Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 25 February 2012 12:47

የኢህአዴግ ተቃውሞ እየመረረ ነው - መንግስትን በሙስና እየከሰሰ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የብዙ ዜጎች ጭንቀት ግን የኑሮ ውድነት እና ስራ አጥነት ሆኗል

መንግስት ላይ የሚሰነዘሩ አንዳንድ ትችቶች፤ እጅግ የመረሩ ከመሆናቸው የተነሳ ያስደነግጣሉ። ከሽብር ጥቃት በላይ የሙስና አደጋ ይብስብናል የሚል ትችትና ተቃውሞ ስትሰሙ፤ ደንገጥ ማለታችሁ አይቀርም። እንግዲህ አስቡት። የሽብር ጥቃት ለማድረስ አስበዋል ወይም ፅፈዋል፤ ወይም በስልክ ተነጋግረዋል ተብለው የተከሰሱ ሰዎች፤ ከ10 አመት በላይ እስር ተፈርዶባቸዋል። አገሪቱን ደም ሊያለብሷት ነበር በሚል ስሜትም፤ “አኬልዳማ” የተሰኘ የቲቪ ፊልም ተሰርቶባቸዋል። ታዲያ፤ የመንግስት ሙስና ከሽብር ጥቃት የባሰ አደጋ ሆኗል የተባለው፤ ምንኛ አስፈሪ ደረጃ ላይ ቢደርስ ይሆን?

መቼም፤ እንደዚህ አይነት ጠንካራ ትችትና ተቃውሞ መንግስት ላይ ለመሰንዘር ትልቅ ድፍረት ይጠይቃል። “ፅንፈኛ፤ ፀረ ልማት፤ ፀረ ሰላም፤ ጨለምተኛ፤ መርዶ ነጋሪ” የሚል ውግዘት ሊያስከትል ይችላልና። ማስፈራሪያና እስር ሳይቆጠር ማለት ነው። ደግነቱ፤ መንግስት ላይ ጠንካራ ትችትና ተቃውሞ የተሰነዘረው ከኢህአዴግ በኩል ነው። ለዚያውም ከፓርቲው አመራር፤ ለዚያውም ፓርቲው ከነአጋሮቹ ከ99.6 በመቶ በላይ በተቆጣጠረው ፓርላማ ውስጥ ነው።

ከሰሞኑም በአዲስ አበባ ምክር ቤት ተመሳሳይ የሰላ ትችትና ተቃውሞ ተስተጋብቷል። ሙስና የህዝብ እሮሮ እየሆነ መምጣቱን የተናገሩት የከተማዋ ከንቲባ፤ የከተማዋን የእድገት ፍጥነት እየገታ ነው ብለዋል። የልማትና የመልካም አስተዳደር ዋነኛ ማነቆ ሙስና እንደሆነም ከንቲባው ተናግረዋል - ተገቢ ያልሆነ ጥቅም መስጠትና መቀበል እንዳልተወገደ፤ እንዲሁም መልኩን እየለዋወጠ እንደሚከሰት በመግለፅ። እውነትም፤ ኢህአዴግ መንግስት ላይ አምርሯል ያስብላል። ትናንትናና ከትናንት በስቲያ በተካሄደው የኦሮሚያ ምክር ቤት ስብሰባስ? ያው፤ ትልቁ ጠላት ሙስና ነው ተብሏል።

በዚሁ ሳምንት በተካሄደው ሌላኛው ስብሰባ ላይም እንዲሁ፤ የሙስና ነገር ዋነኛ ጉዳይ ሆኗል። የሙስናን አደገኛነት የገለፁጽ አቶ ስብሃት ነጋ፤ ገና ከቁጥጥር ውጭ ወደመሆን ያልደረሰው ሙስና፤ አሁን ያለው አያያዝ ከቀጠለ ከቁጥጥር ውጭ ሊሆን እንደሚችል ስጋታቸውን ጠቁመዋል። ሃይለኛ ትችት ነው። የመንግስት ሙስና ይህን ያህል አስጊ ሆኗል?

ሰኞ እለት የተካሄደውን የመንግስት ሰራተኞች (የሲቪል ሰርቪስ) ሚኒስቴር ስብሰባ ጨምሩበት። መቼም፤ ያ ብዙ የተነገረለትና ብዙ ገንዘብ የወጣበትን፤ ብዙ የተዘመረለትና ብዙ ጊዜ የፈሰሰበትን “ቢፒአር” ታውቁታላችሁ። ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ እንደሆነ፤ በ97 የምርጫ ወቅት ሳይቀር በተደጋጋሚ ተወድሷል። በመንግስት ሚዲያ ስለ ቢፒአር ሲሰራጭ የነበረው ዜናና ዘገባማ ለቁጥር ያስቸግራል። የመንግስት ፖሊሲ ይሁን ስትራቴጂ በቅጡ ባይለይለትም፤ “ቢፒአር” እንዲያ እየተጨበጨበለት አስር አመት ሊደፍን ምንም አልቀረውም። ግን ክብረ በአል አልተዘጋጀለትም።

የመንግስት መስሪያ ቤቶች፤ በቢፒአር ከፍተኛ ለውጥ አምጥተናል እያሉ በሚዲያ ሲናገሩት እንደነበረ ያስታወሱት የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትር አቶ ጁነዲን ሳዶ፤ ውጤቱ ግን ከዚህ ውጭ እንደሆነ ጠቅሰዋል። የቢፒአር ነገር በተግባር የተንዛዛ ቢሮክራሲን ለማስተካከልና ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት ሳይሆን፤ ስልጣንና ሹመት ለመሻማት እንደዋለ ተናግረዋል ሚኒስትሩ። ቢፒአር፤ ሃብት ሲዘርፉና ሲያዘርፉ ለነበሩ ሙሰኞች መገልገያ ሆኗል በማለትም ጠንካራ ትችት ሰንዝረዋል።

 

“ጠርጣራ” ጥያቄዎችና መላምቶች

ኢህአዴግ ምነው መንግስት ላይ አመረረ የሚል ስሜት አልተፈጠረባችሁም? ምክንያቱስ ምን ይሆን የሚል ጥያቄም ሊጭርባችሁ እንደሚችል እገምታለሁ። ከባድ ጥያቄ ነው። በቅንነት ከታየ፤ የመንግስትን ሙስና አምርሮ መቃወምና መተቸት ምንም ስህተት የለውም። በእርግጥ፤ “ማን ነው ማንን የሚተቸው?” ግር መሰኘታችን አይቀርም።

ትችቶቹ ሲታዩኮ፤ አንድ አለማቀፍ አጣሪ ኮሚሽን ወይም ሂዩማን ራይትስ ዎች፤ መንግስት ላይ ያወረዱበት ወቀሳና ተቃውሞ ይመስላል። የመንግስት ስልጣን የያዘው ገዢ ፓርቲ (ኢህአዴግ)፤ መንግስት ላይ የሰላ ትችት ይሰነዝራል - ጥፋተኛ ነህ ብሎ እንደመውቀስ ነው። ግር የሚያሰኝ ቢሆንም፤ በቅንነት ብናየውና ብናደንቀውስ? ብትሉ አልተሳሳታችሁም። በሌላ በኩል ደግሞ፤ ፓለቲካንና ፓርቲን ማመን አስቸጋሪ እየሆነ ተጠራጣሪነት ስለሚያጠቃን፤ ብዙ አሉታዊ መላምቶች የሚያስቡ ሰዎች አይጠፉም። ምናልባት የሚራገፉ ባለስልጣናት ይኖሩ ይሆን? “መተካካት” የሚባለው ነገር እክል ገጥሞት ከሆነስ? ምናልባት የተቃዋሚዎችን ጩኸት ለመቀማትና ዝም ለማሰኘት የታሰበ ቢሆንስ? አስቸጋሪ ጥያቄ ነው። ሌሎች ችግሮችን ለመሸፈንና ለማድበስበስ ይጠቅም ይሆን እንዴ?

ኢህአዴግ በመንግስት ላይ የመረረ ትችት መሰንዘሩ፤ በተለይ ለተቃዋሚ ፓርቲዎችና ለተቃዋሚ ፖለቲከኞች እጅግ ፈታኝ ነው። መንግስት በሙስና ተዘፍቋል፤ ቢፒአር የስልጣን ማጠናከሪያ መሳሪያ ሆኗል፤ ህዝቡ በመንግስት ተማሯር እያሉ “ሲጮሁ” የነበሩ ተቃዋሚዎች ዘንድሮ ምን ይበሉ? የራሱ ገዢው ፓርቲ የኢህአዴግና የመሪዎቹ “ጩኸት”፤ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች የበለጠ ሆኗል። ኢህአዴግ መንግስት ላይ ተነስቶበታል።  እንግዲህ፤ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ስራ ኢህአዴግን መቃወም ከሆነ፤ “መንግስትን አትንካብን፤ ኢህአዴግ መንግስት ላይ የሚሰነዘረውን ፅንፈኛ ተቃውሞ እንቃወማለን” ሊሉ ነው? ችግርኮ ነው።

ለነገሩ ኢህአዴግ የተቃዋሚዎችን ጩኸት ለመቀማት አስቦ ላይሆን ይችላል። ምናልባት፤ የሚራገፉ ባለስልጣናት ይኖሩ ይሆን? እንደ ኢህአዴግ የመሳሰሉ ፓርቲዎች፤ እያሰለሱ መንግስትን በሰላ ትችት የማጣደፍ ባህርይ አላቸው። ገሚሶቹን ባለስልጣናት ለማራገፍ ሲያስቡ፤ “ሂስና ግለሂስ” ያበዛሉ። ለነገሩ ባለፉት ሰባት አመታት ኢህአዴግ ያሰባሰባቸው አባላት አሁን ከባድ ሸክም ሊሆኑበት እንደሚችሉ መገመት አይከብድም። “አግበስብሰን ያስገባናቸው” የሚል አገላለፅ ሲጠቀሙ ካያችሁ፤ ችግር አለ ማለት ነው።

ግን አዲሶቹ ሰዎች ችግር ከፈጠሩ፤ መተካካት የሚባለውስ ነገር ምን ሊሆን ነው? ሁለት አመት ብቻ ነው የቀረው። እንግዲህ፤ ኢህአዴግ ደጋግሞ ተናግሯል - መሪዎች በምርጫ ከስልጣን ይወርዳሉ ብሎ እንደማያስብ። ቢያንስ ለ20 አመታት ስልጣን ላይ መቆየት አለብኝ ብሏል። ለ20 ለ30 አመት ስልጣን ላይ መቆየትማ አምባገነን ያሰኛል። እናስ ምን ተሻለ? የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ እንደሚያደርገው፤ መሪዎችን በየ10 አመቱ መለወጥና መተካት የፈለገ ይመስላል። የኩባ ኮሙኒስት ፓርቲም፤ ተመሳሳይ የመተካካት አሰራር ለመጀመር አምና ወስኗል። ኢህአዴግማ ቀድሞ ጀምሯል። በሚቀጥሉት ሁለት አመታትም፤ ነባር ባለስልጣናትን በሙሉ በአዳዲስ ተክቼ አጠናቅቃለሁ ብሏል። ነገር ግን፤ አዲሶቹ ሰዎች ችግር ከፈጠሩና የሙስና አደጋ ከተባባሰ፤ “ኧረ ነባሮቹ ይቆዩልን” የሚል ሃሳብ መፈጠሩ ይቀራል?

እንዲሁ ስንጠረጥር ብንውል፤ ትክክለኛውን መልስ አናገኝ ይሆናል። ግን መጠርጠር እናቆማለን እንዴ? ብዙ ሰዎች አያቆሙም። ኢህአዴግ እለት በእለት፤ የመንግስት ሙስናና የሃይማኖት አክራሪነትን እየደጋገመ የሚያወግዘው፤ መወገዝ እንዳለባቸው ጠፍቶን ሳይሆን ሌላ ሌላውን እሮሮ ለማስረሳት ቢሆንስ? ደግሞም፤ በቅርቡ በፀረሙስና ኮሚሽንና በአለም ባንክ ትብብር በተደረገው ጥናት እንደተገለፀው፤ የአብዛኛው ሰው ዋና ጭንቀት፤ የኑሮ ውድነት እና ስራአጥነት ናቸው። ከዚያም የትራንስፖርት እጥረት፤ የምግብ እጥረት እና ሌሎችም። ሙስና በ7ኛ ደረጃነት ነው የተጠቀሰው። ከኢኮኖሚ ውጭ የሆነው ሌላኛው የፖለቲካ ችግር፤ የነፃነት መጥበብ ይመስለኛል።

 

የኑሮ ውድነትና አጃቢዎቹ

ካለፉት 5 አመታት ወዲህ እየከፉ ከመጡ ችግሮች አንዱና ዋናው የኑሮ ውድነት መሆኑ ላያከራክር ይችላል። ነገር ግን፤ የኑሮ ውድነት እንዲሁ ለብቻው ተነጥሎ የሚወለድና የሚፈጠር ችግር አይደለም። መንስኤዎችና አጃቢዎች አሉት። መንግስት፤ በደርግ ጊዜ እንደተደረገው ወይም በሌሎች ሶሻሊስት አገራት እንደታየው፤ ግዙፍ ኮርፖሬሽኖችን እያቋቋመ ነው። በየክልሉ መንግስታዊ የኮንስትራክሽን ድርጅቶችን መመስረት ጀምሯል።

መንግስት በቢዝነስ ስራዎች ላይ እየተሰማራ፤ በኢኮኖሚ ውስጥ የነበረውን ትልቅ ድርሻ ይበልጥ እያሳደገ መግነን የሚችለው ግን እንዲሁ በባዶ አይደለም። ከዜጎች ተጨማሪ ታክስና ግብር ይሰበስባል። ለግል እንቨስትመንትና ለግል ቢዝነስ መሰጠት የነበረበት ብድር ወደ መንግስት እንዲሄድ ይደረጋል። ከባንክ ብድሮች መካከል ወደ 70 በመቶ ያህሉ የመንግስት ድርጅቶች እየወሰዱ ናቸው። በዚህ ምክንያት የግል ቢዝነስ እድገት ሲዳከም፤ የስራ እድሎችም መጥበባቸው አይቀርም። ግን ይህ ብቻ አይደለም።

በታክስና በግብር የሚሰበሰበው ገንዘብ እንዲሁም ከባንክ የሚመጣው ተጨማሪ ብድር፤ ለመንግስት ፕሮጀክቶች በቂ አይሆንም። እናም ያንኑን የወረቀት ገንዘብ በብዛት ያትማል። በዚህም ምክንያት ነው፤ ባለፉት አራት አመታት ብር እየረከሰ፤ የሸቀጦች ዋጋ እየናረ ኑሮ እግጉን የተወደደው።

አንዳንድ የኢህአዴግና የመንግስት ሰዎች ግን ይህንን መስማት አይፈልጉም ነበር - “ፀረ ልማት ተቃውሞ፤ ከንቱ ትችት” በማለት ሲያጣጥሉትም ነበር። ዛሬ ግን፤ ኢህአዴግ ራሱ ያምናል፤ ቅጥ ያጣ የብር ህትመት፤ ዋነኛው የኑሮ ውድነት መንስኤ እንደሆነ የኢህአዴግ መሪዎች በአደባባይ በተደጋጋሚ ተናግረዋል።  ይህም ብቻ አይደለም።

የመንግስት ኮርፖሬሽኖችና ኩባንያዎች እየገዘፉ ሲመጡ፤ በቢዝነስና በኢኮኖሚ ውስጥ የመንግስት ድርሻዎች እያበጡ ሲሄዱ፤ በዚያው መጠን ለሃብት ብክነትና ለዝርፊያ እንዲሁም ለሙስናና ለአድልዎ ሰፊ በር ይከፈታል። ይህንን ሃሳብ፤ እንደ ጭፍን ተቃውሞና እንደ ክፉ ትችት የሚቆጥሩ ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ይገባኛል። ነገር ግን፤ መንግስት ኢኮኖሚ ውስጥ በስፋት ሲገባ፤ የሙስናና የብክነት አደጋው እንደሚጨምር ራሱ ኢህአዴግም ያምናል - የራሱ ሰነዶች ውስጥ ፅፎታልና። በብር መርከስ ሳቢያ የተፈጠረው የኑሮ ውድነት ለብቻው የተከሰተ ችግር አይደለም - መንግስት ቢዝነስ ውስጥ በስፋት እየገባ፤ የሃብት ብክነትና ሙስና ሲስስፋፋ፤ የግል ቢዝነስና የስራ እድል ይዳከማል።

 

የነፃነት መጥበብና አጃቢዎቹ

ከ97 የምርጫ ቀውስ ወዲህ ደረጃ በደረጃ፤ የዜጎች ነፃነት ይበልጥ እየጠበበ መጥቷል። ስለ ኑሮ ውድነት እና ስለ ስራ አጥነት ለመነጋገር፤ ለመወያየትና ሃሳብ ለመለዋወጥ እንኳ አስቸጋሪ ሆኗል። በእርግጥ፤ ነፃነት ሰፋ ሲል፤ ስልጡን ክርክርናና የበሰለ ውይይት ብቻ አይደለም የሚፈጠረው። መንጫጫት፤ መሰዳደብ፤ መንዛዛት፤ “መቀወጥ” የሚያምራቸው ብዙ ናቸው። ነገር ግን፤ ቢያንስ ቢያንስ፤ ከዚሁ ጋር አብሮ ለስልጡን ክርክርና ለበሰለ ውይይት በቂ ነፃነት ይኖራል። ደግሞም፤ ጫጫታውንና ቀውጢውን ለማስቀረት፤ ነፃነትን ማጥበብ፤ ሰላምና ፀጥታ ይገኛል ማለት አይደለም።ነፃነት የጠበበ ጊዜ፤ ከሁሉም በፊት የሚመናመኑት፤ ስልጡን ክርክርና ውይይት ናቸው። በዚሁ ምትክም፤ በሃይማኖት ወይም በብሄር ብሄረሰብ ሰበብ፤ በጭፍን እምነትና በጭፍን ስሜት ፀብ የሚያራግቡ፤ የሚንጫጩና “የሚቀውጡ” ሰዎች ለብቻ ጎልተው ይወጣሉ። አሁን አሁን የምናየውም፤ ይህንኑን አሳዛኝና አሳፋሪ ትእይንት ነው። ስለ ፖለቲካ ወይም ስለ ኢኮኖሚ ወሬ በተነሳ ቁጥር፤ አፍታም ሳይቆይ በጭፍን የዘረኝነት ስሜት ውስጥ መዘፈቅና መንቦራጨቅ ይጀምራል። ኢትዮጵያን የሚመለከቱ የኢንተርኔት ወሬዎችንም መመልከት ትችላላችሁ። ብልጭ ብለው የሚጠፉና የሚደበዝዙ ሳይሆኑ፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፉና እየተጠናከሩ የመጡት የኢንተርኔት አምባዎች፤ በሃይማኖት ንትርክ ላይ ያተኮሩ ናቸው።

በፓለቲካና በኢኮኖሚያ ዙሪያ የሚከናወኑ ሰላማዊ ሰልፎች በጠፉበት በአሁኑ ዘመን ካየናቸው የአደባባይ ሰልፎች መካከል፤ ብዙዎቹ ከሃይማኖት ውዝግብ ጋር የተያያዙ ናቸው። በአጭሩ ጭፍን የዘረኝነት ስሜትና ጭፍን የሃይማኖት እምነት ተመችቷቸዋል። እውነትም፤ ነፃነትን በማጥበብ፤ ስልጣኔና ስክነት አይገኝም። ምናልባት፤ በቅርቡ በሚዲያ ይጀመራል የተባለው የፖርቲዎች ክርክር፤ በቅንነት ከተካሄደና ጥሩ ጅምር ሊሆን ይችላል - ቀስ በቀስ የዜጎችን ነፃነት በሁሉም መስክ ለማስፋፋት።ከላይ እንደገለፅኩት፤ ዋነኞቹ የወቅቱ ችግሮች፤ የኑሮ ውድነትና የነፃነት መጥበብ ናቸው - ከነአጃቢዎቻቸው ጋር። ከአጃቢዎቹ መካከል ሙስና እና የሃይማኖት አክራሪነት ሊጠቀሱ ይችላሉ። ኢህአዴግ፤ ሙስናን እና አክራሪነትን እየደጋገመ መቃወም ማዘውተሩ ስህተት አይደለም። በእርግጥ፤ ለሃያ አመታት የመንግስትን ስልጣን የያዘ ፓርቲ፤ የመንግስትን ሙስና ሲያወግዝ መስማት ... የሆነ ቅር ቅር የሚያሰኝ ነገር እንዳለው ጠቅሻለሁ። የመንግስትን ሙስና የሚቃወምበት ሁኔታው ሲታይ፤ ኢህአዴግ ጨርሶ መንግስት ውስጥ ምንም ድርሻ የሌለው ገለልተኛ አጣሪ ቡድን ያስመስለዋል።

እንዲያም ሆኖ፤ ሙስናን እንዲሁም አክራሪነትን፤ ማውገዝና መቃወም ጥሩ ነው። ነገር ግን፤ ሙስናና አክራሪነት ዋነኛ ችሮች ሳይሆኑ፤ አጃቢዎች ናቸው። የኑሮ ውድነትንና የመንግስት መግነንን ወደ ጎን ትቶ፡ ሙስና ላይ ብቻ ጣት መቀሰር ዋጋ የለውም፤ የኑሮ ውድነቱን ሊያስረሳን ወይም ሊፈታልን አይችልም። የነፃነት መጥበብንና የመንግስት መግነንን ወደ ጎን ገፍቶ፤ የሃይማኖት አክራሪነት (ጭፍን እምነት) ላይ ብቻ ማተኮር መፍትሄ አይሆንም። በጭፍን እምነት ወይም በአክራሪነት አማካኝነት የሰውን ነፃነት ከነአካቴው ለማጥፋት የሚፈልጉ ቡድኖችን መመከት የሚቻለው፤ ነፃነት በሚያጠብ ሌላ ጭፍን ስሜት አይደለም፤ ነፃነትን በማጥበብም አይደለም። አክራሪነትን መመከት የሚቻለው፤ ነፃነትን የሚሻ ስልጡን አስተሳሰብና ባህል በማጠናከር፤ እናም ነፃነትን በማስፋፋት ነው።

 

 

Read 4629 times Last modified on Saturday, 25 February 2012 12:51