Saturday, 16 July 2016 12:37

በሞተር ሣይክል የአምቡላንስ አገልግሎት ሊጀመር ነው

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(13 votes)

‹‹በአደጋ ወቅት ሰዎችን የሚጎዳው አለአግባብ አፋፍሶ ማንሳት ነው››

   ጠብታ አምቡላንስ በሞተር ሳይክል የአምቡላንስ አገልግሎት ሊጀምር መሆኑን ያስታወቀ ሲሆን አገልግሎቱ በአምቡላንስ መዘግየት ሳቢያ ህይወታቸውን የሚያጡ ወገኖችን ይታደጋል ተብሏል፡፡
የጠብታ አምቡላንስ ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ክብረት አበበ ሰሞኑን ለጋዜጠኞች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የሞተርሳይክል የአንቡላንስ አገልግሎት በመንገዶች መዘጋጋትና በትራፊክ መጨናነቅ ሳቢያ አንቡላንሶች በወቅቱ ከሚፈለጉበት ሥፍራ ደርሰው አፋጣኝ እርዳታ ለመስጠት ባለመቻላቸው ምክንያት ለከፋ ጉዳትና ለሞት የሚዳረጉ ወገኖችን በእጅጉ የሚታደግና በተለይ ከመኪና አደጋ ጋር በተያያዘ ለሚከሰቱ ጉዳቶች ከፍተኛ እገዛ የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡ የሞተር ሳይክል አምቡላንሶቹ ህሙማኑን የማጓጓዝ ሥራ እንደማይሰሩ የገለፁት አቶ ክብረት፤ በአግባቡ የሰለጠኑ የህክምና ባለሙያዎች የህይወት አድን መሳሪያዎችን ታጥቀው በአጭር ጊዜ ውስጥ ከሥፍራው በመድረስ ለህመምተኛው የህክምና እርዳታ እየሰጡ አምቡላንሱ እስከሚደርስ ድረስ የሚጠብቁ ናቸው ብለዋል፡፡ ይህም፤ በደም መፍሰስ፣ በትንፋሽ እጥረትና በልብ መቆም ችግሮች ሕይወታቸው የሚያልፍ ወገኖችን ለመታደግ ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡በአደጋ ወቅት የሞተር ሳይክል አንቡላንሶቹ የትራፊክ መጨናነቅ ቢኖርም እንኳን ተሸሎክልከው በመድረስ ጉዳተኞቹ የከፋ ችግር ሳያጋጥማቸው ከአደጋው ስፍራ እንዲነሱና ህይወት አድን ህክምና ለማግኘት እንዲችሉ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ እገዛ ይሰጣሉ ብለዋል፡፡ በአደጋ ወቅት ከአደጋው ይልቅ ሰዎችን የሚጎዳው አለአግባብ አፋፍሶ ማንሳት መሆኑን የጠቆሙት አቶ ክብረት፤ በአደጋው ከሚሞቱት ሰዎች ይልቅ በአያያዝ ችግር ህይወታቸውን የሚያጡት ሰዎች በቁጥር ይልቃሉ ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የሞተር ሳይክል አገልግሎቱን ለማስጀመር ዝግጅቱ መጠናቀቁንና የሞተር ሳይክል ግዥ፣ ባለሙያዎችን የማሰልጠኑ መሳሪያዎቹን የማሟላቱ ስራ በመጠናቀቁ በቅርቡ ስራ እንደሚጀመር አቶ ክብረት ገልፀዋል፡፡


Read 4539 times