Saturday, 18 February 2012 11:15

ዘር፣ ዘረኝነትና ዘረ - መል

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(2 votes)

ለተፈጥሮ የነበረኝ አመለካከት እንደ ዥዋዥዌ ወደ ሁለት አቅጣጫ የሚወዛወዝ ነበር፡፡ ሁለቱም አቅጣጫዎች ጽንፈኝነትን የሚያበረታቱ እና እርስ በራሳቸው ደግሞ ተቃራኒ ጠላታሞች ነበሩ፡፡ ዥዋዥዌው ቀጥ ብሎ ሲቆም ብቻ ነው ሰላምን ማግኘት የሚቻለው፡፡ የዥዋዥዌ መቀመጫ ከመሬት ጋር ተተክሎ ግራ እና ቀኝ ዘመም መሆኑን ሲያቆም፡፡ ዥዋዥዌ በእርግጥ ለተወሰነ አመታት ተቀምጠው ሲወዛወዙበት ግልቢያው ደስ ይላል፡፡ ናላ ማዞሩ… የሄዱ መስሎ መመለሱ፡፡ የተመለሱ መስሎ መሄዱ… ደስ ይላል፡፡ ለዘላለም ሲሆን ግን ይሰለቻል፡፡ ያቅለሸልሻል፡፡ እየተመለሱ ማስመለስም… መዝረክረክም ሊኖር ይችላል፡፡ ዥዋዥዌው በደርሶ መልስ ከሚደጋግማቸው ጽንፎች አንዱ፤ ተፈጥሮን ከልክ ያለፈ ከመውደድ ጀምሮ እስከ ማምለክ ወይንም መፍራት የሚደርስ ነው፡፡ ሁለተኛው ጥግ ደግሞ፤ ተፈጥሮን ከመጠን ያለፈ መጥላት እና ከጥላቻ የተነሳ (በተፈጥሮ ህግ የሚመራም ሆኖ) ተፈጥሮን ለማውደም መሞከር ናቸው፡፡

ሁለቱም የዥዋዥዌ ተቃራኒ መድረሻዎች ከእውቀት ማነስ የሚመነጩ ናቸው፡፡ የሰው ልጅን የተፈጥሮ አሰራር ችላ ብሎ ወይም ንቆ.. ሰው የሰራውን ዘመናዊ መኪና ወይም ሮኬት ማዳነቅ ከተፈጥሮ ጥላቻ የመነጨ የእውቀት ማነስ ነው ለኔ፡፡ የሰው ልጅ የተፈጥሮ አእምሮ አሰራር ውስብስብነት ከየትኛውም ኮምፒውተር አሰራር በትልቅ የሀይል ቁጥር ብዜት መጠን (የላቀ) የራቀ ነው፡፡

ተፈጥሮን ማንበብ ያልቻለ ህይወትን ማንበብ አይችልም፡፡ ህይወትን ሳያነብቡ መኖር ይቻላል፡፡ ተፈጥሮ ድርሰቱን ጽፎቷል፡፡ ይቅርና የተፈጥሮን ድርሰት… የሰውን የቃላት ቅንብር ድርሰት ማንበብ አለመቻል “መሐይም” ያስብላል እንጂ ሞትን አያስከትልም፡፡ በመሆን ያለውን ነገር እየሆነ ያለበትን ሂደት (ምናልባትም ምክንያት) እናውቅ እንደሆነ እንጂ ሂደቱን ማቆም አልቻልም፡፡

ተፈጥሮ ላይ ያመጽኩባቸው አመታት (ሜታፊዚክሳዊ አመጽ) ወይም ተፈጥሮን እንደ አምላክ አንግሼ የሰገድኩባቸው አመታት (ምናብ ወይ ምሳሌ) ለዚህ መጣጥፍ አይጠቅሙም፡፡ ሁለቱም የቀድሞ አቅጣጫዎቼ ከጽንፈኛነት የመነጩ ነበሩ፡፡ ጽንፈኛነት ካለማወቅ የሚመነጭ ነው፡፡ እውቀት ተቃራኒዎችን ማገናኘት መቻል ነው፡፡ እውቀት መለያየት ሳይሆን ማጣመር ነው ትርጉሙ፡፡ አካልና ሀሳብን ለያይቶ ለልዩነቱ ወደ አንዱ ወግኖ ማጋደል ሳይሆን መሀከለኛ ሆኖ መቃናት ነው፡፡ እውነት እና እምነት፣ ግብረገብ እና ግብረ አራዊት፣ ምድር እና ሰማይ፣ ተፈጥሮ እና ተሞክሮ፣ ተፈጥሮ እና ፍጡር፣ ውስጥ እና ውጭ፣ ግራ ጐኔ(ሴት) ቀኝ ጐኔ (ወንድ)…ማለቂያ የለውም፡፡ ዥዋዥዌው በተቃራኒ አቅጣጫ የሚደርስ እና የሚመለስባቸው ዘርፎች፡፡

ይሄንን የመሀከለኛ የእውቀት ቦታ ካገኘሁባቸው መጽሐፍት አንዱን የፃፈው ሪቻርድ ዳውኪንስ ነው፡፡ የመጽሐፉ ስም “The Selfish Gene” ተብሎ ይጠራል፡፡ የዛሬ ሰለሳ ስድስት አመት ገደማ የተፃፈ ነው፡፡ ሪቻርድ ዳውኪንስ የአለም መሪ “Athiest” (ኢ-አማኒ) ነው በማለት ለሳይንስ እና ለዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሀሳብ ሽንጡን ገትሮ የሚሟገት ዘመናዊ ዳርዊን ነው፡፡ የላቀ ጭንቅላት ይዘው ነገር አለሙን ከሚዘውሩት ሀሳባዊያን መሀል የሚመደብ፡፡

ከዚሁ መጽሐፍ (The Selfish Gene) በመነሳት የተለያዩ ተቃራኒዎችን መመልከት ይቻላል፡፡ ችያለሁ፡፡ በተፈጥሮ እና ተመክሮ መሀል ያሉ መራራቆችን ሳይሆን ተመሳሳይነቶችን፡፡ በሰው እና እንስሳ መሀል ያሉ ልዩነቶችን ሳይሆን አንድነቶችን፡፡ የህያው ፍጡር (Organism) የህይወት ግብ አንድ መሆኑን እና ግቡን ለመምታት መፍጨርጨሩ ዋነኛ የህይወት ትርጉሙ መሆኑን ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡ እውነት ለማድረግ ግን በጽሑፌ አልሞክርም፡፡ እኔ እና እናንተ ባንስማማበትም እውነት የሆነ ነገር እውነት ነው፡፡ እኔና እናንተ ስለተስማማን የተፈጥሮ ህልውና አይለወጥም፡፡ ለማንኛውም ግን እኛ እንናበብ፡፡ ሁላችንም የዘረ መል ውጤቶች ነን፡፡ ዘረ መልን እኛን እንዲያስገኝ አድርጐ የፃፈው ተፈጥሮ ነው፡፡ ዘረ መልን ከወላጅ ልጅ ይወርሳል፡፡ የወላጅ ዋነኛ ተግባር ጥሩ ዘረ መሉን በተቃራኒ ፆታ እንቁላል በኩል አድርጐ አቀላቅሎ ማሳለፍ ነው፡፡ ማውረስ አና ራሱን የመሰለ ልጅ ወልዶ እንዲያድግ ማድረግ፡፡ በአጭሩ ከተፈጥሮ የተጣለብን ተልዕኮ ይኼ ነው፡፡

(ለዚህም ነው የቫለንታይን (የፍቅረኛሞች) ቀን ከፋሲካ በበለጠ ሁኔታ በሀገራችን እየተከበረ ያለው፡፡ የተፈጥሮ ተልእዕኮን መፈፀም የሚቻልበትን አጋጣሚ መፍጠር በበአል ደረጃ ከተጀመረ ለፍጡሩም አሸወይና የሚያስብል ነው!)

ይኼንን የተፈጥሮ ተልእኮ ተቃራኒ ፆታዎች አንድ ላይ ሆነው እንዴት ነው የሚወጡት? የጨዋታው ህግስ ምን ይመስላል? የሰውኛ (የተመክሮ) አይን እና የተፈጥሮ (የዘረ - መል) አይን ተልዕኮውን ለመወጣት ሲባል የሚከናወኑ ሂደቶች እና ውጣ ውረዶች ምን አይነት ናቸው? ተልዕኮአቸውን አንድ ላይ ለመወጣት ሲገጥሙ ወንድና ሴት ምን ይመስላል አሰላለፋቸው (ሁሉም ጨዋታ ህግ፣ እስትራቴጂ፣ ታክቲክ እና የማሸነፍ እና መሸነፍ ወይንም አቻ የመውጣት ሂደት አለው)

ወንድና ሴት ምን ማለት ነው?

ፆታ የሚያስፈልጋቸው ፍጡራን እንዳሉ ይታወቃል፡፡  ወደ አነስተኛ እንስሳት ስንወርድ አሜባ ወንድ እና ሴት የሚል ፆታ አያስፈልገውም፡፡ ራሱን ለሁለት በመክፈል ይራባል፡፡ ፈንገስም እንደዛው ነው፡፡ እንደ ዓሣ አይነቱ ፍጡር ደግሞ፤ ወንድና ሴት የሚል ከውልደት እስከ ሞት አንዴ ከታተመበት በኋላ የማይቀየር ፆታ ይዞ እድሜ ልኩን አይዘልቅም፡፡ ወንድና ሴቱ በእየጊዜው ፆታ ይቀያየራሉ፡፡

አንድ ዙር ሴቷ እንቁላል ከጣለች ለተከታይ ዙር ወንዱ ሴት ይሆንና በተራው ይጥላል፡፡ አጉል ብልጥ ሆኖ ሚስቱ ስታምጥ ሁሌ ከሩቅ ሆኖ ማየት አይችልም፡፡ እንደ ወንድ አውራ ዶሮ ጠዋት ጠዋት ብቻ በመጮህ ተንቀባርሮ መኖር በተፈጥሮ ለዓሣ አልተፈቀደለትም፡፡

ለማንኛውም ወደ ሰው ዘር ስንመጣስ ወንድ እና ሴት ምን ማለት ነው? ብለን እንጠይቃለን፡፡ ወንድነትን ሱሪ በመልበስ ሴትነትን ደግሞ ቀሚስ በማሳጠር ወይንም በማስረዘም ልንከፍል እና ልንመድበው እንችላለን? ወይንስ “ባንጠለጠለ” እና “ባላንጠለጠለ” ነው ምድቡ የሚሰራው?

ብልትም ፆታን ለመመደብ አያገለግልም ይለናል  ዳውኪንስ፡፡ ለምሳሌ እንቁራሪት ብልት የሚባል ነገር የለውም፡፡ ከወንዱ ወደ ሴቷ አካል የሚሰርጽ ነገር የለም፡፡ እንቁራሪቷ ወደ ውጭ እንቁላል ስታፈተልክ ወንዱ ውጭ ሆኖ ዘር ፍሬውን በመርጨት እንዲዳብሩ ያደርጋል፡፡

ስለዚህ ወንድና ሴትንም በሰው ልጅ ላይ ለመለየት ውጫዊ መገለጫዎች አያገለግሉንም፡፡ ወደ ውስጥ እንግባ፡፡

ወደ ሰው ሰውነት ስንገባ ሁለት የተለያዩ የመራቢያ ህዋሶችን እናገኛለን፡፡ አንደኛው የእስፐርም ህዋስ ሲሆን ሌላኛው የዕንቁላል ህዋስ ነው፡፡ የዕንቁላል ህዋስ የሚያመነጨው የሰው አይነት “ሴት” ተብላ ትጠራለች፡፡ እስፐርም የሚያመነጨው ደግሞ ወንድ ተብሎ ይጠራል፡፡ ወንድነትም ሆነ ሴትነት በጥቅሉ ፍችው ይህ ነው፡፡

ለአንድ አላማ ሊተባበሩ ወንድና ሴት እድሜ ልካቸውን ይፈላለጋሉ፡፡ ተፈጥሮ ነው፡፡ የተፈጥሮን ተልዕኮ ማሟላት ደግሞ የወንድ እና የሴት ተፈጥሯቸው ነው፡፡

የተፈጥሮ ተልዕኮ ይህ ከሆነ ለምን በተቻላቸው መጠን ዘጠኝ ወር እየጠበቁ ምድርን ልጅ በልጅ አያደርጓትም? አላደረጓትም? ግን የተፈጥሮ የጨዋታ ህግ እንደዛ አይደለም የተፃፈው፡፡ መውለድ ብቻ ሳይሆን ማሳደግም ሊነጣጠል የማይችል የጨዋታው  ግዴታ ነው፡፡…መውለድ እና ማሳደግም አይበቃም፡፡ ያደገው ዘር በህይወት ቆይቶ ራሱን ሊተካ እና ተተኪውም መተካት መተካካቱን እንዲቀጥል ማስቻል አብሮ ያለ የማይነጣጠል የተልዕኮው ግዴታ ነው፡፡

ዘሩን በተለያየ ሴቴ እንቁላል ላይ የሚሰራ ወንድ ማስረገዝ ካልቻለ… በተፈጥሮ ጨዋታ ተሸንፏል፡፡ ማስረገዝ እና ማስወለድ ችሎ ማሳደግ ያልቻለ አባት (ዘሩም) ሆነ እናት (ዘሪቱ) በተፈጥሮ/ ፍጡር ጨዋታው ተሸንፈዋል፡፡ በዘረ -መል (gene) ቋንቋ ማሸነፍ እና መሸነፍ “ጥሩ” አና “መጥፎ” ዘረ - መል በሚባል ስያሜ ይገለፃል ይለናል ዳውኪንስ፡፡ ማሸነፍ የቻለው “ጥሩ” ዘረ - መል ነው፡፡ የተሸነፈው ደግሞ “መጥፎ” ዘረ-መል …፡፡

የተፈጥሮ ጨዋታን የማሸነፊያ አቋራጭ መንገድ የለም

…በጂም ውስጥ ክብደት በማንሳት ከዳበረው ጡንቻ…በከባድ ስራ እና በእውነተኛ የህይወት ውጣ ውረድ የዳበረው ጡንቻ ይበልጣል፡፡ ጠንካራ ጡንቻን ለምትወልደው ልጅ ማውረስ የፈለገች ሴቴ እንቁላል በተፈጥሮ አይኗ (በዘረ መል አይኗ) የምትመርጠው በህይወት ውጣ ውረድ የተፈተነውን ጡንቻ ነው፡፡ ግን ጡንቻ ብቻ የወረሰ ልጇ መኖር አይችልም፡፡ በተለይ አባትየው ጡንቻውን ያገኘው በድብድብ ከሆነ  ለልጁም የሚያወርሰው የድብድብ ውጤት የሆነውን ጡንቻውን ነው፡፡ በድብድብ ከተገኘው ጥንካሬ በስራ የተገኘው በህይወት ለመቆየት ይጠቅማል፡፡ የተደባዳቢው ጡንቻ ወደ ህግ ቦታ ቀርቦ ዘብጥያ ይወርዳል፡፡ አባት ልጁን ማሳደግ አይችልም፡፡ ተፈጥሮ ራሷ አሸናፊውን ዘረ መል የምትመርጠው በስነ ምግባር ህግ መዝና ነው፡፡ ተፈጥሮ ራሷ ስነምግባርን ትደግፋለች (እዚህ ነጥብ ላይ በቀጣይ ክፍል በስፋት እመለስበታለሁ፡፡)ሌላ የእንስሳ አይነትን እንደ ምሳሌ እንጥቀስ:- ባለጥቁር ራሱ የባህር አሞራ (blackhead gull) እንቁላል የሚጥሉበትን ጐጆ መሬት ላይ ነው የሚሰሩት፡፡ በብዛት ሆነው አንድ ቦታ ላይ ነው እንቁላሎቻቸውን ጥለው እስኪፈለፈሉ አንድ ላይ የሚሰፍሩት፡፡ ጫጩቶቹ ሲፈለፈሉ በጣም ትንንሽ እና በቀላሉ የሚዋጡ የሚሰለቀጡ አይነት ናቸው፡፡ አንዱ አሞራ ለጫጩቶቹ የሚመግበውን አሣ ፍለጋ ተነስቶ ሲበር ከጐረቤቱ ያለው አሞራ ጫጩቶቹን ለቀም አድርጐ መዋጥ የተለመደ ነገር ነው፡፡ ተንከራትቶ ከማግኘት በአቋራጭ መድረስ የሚለው አስተሳሰብ በሰውኛ ሳይሆን በሌሎቹም አራዊቶች ላይ የሚከሰት ነገር ነው፡፡ ግን እዚህ ላይ መዘንጋት የለብንም፡፡ በአቋራጭ ለቀም አድርጐ የሚበላው በትክክለኛ መንገድ ፈልጐ አድኖ የመያዝ አቅም ወይንም ብልሀት ስለሌለው ነው፡፡ በመሆኑም ደካማ ዘር ነው፡፡ ወይንም ዘረ መል፡፡ ያኛው ትክክለኛው አሞራ ደግሞ በቀጥተኛው መንገድ ከባህር አሣ ለማጥመድ ሲሄድ፣ ጫጩቶቹን የሚያስበላ ከሆነ ከመጠን ያለፈ የዋህ በመሆኑ የራሱን ጥሩ ዘር ወደ ቀጣዩ ትውልድ ማሸጋገር አልቻለም፡፡ ስለዚህ የዋሁም አሞራ  የተሸነፈ ወይንም መጥፎ ጂን ነው የያዘው፡፡ “አጨዋወቱ ጥሩ ነበር ግን ለውጤት አልበቃም” እንደሚባለው አይነት፡፡

ዘር፣ ዘረኝነት እና ዘረ - መል

ዘረ - መል ገብጋባ ነው የተባለው በ”የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው” አገላለጽ ተልዕኮውን ማሳካት ስላለበት ብቻ ነው፡፡ የተፈጥሮ (ሠሪው) ራሱ ስሪቱ ተልዕኮውን ሲያሳካ ብቻ ደስተኛ እንዲሆን አድርጐ አበጅቶታል፡፡

ዘመዳምነት ማለት ከአንድ ዘረ መል የተቀዱ ማለት ነው፡፡ ማንም ፍጡር ወደራሱ ዘር ማድላቱ በውስጠ ታዋቂነት (ወይንም አላዋቂ ደመነፍሳዊነት) የራስን እና መሰል ዘረ መሎችን ለማብዛት፣ ለመተካት፣ ለማሻገር የሚደረግ ሙከራ ነው፡፡ Blood is thicker than water የሚለው አባባል ለአማርኛ “ዘመድ ከዘመዱ አህያ ካመዱ” ከሚለው ጋር በጣም ይቀራረባል፡፡ (መቼም ሰው ባለው ነገር ነው የሚተርተው፤ እኛ ዘንድ አህያ እና አመድ በብዛት ቢኖር ነው፡፡ እነ እንቶኔ ጋ ደግሞ “ደም” እና ምናልባት የደም ጥራት መለኪያ በብዛት ሳይኖር አይቀርም፡፡ “ዘመድ ከዘመዱ ሲባል አከንባሎም ወደ ከብቶች በረት ሮጠች” የሚል የኦሮምኛ አባባልም አለ…)ይህንኑ የዘመዳምነት አስተሳሰብ ከእንስሳት አለም አንድ ምሳሌ ወስደን እናገናዝበው፡፡ Vampirt bat የሚባል ደም የሚጠጣ የሌሊት ወፍ አይነት አለ፡፡ የሌሊት ወፍ እንደ ሰው የእለት ጉርሱን ለማግኘት በእየሌሊቱ ለአደን ይወጣል፡፡

ምግቡን ከሚያንቀላፋ እንስሳ ደም ስር ላይ ተጣብቆ ለመምጠጥ፡፡ አመጣጠጡ ደግሞ የዋዛ አይደለም፡፡ አንዳንዴ ከመምጠጡ የተነሳ ደም የተወሰደበት እንስሳ ከተኛበት እንቅልፍ ሳይነቃ በዛው ይመርሻል፡፡ ከሚገባው በላይ በደም ጠግቦ (ሰክሮ) የወጣው የሌሊት ወፍ ምንም እድል ላልገጠማቸው መሰሎቹ ከሆዱ የደም ማጠራቀሚያ እያወጣ እያፈረፈረ ያጐርሳቸዋል፡፡ እነዚህ ተቋዳሾች የራሱ ልጆች ይሆናሉ፤ በመጀመሪያ ደረጃ፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ዘመዶቹ ናቸው፡፡ ዘመዶቹ ካልሆኑ ደግሞ እሱ ያደገበት ዋሻ አባላት ናቸው፡፡ ዘመድም ሆነ ጐረቤት (የሰፈር ልጅ) ለሰው ልጅም ቅርቡ ነው፡፡ የሰው ልጅም መጀመሪያ ማካፈል ካለበት የሚያደርገው፣ ደም መጣጩ የሌሊት ወፍ ያደረገውን የክፍፍል ስርዓት ነው፡፡ ዘረኝነትም…ተፈጥሯዊነት ነው፡፡

(ይቀጥላል)

 

 

Read 3374 times Last modified on Saturday, 18 February 2012 11:33