Saturday, 25 June 2016 12:24

እምብዛም ያልተወደዱ እጩ ፕሬዚዳንቶች!!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(16 votes)

ቢሊዬነሩ ትረምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ገንዘብ አጥሯቸዋል
“ትረምፕ አሜሪካንን እንዲያከስር መፍቀድ የለብንም” ሂላሪ ክሊንተን
“የሂላሪ ክሊንተን ፀጉር የእውነት አይደለም፤ዊግ ነው” ዶናልድ ትረምፕ
   በመጪው ህዳር ወር በሚካሄደው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ፣ሁለት ተወዳጅነት የሌላቸው እጩ ፕሬዚዳንቶች የሞት ሽረት ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ (የቃላት ጦርነቱ አሁንም ተጧጡፏል!) የኦባማን ሌጋሲ አስቀጥላለሁ የሚሉት ሄላሪ ክሊንተንና ፈርስት አሜሪካ የሚል መርህ የሚከተሉት ዶናልድ ትረምፕ፤ሁለቱን የአሜሪካ ፓርቲዎች ወክለው ዋይት ሃውስ ለመግባት ይወዳደራሉ፡፡ በእርግጥ ለዲሞክራቷ እጪ ፕሬዚዳንት ሂላሪ ክሊንተን፣ ዋይት ሃውስ መግባት ብርቅ አይደለም፡፡ ዕድሜ ለባለቤታቸው! በቀዳማዊት እመቤትነት (first lady) ለ8 ዓመት ኖረውበታል፡፡ የአሁኑ ግን በእጅጉ ይለያል፡፡ ሂላሪ ቱጃሩን ትረምፕ  በምርጫው ድባቅ ከመቱ (እንደ አፍ ባይቀልም!) ለአሜሪካ ህዝብ ሳይሆን ለራሳቸው ትልቅ ታሪክ ይሰራሉ፡፡ አንደኛ፤የመጀመሪያዋ ሴት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በመሆን በታሪክ መዝገብ ይሰፍራሉ (ትረምፕ ግን የሚተኙላቸው አይመስልም!) ሁለተኛ፤ባልና ሚስት ለሦስተኛ ጊዜ ዋይት ሃውስን ይሽሞነሞኑበታል፡፡ (ሂላሪ -ፕሬዚዳንት፣ቢል ክሊንተን- ቀዳሚ ባል!)
በነገራችን ላይ ሁለቱ እጩ ፕሬዚዳንቶች ለአሜሪካዊያን “ከዝንጀሮ ቆንጆ ምን ይመራርጡ” ወይም ዘ ሌሰር ኢቭል የሆኑባቸው ይመስላል፡፡ በአሜሪካ የቅርብ ዓመታት ታሪክ እንደ ሁለቱ እጩዎች የተወዳጅነት ሞገስ ያጣ ኖሮ አያቅም ነው የሚባለው፡፡ (አያድርስ እኮ ነው!) የምርጫ ፉክክሩ ወይም ክርክሩ ከተጀመረ ወዲህ በየጊዜው የሚሰበሰብ የህዝብ አስተያየት እንደሚጠቁመው፤ግድ ሆኖበት እንጂ ሁለቱንም አብዛኛው ህዝብ አይወዳቸውም፡፡ በቁጥሩ መሰረት ከሄድን የበለጠ የማይወደዱት ቢሊየነሩ ዶናልድ ትረምፕ ናቸው፡፡
 60 በመቶ ገደማ  አሜሪካውያን ለእኚህ እጩ ፕሬዚዳንት አሉታዊ አመለካከት አላቸው፡፡ ዲሞክራቷ ሂላሪ ክሊንተን ከተፎካካሪያቸው በ4 ነጥብ ተሽለዋል፡፡ 54 በመቶ ያህሉ አሜሪካውያን ለሳቸው በጎ አመለካከት የላቸውም፡፡
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤በአሜሪካ ታሪክ እ.ኤ.አ ከ1984 ወዲህ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ ለእጩ ተፎካካሪዎች አሉታዊ ስሜት ሲያንፀባርቅ የዘንድሮ የመጀመሪያው ነው፤በሂላሪና በትረምፕ፡፡ (የከሸፈ ምርጫ በሉት!)  
አስገራሚው ነገር ምን መሰላችሁ? አንዳንድ አሜሪካውያን ከሞቱም በኋላ ለእጩዎቹ ያላቸውን አሉታዊ ስሜት በዜና እረፍታቸው ላይ እንዲገለጽላቸው ማድረግ ጀምረዋል፡፡ (የመጨረሻ ፖለቲካዊ አቋም በሉት!) በነገራችን ላይ በህይወት እያሉ የራስን ዜና ዕረፍት (obituary) መጻፍ ሳይጠቅም አይቀርም፡፡ (በስመአብ!! ሶስቴ አማትቤአለሁ!)  
እናላችሁ-----ባለፈው ወር ወደ ላይኛው ቤታቸው የተሻገሩት የ68 ዓመቷ የቨርጂኒያዋ ባልቴት ዜና ዕረፍት ላይ የወጣው ጽሁፍ ፖለቲካዊ ምፀት ቢባል ይሻላል፡፡ #ሁለቱን እጩዎች ከመምረጥ ሞትን መርጣለች” ሲል ዘግቧታል-አንድ ድረገጽ፡፡
 “ሜሪ አን ኖላንድ፤በህዳር ወር በሚካሄደው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ላይ ዶናልድ ትረምፕን ወይም ሂላሪ ክሊንተንን ከመምረጥ የእግዚአብሄርን ዘላለማዊ ፍቅር መርጣለች” ይላል -ዜና ዕረፍቱ፡፡ በዜና ዕረፍት የመጨረሻ የፖለቲካ መልዕክት በማስተላለፍ፣የቨርጂኒያዋ እማወራ የመጀመሪያዋ አይደሉም፡፡ ባለፈው ጥር ወር ላይ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት የ70 ዓመቱ የፒተርስበርግ አዛውንት ጄፍሪ ኮኸን፤ በዜና ዕረፍታቸው ላይ፤ወዳጅ ዘመዶቻቸው ዶናልድ ትረምፕን እንዳይመርጡ አደራ ብለዋል፡፡ (እንዴት ቢጠምዷቸው ነው!)
እንዲያም ሆኖ ግን አሜሪካውያን ለጊዜው ሌላ ምርጫ የላቸውም፡፡ ጊዜና ዲሞክራሲ ተባብረው ዶናልድ ትረምፕና ሂላሪ ክሊንተንን ጥለውባቸዋል፡፡ (አማራጩ የተሻለውን #ሰይጣን” መምረጥ ብቻ ነው!) ህዳር መጥቶ ምርጫው እስኪለይለት ግን እረፍት የለም፡፡ የቃላት ጦርነት ተያይዘውታል፡፡ አንዳንዴ የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ፉክክር ሳይሆን የግል ጠብ ሁሉ ይመስላል፡፡ እናም የሂላሪ ክሊንተን ዊግ፣ ፖለቲካ ሆኖ ቁጭ ይላል፡፡
በእርግጥ ብዙ ጊዜ እንዲህ ዓይነቱን ትንኮሳ የሚጀምሩት የሪል እስቴት ከበርቴው ትረምፕ ናቸው፡፡ በዘንድሮ ምርጫ ምን ያልሰማነው አለ? ዶናልድ በአንድ ሚዲያ ላይ ድንገት ስለ ሂላሪ ዊግ አንስተው ነበር፡፡ “የሂላሪ ክሊንተን ፀጉር ዊግ ነው፤ዝም ብዬ እንዳይመስልህ፤በዊግ መሸጫ መደብሬ ተሰልፋ አይቻታለሁ” አሉ - ማስረጃ መሆኑ ነው፡፡ (ትረምፕ ራሳቸውን ኤዲት አያደርጉም!) ክፋቱ ደግሞ ሂላሪም ንቀውት አላለፉትም፡፡ (ልናቀውም ቢሉ ሚዲያው በጄ አይላቸውም!)     
አንድ የቴሌቪዥን ጋዜጠኛ ነበር ጥያቄውን ያነሳባቸው፡፡ ሂላሪም “ዊግ አይደለም--” ብለው መለሱ፡፡ ፒፕል መፅሄት ግን ያመናቸው አይመስልም፡፡ ስለዚህም በራሱ መንገድ ለማጣራት የሂላሪ ፀጉር ሰሪና የሳንታ የውበት ሳሎን ባለቤት የሆነችው፣ሳንታ ኒክልስ ዘንድ ሄዶ ጠየቀ፡- “የሂላሪ ፀጉር የእውነት ነው?” ፀጉር ሰሪዋም፤ “እናንተ ግን በጣም ትገርማላችሁ…እጅግ የሚደንቅ ፀጉር እኮ ነው ያላት” ስትል መለሰች፡፡ በዚህ ብቻ ግን አልበቃትም፡፡ “ሂላሪ ክሊንተን ዊግ አታደርግም፤ የአሜሪካ ቀጣዩ ፕሬዚደንት እንደምትሆንም አምናለሁ” (አይገርምም! ዊግና ፖለቲካ!)
ሰሞኑን ደሞ ተራው የሂላሪ ይመስላል፡፡ ዶናልድ ትረምፕ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆኖ ለመመረጥ በልበሙሉነት ደጋግመው የሚያነሱት፣ስኬታማ ቢዝነስ መመስረታቸውን ነው፡፡ ሂላሪ ግን ሃቁ ሌላ ነው ይላሉ፡፡ ትረምፕ፤በቢዝነስ ስራቸው ተደጋጋሚ ኪሳራ እንደደረሰባቸው በመጠቆም “አሜሪካንን እንዲያከስር ግን ልንፈቅድለት አይገባም፤;ብለዋል፡፡
“በኩባንያዎቹ ውስጥ ሆን ብሎ ከፍተኛ ዕዳ ያከማችና በመጨረሻ ኪሳራ ያውጃል” ብለዋል፤ ሂላሪ - የካዚኖ ቤቱን (ቁማር) ኪሳራ በመጥቀስ፡፡ ዶናልድ ትረምፕ ግን ይሄን ሁሉ አይቀበሉትም፡፡ አራት ጊዜ ኪሳራ እንደደረሰባቸው የተናገሩት ትረምፕ፤“ስለ ገንዘብም ሆነ ስለ ዕዳ ከእኔ በላይ የሚያውቅ የለም፤ሂላሪ ግን አሜሪካን ዕዳ ውስጥ ዘፍቃታለች” ሲሉ መልሰው ወደ ሂላሪ ተኩሰዋል፡፡ አስገራሚው ነገር ምን መሰላችሁ? ሂላሪ ስለ ትረምፕ ከፍተኛ ዕዳና የቢዝነስ ኪሳራ በስፋት ከደሰኮሩ በኋላ በተሰበሰበ የህዝብ አስተያየት፤ አሜሪካውያን በኢኮኖሚ ጉዳይ የበለጠ የሚያምኑት ከሂላሪ ይልቅ ትረምፕን እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ 51 - በመቶ ትረምፕ! 43 - በመቶ - ሂላሪ!  
አሁን ቢሊዬነሩ ትረምፕ የሚፈተኑበት ችግር ገጥሟቸዋል እየተባለ ነው፡፡ ከፍተኛ የምርጫ ቅስቀሳ ገንዘብ አጥሯቸዋል፡፡ (የምርጫ ዘመቻ ያለ ገንዘብ አይታሰብም!) ሲኤንኤን እንደዘገበው፤ባለፈው ሰኔ መጀመሪያ ላይ በባንክ የነበራቸው የቅስቀሳ ገንዘብ 1.3 ሚ.ዶላር ሲሆን ተፎካካሪያቸው ሂላሪ ግን ለቅስቀሳው 42 ሚ.ዶላር አዘጋጅተዋል፡፡ (ልዩነቱ የሰማይና የምድር ያህል ነው!) እናም የምርጫ ዘመቻውን በቅርበት የሚከታተሉ ተንታኞች ዶናልድ ሂላሪን መፎካከር የሚፈልጉ ከሆነ፣ በፍጥነት ገንዘብ ማሰባሰብ፣የምርጫ ዘመቻ ሠራተኞች መቅጠር---ይኖርባቸዋል ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡ መቼም ትረምፕ ይሄ ይጠፋቸዋል አይባልም!! (ስለ ገንዘብም፣ ስለ ዕዳም፣ ስለ ኪሳራም --- ከእኔ በላይ የሚያውቅ የለም ብለው የለ!!) 

Read 9178 times