Monday, 15 August 2016 09:22

የማንወደውን ብቻ ሳይሆን፤የማይወደንንም አንመርጥም !!!

Written by 
Rate this item
(23 votes)

• “የዘመናት ብሶት የወለደው” ኢህአዴግ፤ ብሶተኞችን አይሰማም!?
• የሩብ ክፍለ ዘመን ዕድሜ ያስቆጠረው “ዲሞክራሲያችን” ፈሪ ነው!!

ሰሞኑን በኦሮሚያና አማራ ክልሎች፣ብዙ ሺዎች የተሳተፉበት የህዝብ ተቃውሞን ተከትሎ፣  በተከሰቱ ግጭቶች ከ140 በላይ ዜጎች በጸጥታ ሃይሎች መገደላቸው ተሰምቷል፡፡ በእጅጉ ያሳዝናል፡፡ (ጦርነት ሆነ እኮ!!) በነገራችን ላይ ኢህአዴግ የዘንድሮ ተቃውሞ፣ከወትሮው በእጅጉ የተለየ መሆኑን አንድም አላጤነውም አሊያም ማጤን አልፈለገም፡፡ (እውነታውን ማወቅ   ያጥወለውላል!)
በኦሮሚያ ክልል ተቃውሞ ከተጀመረ 9 ወር ገደማ ሊሆነው ነው፡፡ እስካሁን 500 ሰዎች ገደማ ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ግጭቱን ተከትሎ በትንሹ ከ10ሺ የማይንስ ነዋሪ ለእስር መዳረጉን ሪፖርቶች ይጠቁማሉ፡፡ በኢህአዴግ የሥልጣን ዘመንና በእኛ ዕድሜ፣ በዚህ መጠን ህዝባዊ ተቃውሞና በዜጎች ላይ የተፈጸመ ግድያ (አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ) አላየንም፡፡  (ኢህአዴግ ደግሞ አሁንም አላየም!) ዛሬም ማታ ማታ በኢቢሲ የምንሰማው፣ ልማታዊ ዜናዎችና ፕሮጀክቶችን ነው፡፡ (#ጸጉራም ውሻ አለ ሲሉት ይሞታል!” አሉ˜)
ለመሆኑ ሁላችንስ በህይወት አለን እንዴ? በዚህ ምስቅልቅል፣ በዚህ ቀውስ፣በዚህ መተራመስ፣በዚህ አለመደማመጥ፣ በዚህ ጭለማ ---- መሃል እስትንፋስ ስላለን ብቻ እየኖርን ነው ማለት አንችልም፡፡ (እያልኖርንም ነው ሊባል ይችላል!!!) ኢህአዴግ ሁሌ መዘግየት ይወዳል፡፡ ምክር ለመስማት----ይዘገያል፡፡ የህዝብ ቅሬታ ለማጤን-----ይዘገያል፡፡ ለህዝብ ቅሬታ  ምላሽ ለመስጠት---- ይዘገያል፡፡ አገር ላይ እየመጣ ያለውን አደጋ ለመገመት--------ይዘገያል፡፡ ሁሌም ይዘገያል---ኢህአዴግ ነፍሴ!
 የህዝብ ተቃውሞ እየተባባሰ ሲመጣ፣ከተለመደው የሰበብ ክሊሼው ተላቅቆ፣ በፍጥነት ወደ መፍትሄ ቢያመራ ኖሮ፣ ቢያንስ ወደ መጨረሻ ግድም የተከሰቱ ግጭቶችና እልቂቶችን ማስቀረት ይችል ነበር፡፡ በዚህም የዜጎችን ህይወት ከጥፋት፣ንብረቶችን ደግሞ ከውድመት ያተርፍ ነበር፡፡ (በትንሹ 140 ዜጎች  ሞተዋል!) ዕውነቱን ለመናገር------ይሄ ማስቀረት ይቻል የነበረ ዕልቂት ነው!!!
የሰሞኑ አሰቃቂ ጥፋትና ውድመት ውስጤን ሲረብሸኝ ሰነበተና ድንገት አንድ ሃሳብ ብልጭ አለልኝ። እናም እንዲህ አልኩ፡- ከእንግዲህ የማንወደውን ብቻ ሳይሆን፤የማይወደንንም አንመርጥም!! እውነቴን ነው ----- ከአሁን በኋላ ወደ ምርጫ ውድድር ለሚመጡ ወይም  ለሥልጣን ፉክክር ለሚቀርቡ ፓርቲዎች፣ የመጀመሪያው መስፈርት፣ለዜጎች የሚሰጡት ክብር ነው፡፡ ህዝቡን ከልባቸው ይወዱታል? ከምር ይቆረቆሩለታል? ለዜጎች ህይወት ዋጋ ይሰጣሉ? በስደት ለሚኖር ኢትዮጵያዊ መብትና ነጻነት ይከራከራሉ? ይሄን የሚያሟሉ መሆናቸው በዲኤንኤ ይሁን በሌላ ሲረጋገጥ ብቻ ነው ለሥልጣን የሚወዳደሩት፡፡ የወደፊት መንግስታችን፤ ሥልጣን ብቻ የሚወድ ሳይሆን እኛንም ጭምር የሚወድ መሆን አለበት፡፡ የማይወደን አይገዛንም!!!
ላለፉት 25 ዓመታት፣ ወደንም ይሁን ሳንወድ የገዛን ልማታዊው መንግስት፤ዜጎቹን ለመውደዱ ማረጋገጫ ማቅረብ ይከብዳል፡፡ ዜጎቹን የሚወድ ቢሆን ኖሮ፤ #ያለ ፈቃዴ ሰልፍ  ወጣችሁ” ብሎ የሃይል እርምጃ ይወስድ ነበር!? (ግን መንግስት የት ነው የሚከሰሰው?) እኔ የምለው --- በሰሞኑ ተቃውሞ ለምንድን ነው የበርካቶች ህይወት ያለፈው? ባለፈው ቅዳሜና እሁድ የሞቱ ዜጎች ቁጥር በእጅጉ ያሻቀበው፣መንግስት ማስጠንቀቂያ ከሰጠ በኋላ ሰዎች ለተቃውሞ በመውጣታቸው ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ (አንድ ወዳጄ፤#መንግስት ማስጠንቀቂያውን በቃና ቲቪ ቢያስተላልፈው ይሻል ነበር አለችኝ!!)  
እናላችሁ---- በአንድ በኩል የተናገሩት ከሚጠፋ በሚል ብሂል፣በሌላ በኩል ኢህአዴግ አልቆለታል ባዮችን እንዳላለቀለት ለማሳየት (#ትዕግስት ፍርሃት አይደለም” ዓይነት!!) ለተቃውሞ የወጡ ዜጎች ላይ የሃይል እርምጃ የተወሰደ ይመስላል፡፡ ምናልባት እኮ ጠንካራነቱን ለማሳየት የፈለገው ለአንዳንድ ዳያስፖራ ታጋዮችና ፖለቲከኞች ይሆናል፡፡ የሞቱት ግን ኑሮአቸው እንዲሻሻል፣መብታቸው እንዲከበር፣ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዲሰፍን-----አደባባይ ወጥተው የጮሁ ምስኪን ኢትዮጵያዊያን ናቸው፡፡
አሳዛኙ እውነታ ደግሞ ምን መሰላችሁ? በዚህ የቀውስ ወቅት እንኳን የሩብ ክ/ዘመን ዕድሜ ያስቆጠረው #ዲሞክራሲያችንም” ሆነ ኢህአዴግ ማስፈራሪያ ያደረገው ህገ-መንግስታችን፤ ዜጎችን ከሞትም ሆነ ከመቁሰል እንዲሁም ከእስር አልታደጓቸውም፡፡ (የ25 ዓመቱ ጎረምሳ “ዲሞክራሲያችን” አሁንም ፈሪ ነው!!) እንደኔ  እንደኔ፣መንግስት ጥንካሬውንና ጀግንነቱን ማሳየት የነበረበት ህገ-መንግስቱን በማክበር ነበር!! አህአዴግ ነፍሴ ያደረገው ግን የተገላቢጦሹን ነው፡፡ (Cገ-መንግስት ያስፈለገው ጥይት እንዲቀር መስሎኝ?!) ለካስ በትልቁ ተሳስቼአለሁ!!
     በነገራችን ላይ ኢህአዴግ፤ለህዝብም ሆነ  በፓርቲ  ተደራጅቶ ለሚካሄድ የተቃውሞ ሰልፍ፤ተመሳሳይ ስሜትና ምላሽ ይኖረዋል ብዬ አስቤም አልሜም አላውቅም፡፡ (ለካስ ህዝብም ተቃወመ ሰማያዊ፤ለውጥ የለውም!!!) ይገርማል፤ግን እንዴት ለውጥ የለውም? ለምሳሌ ሰማያዊ ፓርቲ፤አነሰም በዛም የሥልጣን ተፎካካሪው ነው፤ስለዚህ ተቃውሞውን ብቻ ሳይሆን የሚተነፍሰውንም አየር ጭምር ቢፈራ ችግር የለውም። ህዝብ አደባባይ ወጥቶ፣ብሶትና በደሉን ቢያቀርብ ግን ምን ያስፈራል?? አሁን ለምሳሌ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች፣ ህዝቡ ምን የሚያስፈራ ነገር ጠየቀ? ምን የማይቻል ነገር አድርጉልኝ አለ?? (መቼም ሥልጣን አጋሩኝ አይልም!) ቢጠይቅ እንጀራውን---- ቢጠይቅ አርሶ የሚበላበትን መሬቱን----ቢጠይቅ ለልጆቹ ት/ቤት---- ቢጠይቅ ፍትህ----ቢጠይቅ መብትና ነጻነቱን----ቢጠይቅ ወህኒ የተወረወሩ የትግል ጓዶቹ------ ከእስር እንዲፈቱለት ነው፡፡ ቢጠይቅ በጸጥታ ሃይሎች ለተገደለበት ወንድሙ ወይም ልጁ ካሳ ነው፡፡ በቃ ይሄው ነው!!!
እኔማ----ህዝቡ ተጠራርቶ፣ለተቃውሞ አደባባይ የሚወጣው ችግር አናቱ ላይ ሲቆለልበትና በደልና ግፍ ሲበዛበት እንደሚሆን ከኢህአዴግ ነፍሴ የበለጠ የሚረዳ የለም ብዬ ደምድሜ ነበር፡፡ (በ82“ብሶት የወለደው የኢህአዴግ ሰራዊት” ያለውን አስታውሼ እኮ ነው!!!) የተሸወድኩት ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? ከ25 ዓመት ብሶትና በደል አልባ የሥልጣን ዘመን በኋላም፣ የሌሎችን ብሶትና በደል የሚያዳምጥበት ጆሮ ይኖረዋል ብዬ መገመቴ ነው!!! (ያውም ራሱ በዳይና ብሶት ፈጣሪ በሆነበት አገር!!) በእውነቱ ይቅርታ የመጠየቅ ታላቅ ልማድን ከራሱ ከኢህአዴግ ተውሼ፣እነሆ ይቅርታ እጠይቀዋለሁ!! (ለሽሙጥ ሳይሆን ከልቤ!!) እንዴ----ገና ለገና ከብሶትና ከበደል የተወለደ ፓርቲ ነው ብዬ፣የመላዕክት ሥራ እንዲከውን መጠበቄ ታሪካዊ ስህተት ነው፡፡ (ግፋ ቢል የኮሙኒስቶች ስብስብ ይሆናል እንጂ ፈጽሞ የመላዕክት ስብስብ አይሆንም!!!)  
 ሰሞኑን ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም በፌስቡካቸው ላይ ባሰፈሩት አጭር ማስታወሻ ፅሁፌን እቋጫለሁ፡- ሰላማዊ ተቃውሞን ‹‹በቁጥጥር ሥር አውለነዋል›› ማለት ራሱ ሰብዓዊ መብቶችን ማዳፈናን ማወጅ ነው፡፡ ሰላማዊ ተቃውሞ መፈቀድ አለበት፤ መደመጥ አለበት፣ ሰላማዊ መልስ ማግኘት አለበት፣ እስከ መቼ ነው ሁሉንም ዓይነት ልዩነት በጡንቻ እየዳመጡ (መቆጣጠር) የሚቻለው? መቼ ነው ገዢዎቻችን የሚማሩት? ለመሆኑ የመማር ችሎታስ አላቸው ወይ?”












Read 5537 times