Print this page
Saturday, 23 April 2016 10:32

“-- ውስጤ ነው!” ---- የምለው ፓርቲ አጣሁ!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(22 votes)

· እንደ “ቃና” ቀውጢ የሚፈጥር ተቃዋሚ ፓርቲ ያስፈልገናል!
· “በአገሬ ፊልም እኮራለሁ!” የሚል ንቅናቄ መፋፋም አለበት …
· ኢህአዴግ፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ከዛምቢያ ቢያስመጣስ!?
 
      የሰሞኑን “ድንቅና ብርቅዬ ዜና” ሰምታችሁልኛል? (ቀላል ብርቅዬ ነው!) የዜናው ምንጭ ደሞ ሩቅ እንዳይመስላችሁ … እዚሁ አህጉራችን ውስጥ ነው - ዛምቢያ!! እናላችሁ … ይህቺ አፍሪካዊት አገር በመጪው ነሐሴ ወር ብሔራዊ ምርጫዋን ለማካሄድ ሽር ጉድ በማለት ላይ ትገኛለች፡፡ እኛን ጨምሮ በብዙዎቹ የአፍሪካ አገራት እንደተለመደው በዛምቢያም 13 አነስተኛ (ጥቃቅን አልወጣኝም!) የአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች “ናሽናል ኦፖዚሽን አሊያንስ” የሚል ጥምረት ፈጥረው በጋራ ሲሰሩ መቆየታቸውን ምንጮች ይገልፃሉ፡፡ (የኛም ተቃዋሚዎች ምርጫ ሲደርስ፣“ሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ” ይተረትባቸው የለ!)
 እናሳ? እናማ… የዛምቢያ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥምረት፤ ሰሞኑን በተቃዋሚዎች ታሪክ ተሰምቶ የማይታወቅ በዓይነቱ ለየት ያለ መግለጫ አውጥቷል። (በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለምም ጭምር!)  “ናሽናል ኦፖዚሽን አሊያንስ” ያወጣው መግለጫ ምን ይላል መሰላችሁ? “ገዢው ፓርቲ የጀመረውን ልማት እንዲቀጥል ስለምንፈልግ በነሀሴው ምርጫ ድምፃችንን ለፕሬዚዳንት ኤድጋር ሉንጉ እንሰጣለን” እኔ የምለው … ምኑ ላይ ነው ታዲያ ኦፖዚሽን መሆናቸው? (“በፓርላማ የኢህአዴግ ደጋፊ፣የግል ተመራጭ” የነበሩትን ሰውዬ አስታወሱኝ!)
የአገራችን ተቃዋሚዎች፤የጥምረቱን መግለጫ ሲሰሙ ወይም ሰምተው ከሆነ (በመረጃ እጥረት ይታማሉ ብዬ እኮ ነው!) ምን ይሉ ይሆን? እኔ ግን ስጠረጥር (የደንብ 5” ጠርጣሪዋ ውዴ ትዝ አለችኝ!) እንዲህ የሚሉ ይመስለኛል፡፡ “ከእነስማቸውም ጥቃቅን ተቃዋሚዎች ናቸው!! … እነዚህ ሃቀኛ ተቃዋሚዎች ሳይሆኑ እንደኛ አገር ከገዢው ፓርቲ ቀለብ የሚሰፈርላቸው አጋር ፓርቲዎች ናቸው!!”  (ግን እኮ ዛምቢያና ጦቢያ ለየቅል ናቸው!) ምን ለማለት ነው… እውነቱን ለማወቅ በአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ላይ ደህና ስፖንሰር ፈልጎ ጥልቅ ጥናት ማድረግ ይፈልጋል፡፡ ከዚያ በፊት የሚሰጥ ማናቸውም ድምዳሜ ግን ከሃሜት የዘለለ አይሆንም፡፡ እናንተ-----ኢህአዴግን እርስት አደረግሁት እኮ! (“ማን ላይ ተቀምጠሽ ----”አሉ) እናላችሁ ----ኢህአዴግ ስለ ዛምቢያ የተቃዋሚዎች ጥምረት ምን የሚል ይመስላችኋል? እኔ ጠርጥር ከተባልኩ ግን “ልማታዊ ተቃዋሚዎች ይሏል እንዲህ ነው!!” በማለት እንደሚያወድሳቸው በእርግጠኝነት እጠረጥራለሁ፡፡ (ጥርጣሬዬ በልምድ ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ይታወቅልኝ!) እናላችሁ----ለወደፊት ኢህአዴግ ተቃዋሚዎችን ከዛምቢያ ሁሉ ሊያስመጣ ይችላል፡፡ (የአገር ውስጦቹ ጸባይ የላቸውማ!)
ከዛምቢያ እንውጣና ወለም ዘለም ሳንል ደሞ ወደ አገራችን እንግባ፡፡ እኔ የምለው ግን … የአገራችን ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአገር አማን እንዲህ የሚያናክሳቸው ምንድን ነው? (“ስልጣን በሌለበት የስልጣን ሽኩቻ?” አሉ!) ደሞ እኮ አንደኛው ፓርቲ ከሌላኛው ፓርቲ ጋር ቢሆን የአባት ነው፡፡ የሚገርመው እርስ በርሳቸው መሆኑ ነው፡፡ አንድ ፓርቲ!! እናላችሁ----የመኢአድ ሲገርመን ሰማያዊ ፓርቲ ብሶበት ቁጭ አለ፡፡ (“የት ይደርሳል የተባለ ዛፍ ቀበሌ ቆረጠው” አሉ!) እንዴ-----ከመቼው የአጋች ታጋች ድራማው ተጠናቆ … ከመቼው የገንዘብ እጥረት ተፈጥሮና ለቢሮ ኪራይ የሚከፈል ጠፍቶ … ከመቼው ፓርቲው የመበታተን አደጋ ላይ እንደደረሰ … ግርም እኮ ነው የሚላችሁ፡፡ (ጠቡን ሌሊት ሌሊትም ሳያካሂዱት አይቀርም!) የምርጫ ሰሞን ቢሆን እንኳን በኢህአዴግና በምርጫ ቦርድ ይሳበብላቸው ነበር፡፡ (“ኢህአዴግና ምርጫ ቦርድ ከደሙ ንፁህ ናቸው” … አልወጣኝም!) አሁንስ ሰበቡ ማን ይሆን? (“ሰበቡ…” አለች አስቱ!) አሁን የገባኝ ግን ምን መሰላችሁ? ኢህአዴግ ቢኖርም ባይኖርም----- ተቃዋሚዎች እርስ በእርስ ከመጠፋፋትና ከመበታተን ወደ ኋላ አይሉም፡፡ እንደውም የኢህአዴግ መኖር ዕድሜያቸውን ሳያራዝመው አልቀረም። አያችሁ-----ሁሉም ትኩረታቸውን በአውራው ፓርቲ ላይ ሲያደርጉ እርስ በርስ የመነቋቆር ዕድላቸው ይቀንሳል። (የጋራ ጠላት አላቸዋ!) ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ኢህአዴግም በየአቅጣጫው በመወጠሩ እንደ ደጉ ዘመን” መተነኳኮስ አይታሰብም፡፡ (እዬዬም ሲዳላ ነው” አሉ!) በዚህ መሃል ተቃዋሚዎች ምን ይዋጣቸው? (ሥራ ከምፈታ ልጄን ላፋታ” ሳይሆን አይቀርም!)
እናላችሁ … ባለፈው ቅዳሜ እዚሁ ጋዜጣ ላይ “ሰማያዊ ፓርቲ አደጋ ላይ ነው” በሚል ርዕስ የወጣውን ከፓርቲው ሊቀመንበር ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ አነበብኩና አንጀቴ ቅጥል ቢልላችሁ… እንዲህ አልኩኝ - በሆዴ! “እንደ ‹ቃና ቲቪ›፤ የፖለቲካውን ሰፈር የሚያናውጥ አዲስ ተቃዋሚ ፓርቲ ይዘዝባችሁ!” (እርግማን መሆኑ ነው!)
እውነት ግን እንደ “ቃና” ዓይነት አቧራ የሚያስነሳ (ጣቢያው በአርቲስቶች መንደር እንደፈጠረው ዓይነት ማለቴ ነው!) ተቃዋሚ ፓርቲ ድንገት በጦቢያ የፖለቲካ ንፍቀ ክበብ ላይ ቢከሰት …ምን ትላላችሁ? (እኔስ አንጀቴ ቅቤ ይጠጣ ነበር!) ችግሩ ግን ከነሱ የተሻለ ፓርቲ ከሆነ ተቃዋሚዎቹ የይመስል ህብረት ፈጥረው ያወግዙታል፡፡  
በተለይ ተቃዋሚ ፓርቲው ሥልጡንና በጦቢያ የፖለቲካ መድረክ ላይ ጉልህ ለውጥ እንደሚፈጥር ፍንጮች ከታዩ … አስተማማኝ ደጋፊዎችና የማይነጥፍ ገቢ ያለው ከሆነ … ያረጀ ያፈጀውን የጥላቻና የመጠፋፋት የፖለቲካ ባህል ተረት በማድረግ የዲሞክራሲ ባህልን ለመትከል የሚታትር የ21ኛው ክ/ዘመን ፓርቲ መሆኑ ከታወቀ ---- ጥቂት የፓርቲው መስራቾች በአሜሪካና አውሮፓ ዩኒቨርሲቲዎች የተማሩና የተመራመሩ መሆናቸው ከተሰማ … ከሁሉም በላይ ደግሞ ህዝብ ምን ይፈልጋል … ችግሩና በደሉስ ምንድን ነው? እያለ ድምፁን የሚያስተጋባለት ከሆነና በህዝብ የመወደድ አዝማሚያ ከታየበት ----- በምርጫ ቦርድ ተመዝግቦ፣ህጋዊ ዕውቅና ከማግኘቱ በፊት ልክ እንደ “ቃና ቲቪ” በተቃውሞ እንደሚናጥ ጠርጥሩ፡፡ ወዳጆቼ፤ “ፈራን… ውድድር … ፈራን … ፉክክር … ፈራን… መብለጥ---- መበለጥ --- ፈራን!!” ነው እኮ ነገሩ፡፡ (በፖለቲካው ደሞ ይብሳል!)
እናላችሁ … በየ5 ዓመቱ ምርጫ እየጠበቁ ትብብር---ጥምረት---ግንባር----ቅንጅት----ውህደት---ስምረት----ወዘተ በሚል ህብረት ለመፍጠር ሲታትሩ የከረሙት የተቃዋሚ ፓርቲዎች በአንድ ባላንጣቸው ላይ ክንዳቸውን ለማንሳት በከፍተኛ ወኔ ይነሳሳሉ፡፡ አዲሱ ተቃዋሚ ፓርቲ፤ ህጋዊ ዕውቅና ከማግኘቱ በፊት አንድ የሆቴል አዳራሽ ተከራይተው በመሰብሰብ ሴራቸውን ይዶልታሉ። “የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ጥምረት ጊዜያዊ ኮሚቴ” ሲሉም ለራሳቸው ጊዜያዊ መጠሪያ ይሰይማሉ፡፡ ከዚያስ? ጦርነቱ ተጀመረ ማለት እኮ ነው። በነጋታው የአገሪቱን ሚዲያዎች ከሀ-ፐ ይጠሩና የተቃውሞ መግለጫቸውን ይሰጣሉ - በአርበኛነት ስሜት ተሞልተው፡፡ በዚህ ብቻ ረክተው ግን እጃቸውን አጣምረው አይቀመጡም፡፡ ለጠ/ሚኒስትሩ፣ ለምርጫ ቦርድ፣ ለፓርላማና ለኢህአዴግ ፅ/ቤት…የአቤቱታ ደብዳቤ ያስገባሉ፡፡ (ለነገሩ ሸምግሉን ብለው ጠ/ሚኒስትሩ ድረስ ሄደው የለ እንዴ?!)
ከዚያስ? ከዚያማ እንዲህ የሚነበብ ወይም የሚደመጥ የሚዲያ ዘገባ እንጠብቃለን፡-
የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥምረት ጊዜያዊ ኮሚቴ፤ ለጠ/ሚኒስትሩ፣ ለምርጫ ቦርድ፣ ለፓርላማና ለኢህአዴግ ፅ/ቤት ባስገባው የተቃውሞ ደብዳቤ፤ የአዲሱ ተቃዋሚ ፓርቲ ዕውቅና ማግኘት የምዕራባውያን ልቅ የዲሞክራሲ ባህልን በህዝቡ ላይ በመጫን፣ የተረጋጋውን የአገሪቱን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ከማናወጡም በላይ ህብረተሰቡ ከንቃተ-ህሊናው በላይ በመብት ጥያቄዎች ተሞልቶ ለአመጽ እንዲነሳሳ ስለሚያደርግ መንግስት በአስቸኳይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወስድ አበክሮ ጠይቋል። አዲሱ ፓርቲ የፖለቲካ ፕሮግራሙን መቶ በመቶ ከአሜሪካና አውሮፓ አገራት ቀርጾ ማምጣቱም መንግስት በጽናት ሲዋጋው የኖረውን የኒዮ-ሊበራል ርዕዮተ ዓለም የሚያንሰራፋ በመሆኑ፤ ፓርቲው ፕሮግራሙን 70 በመቶ የአገር ውስጥ፣ 30 በመቶ ብቻ የውጭ በማድረግ ዳግም እንዲቀርጽ መንግስት ጫና ሊያሳድርበት ይገባል ሲል አሳስብል -ጥምረቱ፡፡
ይሄ ካልሆነ ግን እዚሁ ተፈጥረው፣ እዚሁ ከህዝቡ ጋር ያረጁ ያፈጁ ተቃዋሚዎች ህልውና ለአደጋ ይጋለጣል ብሏል - በመግለጫው፡፡ ጥምረቱ በዚህ ብቻ ግን አያበቃም፡፡ የፓርቲው አብዛኞቹ አመራሮች ዳያስፖራ መሆናቸውን በመጥቀስ፣ መንግስት የገንዘብ ምንጫቸውን እንዲመረምር አበክሮ ጠይቋል - የቀለም አብዮት” ይቀሰቅሳሉ የሚል ስጋት እንዳለው በመግለጽ። (“ከአልሻባብ ድጋፍ ያገኛል” አለማለታቸውም እነሱ ሆነው ነው?)
እናላችሁ … ህልውናዬ አደጋ ላይ ነው ብሎ ሲሰጋ እንኳንስ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥምረት የኪነ ጥበብ ማህበራት ጥምረትም ሌላውን እንዴት ያለ መረጃ በጭፍን እንደሚወነጅል በቅርቡ ታዝበናል፡፡ ከዚህ አንፃር … በተወዳጅነት አገሩን ሊቀውጠው ይችላል ተብሎ የተሰጋን አዲስ ተቃዋሚ ፓርቲ፤ “ከሽብርተኛ ቡድን ጋር ይሰራል” ብሎ ስም እስከ ማጥፋት ቢደረስም ያሳዝነን ይሆናል እንጂ ፈጽሞ ሊገርመን አይችልም፡፡ የግንቦት 2007 ምርጫ ሰሞን ሰማያዊ ፓርቲን አይሲስ ብሎ ለመወንጀል ዳር ዳር ሲባል ታዝበናል፡፡ ለምርጫ ቅስቀሳ 92ሚ.ብር መድቧል በሚልም የገንዘቡ ምንጭ ይጣራ የሚል ፌዝም ሰምተናል፡፡ (አሁን እኮ ፓርቲው ለቢሮ ኪራይ የሚከፍለው 18ሺ ብር የለውም ተብሏል!)  
ይሄ ሁሉ ግን ምን መሰላችሁ? “ፈራን … ውድድር … ፈራን … ፉክክር … ፈራን … በሀሳብ ማሸነፍ ------ መሸናነፍ ------ ፈራን  ---  ፍቅር ----ፈራን--!!” ነው!!
ሃቁን ልንገራችሁ አይደል … የናንተን ባላውቅም እኔ ግን “ቀውጢ” የሆነ የ21ኛው ክ/ዘመን “ፀዴ” ተቃዋሚ ፓርቲ ማየት አምሮኛል - ያውም --- ውስጤ ነው!!” የምለው! እስካሁን እኮ “ውስጤ ነው ----” የሚለውን እኮ በቴሌቪዥን ጣቢያ እንጂ በሌላ ጨርሶ አናውቀውም። እስቲ ከመለያየታችን በፊት የዓመቱን ምርጥ ጥያቄ ላሽራችሁ፡፡ ከሚከተሉት ምርጫዎች ውስጥ #ውስጤ ነው!” የምትሉትን በጥሞና ለመምረጥ ሞክሩ፡፡ ካገኛችሁ እሰየው፡፡ በደስታ መፈንጠዝ ነው፡፡ ካላገኛችሁም ችግር የለም፡፡ አንድ ሆንን ማለት ነው፡፡ ፍለጋው አያልቅም የሚለውን ዜማ በረዥሙ እያቀነቀንን ውስጤ ነው!” የምንለውን መፈለጋችን  ይቀጥላል፡፡ በሉ ምረጡ - (በታሪክ 10 ምርጫዎች የቀረቡበት የመጀመሪያው ጥያቄ ይሄ ሳይሆን አይቀርም፡፡)
A/ ኢህአዴግ   B/ ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ   C/ ኢዴፓ  D/ ሰማያዊ   E/ ኢቲቪ/ኢቢሲ     F/ ኢትዮ ቴሌኮም    G/ ፓርላማ    H/ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር  I/ ሁሉም መልስ ነው   J/ መልሱ አልተሰጠም
(ፍለጋው አያልቅም!! መዝፈንና መፈለግ ስለሚለያይ አንድዬ ይርዳን!!)

Read 6178 times