Saturday, 25 February 2012 13:53

የአሜሪካ ኃያልነት አደጋ አንዣቦበታል

Written by  ጥላሁን አክሊሉ
Rate this item
(1 Vote)

የዓለማችን ልዕለ ኃያል አገር የሆነችው አሜሪካን ያለፉትን ስድስት አስርት ዓመታት ኃያልነቷን አስጠብቃ ያደረገችው ጉዞ ውጤታማ ነበር ለማለት ይቻላል፡፡ በተለይም በዓለም ዙሪያ በሰፊው የዘረጋችው የፖለቲካና የኢኮኖሚ መዋቅሯ ከወታደራዊ ጡንቻዋ ጋር ተደምሮ ፍፁማዊ ኃያልነት (absolute powerful) እንድትጎናጸፍ አስችሏታል፡፡ ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለንባብ የሚበቁ የሕትመት ውጤቶች፣ የአሜሪካን ኃያልነት አደጋ እያንዣበበት እንደሆነ እየዘገቡ ነው፡፡

የአሜሪካንን ውድቀት እየዘገቡ ያሉት ደግሞ እዚያው አሜሪካ የሚገኙት ፕሬሶች ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ የአሜሪካ ኃያልነት በቅርቡ እየተንከታኮተ እንደሚሄድ የሚገልጹ ሲሆን፣ የተቀሩት ደግሞ የአሜሪካ ኃያልነት መውደቅ ከጀመረ መሰንበቱን እየዘገቡ ይገኛሉ፡፡

ለዚህም ማስረጃ አሜሪካ በዓለም አቀፍ ፖለቲካ ላይ ያላት የበላይነትና ተጽዕኖ የመፍጠር አቅሟ ፈተና ውስጥ መግባቱን ይገልፃሉ፡፡ ለአብነትም የሚጡቅሱት በአረቡ ዓለም የተፈጠረውን ሕዝባዊ አመጽ ነው፡፡ የቅርብ ወዳጇ የነበሩት ሙባረክ በ18 ቀናት ሕዝባዊ አመጽ ስልጣናቸው ሲገረሰስ ዳር ቆሞ ከማየት ውጪ አጣብቂኝ ውስጥ ለገቡት ሙባረክ የፈየደችው ነገር አልነበረም፡፡ በተጨማሪም ሌሎች ወዳጆቿ የሆኑት የሳውዲ አረቢያው አብዱላህ ቢን አብዱላዚዝ እንዲሁም የባህሬኑ ሃሚዲ ቢን ኢሳ አል-ካሊፋ ላይ የተነሣውን ሕዝባዊ አመጽ መሪዎቹ እንዲወርዱ ባያደርግም ያለ አሜሪካ ጣልቃ ገብነት ሕዝቡ የነፃነትና የዲሞክራሲ ጥያቄዎችን አንስቷል፡፡

በሌላ በኩል በግብጽ በስልጣን ላይ ያለው ወታደራዊ መንግስት፣ ሕዝባዊ አመጽ እንዲነሣ ቀስቅሳችኋል በሚል ወደ 17 የሚጠጉ የአሜሪካንን ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ከዘጋ በኋላ፣ አሜሪካዊያኑም የፍርድ ቤት ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ ከአገር እንዳይወጡ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡ “አል-ሃረም” እና “አል ጎም ሃሪያ” የተባሉት የግብጽ ጋዜጦች፣ የግብጽ የአለም አቀፍ ግንኙነት ሚኒስትር ፋይዛል አቡልናንጋ በመጥቀስ የእስራኤልንና የአሜሪካንን ጥቅም ለማስጠበቅ ሥርዓት አልበኝነቱን አስፋፍተዋል በማለት አሜሪካዊያኑን ግብረ ሰናይ ድርጅቶች እንደነቀፏቸው፡፡

በሙባረክ የሥልጣን ዘመን የሙባረክ ቀኝ እጅ እንደሆኑ የሚነገርላቸው መሀመድ ሁሴን ታንታዊ ላለፉት 30 ዓመታት አሜሪካ ለአገራቸው በየዓመቱ 1.3 ቢሊዮን ዶላር ዕርዳታ መለገሷን እንደውለታ ቆጥረው ከአሜሪካ ጋር ግጭት ውስጥ ሊከታቸው የሚችል ነገር በማድረግ ከመቆጠብ ይልቅ የአሜሪካዊያኑን ድርጅት እንዲዘጋ አዘዋል፡፡ የሚገርመው አሜሪካ ባለፈው ዓመት ሙባረክን ለማውረድ አመጽ ሲካሄድ “ሙባረክ የሕዝቡን ድምጽ መስማት አለባቸው” ብትልም በሕዝባዊ አመጽ የተሳተፉት ወጣቶች ግን “የአሜሪካንን ጣልታ ገብነት አንፈልግም፣ አሜሪካ በአገራችን የውስጥ ጉዳይ አያገባትም” የሚሉ መፈክሮች ሲያስተጋቡ ነበር፡፡ በመሆኑም አሜሪካ በሕዝቡም ሆነ በግብጽ መንግስት ተቀባይነቷ ዋጋ አጥቷል፡፡

እ.ኤ.አ በ2003 ዓ.ም ወዳጇን እንግሊዝን ይዛ ወደ ኢራቅ በመዝመት የሳዳምን አገዛዝ ዶግ አመድ ካደረገች በኋላ የራሷን አሻንጉሊት መንግስት ማስቀመጧ ይታወቃል፡፡ ከስምንት ዓመት ቆይታ በኋላም በኢራቅ የነበሩት ወታደሮቿ ወጥተዋል፡፡ ይሁን እንጂ አሜሪካ የጠበቀችውን ያህል ኢራቅ የተረጋጋችና ለአካባቢው አገራት የዲሞክራሲ ተምሳሌት አልሆነችም፡፡ ወታደሮቿ ኢራቅ እያሉም ሆነ ከወጡ በኋላ ግድያዎችና ፍንዳታዎች በባግዳድ ቀጥለዋል፡፡

የሶሪያ መንግስት በሕዝቡ ላይ እያደረሰ ያለውን ጭፍጨፋ አስመልክቶ የአረብ ሊግ አገራት በተለያየ ጊዜያት ባካሄደው ስብሰባ ሳውዲአረቢያ፣ ኩዌት እና ዮርዳኖስ ከፍተኛ ማዕቀብ እንዲጣል ሲወተውቱ ኢራቅ ግን ድምጸ ተአቅቦ አድርጋለች፡፡ ይባስ ብለውም የኢራቁ ጠቅላይ ሚኒስትር ኑር አልማሌኪ “እኛ ማንንም ለማስደሰት ብለን በሶሪያ መንግስት ላይ የሚወሰደውን እርምጃ አንደግፍም” ብለዋል፡፡ በተጨማሪም የሶሪያ መንግስት ብቸኛ ደጋፊ ኢራን በመሆኑዋ የአረብ ሊግ በሶሪያ ላይ በሚወስደው እርምጃ ከኢራን መንግስት ጋር ግጭት ውስጥ መግባት አንፈልግም ብለዋል - አልማሌኪ፡፡ እንግዲህ ልብ እንበል… አሜሪካ የሶሪያ መንግስት እንዲወገድ የምትፈልገው ከ5ሺህ - 7ሺህ ዜጎችን ጨፍጭፏል በሚል የሰብአዊ መብትና የዲሞክራሲ ሽፋን ቢሆንም እውነቱ ግን ሌላ ነው፡፡ አሜሪካ የሶሪያን መንግስት የማትፈልገው በቀዳሚነት የሶሪያ መንግስትና የኢራን መንግስት ተደጋጋፊ በመሆናቸው ሲሆን ኢራን እየገነባች ካለው የኒውክሊየር ፕሮግራም ጋር ተደምሮ የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት አስጊ ሊሆኑ ይችላሉ በሚል ፖለቲካዊ ስጋት ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አልማሌኪ በእነዚህ ሁለት አገሮች ላይ የአሜሪካ ዛቻና ማስፈራሪያ ከምን የመነጨ እንደሆነ አይጠፋቸው፡፡ ነገር ግን በአገራቸው ሺያትና ሱኒ ሙስሊምች ስላሉ መንግስታቸው ለአሜሪካ ብሎ የሶሪያን መንግስት ቢቃወም በኢራን በኩል ጥያቄ ምልክት ውስጥ ይገባሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አገራቸው የሁለት ተቃራኒ ሙስሊሞች መኖሪያ እንደመሆኗ፤ አንዱን ሲደግፉ ሌላው ቁጣ ማስነሣቱ እንደማይቀር በመገንዘባቸው ነው፡፡ ራሳቸው አልማሌኪም ከወራት በፊት ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃል፤ ኢራቅ ከሶሪያ መንግስት በተቃራኒ ከቆመች የሶሪያ መንግስት በኢራቅ በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት ለማውረድ ሱኒዎችን ማስታጠቁ አይቀርም ብለዋል፡፡ አሜሪካ ከኢራቅ ስትወጣ ሺያቶችንና ሱኒዎችን አሰባጥራ፣ የአሻንጉሊት መንግስት አቋቁማ ብትወጣም የኢራቅ መንግስት የራሱን አቋም እንጂ የአሜሪካንን ፍላጎት የሚያንፀባርቅ አልሆነም፡፡ አሜሪካ በመካከለኛው ምሥራቅ ያላት ተሰሚነት አጠያያቂ እየሆነ መምጣቱ ሳያንስ ከኢኮኖሚ ጋር በተያያዘም ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ገብታለች፡፡

በአሁኑ ወቅት እንደ ካሊፎርኒያ ያሉ አንዳንድ ግዛቶች ከገቢያቸው ይልቅ ወጪያቸው በማመዘኑ በ”ቀይ መብራት” ውስጥ ከተካተቱት ግዛቶች ጐራ ተመድበዋል፡፡ ይህም የሆነበት ዋነኛው ምክንያት ባለሀብቶች ታክስን በመሠወር ወይም በማጭበርበራቸው የተነሳ እንደሆነ ይጠቀሳል፡፡ ታክስን አጭበርብረዋል በሚል ስማቸው ይፋ ከሆኑት ውስጥ፣ ታዋቂው የፊልም አክተር ዌስሊ ስናይፕስ 7ሚሊዮን ዶላር ታክስ በመሰወር፣ 14 ሚሊዮን ዶላር በመክፈል ወደ ሕዋ የመጠቁት የቴሌኮም ቢዝነስ አንቀሳቃሽ ባለሀብቱ ዋልተር አንደርሰን ደግሞ ለመንግስት ገቢ መሆን የሚገባውን 6 ሚሊዮን ዶላር በማጭበርበር ተከሰዋል፡፡ ዊስሊ ሲናይፕስ የሶስት አመት እስር ሲቆረጥበት ዋልተር አንደርሰን 9 ዓመት ተፈርዶባቸው ዘብጥያ ወርደዋል፡፡

የራፕ ሙዚቃ አቀንቃኙ ጃሩል፣ የፊልም ተዋናዩ አልፖቺኖ እንዲሁም የፊልም ዳይሬክተሩ ማርኪም ስኮርሲስ ታክስን ካጭበረበሩ ተርታ ተሰልፈዋል፡፡

የዓለማችን ቁጥር ሁለት ቢሊየነር የሆኑት ዋረን በፌፎትም ቢሆኑ ከገቢያቸው አንፃር በጣም ጥቂት ታክስ እንደሚከፍሉ ተገልጿል፡፡ በመሆኑም በ2011 ዓ.ም በአሜሪካ በታክስ ማጭበርበር ወይም ስወራ ብቻ መንግስት ማግኘት የሚገባውን 300 ቢሊዮን ዶላር ሳያገኝ ቀርቷል፡፡ የአሜሪካ ብሔራዊ ዕዳ ወደ 14 ትሪሊዮን የደረሰ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 1 ትሪሊየኑ ከቻይና የተበደረችው ነው፡፡ የ2011 የአሜሪካ የበጀት ጉድለት (Budget Deficit) ወደ 1.1 ትሪሊዮን ደርሷል፡፡ እንግዲህ አሜሪካ ኃያልነቷ እንዲቀጥል እነዚህ ከባድ ተግዳሮቶችን ማሸነፍ ይኖርባታል፡፡ ይህ ደግሞ አሁን በአሜሪካ በተጨባጭ እየታየ ካለው ሁኔታ አንፃር የሚቻል አይደለም በማለት ተንታኞች ያስረዳሉ፡፡

በቅርቡ ለንባብ የበቃው ኒውስዊክ መጽሔት “America’s ‘OH Shit! Moment” በሚል ርዕስ አሜሪካ በውድቀት አፋፍ ላይ እንደተቀመጠች በሰፊው ትንተና አቅርቧል፡፡

መጽሔቱ ከዚህ በፊት በዓለም ታሪክ ኃያላን ከነበሩ መንግስታት አንዳንዶቹ በአንድ ጀምበር ሲወድቁ፣ ሌሎቹ ደግሞ በሂደት ታላቅነታቸው እንደተንኮታኮተ ገልጿል፡፡ ለምሣሌ ከ1250 ዓ.ም ጀምሮ በደቡብ አሜሪካ ክፍለ ግዛት ኃያላን የነበሩት ኢንካ የተባሉ ጐሳዎች በአህጉሪቷ ላይ የበላይነትን ይዘው እስከ 1530 ዓ.ም የዘለቁ ሲሆን፣ ነገር ግን በ1532 ዓ.ም የስፔን ወራሪዎች የኢንካ ሕዝቦችን በጦርነት ድል ከነሱ በኋላ የኢንካ ኃያልነትና ስልጣኔም እስከወዲያኛው አክትሟል፡፡

ዛሬ በፔሩ የሚገኘው የኢንካዎች በጦርነት የወደመ ፍርስራሽ እንጂ ለታሪክ የተቀመጠ አንዳች ቅርስ እንኳን የለም፡፡ በተመሳሳይ ከክርስቶስ ልደት በፊት የዓለም ኃያል የነበረችው የጥንቷ ባቢሎን በአንድ ጀምበር በፔሪሺያን/ በኢራን) ድምጥማጧ ጠፍቷል፡፡

ብዙዎች ኢራቅን የጥንቷ ባቢሎን ነች ቢሉም የታሪክና የአርኪዮሎጂ ማስረጃዎች እንደሚጠቁሙት ግን የጥንቷ ባቢሎን ሙሉ በሙሉ ወድማለች፡፡ ነገር ግን ከኢራቅ 80 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ፍርስራሽ የጥንቷ ባቢሎን ነች፡፡

መካከለኛውን ምስራቅ እና አብዛኛውን የአውሮፓ ግዛትን ታስተዳድር የነበረች ሮም ጠንካራ የነበረው ወታደራዊ ኃይሏና ስልጣኔ በቀላሉ የምትወድቅ አያስመስላትም ነበር፡፡ ነገር ግን በ16ኛው ክ/ዘመን የፕሮቴስታንት እምነት መስራች ማርቲን ሉተር የሮም ካቶሊክ ቤተክርስቲያንን አስተምህሮ በመቃወም ያካሄደው የተሃድሶ እንቅስቃሴ የካቶሊክ ሃይማኖት ተከታይ የነበሩትን በርካታ አውሮፓዊያን ተሃድሶውን እንዲቀላቀሉ ሲያደርግ የሮም ቤተክርስቲያንም በአውሮፓ ያላት የበላይነትም ከሰመ፡፡

በሌላም በኩል በሮም ውስጥ በራሱ የማኅበረሰቡ አንድነት መላላትና ቀውስ ውስጥ መግባት በሮም መንግስት ውስጥ መከፋፈል እንዲፈጠር አደረገ፡፡ በዚህን ጊዜ ሮም ባልሰለጠኑ ጐሳዎች (Barbarian) ስትወረር ወራሪዎችን ለመመከት የሚያስችል ኃይል አልነበራትም፡፡

ከኢምፓየሩ መውደቅ ጋርም ሮማዊያን አሰርተውት የነበረው ዘመናዊ የውሃ መሄጃ ቻናል ሲሰባበር ታላቁ የሮም ገበያም እንዳልነበረ ሆኗል፡፡

የቅርብ ጊዜ ኃያል አገርንም ማንሳት ይቻላል፡፡ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ከአሜሪካ በተቃራኒ ጐራ ተሰልፋ የነበረችው ሶቭየት ሕብረት ልክ እንደ አሜሪካ ልዕለ ኃያል እንደነበረች ይታወቃል፡፡ የሶቭየት ኃያልነት ያከተመው እ.ኤ.አ በ1989 ዓ.ም አገሪቱ በተለያዩ ግዛቶች ስትከፋፈል ነበር፡፡

በ1500 ዓ.ም የቻይና ሕዝብ ከሰሜን አሜሪካ ሕዝብ በሀብት ይበልጥ ነበር፡፡ በ1970 ዓ.ም ደግሞ የአሜሪካ ሕዝብ ከቻይና ሕዝብ 20 ጊዜ በሃብት በልጧል፡፡ በ20ኛው ክ/ዘመን አሜሪካና ምዕራብ አውሮፓ አገራት የዓለምን 58 በመቶ መሬት የተጠቀሙ ሲሆን፣ 74 በመቶ የዓለምን ኢኮኖሚም የተጠቀሙት እነርሱ ናቸው፡፡

ዛሬ ያለው ሁኔታ ሲታይ ደግሞ የአሜሪካ ሕዝብ ከቻይና ሕዝብ በሃብት እየተቀራረበ ይገኛል፡፡ የስራ ሰዓትን በተመለከተም ከሌላ የኢሲያ አገር ጋር አንፃራዊ መረጃ ቀርቧል፡

ደቡብ ኮሪያ በቀን አሜሪካዊያን ለስራ ከሚያውሉት ሰዓት የበለጠ ይሠራሉ፡፡

በደቡብ ኮሪያ በአመት ውስጥ ያለው የትምህርት ቤት ጊዜ 220 ቀን ሲሆን፣ በአሜሪካ ደግሞ 180 የትምህርት ቀን ነው፡፡ በሌላም በኩል በአሜሪካ በሚገኙት ዩኒቨርሲቲዎች ከፍተኛ ውጤት የሚያስመዘግቡት ከአሜሪካዊያን ዜጐች ይልቅ ከኢሲያ የመጡ ወይም ትውልደ እስያ አሜሪካዊያን ዜጐች ናቸው፡፡

በዓለም ላይ ትላልቅ ከሚባሉት 30 ከሚሆኑት የገበያ መደብሮች 26 የሚሆኑት የሚገኙት በኢሲያ ሲሆን፣ በአሜሪካ የሚገኙት ሶስት ብቻ ናቸው፡፡

የጤና አጠባበቅን በተመለከተ አሜሪካን ለጤና ዘርፍ ከጃፓን በሁለት እጥፍ ከቻይና ደግሞ በሶስት እጥፍ ወጪ እያወጣች ቢሆንም ካለፉት 50 ዓመት ወዲህ የአሜሪካዊያን የዕድሜ ጣሪያ ከ70 ወደ 78 ሲያድግ፣ የጃፓን ከ68 ወደ 83 እንዲሁም የቻይና ከ43 ወደ 73 የዕድሜ ጣሪያ አድጓል፡፡

ታይም መጽሔት “America is in Decline” በሚል ርዕስ ባወጣው ዘገባ ደግሞ፣ አሜሪካ መጠነ ሰፊ የሆነ ገንዘብ ለመኖሪያ ግንባታ፣ እርሻ፣ ለጤና አገልግሎቶችና በዕርዳታና መልክ ታወጣለች፡፡

በእነዚህ ዘርፎች የሚወጣው ገንዘብ የአሜሪካንን ኢኮኖሚ ክፉኛ የሚገዳደርና ለሁለንተናዊ እድገት የሚኖረው ፋይዳ በጣም አነስተኛ ነው በማለት ገልጿል፡፡

በአንፃሩ አሜሪካ በቀጣይ ዘላቂ እድገትና ልማት ወሳኝ ለሆኑት ለሳይንስ፣ ለቴክኖሎጂ፣ ለፈጠራና ለመሠረተ ልማት ግንባታ የምትመድበው በጀት አነስተኛ ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ዘርፎች በቀጣይ ለእድገትና ለስራ ዕድል መመቻቸት ወሳኝ ነገሮች ናቸው ብሏል፡፡

በዘመነ ግሎባላይዜሽን የኢንዱስትሪ ምርቶችና አገልግሎቶች መላውን አለም በሚያዳርሱበት ወቅት ለአገሮች ዕድገት ወሳኝ እየሆኑ መምጣታቸው በርካታ አገሮች ከአሜሪካ የተሻለ ውጤት የሚያስመዘግቡባቸው መለኪያዎች ሆነዋል በማለት ታይም መጽሔት ያብራራል፡፡

ጆን ጋልቱንግ የተባሉ የኖርዌጂያን ተወላጅና የማህበራዊ ሳይንስ ፕሮፌሰር፣ አማራጭ የኖቤል ሽልማት ተሸላሚ እንዲሁም በብዙ አገራት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በማስተማር የላቀ ልምድ ያላቸው ምሁር ስለአሜሪካ የወደፊት ዕጣ ፈንታ አስመልክቶ “The Fall of the US Empire” በሚለው ጥናታዊ ጽሑፋቸው ላይ፣ አሜሪካ በዕርዳታ ስም እንዲሁም ለጦርነት በምታወጣው ከፍተኛ ወጪ ምክንያት ቀውስ ውስጥ መግባቷን ይጠቅሳሉ፡፡

በኢራቅ ጦርነት ወደ 747 ቢሊዮን ዶላር፣ ለአፍጋኒስታን ጦርነት 229 ሚሊዮን ዶላር ያወጣች ሲሆን በድምሩ ከ1 ትሪሊዮን በላይ ወጪ አድርጋለች፡፡

እርዳታን በተመለከተ ለተባበሩት መንግስታት በየአመቱ ከምትሰጠው ከፍተኛ በጀት ውጪ በተባበሩት መንግስታት ስር ለሚገኙት እንደ የአለም የምግብና የእርሻ ድርጅት (FAO)፣ ዓለም አቀፍ የስደተኞች ኮሚሽን (UNHCR) ዩኒሴፍ እና ዩኒስኮን ጨምሮ በርካታ ድርጅቶች የሚደገፉት በአሜሪካ ነው፡

ፕሮፌሰር ጆን ጋልቱንግ፤ አሜሪካ የዓለምን ፖለቲካና ኢኮኖሚ በበላይነት ለመቆጣጠር ያደረገችው ጥረት ሁሉ ራሷን ወደ ውድቀት ይዟት እየሄደ ነው በማለት ገልፀዋል፡፡

በመሆኑም ቀድሞ በተለያየ ጊዜያት ተነስተው እንደከሰሙት ኃያላን መንግስታት አይነት እጣ የአሜሪካ መንግስትም እንደሚገጥመው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

 

 

Read 5501 times Last modified on Saturday, 25 February 2012 13:58