Saturday, 03 March 2012 15:13

በከበረ የተፈጥሮ ሃብት የከበረ ኢንቨስትመንት

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(22 votes)

በጌጣጌጥ ሰሪዋ ራሄል መኩርያ በኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍሎች የከበሩ ድንጋዮች ሃብት እንዳለ ይነገራል፡፡ የዓለምን የከበሩ ድንጋዮች ገበያ 95 በመቶ ከተቆጣጠረችው አውስትራሊያ እንዲሁም ከአሜሪካና ከሜክሲኮ በመቀጠል ኢትዮጵያ እየተጠቀሰችም ነው - በከበሩ ድንጋዮች ሃብቷ፡፡ ነገር ግን የከበሩ ድንጋዮች የወርቅንና የዳይመንድን ያህል እንኳን በአገር ውስጥ ገና አልታወቁም፡፡ በደቡብ አፍሪካ ከከበሩ ድንጋዮች ጌጣጌጥ በመስራት ለአውሮፓና ለኢትዮጵያ ገበያ የምታቀርበው ወ/ሮ ራሄል መኩሪያ ዘርፉ ሰፊ የኢንቨስትመንት ዕድሎች እንዳሉት ትናገራለች፡፡ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ለአገሪቱ በማስገኘት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልፃለች፡፡ ወ/ሮ ራሄል እንዴት ወደሙያው እንደገባች፣ ስለከበሩ ድንጋዮች ገበያና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ግሩም ሰይፉ ጋር ቃለምልልስ አድርጋለች፡፡

በከበረ የተፈጥሮ ሃብት የከበረ ኢንቨስትመንት

ከሙያሽ ጋር እንዴትና መቼ ተዋወቅሽ?

በምኖርበት ደቡብ አፍሪካ ነው፣ በኬፕታውን መንገድ ላይ እየሄድኩ ሳለሁ አንድ ወጣት የሆነ ጥግ ይዞ ጌጣጌጥ ሲሰራ ተመለከትኩ፡፡ ጠጋ ብዬ አስተምረኝ ስል በትህትና ጠየቅኩት፡፡ ከከፈልሽኝ ችግር የለም ብሎ ወዲያውኑ በተቀመጠበት ስለሙያው ነገረኝ፡፡ ጌጣጌጦቹን እንዴት እንደሚሰራቸውም አሳየኝ፡፡ ሞክሪ ብሎ እድሉን ሲሰጠኝ አንድ ትንሽ የእጅ አምባር ሰራሁ፡፡ በፈጠራዬ ተደነቀ፡፡ ከጊዜ በኋላም ስለተማረበት ትምህርት ቤት ነገረኝ፡፡

ትምህርት ቤት ገባሽ?

የትምህርት ቤቱ አስተማሪ ኢትዮጵያዊ ይፈልግ ነበር፡፡ ከኢትዮጵያ ጌጣጌጦችን በተለይ አልቦ የሚባለውን የሚያስመጣለት ይፈልግ ነበር፡፡ አልቦ ከኒኬል የሚሰራ ነው፡፡ በትምህርት ቤቱ ክፍያ ቀንሶ እንዲያስተምረኝ የተስማማነው በአገር ቤት ካሉ ሰዎች ጋር በመገናኘት ባህላዊ ጌጣጌጦችን ላመጣለት ቃል ገብቼ ነው፡፡ በዚህ መንገድም  ለሁለት ዓመታት በዚያው የጌጣጌጥ ስራ ትምህርት ቤት ተማርኩ፡፡ አስተማሪው የምሰራቸውን እየተመለከተ ደጋግሞ ያደንቀኝ ነበር፡፡ አንዳንዴ እንደውም ሌላ የሚያስተምርሽ አለ ወይ እያለ በመገረም ይጠይቀኝም ነበር፡፡

በመማሬ ጌጣጌጥ ለመስራት ከነበረኝ ተፈጥሯዊ ፍላጎትና ተሰጥኦ ጋር በጣም ለውጥ አሳየሁ፡፡ በትምህርት ቤቱ በከበሩ ድንጋዮች ጌጥ እንዴት እንደሚሰራ፤ ከምን ከምን እንደሚሰራ፤ እንዴት ዲዛይን እንደሚደረግ፤ የከበሩ ድንጋዮች አቆራረጥ እንዴት እንደሆነና ሌሎችንም መሰረታዊ እውቀቶች በደንብ አገኘሁ፡፡ ኬፕታውን ጎዳና ላይ ያንን ደቡብ አፍሪካዊ የጌጣጌጥ ባለሙያ አግኝቼ ባልጠጋ ኖሮ ሙያው በውስጤ እንዳለ አላውቅም ነበር፡፡ ከትምህርቱ በኋላ ግን ሙያው ልቤ ውስጥ አደረ፡፡ ቀን ቀን እየተማርኩ ወደ ቤቴ ስመለስ እራሴን በከፍተኛ ልምምድ እና የፈጠራ ስራ በመወጠር ሙያውን ተላመድኩ፡፡ አስተማሪዬ በየጊዜው የቤት ስራ ሲሰጠኝ የበለጠ አድርጌ  እሰራ ነበር፡፡ በትምህርት ቤቱ የምንማረው የሌላ ሰውን ሞዴል መስራት ብቻ ሳይሆን የራሳችንን ፈጠራም እንሰራለን፡፡ ጌጣጌጦችን የምንሰራው ደግሞ በከበሩ ድንጋዮች ነበር፡፡ አንዳንዶቹ ድንጋዮች በፋብሪካ በሚያስፈልግ ቅርፅ እና የቀለማት ውህድ ተዘጋጅተው ስለሚቀርቡ ዋናው ስራችን እነዚህን ድንጋዮች ለብቻቸውም ሆነ እርስ በርስ በማዋሃድ ጌጥ መስራት ነበር፡፡

ትምህርቱን እንደጨረስሽ ወዲያውኑ ወደ ንግድ ገባሽ ማለት ነው?

ወዲያውኑ አልነበረም፡፡ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ያልደፈሩትን ነገር ለመጀመር ቀላል አልነበረም፡፡ ጭራሽ እኔ በገባሁበት ዓይነት የስራ ፈጠራ ብዙ ሰው አልተሰማራም፡፡ ታዋቂ ኢትዮጵያዊ የልብስ ዲዛይነር መኖሯን ሰምቻለሁ፡፡ ከዚያ ውጭ በራሱ ሙያና ፈጠራ ሰርቶ መተዳደርያውን የፈጠረ ብዙ የለም፡፡ ከተማርኩ በኋላ ሙያው ተዋሃደኝ፡፡ የተማርኩት ማርኬቲንግ ነበር፡፡ የጌጣጌጥ ስራ ከተማርኩና ሱቅ ከፍቼ መስራት ከጀመርኩ በኋላ ግን ሌት ተቀን የማስበው ይህንኑ ሙያዬን ሆነ፡፡ ከጆሃንስበርግ ወጣ ብላ በምትገኝ ሮዝባንክ በተባለች ከተማ ሱቅ አገኘሁ፡፡ የመስሪያ እቃዎችና የከበሩ ድንጋዮችን ሰብስቤ በሱቁ ስራ ስጀምር 200ሺ ራንድ ገደማ መነሻ ካፒታል ይዤ ነበር፡፡ የትንሿ ከተማ ነዋሪዎች ብዙዎቹ የውጭ ዜጎች ናቸው፡፡ ወደ ገበያው በርካታ ቱሪስቶች ይመጡ ነበር፡፡ ሱቄ ሙሉ ለሙሉ ገፅታው ኢትዮጵያን የመሰለ ነበር፡፡ ባንዲራው አለ፤ ባህላዊ ቁሳቁሶች፤ በባህላዊ መንገድ የተሰሩ ጌጣጌጦች፤ የተለያዩ የአገር ቤት እደጥበብ ስራዎች የሱቁን ድባብ ይገልፃሉ፡፡ ጌጣጌጦች የምሰራው በጣም በሚታወቁ የከበሩ ድንጋዮች መሆኑ የሱቄን ገበያ ልዩ ያደርገው ነበር፡፡ በሱቁ ውስጥ ብቻ ሳይሆን አንዳንድ ስራዎቼን ወደ አሜሪካ፣ ጣሊያን፣ እንግሊዝና ወደተለያዩ የዓለም ክፍሎች በመላክ የውጪ ደንበኞችም አፈራሁ፡፡ ጌጣጌጦቼን በብዛት ሰርቼ በወኪልነት ሽያጭ ለሚያከናውኑት ሰዎች እሸጥላቸዋለሁ፡፡ እነሱ አውሮፓ እና አሜሪካ ይሸጡልኛል፡፡  በኢትዮጵያ በሸራተንና በሂልተን ሆቴሎች ጌጣጌጦቼን የሚሸጡልኝ ወኪሎቼ ዛሬም አብረን እየሰራን ነው፡፡

የጌጣ ጌጥ ሱቁን ከከፈትሽ በኋላ ገበያው እንዴት ነበር?

በሱቄ በማቀርባቸው እቃዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ደንበኞች ማፍራት ችዬ ነበር፡፡ አንዳንድ ደንበኞቼ ሊገዙ መጥተው በሚያገኙት በጣም ይደሰታሉ፡፡ አድናቆታቸውን ለመግለፅ “እባክሽን ስምሽን ጌጡ ላይ ቅረጪበት” እያሉ የሚጎተጉቱኝ ገዢዎችም ነበሩ፡፡ የምስራቸውን ጌጣጌጦች በጅምላ እየወሰዱ ወደተለያዩ አገሮች ይልኩና ይወስዱ የነበሩ ድርጅቶችም በማቀርባቸው ጌጦች ትርፋማነት በመርካታቸው ብዙ ትእዛዞች የጐርፉልኝ ነበር፡፡ እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን በወርቅ ወይም በአልማዝ ማዕድን የተሰሩ ጌጣጌጦችን እንጅ በከበሩ ድንጋዮች የሚዘጋጁትን የመግዛት ብዙ ልምድ የለም፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ስለከበረ ድንጋይ ያለው እውቀት አነስተኛ በመሆኑ ነው፡፡ እናም ጌጣጌጦቹን ንብረት ለማድረግ ድፍረት አልነበረም፡፡

በከበሩ ድንጋዮች  የሚሰሩ ጌጣጌጦችን  በአገር ውስጥ ገበያ ለማጧጧፍ አልተቻለም ነው?

ሰዎች በከበሩ ድንጋዮች የሰራኋቸውን ጌጣጌጦች ይመለከቱና በመጀመርያ ዋጋ ይጠይቃሉ፡፡ ከዛም ከምንድነው ከወርቅ ነው ከአልማዝ የተሰራው ይላሉ፡፡ ከከበረ ድንጋይ ስትላቸው አያምኑም፡፡ ቅድም እንደነገርኩህ በደቡብ አፍሪካ የሰራኋቸውን ጌጣጌጦች እዚህ ለአገር ቤት ገበያ ሳቀርብ በሂልተንና ሸራተን ሆቴል የገዙ ደንበኞች እንዲህና በዚህ የከበረ ድንጋይ ጌጥ ስሪልኝ እያሉኝ በትዕዛዝ መስራት ጀመርኩ፡፡

ይሁንና ዋና የገበያ መዳረሻችን አገር ውስጥ ሳይሆን በውጭ አገራት ነው፡፡ ይሄ ገበያ ኢትዮጵያ በዓለም ደረጃ የምትተዋወቅበትን እድል ይፈጥራል፡፡ የውጭ ገበያ ላይ ትኩረት የምናደርገው ስለከበሩ ድንጋዮች በቂ እውቀት ስላላቸው ብቻ ሳይሆን የተፈጥሯ ሃብቷን ለምንጠቀመው ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ ለማስገባትም ነው፡፡

ኢትዮጵያ በከበሩ ድንጋዮች የተፈጥሯ ሃብቷ ከዓለም ጥቂት አገራት ተርታ ትመደባለች፡፡ የከበሩ ድንጋዮች የዓለምን ገበያ 95 በመቶ በተቆጣጠረችው አውስትራሊያ ብቻ ሳይሆን ከሜክሲኮ እና ከአሜሪካ ሌላ ኢትዮጵያም አንዷ ሆናለች፡፡

አገራችን በተፈጥሯ ሃብቷ ያላት የከበሩ ድንጋዮች ክምችት የሚያስከብራት ነው፡፡ ከ20 እና 30 በላይ ዓይነት የከበሩ ድንጋዮች በብዛት ይገኛሉ፡፡ መንግስት ለከበሩ ድንጋዮች ትኩረት ሰጥቶ መስራት ጀምሯል፡፡ የከበሩ ድንጋዮች ይገኙባቸዋል የተባሉ አካባቢዎችን በመከለል ላይ ነው፡፡ አንዳንድ የማዕድን ቁፋሮዎችን የሚያከናውኑ ኢንቨስተሮችና ወደዚሁ መስክ ለመግባት የሚፈልጉ ድርጅቶች ቅድመ ጥናቶችን በማከናወን ላይ ናቸው፡፡ መንግስት ወደዚህ ኢንቨስትመንት ማተኮር መጀመሩም ይታያል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ የሚገኘውና ሰው የሚያውቀው “ኦፓል” የተባለውን የከበረ ድንጋይ አይነት ነው፡፡ በቀለማቸው ህብር የሚያስደንቁ፤ በብዙ የዓለም ክፍል የማይገኙ ብርቅዬ የከበሩ ድንጋዮች የኢትዮጵያን ከርሰምድር ሞልተዋል፡፡ ፔሪዴት፤ ሳፍየር፤ አምበር፤ ኤመራልድ፤ ቲርኳይዝ፤ ቶፓዝ፤ ሩቢ፤ ዳይመንድ በኢትዮጵያ ይገኛሉ፡፡ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የፈሰሰባቸውና በዘመናዊ መሳርያዎች የተደራጁ የማእድን ማውጫ ፋብሪካዎች ያስፈልጋሉ፡፡ የከበሩ ድንጋዮችን በአግባቡ በተለያየ ማዕዘንና ቅርፅ፣ መጠናቸውንና ቀለማቸውን አዋህዶ ለማቅረብ የሚያስችሉ መሳርያዎች ስለሌሉ ከዚህ ተቆፍሮ የሚወጣው በቀጥታ ወደ ውጭ አገር ይሄዳል፡፡ እዚህ አገር ላይ ጌጥ የሚሰሩ ባለሙያዎች የተዘጋጁ የከበሩ ድንጋዮችን ከውጪ ያስመጣሉ፡፡ ይህን ሁኔታ የሚቀይር ሰፊ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ያስፈልጋል፡፡ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ከሰራበት ደግሞ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኝ የኢንቨስትመንት መስክ ነው፡፡

የከበሩ ድንጋዮች እንዴት ይታወቃሉ?

የከበሩ ድንጋዮች በቅርፃቸው፤ በተፈጥሯዊ ባህርያቸው፤ በቀለማቸው ህብር ይለያሉ፡፡ በዘመናዊ መንገድ ተቆፍረው ወጥተው በወቅቱ ቴክኖሎጂ በተለያያ ቅርፅና መልክ በጥሬ እቃነት መዘጋጀታቸው፣ በየአገሩ በብዛት የማይገኙ ማዕድኖች መሆናቸውም ተወዳጅ ያደርጋቸዋል፡፡

ብዙዎቹ የከበሩ ድንጋዮች ብርሃን የሚያስተላልፉ፣ በውስጣቸው አስገራሚ ቅርፆችን የያዙ፤ የሚያንፀባርቁ፤ እንደ ቀስተዳመና በተለያዩ ቀለማት የተዋቡ እና እንደ አካባቢው ሁኔታ ቀለማቸውን የሚለዋውጡ ሲሆኑ ትኩር ብለው ሲመለከቷቸው የሚያመራምሩና የሚያነጋግሩ፤ ባህርያቸውን ለመረዳት ጥናት ውስጥ የሚከቱ፤ ልተረጉማቸው ልታነባቸው የምትሞክራቸውም ናቸው፡፡

ከከበረ ድንጋይ አንድ ጌጥ ለመስራት ምን ያህል ጊዜ ይወስድብሻል? ዋጋቸውና አይነታቸውስ?

በምሰራቸው ጌጣጌጦች ላይ በየጊዜው አዳዲስ ፈጠራዎችን ማከል እወዳለሁ፡፡ ለአንድ ጌጥ አንድ ፈጠራ የሚል እምነት ስለያዝኩ ደግሜ የምሰራው ሞዴል የለም፡፡ የሰራሁት ጌጥ ተወዶ በትእዛዝ ይሰራልን ብለው ሰዎች ካልጠየቁኝ ደግሜ አልሰራም፡፡ በከበሩ ድንጋዮች የተሰሩ ጌጦችን በሌላ ሞዴል ለመቀየር የግድ አስፈላጊ ከሆነ የአንገት ሃብል የነበረውን የድንጋይ ብዛት ቀንሶ የእጅ ብራስሌት የመስራት ሙከራዎች አሉ፡፡ ግን አንዴ በከበረ ድንጋይ የተሰራ ጌጥ የከበረ ቅርስ ስለሚሆን፣ አፍርሶ ሌላ መስራት ጌጡ ያለውን ክብር መቀነስ በመሆኑ ይህን ተግባር ብዙ አልደፍረውም፡፡ በየጊዜው በአዳዲስ ፈጠራዎች መጠመዴ ለመሻሻሌ ምክንያት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ የከበሩ ድንጋዮች ጥሬ እቃ ሆነው ሲቀርቡ በጌጣ ጌጥ ስራ የሚወድቅ ነገር የላቸውም፡፡

አንዳንድ ጌጦችን ለመስራት 15 ደቂቃ እንኳን አይፈጅብኝም፡፡ ብዙዎቹን በአማካይ በ30 እና40 ደቂቃዎች ነው የምሰራው፡፡ አልፎ አልፎ ሃሳብ ያጥርና የማሳድራቸውና ለሳምንታት የማልጨርሳቸው የጌጥ ሞዴሎች ያጋጥሙ ይሆናል፡፡

በየትኛውም ድንጋይ፤ አይነትና ዲዛይን ብሰራም አንዱን በአንዱ እያካስኩ የሰራኋቸውን ጌጦች እሸጣቸዋለሁ፡፡

በከበሩ ድንጋዮች የሚሰሩ ጌጣጌጦች ጥቅም ምንድነው?

በከበሩ ድንጋዮች ሙሉ ጌጣጌጥ መስራት ይቻላል፡፡ የአንገት ሃብል፤ የእጅ አምባር፤ የጣት ቀለበቶች እና የተለያዩ ጌጣጌጦች ይሰራሉ፡፡ እነዚህ ጌጦችን ሃብትና ቅርስ አድርጎ መኖር ይቻላል፡፡ ለሰርግና ለልደት የሚሰጡ ልዩ ገፀ በረከትም ናቸው፡፡ ለተለያዩ ግብዣዎች ማጌጫ ናቸው፡፡ በከበሩ ድንጋዮች በሚሰሩ ጌጦች መዋብ ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ የባለጠግነት መገለጫና የስኬትና የክብር ስሜት ማንፀባረቂያ ነው፡፡

ሙያሽን፤ የኢንቨስትመንት ሃሳብሽንና የምርቶችሽን ገበያ ለማስፋት ምን እየሰራሽ ነው?

ዎርልድ ውመን ትሬድ ፌር አፍሪካ ከሚባል ድርጅት ጋር እየሰራሁ ነው፡፡ ድርጅቱ እውቀታቸው ከአገራቸው አልፎ አለም ገበያ ላይ የሚያኮራ ሰዎች ቦታው እንዲደርሱ የሚሰራ በመሆኑ በዚህ አለማ በጋራ መስራት ጀምረናል፡፡ ዎርልድ ውሜን ትሬድ ፌር አፍሪካ ከ1 ዓመት በፊት ፈቃድ አውጥቶ በአዲስ አበባ ስራውን የጀመረ ድርጅት ነው፡፡ የድርጅቱ ዲያሬክተርና ሪጅናል ሪፕረዘንታቲቭ የሆነችውን ወይዘሮ መቅደስን በእናቴ በኩል ተዋውቄ አስገራሚ እድል ተገኝቷል፡፡ወይዘሮ መቅደስ በከበሩ ድንጋዩች እውቀቱ ስላላት የሰራኋቸውን ጌጦች ተመልክተው ባለኝ  የፈጠራ ችሎታ እና  በሙያው ሊኖር የሚችለውን ከፍተኛ ውጤት ስለሚያውቁት  ስራዎቼን ለማስተዋወቅኢኮኖሚ እድገትና በስራ ፈጠራ ትልቅ ድርሻን እንደማበረክት አምነው  ስራ ጀምረናል፡፡  በነሐሴ ወር ላይ በኒውዮርክ ዎርልድ ወመን ትሬድ ፌር አሜሪካ በሚዘጋጀው  ትልቅ ትሬድ ፌር ላይ እንድሳተፍ በመወሰኑ ስራዎችን ለዓለም አቀፍ ገበያ ለማስተዋወቅ እየሰራን ነው፡፡

በተለያዩ  የዓለም ክፍሎች እንዲተዋወቅ ድርጅቱ የበኩሉን ያደርጋል፡፡ ወይዘሮ መቅደስ ሙያሽና የፈጠራ ችሎታሽ ለዓለም አቀፍ ገበያ የተዘጋጀ መሆኑ ስራችንን ያቀለዋል ብለውኛል፡፡ዎርልድ ውመን  ትሬድ ፌር አፍሪካ ገበያን ለማስፋትና የተደበቁ እውነቶችን በማውጣት ኢትዮጵያ በዚህ ኢንቨስትመንት መስክ ያላትን አቅም ለመላው ዓለም ለመግለፅ ብሎም ለማሳወቅ እይሰሩ ነው፡፡

በከበሩ ድንጋዮች ዙርያ ባለው የኢንቨስትመንት አቅጣጫ መቶ በመቶ እምነት ስላለን ከባንኮች በተለይም የወርልድ ውመን ትሬድ አፍሪካ የክብር አባል ከሆነው በኤምኤስኤምኢኤስ ዙርያ ለመስራት ባወጣው እቅድ መሰረት  ከቡና ኢንተርናሽናል ባንክ ጋር ለመስራት እየተንቀሳቀስን ነው፡፡

ዎርልድ ውመን ትሬድ ፌር አፍሪካ የመጀመርያው ስራዬ የኤክስፖርት ፈቃድ ማውጣት እንደሆነ ገልፀውልኛል፡፡ ይህን ማድረግ ከመንግስት በአገር ውስጥ እየሰሩ ካሉ የከበሩ ማእድናት አውጭ ኩባንያዎች፤ ከተለያዩ የውጭ ጥሬ እቃ አቅራቢዎች ጋር መስራት ያስችላል፡፡ ድርጅቴን አፍሪካ አዶርመንት ብለን ሰይመነዋል፡፡ ትርጉሙም አፍሪካ የፍቅርና የክብር እቃ አላት፤ አፍሪካ ውድ ናት፤ አፍሪካ ታኮራለች፤ አፍሪካ ከምንም ክብር አላት የሚለውን ይገልፃል፡፡ በእያንዳንዱ የከበሩ ድንጋዮች ጌጣጌጥ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን አፍሪካን በማስተዋወቅ ልንሰራበት ነው፡፡

በመጨረሻ…

በሙያዬ የበለጠ ማደግ እፈልጋለሁ፡፡ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ያላትን እምቅ ሃብት በመጠቀም በመላው ዓለም ገበያ ፈጥሬ የመስራት ጉጉትም አለኝ፡፡ በከበሩ ድንጋዮች በሚሰሩ ጌጣጌጦች ያሉትን የኢንቨስትመንት እድሎች በፈርቀዳጅነት በመጠቀም ራሴን ከማሳደግ ባሻገር የዜግነት ግዴታዬን ለመወጣት እፈልጋለሁ፡፡

አሁን ለደረስኩበት ደረጃ ከሁሉ በፊት ምስጋናዬ ለእግዚአብሄር ነው፡፡ በጥሩ ስነምግባር እያነፁ ያሳደጉኝን አባቴ አቶ መኩርያ ይማምንና እናቴ ወይዘሮ ብርቅነሽ በሽርን አመሰግናለሁ፡፡  ሙያዬን እዚህ ደረጃ ለማድረስ በደቡብ አፍሪካ ከጅምሩ ያደረግኩትን ጥረት በመደገፍና ሞራል በመስጠት እገዛው ያልተለየኝ ባለቤቴ ሚካኤል ቦካምንፒን አመሰግነዋለሁ፡፡ ወይዘሮ ሮዛ ካርሎ ሃሳቦቼን በማብዛት፤በቅንነት በማበረታትም ለሰሩት ውለታ ይመስገኑልኝ፡፡

 

 

Read 10914 times Last modified on Monday, 05 March 2012 15:34