Monday, 05 March 2012 14:32

የተቀረቀሩ የጥበብ አድማሣት - ሽንቁሮች

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(0 votes)

አንድ የሀገራችን ውድ ሃያሲ ስለዘመኑ ግጥሞች አንሥቶ ሲናገር “… የሚያሣዝነኝ፣ ፍሬ ያላቸውም በገለባዎች መዋጣቸው ነው፡፡” ማለቱ ዛሬም ይገርመኛል፡፡ ስለ ግጥም ብዙ ጊዜ በዚሁ ጋዜጣ ላይ ፅፌያለሁ፡፡ የራሴን አመለካከት ብቻ ሣይሆን ታላላቅ የሚባሉ የዓለማችን የግጥም ፈርጦችንም ጠቅሻለሁ፡፡ ይህ ሁሉ ግን ስለ ግጥም ታላቅነት በሰዎች ልብ ውስጥ ለመቅረፅ ካለኝ ጉጉት ነው፡፡ ሊያድጉ የሚገባቸው እንዲያድጉ አቅሙ የሌላቸው የመሮጫውን መም እንዲሠናበቱና የራሳቸውን ዘውግ እንዲያሣድዱ፡፡

ግጥም ለማጣጣም ፍላጐት ያሥፈልጋል፣ ከፍታውን ለመመተር ደግም ግጥምንና ስለ ግጥም የተፃፉ መፃሕፍትን ማሣደድ የግድ ይላል፡፡ በየትኛውም ዘውግ ደግሞ ያንዱን ሥራ ካንዱ ጋር ሥናለካካ የሚለያዩባቸው ውበቶችና እንከኖች ይኖራሉ፡፡ ከዚህ በፊት ለማሣየት እንደሞከርኩት አንዱ በቋንቋ የበለፀገ ይሆንና ሀሣቡ ገለባ ወይም ብርቅ ያልሆነ ይሆናል፡፡ ሌላው ደግሞ ብርቅ ሀሣብ ድንቅ እይታ ይኖረውና በመናኛ ቃላት ጀርባ ሲያስቀምጣቸው ክብራቸው ዝቅ ይላል፡፡ ውድ አልማዝን በ10 ሳንቲም ፌስታል የማንጠልጠል ያህል፡፡ ታዲያ በዘመናችን ዝቅ ያለውን የግጥም ክብር ለማሥመለስ ብዙ ጥረት ማድረግ ሲገባ ሁሉም እንደተለመደው አንገቱን ቀብሮ በምናገባኝ መከተቱ አሣዛኝ የዘመናችን መልክ ነው፡፡ አንዳንዶቹ በመደለያና በጓደኝነት እዚህ ግባ የማይባሉትን ግጥሞች ቄንጥ እያወጡ ግጥሙን ለመግደል የራሳቸውን ድንጋይ ወርውረዋል፡፡ በደሙ ማን መቼ እንደሚጠይቃቸው ባላውቅም ሌሎቹ ደግሞ ተስፋ የሚታይባቸውን እንኳ “አይዟችሁ! ባለማለታቸው ተጠያቂ ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህ እንግዲህ የኛ የሀበሻዎቹ ችግር ብቻ አይመሥለኝም፡፡ አንዴ አሜሪካዊያኑ ደራስያንና ሃያሲያን ውሏቸው ባንድ ሆኖ ጓደኝነታቸው ፀንፎ ሥነ ጽሑፉ ብቻ ሣይሆን ሂሱ ራሱ - ገደል ገብቶ እንደነበር አሣዛኝ ታሪኩ ተፅፎ አንብቤያለሁ፡፡

እኔም በግሌ የበድሉ ዋቅጅራን “ፍካት ናፋቂዎች” … በቋንቋና በሀሣብ ብስለት - የመሰጡኝን፣ የበዕውቀቱ ሥዩምን የላቁ ሀሣብ የያዙ ግጥሞችና የታገልን የቋንቋ ሀብቶች ጨምሮ - የሌሎችን ጥቂት ገጣሚያን ስራዎች ለመዳሠሥ ሞክሬ ነበር፡፡ ምክንያቱም ያሉትን ካልመረቅን፣ የሌሎችን መርገም ብቻ ዋጋ የለውምና፡፡

ስለ ሀገራችን ግጥሞች ሣሥብ የነቢይ መኮንንን፣ የወንድዬ ዓሊን፣ የዳዊት ፀጋዬን፣ የሜሮን ጌትነት (ዳቦ ቆሎ ግጥሞች) እንደ ተስፋ ግጥሞች - በስለት አያለሁ፡፡ የቅርቦቹንም አጤናቸዋለሁ፡፡ የዜማና የምት፣ የቃላት ከፍታቸውን እንደ ችግር ብወሥድም፡፡

ከሦስት ዓመት በፊት የገዛሁት በጣምም ያልተገረምኩበት፣ ግን ደግሞ ቆንጥጦ እየያዘኝ ፈልጌ የማነብበው የአንዲት እንስት ገጣሚት ግጥም በእጄ አለ፡፡ እየቆየሁ መጽሐፉን እፈልገዋለሁ፡፡ አነብበውና እገረማለሁ፡፡ ተገርሜ “ይህቺ ልጅ ሌላ ብትፅፍ” እያልኩ እጓጓለሁ፡፡ ልጅቱ ግን አልደገመችም፡፡ “ለምን ይሆን?” ብዬ አሰብኩ፡፡   “ግን ጥሩ ነገሯን እንኳ መች ነግረናት?” ብዬ ራሴን ወቀስኩ፡፡ የመጽሐፍዋ ጥራዝ ደንደን ያለ አይደለም፡፡ የገጣሚዋ የቃላት ከፍታም ብዙ አይደለም፡፡ … ግን ከፍ ያለ አተያይ፣ ጥሩ ምልከታ አላት፡፡ “ተራማጁ ሐረግ” ይላል - ግጥሟ፡፡ “ይህቺ ልጅ ብትፅፍ” ታድጋለች!” ይለኛል ልቤ፡፡ ምክንያቱም ወጣት ናት፡፡ ገና በዕድሜ፣ በልምድና በገጠመኝ ስትሣል፣ በንባብ ሥትዳብር ብዙ ማየት ትትላለች ብዬ አሠብኩ! እና የኔስ ልብ ግጥሞችዋን ለመምረጥ በከንቱ የባተተ? አይመሥለኝም፡፡ የማረከኝ ነገር አለ፡፡ ታዲያ - ለዳኝነት የተወሰኑትን ግጥሞች ከፍሬሕይወት ካሣ “ተራማጁ ሐረግ” ለምን አናነብብም? ራሴ በገዛሁት መጽሐፍ የኮከብ ምልክት ያደረግሁባቸውን መርጬ አሠፍራለሁ - ጥቂቱን፡፡

ተወው!

አይግረምህ ፍቅሬ

አትደነቅ ውዴ!

በተፈጠረው ጥል

በፀናው ጠባችን

በመካከላችን፡፡

 

ገና ያኔ ድሮ

ጥንድ አካል

ጥንድ አምሳል

ባህሪያችን ለየቅል

ሆኖ ነው ነገሩ

ያለመቀላቀል ያለመዋሃዱ

ፍቅራችን ሲማከል

መዝቀጡ መጥለሉ፡፡

ሀሣቡ ወደ አዳምና ሄዋን ግንድ ይሄዳል፡፡ ያኔም የተለያየን ሁለት ስለሆንን አሁንም ዘይትና ውሃ መሆናችን ከዚያ የመጣ ስለሆነ ለምን አንድ አልሆንንም ብለህ አትደነቅ እያለች ነው - ገፀባህሪዋ! ካለንበት ወደ ኋላ ሄደን ሥናየው እውነት ነው፡፡ ፍቅራቸው መማሠሉ ደግሞ በችግር መፈተኑ መሠለኝ፡፡ አሁን ደግሞ “ሰው ሰይጣን” የሚለውን ሌላ ግጥሟን እንይ፡፡

ሰይጣን ለምን ይጥፋ - ይኑር በገፍ በገፍ

የስህተታችን ጋሻ - እኮ ለምን ይርገፍን!!

በሰው ልጅ አጥፊነት

በሱው ባይሳበብ

እሱ ባይጋራን

እሱ ባይቀጣ

እሱ ባይገረፍ

ማን ቁሞ ያይ ነበር - ስንት ሰው ሲጐዳ

ስንት ሰው ሲቀሰፍ?

ይህ ሂስ በሃይማኖት ካባ፣ ስህተታችንን ለምንሸፍነው አመፀኞች የተፃፈ ነው፡፡ ሀሣብ አውጠንጥነን፣ አልመን ካበቃን በኋላ “ሰይጣን አሣሣተኝ” ብለን በእርሱ እናላክካለን፡፡ እርሱ ደግሞ አይታይ ነገር፤ ተጠርቶ አይጠየቅ! በእምነት “ሰይጣን አሣሥቶት ነው” ብለን ራሣችንን እናሣሥታለን፡፡ ፍሬ ሕይወትም በዚህ ሰበባችን ነው ያሽሟጠጠችው!

“የተራማጁ ሐረግ” ደራሲ ሌላም ቀልቤን የሳቡኝ ግጥሞች አሏት፡፡ “ኖር!” የሚለው ርዕስ ተመችቶኛል፡፡

በእንግዳ አክባሪ አገር

ህፃናት ሲወለዱ እጆቹን አጣጥፎ

እልል ብሎ ከጠበቀ

እጅጉን ተሻለ

እነሱ ሲመጡ ቦታ የለቀቀ፡፡

ይህች አጭር ግጥም እንደንፋስ ብዙ ቦታ ትበትነናለች፡፡ ውስጠ ወፍራም ትመሥላለች፡፡

አዲሱን ትውልድ “እልል” ብሎ ብቻ አይደለም መቀበል፣ ይልቅስ ቦታም ሊሰጠው ይገባል! የሚል ሞጋች ድምፅ ከውስጡ በቀስታ ተደብቆ፣ በሕሊና በሃይል የሚጮህ ይመሥላል! ይህንን ሥናይ ገጣሚዋ ገና ልትፅፍ፣ ልታድግ ትችላለች  የሚል ጉጉት ውስጣችን ይፈጠራል፡፡  ብትበረታና ብታድግ ጥቅሙ ለኛ ነው፡፡ ጥሩ ግጥሞች አንብበን እንደ ቢራቢሮ በአበባ ሀሣቦች ላይ በምናብ እንበርራለን! ግጥም አበባ  ነው! የሕይወት ማር የሚጋገርበት፡-

የመሠናበቻ ግጥም ምርጫዬ “ያለኔ ያላንተ” የሚለው ይሁን!

ደመና ፈትዬ … ኩታ ደርቤያለሁ

ኮከቦች ዘግኜ … አዝራር ተክያለሁ

በቀስተ ደመና .. ሽንጤን ታጥቄያለሁ

ላንገቴ ጨረቃን … ጌጥ አሰርቻለሁ

ከመብረቅ ብልጭታ … ሳቄን ቀምሜያለሁ

እናም ወዳጄ ሆይ ካንተነትህ ወፍጮ

ፍቅር ከተቋተ

ለውበቴ ድምቀት … ጨለማ ሁን አንተ፡፡

ካንዱ ስንኝ በስተቀር የውበትና የብርሃን ምንጮች ውስጥ ገፀ ባህሪዋ ስለተንተገተገች አሁን ብርሃንዋን ለማድመቅ የቀራት ነገር አለ፡፡ ያም ጨለማ ነው፡፡ ስለዚህ ጓደኛዋ/ፍቅረኛዋ ፍቅር ካለው ለርሷ ብርሃን ጨለማ መሆን አለበት!! .. ዳኝነቷ ምን ያህል ጤናማ እንደሆነ የፍቅር አምላክ ይፈትሸው ብለን እናሽሟጥጥ እንጂ በየፊናችን እንገረማለን!

ስለዚህ የገጣሚዋ እሸት ግጥሞች ተስፋ ሰጪ ናቸው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ምናልባትም ግጥሙ ከመታተሙ በፊት በአርታኢ ቢታዩ የተሻሉ ሊሆኑ ይችሉ ነበር፡፡ የዓለማችን ብርቅዬ ገጣሚ ኤሚሊ ዲክንሰንም ግጥሞች የተወለወሉት በበሳል አርታኢያን ነበረና! … ስለዚህ እኛም የተቀረቀሩ የጥበብ አድማሳትን ሸንቁረን ተስፋዎቻችንን ማየት ያለብን ይመስለኛል፡፡

 

 

Read 3263 times Last modified on Monday, 05 March 2012 14:35