Saturday, 26 March 2016 11:19

ዶናልድ ትረምፕ፤ “ሳይቆነጠጡ” ነው ያደጉት!?

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(27 votes)

ያልተሳደቡት ጋዜጠኛ፣ ፖለቲከኛ፣ ቴሌቪዥን ጣቢያ፣ አገራት… የሉም

   ባለፈው ማክሰኞ ለአውሮፓዋ መዲና ለብራስልስ ክፉ ቀን ነበር፡፡ በብራስልስ ኤርፖርትና ባቡር ጣቢያ ላይ በደቂቃዎች ልዩነት በተፈፀመ የአሸባሪዎች የቦንብ ጥቃት ከ30 በላይ ሰዎች ለሞት ሲዳረጉ፣ ከ300 የሚበልጡት ደግሞ ቆስለዋል፡፡ አይሲስ የተባለው አሸባሪ ቡድንም ለደረሰው ጥቃት ኃላፊነቱን እወስዳለሁ ብሏል፡፡ የብራስልሱ አሰቃቂ የጥቃት ዜና ከተሰማ በኋላ አሜሪካ ራሷን ከተመሳሳይ የሽብር ጥቃት ለመከላከል የጥበቃ ኃይሏን በተጠንቀቅ ወድራ አገርና ህዝብን ለመታደግ ትጋት ይዛለች - ባለፈው ረቡዕ CBS እንደዘገበው፡፡
ባለፈው ሐሙስ በቤልጂየም የጥቃቱን ሰለባዎች ለማስታወስ በተደረገው የህሊና ፀሎትና ሻማ የማብራት ሥነ ሥርዓት ላይ የቁጭት፣ የድንጋጤ፣ የሃዘን እንዲሁም የቁርጠኝነትና የአንድነት ዥንጉርጉር ስሜት ተንፀባርቋል ብሏል - የCBS ዘጋቢ፡፡ ከአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት በኋላ ሌላ የአንድ ደቂቃ ደማቅ ጭብጨባ ተስተጋብቷል፡፡ የCBS ጋዜጠኛ፣ “Long live the Belgians!” (ረዥም ዕድሜ ለቤልጂየሞች!) የሚል መፈክር መስማቱንም ዘግቧል፡፡
ከሁሉም የሚያስገርመው ደግሞ ቤልጂየሞች የሞቱትን የዘከሩት የ8 እና 10 ዓመት ህፃናት ልጆቻቸውን ይዘው ነበር፡፡ “ለቤልጂየም እንዲፀለዩላት ነው ያመጣኋቸው” ብላለች አንዲት ያዘነች እናት፡፡ ይሄ በእርግጥም ብዙ ብርታት … ብዙ ፅናት … ብዙ ጥንካሬ … ብዙ ድፍረትን ይጠይቃል፡፡
ይሄ ሁሉም ሆኖም ቤልጂየሞች ለመንግስታቸው … ለፖሊስና ደህንነት ተቋሞቻቸው የሚያቀርቡት ፈታኝ ጥያቄ አላቸው፡፡ የሽብርተኛ ቡድኑ ቤልጂየም መዲና ብራስልስ እምብርት ላይ አፓርትማ ተከራይቶ … የቦንብ ማምረቻ ፋብሪካ መስርቶ … ቦንብም ሰርቶ ወደ ብራስልስ ዓለም አቀፍ ኤርፖርትና ባቡር ጣቢያ አጓጉዞ… ህዝቡን እስኪፈጅ ድረስ … መንግስት … ፖሊስ … የደህንነት ኃይል… የማንን ጎፈሬ ሲያበጥሩ ነበር? ተገቢና ምክንያታዊ ጥያቄ ነው፡፡
በብራስልስ የተፈፀመው የሽብር ጥቃት፣ በአሜሪካ አይሲስ ዳግም የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የክርክር አጀንዳ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ አርጀንቲናን እየጐበኙ የነበሩት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፤ “ዓለም ህብረት መፍጠር እንዳለበት ይሄ ሌላኛው የማንቂያ ደወል ነው” ብለዋል - የብራስልሱን የሽብር ጥቃት፡፡
ኦባማን “ወሬ እንጂ ተግባር ላይ የለበትም” በሚል አጥብቀው ሲያወግዙና ሲነቅፉ የሚደመጡት የሪል እስቴት ከበርቴውና የሪፐብሊካን እጩ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ተፎካካሪ ዶናልድ ትራምፕ ጥቃቱን በተመለከተ ሲናገሩ፤ “አይሲስን ለመደምሰስ እንደ መጨረሻ አማራጭ ኒውክሌር እጠቀማለሁ፤ ጠላቶቻችን ናቸው” ብለዋል፡፡ ከዚህ አስተያየታቸው ቀደም ብለው የቤልጂየምን መንግስትም ነቅፈዋል - እንደልባቸው የሚናገሩት ትራምፕ፡፡ “ባለፈው ዓመት በፓሪስ ለተፈፀመው የሽብር ጥቃት ተጠርጣሪ ነው ተብሎ ከቀናት በፊት በቤልጂየም የተያዘውን ሳላህ አብዲሰላም፣ የቤልጂየም ባለስልጣናት በቶርቸር ቢያሰቃዩት ኖሮ የጥቃቱን እቅድ በፍጥነት ስለሚናገር፣ አደጋውን ቀድሞ መከላከል ይችሉ ነበር” ሲሉ ለሲኤንኤን ጋዜጠኛ ዎልፍ ብሊትዘር ነግረውታል፡፡
የቴክሳሱ ሴናተርና የፕሬዚዳንታዊ ምርጫው እጩ ተፎካካሪ ቴድ ክሩዝ በበኩላቸው፤ በአሜሪካ የሚገኙ የሙስሊም መኖሪያ አካባቢዎች ላይ ፖሊስ ቅኝት ማድረግ አለበት ብለዋል፡፡ ሃሳባቸው በእነ ሂላሪ ክሊንተን ውድቅ ቢደረግም፡፡ ስድብን እንደ መዝናኛ የያዙት የሚመስሉት ዶናልድ ትራምፕና ተፎካካሪያቸው ቴድ ክሩዝ፤ የፖለቲካ ጦርነታቸውን ከሰሞኑ እስከ ግል ህይወታቸው (ገበናቸው) ድረስ በመውሰድ በሚስቶቻቸው ጭምር መነቋቋር እንደጀመሩ CNN ዘግቧል፡፡
ነገርዬው ያላማራቸው የቴክሳሱ ሴናተር ቴድ ክሩዝ ታዲያ በትዊተር ገፃቸው ላይ እንዲህ ሲሉ ፃፉ፤ “ዶናልድ፤ የቃላት ጦርነቱን ከእኔው ጋር ብቻ ቢያደርገው ይሻላል፤ “Heidi is way out of his league” ሄይዲ (ባለቤታቸው ናት) አትመጥነውም፤ ትልቀዋለች” … ሆኖም ግን ክሩዝ አሁንም ከዘለፋ አላመለጡም፡፡
ሚስቱን ለመግለፅ የተጠቀመባት አባባል ከኦስካር አሸናፊው ማይክል ዳግላስ “The President” (1995) ፊልም የሰረቃት ናት ሲሉ ትራምፕ ክሩዝን ወንጅለዋል፡፡ “ዋሾው ክሩዝ .. የውጭ ፖሊሲ ከእኔ ላይ ሰረቀኝ … አሁን ደግሞ ከዳግላስ ፊልም ላይ አንዲት አባባል ሰረቀ …  ታማኝነት የጎድለው ፖለቲከኛ ማለት ይሄ ነው” በማለት በትዊተር ገፃቸው ላይ ላይ አሰፈሩ፡፡ በፊልሙ ላይ የዳግላስ ገፀ ባህርይ ስለ ሴት ጓደኛው ሲናገር፤ “If you want a character debate BoB, you better stick with me because Sydney Ellen Waid is way out of your league” ይላል፡፡ የክሩዝ ጥፋት አባባሉን መጠቀማቸው ሳይሆን ምንጭ አለመጥቀሳቸው መሆኑን አንዳንድ ሚዲያዎች ጠቁመዋል፡፡
አሁን ሴናተሩ ወደ ልምምጥ የገቡ ይመስላል (የሚስት ነገር ሆኖባቸው ነዋ!) እናም በትዊተር ገፃቸው እቺን አሰፈሩ፤ “ዶናልድ፤ ልበኛ ወንዶች ሴቶችን አይዘልፉም፤ ሚስትህ ውብ ናት፤ ሄይዲም የዘላለም ፍቅሬ ናት” (አንድዬ ይርዳቸዋ!)
በነገራችን ላይ ትራምፕ የስድብ ሱስ ያለባቸው ሁሉ ይመስሉኛል፡፡ በእኛ አገር ቢሆን “ሳይቆነጠጡ ያደጉ” ሊሆኑ እንደሚችሉ እገምት ነበር፡፡ የተሳዳቢነታቸውን ነገር በተመለከተ ግን የCNN ዘገባ በመረጃዎች አረጋግጦልኛል፡፡ ወደ ፕሬዚዳንታዊ የምርጫ ዘመቻ ከገቡ ወዲህ ብቻ 200 ሰዎችን … ቦታዎችን … ነገሮችን (ቁሶች) ተሳድበዋል - ትራምፕ፡፡ ለምሳሌ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ኦፊሽያል ቢሮ ውስጥ ያለውን ንግግር ማድረጊያ (አትሮንስ) ለምን እንደጠመዱት አይታወቅም፤ “በኦቫል ቢሮ የሚገኘው አትሮንስ ግራ አጋቢ ይመስላል፤ ደስ አይልም” ሲሉ ነቅፈውታል፡፡ ትራምፕ አገራትንም አይምሩም፡፡ የአሜሪካ አጋር ናት የምትባለውን እንግሊዝን፤ “ከባድ የሙስሊም ችግራቸውን ለመሸፋፈን መከራቸውን ይበላሉ” ብለዋታል፡፡ ለጋዜጠኞችማ ፈጽሞ አይመለሱም፡፡ “New Day” የተሰኘውን የCNN የዜና ፕሮግራም፤ “በደንብ አላስተናገዱኝም፤ ከአሁን በኋላ አልመለከታቸውም” (ይሄማ ከምስጋና እኩል ነው - ለትራምፕ!) ጄኔፈር ሩቢን የዋሺንግተን ፖስት ጦማሪ (blogger) ናት፡፡ ዶናልድ ትራምፕ አፍ ውስጥ ስትገባ ምን ተባለች? “ከዶማዎቹ ጦማሪያን አንዷ ናት፤ ከማርኮ ሩቢዮ ጋር ፍቅር ይዟታል” ሲሉ ወረፏት፡፡ (ይታያችሁ! ሩቢዮ እኮ ባለትዳርና ተፎካካሪያቸው ነው!)
የሳውዝ ካሮሊና ገዢ የሆኑትን ኒኪ ሃሌይ ምን ቢሉ ጥሩ ነው? “የሳውዝ ካሮሊና ህዝብ በኒኪ ሃሌይ ያፍራሉ” በማለት ዘለፋ ሰንዝረዋል፡፡ እንደ ዲሞክራቶቹ ሂላሪ ክሊንተንና ባራክ ኦባማ የተሰደበም፣ የተዘለፈም ግን የለም፡፡ ሂላሪ ላይ ከሰነዘሩት ዘለፋ ሁሉ በእጅጉ ምግባር የጐደለውና “አሳዳጊ የበደላቸው” የሚያሰኘው፤ “ሂላሪ ክሊንተን ባሏን ማርካት ሳትችል፣ የአሜሪካን ህዝብ ማርካት እችላለሁ ብላ እንድታስብ ያደረጋት ምንድን ነው?” ሲሉ የጠየቁት ነው፡፡ (ከወደፊቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ይሄን መስማት ይሰቀጥጣል!) ሂላሪ ላይ የተሰነዘረው ይሄ ብቻ ግን አይደለም፡፡ “ትልቅ የብሄራዊ ደህንነት ስጋት”፣ “ምኗም ለፕሬዚዳንት የማይሆን”፣ “ደካማና ውጤት የለሽ”፣ “በሙስና በእጅጉ የተካነች…” እኒህ ሁሉ ከትራምፕ ወደ ሂላሪ የተወረወሩ ስድቦች (ዘለፋዎች) ናቸው ( “ያልተቆነጠጡ” ቢባሉ አይበዛባቸውም!)
 በዶናልድ ትራምፕ እንዳመጣላቸው መናገር ግራ የተጋባውና ስጋት የገባው አንድ አሜሪካዊ “በዚህ አኳኋንዎና አነጋገርዎ” ጋዜጠኛ ዋይት ሃውስ ሲገቡስ?” የሚል ጥያቄ ሰነዘረ፡-
ትረምፕም በፍጥነት፤ “አጐቴ በትልቅ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ፕሮፌሰር ነው” አሉ፡፡ ሲያስቡት ግን ዋይት ሃውስ የሚገቡት እሳቸው ናቸው፡፡ እናም እንዲህ ሲሉ አስተካከሉ፤ “እኔም ብሆን በጥሩ ዩኒቨርሲቲ ነው የተማርኩት”
የሪል እስቴቱ ከበርቴው የራሳቸውም ዩኒቨርሲቲ እንዳላቸው ሰምቻለሁ - ትረምፕ ዩኒቨርሲቲ! ይሄ ሁሉ ግን ዩኒቨርሲቲ መማራቸውን አያረጋግጥም (እኔማ በደጃፉም ያለፉ አይመስለኝም!) ከሁሉም ያሳዘነኝ ግን ምን መሰላችሁ…እኛ ሁሉ የምንኮራበትና የምንመካበት “የአሜሪካ ዲሞክራሲ” በአምባገነኑ ትራምፕ ሊደፈጠጥ መሆኑ ነው! (አሜሪካን ፈጣሪ ይሁናት!)

Read 11291 times