Print this page
Saturday, 09 April 2016 11:52

መብራትም--- ውሃም---- ስልክም--- በ“ሳተላይት”?!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(26 votes)

· ያኔ በልበሙሉነት ----- “ሳተላይት ውስጤ ነው” እንላለን!!
· የቲቪ ተመልካችን “ጠብቁኝ” እያሉ፣ ቫኬሽን መውጣት ቀረ!
· “የቢራ ምርቶች፤ የጠጃችንን ህልውና አደጋ ላይ ጥለውታል”
   ባለፈው ሳምንት የአርቲስቶችን መንደር አናወጠ የተባለው “ቃና” ቲቪ አጀማመሩ ያስደስታል፡፡ (#የሚወጣ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል” እንዲሉ!) ጥራት ያለው ምስል ---- ማራኪ ቋንቋ-- የተቀናጀ የተዋንያን አነጋገር ወዘተ---ብዙዎች ሲያደንቁት፣ ሲደመሙበት ሰምቼአለሁ፡፡ በእርግጥ ለማመስገንም ሆነ ለመውቀስ ጊዜው ገና ነው፡፡ ሆኖም አጀማመሩ አዘላለቁን ይጠቁማል፡፡  እናም ትልቅ ተስፋ ነው፡፡ በነገራችን ላይ የውጭ ፊልሞችን በአማርኛ ትርጉም ማየት አይደላኝም፡፡ “ፎርጂድ ፊልም”----- ያየሁ ነው የሚመስለኝ፡፡ (የአማርኛ አልወጣኝም!) እናላችሁ …. ከተመለከትኩ አይቀር የእንግሊዝኛ ፊልሞችን (በትላልቅ ዲክሽነሪ ታግዤም ቢሆን!) አያለሁ እንጂ በሁለተኛና ሦስተኛ ቋንቋ የተተረጎመ (ከአረብኛ - እንግሊዝኛ - አማርኛ!) አልሞክረውም!! ቃና በአማርኛ ተርጉሞ ማቅረቡ ግን ግሩም ነው፡፡  
እናላችሁ … “ቃና” ቲቪ ደስ የሚለኝ ትርጉም ፊልሞችን እኮመኩምበታለሁ በሚል ጉጉትና ተስፋ አይደለም፡፡ (ትርጉም አይደላኝም ብያችኋለሁ!) ግን በቃ ----- በአንድ ጊዜ በዚህን ያህል መጠን ለተመልካች አማራጭ ፊልሞችን (“ፊልም በየዓይነቱ” በሉት!) ያቀረበ ጣቢያ አይቼ ስለማላውቅ “ቃና” ተመቸኝ፡፡
 አንዱ #ውለታቢስ” የቃናን የምስል ጥራት ሲገልፅ፤“ቃና፤ኢብኮ ስቲም ገብቶ ማለት ነው” ብሏል፡፡ (የ50 ዓመት ባለውለታችን እኮ ኢቢሲ ነው!) ወደ ጀመርኩት ልመለስ፡፡ እንደሚመስለኝ ቃናን የወደድኩት የቲቪ “ማዕዳችንን” በአንዴ ስለሞላልን ነው፡፡ ዓይናችንን ከስስትና ከረሃብ ስለታደገልንም ይመስለኛል፡፡ በቃ የምናየው ነገር ስላንበሻበሸን፡፡ እንዴ … ዋናውን ነገር ረስቼው … ሌላው ቃናን የወደድኩበት ምክንያት ወደ ስርጭት ከመግባቱ በፊት… ህዝቡ ምን ይመለከታል? ምንስ ነው ምርጫው? ብሎ ጥናት በማድረጉ ነው፡፡ (አድርጌአለሁ ብሏል!) ከጥናቱ ውጤት ተነስቶም የውጭ ፊልሞችን (ጃፓን - ህንድ - ቻይና - ቱርክ--) ወደ አማርኛ በማስተርጎም እነሆ በረከት አለን፡፡ እንደ ኩባንያ ወደ ቢዝነስ ከመግባቱ በፊት የገበያ ጥናት ማድረጉ ምን ያስገርማል ---- ልትሉኝ ትችላላችሁ፡፡ ነገር ግን የ50 ዓመት ባለውለታችን ኢቢሲ፤ እንኳን ሲጀምር አሁንም እንኳ ትዝ ብለነው እናውቃለን? ስለ ተመልካቹ ጥናት አድርጎ ያውቃል? የእኛ ደስታና እርካታ ለሱ ምኑ ነው? እንደውም አንዳንዴ ------ ደስ አላቸው ከተባለ ንድድ ብሎ የሚያድር ይመስለኛል፡፡ ባይሆንማ ኖሮ ደህና ፕሮግራሞች በአጭሩ አይቀጩም ነበር፡፡ ዕድሜ ይኖራቸዋል፡፡ ግን አላየንም፡፡ እናላችሁ---ተመልካች - ተኮር የቴሌቪዥን ጣቢያ ሳገኝ ደስ ባይለኝ ነበር የሚገርመው፡፡  
እኔና ፊልም የሚያጠና አንድ ወዳጄ፤ባለፈው ሳምንት በ “ቃና” ቲቪ መጀመር ተደናግጠው፣የተደናገጠ መግለጫ ያወጡትን የኪነጥበብ ማህበራት አፍ ለአፍ ገጥመን አማናቸው፡፡ እኔ የምለው ግን ---- የሰዓሊያን ማህበር ደሞ ምን ሆንኩ ብሎ ነው ጀማውን የተቀላቀለው? በቅርቡ እንዲህ የሚል መግለጫ እንደሚያወጣ አትጠራጠሩ፡፡ #ባህል---ትውልድ---ልጆቻችን---ወዘተ--ብለው አጭበርብረውኝ ነው ---- ህዝቡን ይቅርታ እጠይቃለሁ” (ፋሽን ነዋ!)  የውጭ ስዕሎች ወደ አማርኛ እየተተረጎሙ ሊቀርቡ ነው ተብሏል እንዴ?   
እናላችሁ-----ያ ፊልም የሚያጠና ወዳጄ፤ የውጭ ፊልሞች በአማርኛ ተተርጉመው መቅረባቸው --- አጭር ዕድሜ ያለውን የቴሌቪዥን ድራማ ታሪካችንን ዶግ አመድ ያደርገዋል---የባህል ወረራ ያስፋፋል----ትውልድ ይገድላል--- ወዘተ ያሉት ጉዳይ በጣም ነው ያሳቀው፡፡ እናም እንዲህ አለኝ፤“የቢራና የወይን ጠጅ መምጣት፣ለጠላና ለጠጅ ህልውና አደጋ ነው----እንደማለት እኮ ነው?”
እውነቱን ነው፡፡ እንግዲህ ------ ቢራና ወይን ጠጅ አገራችን ከገቡ ስንት ዘመናቸው? ነገር ግን ማንም ለማንም አደጋ ሲሆን አላየንም፡፡ ሁሉም የምርጫውን ይጎነጫል፡፡ በርግጥ በጠጅ ጠመቃና ሽያጭ የሚተዳደሩ ግለሰቦች፣ በማህበር የመደራጀት ዕድል ቢያገኙ፣ “የቢራ ምርቶችና የድራፍት ዓይነቶች እንደ አሸን መፍላት፣ የጠጅ ጠጪውን ቁጥር አውርዶብናል” የሚል ስስ ቅሬታ ሊሰነዝሩ ይችላሉ፡፡ “መንግስት የቢራ ፋብሪካዎችን ይዝጋልን----እኛ ብቻ የባህሉን ጠጅ በውድም በግድም ለጠጪው እንጋተው” የሚል ድፍረት ግን አይሞካክሩም፡፡ (እውነታውን ያውቁታላ!) ከመሃላቸው ልበ ብሩህ ከተገኘ ደግሞ ------ ጠጅና ጠላን ወደ ቢራ ደረጃ ከፍ ለማድረግ ኬሚስቶችን ቀጥሮ፣ ጥናትና ምርምር ያደርግ ይሆናል፡፡ በቃ!!!
እኔ የምላችሁ… ይሄ “ሳተላይት” የሚሉት “ምትሃተኛ” ቴክኖሎጂ ------ በአንድ ጀንበር ከሰው እኩል አደረገን አይደል?! (ከአገራትም ጭምር እንጂ!) ይታያችሁ … ለግማሽ ክ/ዘመን ከንጉሱ ጊዜ ጀምሮ አየሩን በሞኖፖል ተቆጣጥሮት የቆየው ኢቲቪ ነበር፡፡ (እነ “ቃና” ሲመጡ ማለቃቀስ የነበረበት እኮ ኢቲቪ ነው!) ከዕለታት አንድ ቀን ደሞ ኢቢኤስ ድምፁን ሳያሰማ ወይም ሳንሰማ (በሳተላይት) ቤታችን ገብቶ አገኘነው፡፡ የዛሬ 7 ወር ግድም መስከረም ላይ በጦቢያ ምድር የምናውቃቸው ኢቢሲ እና ኢቢኤስ ብቻ ነበሩ፡፡ ዛሬስ? ናሁ --ቃና --- ዋልታ --- ENN …. የጆሲ ቻናል ….ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ 5 የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ማለት ነው፡፡ መስከረም እስኪጠባ ደግሞ ሌላ 5 አናጣም፡፡ ዕድሜ ለሳተላይት ቴክኖሎጂ!! እርግጠኛ ነኝ ---- ብሮድካስቲንግ የሚሰጠውን ጣቢያ ብንጠብቅ ኖሮ-----በአንድ ጀንበር ተዓምር አናይም ነበር፡፡  (20 ዓመት ጠበቅን እኮ!)  
እናላችሁ ---- ሳተላይት በአገራችን የፈጠረውን የሚዲያ አብዮት (ተዓምር) ስመለከት----- በውስጤ አንድ ነገር ተመኘሁ (የሞኝ ቢመስልም!) ምን መሰላችሁ? ልክ እንደ ቴሌቪዥን ጣቢያዎቹ፣ መብራትም--- ውሃም---- ስልክም---- በሳተላይት አማካኝነት ቤታችን ድረስ ሰተት ብሎ እንዲገባልን ተመኘሁ፡፡ (ያለ ጣጣ ፈንጣጣ!) ከሆነ አይቀር ደግሞ አንድ ብቻ አይደለም (እንደ ቲቪው አማራጮች ያሉት!)
ዋናው ሃሳቤ ለዓመታት በእነዚህ ዘርፎች ያየነውን አበሳ ለመካስና ዳግም እንዳይገጥመን ለማድረግ ነው፡፡ ባለቤቱ ኢህአዴግ መራሹ መንግስት፣ ብሎ ብሎ አልሆነለትም፡፡ ለዚህ ነው ከተጨባጭ መፍትሄ ህልም ወደሚመስል ምኞት የገባሁት፡፡ (የጨነቀው እርጉዝ ያገባል አሉ!) ከምሬ ነው የምላችሁ ---- ምኞቴ ከተሳካ አደባባይ ወጥተን----- “ሳተላይት ኔትዎርክ ውስጤ ነው” እንላለን!!! (ስለት እንደማግባት አስቡት!) እኒህን ሁሌ አገልግሎቶች የኢህአዴግን ፊት ሳናይ ቤታችን ድረስ ከመጣልን (ከቴሌ ቁጥጥርም ተገላገልን ማለት ነው!) እንደ አቡነ ዘበሰማያት ብንደግመውስ?! አዎ ---- “ሳተላይት ኔትዎርክ ውስጤ ነው!!!” (አባባሉ ለዛሬ ብቻ በውሰት የተወሰደ ነው፤“ቃና ውስጤ ነው” ከሚለው!)
ሠናይ ሰንበት!!
Read 6983 times