Saturday, 30 July 2016 13:53

ኢህአዴግ በመስቀለኛ መንገድ ላይ ነው!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(43 votes)

· የወልቃይት የማንነት ጥያቄ? ያገረሸ ተቃውሞ በአርሲ? የጎሳ ፖለቲካ ጣጣ?
· ምሁራን ደንግጠው ድምጻቸውን የሚያሰሙት አገር ምን ስትሆን ነው?!
· “ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!” የሚል ከኢህአዴግም ከተቃዋሚም አልገጠመኝ!
· የአሜሪካ መሪዎች፤‹‹God Bless America!!›› ሲሉ ያስቀኑኛል

  አገራችን ጦቢያ------እንደ ዘንድሮ ክፉኛ የተፈተነችበት ጊዜ ያለ አይመስለኝም - በተለይ ባለፉት 25 ዓመታት፡፡ ብዙዎች ገና ለገና የሥልጣን ኮርቻውን የተቆናጠጠው ኢህአዴግ ነው በሚል ስሌት፣ ፈተናውን የገዢው ፓርቲ ብቻ ለማድረግ ሲዳዳቸው ታዝቤአለሁ፡፡ ግን በእጅጉ ስተዋል ወይም ተሳስተዋል፡፡ ፈተናው የሁላችንም ነው፡፡ ፈተናው በአገር የመጣ ነው፡፡ በእርግጥ ኢህአዴግ በመስቀለኛ መንገድ ላይ ነው፡፡
በነገራችን ላይ ኢህአዴግ መንግስት፣እኛ ህዝብ እስከሆንን ድረስ ፈተና በተናጠል አያገኘንም፤ በጋራ እንጂ፡፡ ኃጢያቱ የእኛ ወይም የኢህአዴግ ሊሆን ይችላል፡፡ (ብዙ ጊዜ የኢህአዴግ ነው!) ፈተናው ሲመጣ ግን ለሁላችንም ነው፡፡ እስቲ አስቡት---ለበርካታ ወራት የኦሮምያ ክልልን ያመሰው ተቃውሞና ግጭት--- በሰሜን ጎንደር ከቅማንት ጥያቄ ጋር ተያይዞ የተከሰተው ግጭት---ከዚያው ከጎንደር ሳንወጣ በወልቃይት የማንነት ጥያቄ ሰበብ የተፈጠረው ሌላ ዙር ግጭትና እልቂት---እዚህ አዲስ አበባ መንግስት ህገወጥ ቤቶችን ሊያፈርስ ሲሞክር በተፈጠረ ግጭት የጠፋው ህይወት-----ከዚያም አልፎ ደስ ወደማይልና ወደሚያስፈራ የጎሳ ፖለቲካ (ግጭት) ለማምራት ፍንጭ መታየቱ------ሁሉም ዘግናኝ፣ ሁሉም ለአገር የማይበጅ፣ ሁሉም ወደ ኋላ የሚመልሰን----ፈተና ነው የተጋፈጥነው። እኒህ ታዲያ በምን ሂሳብ ለኢህአዴግ የመጡ “ፈተናዎች” ናቸው ተብለው ቸል ሊባሉ ይችላሉ?! እርግጥ ነው ከላይ ለጠቀስናቸው ተቃውሞዎች፣ አመጾች፣ ኩርፊያዎች፣ ብሶቶች፣ ቀውሶች፣ አለመረጋጋቶች፣ ግጭቶች----ዋና ተጠያቂው ኢህአዴግ ነው። ኃጢያቱ ወይም ጥፋቱ የሌላ የማንም ሳይሆን የራሱ ብቻ ነውና፡፡ እራሱም ይሄን አልካደም። ለኦሮምያ ችግር ጠ/ሚኒስትሩ ህዝቡን ይቅርታ ጠይቀዋል። ከቅማንቶች ጋር ተያይዞ ለተከሰተው ግድያ የአማራ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚዳንት ይቅርታ መጠየቃቸውን ሰምተናል፡፡ ላለፉት 25 ዓመታት እቺን አገር በፈለገበት አቅጣጫ ሲዘውራት የኖረው ራሱ ኢህአዴግ በመሆኑ ጥፋቱም ልማቱም የሱው ናቸው፡፡ የዛሬዋ ጦቢያ በምንም ተዓምር የጃንሆይ ወይም የደርግ ሥሪት አይደለችም - አብዮታዊ ዲሞክራሲው ኢህአዴግ የፈጠራት ናት፡፡ በፈጠራ ሂደት ደግሞ አውቆም ሳያውቁም፣በእውቀት ማነስም በዕብሪትም ብዙ ኃጢያቶች ሊሰሩ ይችላሉ፡፡ ምናልባት የዘንድሮው ፈተና የከበደው ከብዙ ኃጢያቶች የተወለደ ሳይሆን አይቀርም፡፡ እኛ ከጥቂቶቹ በቀር የትኛውን ጥፋት የቱ ጋ እንደፈጸመ ላናውቀው እንችላለን፡፡ እሱ ግን አሳምሮ ያውቀዋል፡፡ የሆኖ ሆኖ ግን ለኢህአዴግ የተላከው ፈተና በሉት መከራ ለኛም መትረፉ አይቀርም፡፡ ኢህአዴግ ብቻውን የሚፈተነው ነገር የለም - ከሚመራው ህዝብ ጋር እንጂ!!  
አንዳንዶች እንደሚመስላቸው፣ የአንድ ፓርቲ ፈተና ቢሆንማ…. ዕዳው ገብስ ነበር፡፡ (ፓርቲው እንደ ፍጥርጥሩ ይወጣዋላ!) ግን አይደለም፡፡ ፈተናው በአገር የመጣ ነው፡፡ ሌላው የማንክደው እውነት ደግሞ ምን መሰላችሁ? ኢህአዴግ ለእዚህ ሁሉ ፈተና ራሱንም እኛንም የዳረገን፣ በአንድ ጀንበር በሰራው ጥፋት ወይም ስህተት ብቻ አይደለም፡፡ ለዓመታት በማንአለብኝነት በተከማቸ የጥፋት ተራራ ነው ለዚህ ፈተና የበቃነው (“አቤቱ ወደ ፈተናም አታግባን” ቀላል ፀሎት እንዳይመስላችሁት!)
ከሁሉም የሚገርመውና የሚያሳስበው ደግሞ ምን መሰላችሁ? ከምንግዜውም በበለጠ በአገሪቱ ላይ ዝምታ መንገሱ ነው!! (‹‹ዝምታው ይሰበር›› የሚል ደፋር እንኳን ጠፍቷል!) መንግስትን ጨምሮ (ከኃይል እርምጃው ውጭ!) ሁሉም ወገን  በዝምታ ተሸብቧል፡፡ በዝምታ መሸበብ ብቻ ሳይሆን ከመቼውም ጊዜ በከፋ ሁኔታ እውነቱን የመሸሽ አባዜም ተጠናውቶናል፡፡ (ኢህአዴግን የሚወዳደረው የለም!) ከማንም በላይ ምሁራኖቻችን ዝምታን መመርጣቸው ደግሞ የበለጠ የዝምታ አዘቅት ውስጥ የሚከት አሳዛኝ ጉዳይ ነው፡፡ ልማታዊነትን ሲሰብኩን የነበሩ የሃይማኖት ተቋማትና መሪዎችም እንዲሁ ዝምታን መምረጣቸው ሌላው የዘመኑ እንቆቅልሽ ሳይሆን አይቀርም፡፡
አገር በእንዲህ ያለ ፈታኝ ችግር ውስጥ ስትወድቅ ባይጠየቁም እንኳን (መቼም ኢህአዴግ የሃሳብ እርዳታ አይመቸውም!) መፍትሄ ማዋጣት ተገቢ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ (ተሳሳትኩ እንዴ?) ወይስ ኢህአዴግ፤ ‹‹ራሴ የፈጠርኩትን ችግር ራሴው እወጣዋለሁ፤ ትንፍሽ ብትሉ ነግሬአለሁ!” የሚል ማስጠንቀቂያ (በምስጢር መሆን አለበት!) ሰጥቷቸው ይሆን?! ወይንስ ‹‹ልማታዊ ፓርቲያችን የሚወስደውን ማናቸውንም እርምጃዎች እንቀበላለን›› የሚል አቋም አስቀድመው ይዘው ይሆን? (ግራ ተጋባን እኮ!)
እስቲ ይታያችሁ… አገር በየአቅጣጫው በተቃውሞና በግጭት ስትናጥ… በትናንሽ ችግሮች ሳይቀር የዜጎች ህይወት ሲያልፍና የአካል ጉዳት ሲደርስ… በሰበብ አስባቡ ንብረት ሲወድምና ሲቃጠል… እንዴት እያዩ ---- እየሰሙ ዝም ይባላል? ያውም በአገር ላይ ተቀምጦ፡፡ ውይይት----ሽምግልና----የመፍትሄ ሃሳብ--እርቅ ---- ብቻ ምንም ይሁን-----ትንሽ እንኳ መሞከር የአባት ነው፡፡ ለመሆኑ በአገሪቱ በዚህ ዓመት የተከሰቱ ግጭቶችና መንስኤያቸውን አጥንቶ ለመፍትሄ የተንቀሳቀሰ ምሁር፣ ዩኒቨርስቲ፣ ተቋም---አለ? ከ32 የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች፣ ለአገሪቱ ፖለቲካዊም በሉት ኢኮኖሚያዊ አሊያም ማህበራዊ ቀውስ መፍትሄ የሚዘይድ አንድ ዩኒቨርሲቲ እንኳን የለንም ማለት ነው? ስንት የሃይማኖት ተቋማት ባሉባት አገር፣ ህዝብን ብቻ ሳይሆን መንግስትን ጭምር አሳምነው (መሪዎች ልብ እንዲገዙ መጸለይንም ይጨምራል!) አገር ሰላም እንዲሆንና ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ ቀን ከሌሊት ሲተጉ ማየት አልነበረብንም?! ቆይ----በኦሮምያ ክልል ግጭት ተባብሶ ስንት ሰው ሲሞት ነው የጦቢያ ምሁራን መደንገጥ የሚጀምሩት?
በቅርቡ በአሜሪካ አንድ ጥቁር በፖሊስ መገደሉን ተከትሎ፣ አምስት የሚደርሱ የአሜሪካ ፖሊሶች በሌላ ጥቁር ግድያ ተፈጽሞባቸው ነበር። (በታጣቂ ግለሰቦች የሚገደሉ የፖሊሶች ቁጥር ጨምሯል) በዚህም የተነሳ አገሪቱ ታምሳ ነበር፡፡ ጥቃቱ በተፈጸመ ማግስት ታዲያ ABC የተባለው ታዋቂ የአገሪቱ  ቴሌቪዥን ጣቢያ፣ በቀጥታ የተሰራጨ የህዝብ ውይይት አዘጋጅቶ ነበር። በዚህ ውይይት ላይ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ አቦማ፤ በጣቢያው ተገኝተው ከዜጎች ለሚነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሾችን ሰጥተዋል። ሌሎች የቴሌቪዥን ጣቢያዎችም ጉዳዩን ዋና አጀንዳቸው በማድረግ፣ የዩኒቨርሲቲ ምሁራንን፣ የህግ ባለሙያዎችንና የመብት ተሟጋቾችን (ከጥቁሮችም ከነጮችም) እየጋበዙ፣ ሲያወያዩ ሰንብተዋል፡፡ ይሄ ደግሞ ለይስሙላ ብቻ የሚያደርጉት አይደለም፤ከውይይት የመፍትሄ ሃሳብ ሊገኝ ይችላል በሚል ነው፡፡ በዚያ ላይ ውይይት፣ ሃሳብን መግለጽ፣የባለሙያ ትንተና መስማት---መደገፍና መንቀፍ (ግን በምክንያታዊነት) ባህላቸው ሆኗል፡፡  እኛስ? በእንዲህ ያለው ክፉ የፈተና ጊዜ እንኳን ግጭቶችን ለማብረድ፣ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን፣ ጥያቄዎችን በሃይልና በአመጽ ሳይሆን በውይይትና በድርድር ምላሽ የሚያገኙበትን መንገድ ለመፍጠር ብንተጋ ያቅተናል? ይፈትነን ይሆናል እንጂ ፈጽሞ አያቅተንም፡፡ ይሄን የምለው ችግሮችን በውይይት መፍታት ለአገራችን እንግዳ መሆኑ ጠፍቶኝ አይደለም፡፡ ልማታዊ መንግስታችን በልማት ከመወጠሩ የተነሳ ከዚህ ቀደም ለውይይት ቢጋበዝ፣ “ሥራ ፈቶች” በሚል ችላ ሊለው እንደሚችል ሳይታለም የተፈታ ነው። አሁን ግን ፈጽሞ አያደርገውም ባይ ነኝ። ለምን ቢባል? የዜጎች ጥያቄ ምላሽ ሳያገኝ፣ አገር በተቃውሞና በአመጽ እየተናጠች፣ስለ ልማት ላውራ ቢል እንደማያዋጣው ወይም ሰሚ ጆሮ እንደማያገኝ ያውቀዋል፡፡ (ደግሞስ ልማቱ ለማን ሆነና?) ሆኖም ግን እስካሁን ዝምታው ይሰበር›› የሚል ደፋር ወደ አደባባይ አልመጣም። የአገሪቱን ብሄራዊ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያ የሚያስተዳድረው፣የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) የውይይት መድረክ በመፍጠር ረገድ ምን ሰራ? የመንግስትን መግለጫ በፕሮፓጋንዳ አጅቦ፣ በየሰዓቱ ከማስተጋባት ውጭ ምንም አላየንም!!
አሁን በግልፅ እንደሚታየው ከገጠመን ችግርና ፈተና የባሰው ደግሞ መንግስት ችግሩን የሚፈታበት ወይም ፈትቼዋለሁ ብሎ የሚያስብበት መንገድ ነው፡፡ ሰሞኑን በአርሲ የኦሮምያ ተቃውሞ ማገርሸቱን ሰምተናል፡፡ ገንኖ አይውጣ እንጂ ቀደም ሲልም በተለያዩ የኦሮምያ ክልሎች ግጭቶች አንደነበሩ ይታወቃል፡፡ መንግስት ለተከሰተው ችግር ራሱን ሙሉ በሙሉ ተጠያቂ አድርጎ ሲያበቃ፣ህዝቡን በይፋ ይቅርታ ከጠየቀ በኋላ፣ (ያውም መንግስት ከተቃዋሚዎቹ ሳይቀር ምስጋና ያገኘበት ይቅርታ ነበር!) ለምን በክልሉ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት አልተፈጠረም? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት፤የመንግስት ይቅርታ ከአንገት እንጂ ከአንጀት አልነበረም፡፡ በዚህም የተነሳ በግጭቱ ሳቢያ ወዳጅ ዘመዶቻቸው የተገደሉባቸው…የአካል ጉዳት የደረሰባቸው----ካሳ አልተሰጣቸውም። ግጭቱን ቀስቅሰዋል ተብለው የታሰሩ ብዙ ሺ ዜጎችም ከእስር አልተለቀቁም፡፡
የመልካም አስተዳደር ችግር… መፍትሄ አላገኘም፡፡ መንግስት ራሱ ያመነበት የስራ አጥነት ችግር አልተፈታም፡፡ አሁንም መንግስት ለህዝብ ተቃውሞ ምላሹ የሃይል እርምጃ ነው፡፡ እኒህ ሁሉ ነገሮች ተደማምረው በክልሉ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዳይሰፍን አድርገዋል ይላሉ - የፖለቲካ ተንታኞች፡፡
አሁንም ቢሆን መንግስት እውነቱን ከመጋፈጥ ውጭ አማራጭ እንደሌለው  መገንዘብ ያለበት ይመስለኛል፡፡ ህዝብ ለተቃውሞ አደባባይ በወጣ ቁጥር የግንቦት ሰባትንና የሻዕቢያን ስም መጥራት የስንፍና ምልክት ነው፡፡ ይልቁንም በተቻለ መጠን ለህዝብ ጥያቄዎች መልስ እየሰጠ፣ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸረ የመጣውን ተዓማኒነቱን ለመመለስ መትጋት ሳይኖርበት አይቀርም፡፡ በህዝብ ዘንድ ዓመኔታ ሳይቀዳጁ አገር መምራት አስቸጋሪ ነው፡፡ (ሞክሬው ባላውቅም!)    ግን መንግስትስ ህዝቡን ያምነዋል? ህዝብና መንግስት ሆኖ ለመቀጠል መተማመን የግድ ነው፡፡  
ኢህአዴግ በእንዲህ ያለው የቀውስ ጊዜ እንኳን ከፓርቲው ውጭ ላሉ ሃሳቦችና ትችት ቀመስ ምክሮች ጆሮውን ይስጥ!! ከነባር ልማዳዊ የፓርቲ አሰራሩ ተላቅቆ፣ ፈተና ለቀቅ ያለ የአመራር ስትራቴጂ ይቀይስ - መሰረቱን ፍጹም ሃቅ ላይ ያደረገ፡፡ እናም --- ከምንጊዜውም በተለየ ለህዝብ እሮሮና አቤቱታ ፈጣን ምላሽ ይስጥ!! አንዳንዴ ህዝብ በምርጫ ማግስትም (ያውም በ100 ፐርሰንት አሸንፎ---) ተቃውሞና ጥያቄ ሊያቀርብ እንደሚችል ከዘንድሮው ፈታኝ ክስተት ግንዛቤ ይወሰድ!! (በዚያውም እውነቱን ይጋፈጠው!)
በአገር ላይ የመጣብንን ፈተና አንድዬ ቀለል ያድርግልን!! ለመሪዎቻችን ልቡና ይስጥልን!! ምሁራኖቻችንንም ሆነ የሃይማኖት መሪዎቻችንን ከአድርባይነትና ከፍርሃት ድባብ ያውጣልን!!
በነገራችን ላይ ለአገራቸው ባላቸው ጥልቅ ፍቅርና ከበሬታ፣ በአሜሪካ ፖለቲከኞች እንዴት እንደምቀና አልነግራችሁም፡፡ (የሚጋባ ፍቅር እኮ ነው ያላቸው!!)…የሁሉም የንግግር መዝጊያ ደግሞ፤‹‹God Bless America!!›› (እግዚአብሔር አሜሪካን ይባርክ) የሚል ነው፡፡ ይሄም ለእኔ ለአገራቸው ያላቸውን ጥልቅ ስሜትና ልባዊ መውደድ ነው የሚያሳየኝ፡፡ የአገሬ ፖለቲከኞች ከአሜሪካውያን እቺን አባባል ኮርጀው፤ ‹‹God Bless Ethiopia!!›› (እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ) ቢሉ ደስታውን አልችለውም፡፡ (ታዲያ ከአንገታቸው ሳይሆን ከአንጀታቸው!) ወይም ደግሞ የሸገር ኤፍኤም፣#ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!” መፈክር፣እንደ ባህል በፖለቲከኞችና በዜጎች ዘንድ  ቢለመድ፣ለመጪውም ትውልድ የአገር ፍቅር ስሜት መፍጠሪያ መንገድ ይሆን ነበር፡፡
ከእኔ ይጀመራ -
 ‹‹God Bless Ethiopia!!››
 ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!” (ደግ አገር እኮ ነው ያለን!!)
Read 10814 times