትም ቢሆን፤ ከክልል የእስልምና ጉዳይ ምክር ቤት ጋር ነው የምንሠራው፡፡  ስለዚህ አሁን የተባሉት ችግሮች ወደ እኛ አልመጡም፡፡ እኛ ጋ ቢመጡና መፍትሔ ቢያጡ ኖሮ እንደ ችግር መናገር ይቻል ነበር፡፡

አሁን ያለው መተዳደሪያ ደንብ ሲወጣ የሙስሊሙ ማህበረሠብ ተወያይቶበታል?

በ1998 ዓ.ም ምርጫ ላይ የወጣ ደንብ አለ፡፡ በ2001 ዓ.ም ደግሞ ሀረር ላይ ተሻሽሏል፡፡ በየአመቱ በየጉባኤው ላይ ደንቦች ይሻሻላሉ፡፡ አስፈላጊነቱ ሲታይ በ2004 ላይም ተሻሽሏል፡፡ ህዝቡን ለማወያየት በመዋቅር ነው፡፡ ውክልና አለው፡፡ በፌደራል ደረጃ በስራ አስፈፃሚ ውስጥ ያሉ አባላት ክልሎችን ወክለው የመጡ ናቸው፡፡ ጠቅላላ ጉባኤ ውስጥ ደግሞ ከየክልሉ አስራ አንድ አባላት የሚወከሉበት ነው፡፡ ብለን የምንጠራው ከየክልሎ 11 አባላት የክልል ስራ አስፈፃሚ አባላትን ያካተተ ነው፡፡ ደንቡ የሚሻሻለውም የሚቀነሰውም በጠቅላላ ጉባኤው ውሳኔ ነው፡፡ ስራ አስፈፃሚዎቹ የማህበረሰቡ ተወካይ ስለሆኑ አዲስ ማሻሻያ ስንፈልግ በየመስጂዱ ውይይት ይደረጋል፡፡ አሁን ግን በጠቅላላ ጉባኤ ስለሆነ ይሔንን የመወሠን ሀላፊነት ያለው ጠቅላላ ጉባኤው ነው፡፡

የሙስሊሙ ማህበረሠብ መተዳደሪያ ደንቡን መቀበሉን የምትከታተሉበትና ችግሮች ሲኖሩ መፍትሄ የምትሰጡበት መንገድ አለ?

ማህበረሠቡ እራሱ የሚያነሳው ችግር ይኖራል፡፡ ህጋዊውን መንገድ ተከትሎ ጥያቄዎችን ያቀርባል፡፡ ለምሳሌ በአዲስ አበባ አስተዳደራዊ ችግር ካለ ወደ አ/አ እስልምና ጉዳዮች ይሄዳሉ፡፡ በዚሁ መፍትሄ ካልተገኘ፣ ወደ ፌደራል ነው የሚሔዱት፡፡ ይሔ አንዱ የመፍትሔ መንገድ ነው፡፡ ሆኖም መተዳደሪያ ደንቡ ላይ ቅሬታ አለኝ የሚል አልመጣም፡፡

በ1999 እና ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ መተዳደሪያ ደንቡ ላይ ችግር አለ ተብሎ ቅሬታ ቀርቦ አልነበረም?

ባለፈ ነገር ላይ አስተያየት መስጠት አይቻልም፡፡ አሁን እየሠራን ያለነው እነዚህን ችግሮች ለማሻሻል ነው፡፡ የተነሱትን ችግሮች ለመፍታት ሠርተናል፡፡ አናሻሽልም አላልንም፡፡ ችግሮችን ለመፍታትና ለማሻሻል ሰርተናል፡፡ የበለጠ ህብረተሠቡን አስደስቷል አላስደሠተም በቀጣይ የምናየው ይሆናል፡፡ ከ2001 ጀምሮ አዲስ ስራ አስፈፃሚ ነው የተሾመው፡፡ ስለዚህ ጥያቄዎቹን ለማረም በሩ ክፍት ነው፡፡

አህበሽ የተሰኘ የእስልምና አስተምህሮ ላይ ስልጠና እየተሠጠ ነው፡፡ አህበሽ ምንድነው?

እስልምና ጉዳዮች ም/ቤት ለሙስሊሙ ህብረተሠብ ይጠቅማል ብሎ በሚያስባቸው ጉዳዮች ላይ ስልጠናዎችን ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ ለኢስላም የሚጠቅም ጥሩ አስተምሮ ነው ተብሎ ስለታሠበ ነው፤ ይሔንን ስልጠና እየሠጠን ያለነው፡፡

በአንድ በኩል አህበሽ በአለም ካሉት ዋና ዋና የእስልምና አስተምህሮዎች አንዱ ነው ይባላል፡፡ በሌላ በኩል ከሃይማኖቱ ያፈነገጠ ነው በማለት የሚቃወሙ አሉ  እናንተ እንዴት ተቀበላችሁት?

በተቃውሞ የሚሰራጩት ወሬዎች ሃሰት ናቸው፡፡ የበርካታ አገሮችንም ማየት ይቻላል፡፡ በሀገር ውስጥም እስካሁን ባሉት ስልጠናዎች መመልከት ይቻላል፡፡ በተቃውሞ ከሚሰራጨው የሃሰት ውንጀላ ጋር ፍፁም የተቃረነ ነው፡፡ የፈጠራ ተቃውሞ ነው፡፡ የአህበሽ አስተምህሮ ሴቶች ሒጃብ አይጠቀሙም አይልም፡፡ ቁርአን የጅብሪል ቃል ነው አይልም፡፡ እንደዚያ ይላል እያሉ ሌላም ብዙ የሚያስወሩ ቢኖሩም ሃሰት ነው፡፡ እነዚህ ጉዳዮች በስልጠናው ላይ ይቅርና በሰልጣኞች ላይም የለም፡፡ ጥናት ተካሂዶበት የተዘጋጀ ስልጠና ነው፡፡

ጥያቄ  ስለዚህ እስልምና ጉዳዮች የቆመው ለቁርአንና ለሀዲስ ነው፡፡ ከዛ ያፈነገጠ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ቆሞ ነበር፡፡ ስልጠናው ላይ የነበሩ ሠዎች ሊመሠክሩ ይችላሉ፡፡ ይሔንን አይነት አስተሳሰብ ጥናት ተደርጐበት አምነንበት ነው ስልጠና እንዲሠጥ የተደረገው፡፡

ጥናቱን ያጠናው ማነው?

አሁን ስልጠና እየተሠጠ ያለው ሼህ አብደላ ሐረሪ የተባሉ የሚያስተምሩበትና ያጠኑት ነው፡፡

ስልጠናውን የሚሰጡት የሊባኖስ ዜጐች ናቸው?

መጀመሪያ አካባቢ እነሱ ነበሩ፡፡ በቀጣይ ይሔንን ስልጠና ኢትዮጵያዊያን እየሠጡ ናቸው፡፡

ማህበረሰቡ ስልጠናውን ተቀብሎታል?

ብዙም ተቃውሞ የለብንም፡፡ አንዳንድ በውጪ ያሉ የተወሰኑ ምሁራን ሊናገሩ ይችላሉ ሌላ ቅሬታ ግን የቀረበ የለም፡፡

በሀረር በተካሔደ 8ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ በሙስና የተጠቆሙትን አመራሮች በህግ እንጠይቃለን ብላችሁ ነበር፡፡ ምን ላይ ደረሠ?

ይሔ በህግ ክፍል የተያዘ ነው፡፡ ህጋዊውን መንገድ ተከትሎ በሒደት ላይ ነው፡፡

አህበሽ ስልጠናን ያልወሠደ ወይም የተቃወመ ኢማም ከኢማምነቱ ይነሳል ወይም ይታሠራል የሚሉ አሉ፡፡ እውነት ነው?

ይሔ ፀረ-ዲሞክራሲ አስተሳሰብ ነው፡፡ ማንኛውም ሠው መማር ባለበት ሁኔታ እንዲማር ይጋበዛል፡፡ የማይፈልግ ይሔዳል፤ ይሔን ያልተከተለ ብለን እስልምና ጉዳዮች ያወጣነው መመሪያ የለም፡፡ ከዞን እስከ ክልል በመስጂድ ደረጃ በግድ ስልጠናውን እንዲወስድ የተደረገ የለም፡፡ በደሴ ላይ አህበሽ የተባለውን ስልጠና አንወስድም ያሉ ኢማሞች እንደታሰሩና ፅ/ቤቱም እንደታሸገ ሲነገር ሰምተናል፡፡

የተነሱት ችግሮች ከስልጠናው ጋር የተያያዙ አይመስለኝም፡፡ መስጂድ አይወክለንም ከሚል አይነት እንቅስቃሴና ንክኪ በስተቀር፣ ከስልጠና ጋር በተያያዘ የተከሠተ ነገር የለም፡፡

ቅሬታዎች እየተደራረቡ ከሚሄዱ ምርጫው እንዲፋጠን ለምን አታደርጉም?

ምርጫውን ለማከናወን 44 ሚሊዮን ብር በጀት ተጠይቋል፡፡ ይሔ ደግሞ አሁን ስልጠናም እየተሠጠ በመሆኑ ይከብዳል፡፡ ከስልጠናው በኋላ እናደርገዋለን ብለናል፡፡   የምርጫ ጥያቄ የመጣው በሀገር አቀፍ ደረጃ አይደለም፡፡ በአዲስ አበባ በተወሠነ አካባቢ ላይ ነው፡፡ በክልሎች ደረጃ ጥያቄ የለም፡፡ የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት አመራር በዘፈቀደ እንዳሻው ሲፈልግ በስልጣን ላይ መቆየትም መውረድም የሚችል አይደለም፡፡ ህጋዊውን መንገድ ተከትሎ በጠቅላላ ጉባኤው ውሳኔ መሰረት ይሰራል፡፡ ይሔ አስፈፃሚ አካል ነው፡፡ ጥያቄው አገራዊ ከሆነ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ መጥራት ይቻላል፡፡ በአንድ አካባቢ የሚነሱ ጥያቄዎች ሀገራዊ ጥያቄዎች ላይሆኑ ይችላሉ፡፡

ችግሩ በተወሰነ አካባቢ ብቻ ቢሆን እንኳ፤ ያንን ችግር ካልፈታችሁ ችግሩ ወደ ሌላ አይዛመትም?

ጥያቄዎችን እንቀበላለን፡፡ አይወክሉንም እያሉ የሚናገሩ ሰዎች፤ አጀንዳቸውን መለየትና ምንድነው የሚፈልጉት የሚለው መታወቅ አለበት፡፡

የሙስና ችግሮች አሉ ስለሚባለውስ ም/ቤቱ ምን ይላል?

እስካሁን በሰነድ የተደገፈ ነገር የለም፡፡ ወሬ ነው የሚሰማው፡፡ ምክር ቤቱ ኦዲት ተደርጓል፡፡ በውጪ ኦዲተሮችም ታይቶ ምንም ችግር እንደሌለ ለጠቅላላ ጉባኤው ሪፖርት ቀርቦ ፀድቋል፡፡

የአወሊያ ት/ቤት መምህራኖች ተባረው የተመለሱት ለምንድነው?

በመጀመሪያ የራሱን ማስተካከያ ለማድረግ ተሞክሯል፡፡ የተማሪዎችን ተቃውሞ ማክበር ስለነበረበት የተማሪዎችን ጥያቄ አክብሮ አስተማሪዎችን መልሷል፡፡

አክራሪ ወይም ህገወጥ ናቸው የምትሏቸው ሰዎች ችግር ያመጣሉ ብላችሁ የምትፈሩት ነገር አለ?

እንደ ድርጅት አንፈራም፡፡ እንደ ሙስሊም ሁሉም ሰላማዊ ሆኖ እንዲኖር ነው የምንፈልገው፡፡ በቡድን የተደራጁ ግለሰቦች መስጊዶች ላይ ችግር እንዳይፈጥሩ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበትም ትምህርት እየተሰጠ ነው፡፡

 

 

Read 21663 times Last modified on Saturday, 18 February 2012 12:49