Monday, 15 August 2016 09:27

ትራምፕ፤ ፕሬዚዳንት ኦባማ የአይሲስ መስራች ናቸው አሉ

Written by 
Rate this item
(9 votes)

   በዘንድሮው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሪፐብሊካንን ወክለው በመወዳደር ላይ የሚገኙት አወዛጋቢው ዕጩ ዶናልድ ትራምፕ፤ ለደጋፊዎቻቸው ባደረጉት የምረጡኝ ቅስቀሳ ላይ፣ “ፕሬዚዳንት ባራክ ሁሴን ኦባማ÷ የአሸባሪው ድርጅት አይሲስ መስራች ናቸው” ሲሉ መናገራቸውን ኤቢሲ ኒውስ ዘገበ፡፡ ትራምፕ ባለፈው ረቡዕ ምሽት በፍሎሪዳ ሰንራይዝ ከተማ ባካሄዱት የምረጡኝ ቅስቀሳ ንግግራቸው ላይ፣“አይሲስን የመሰረቱት ፕሬዚዳንት ኦባማ ናቸው” በማለት ሶስት ጊዜ ደጋግመው የተናገሩ ሲሆን “ከእሳቸው ጋር በመሆን አሸባሪውን ድርጅት የመሰረቱትም ተንኮለኛዋ ሄላሪ ክሊንተን ሳይሆኑ አይቀሩም” ሲሉ ወንጅለዋቸዋል፡፡
አወዛጋቢው ትራምፕ፤በንግግራቸው ወቅት ኦባማን በሙሉ ስማቸው ባራክ ሁሴን ኦባማ ብለው መጥራታቸው፣ ፕሬዚዳንቱ የእስልምና እምነት ተከታይ ናቸው የሚለውን ሃሜት ለማጉላት በማሰብ ነው ያለው ዘገባው፤ኦባማ ስለ ሽብርተኝነት ሲያወሩ አክራሪ እስላማዊ ሽብርተኝነት ብለው ለመናገር አይደፍሩም ሲሉ መንቀፋቸውንም ጠቁሟል፡፡ ፡፡
“ሂላሪ ክሊንተንም ፕሬዚዳንት ኦባማን ላለማስቀየም ሲሉ ይህንን አባባል በንግግራቸው ላይ ተጠቅመውት አያውቁም” ያሉት ትራምፕ፣ ይህም የሆነው ኦባማን ካስቀየምኩ የከፋ ነገር ይገጥመኝ ይሆናል በሚል ስጋት ነው ብለዋል፡፡ ዘ ኢንዲፔንደንት በበኩሉ፤ትራምፕ የወቅቱን የአሜሪካ አስተዳደር ከአይሲስ ምስረታ ጋር በተያያዘ ተጠያቂ ሲያደርጉ የመጀመሪያ ጊዜያቸው እንዳልሆነ በመጠቆም፣ ባለፈው ሃምሌ ላይም አይሲስን የፈጠሩት ሄላሪ ክሊንተን ናቸው ማለታቸውን አስታውሷል፡፡

Read 5808 times