Monday, 29 August 2016 10:34

ሃሳብዎን በ“ነፃነት” ይግለጹ!!

Written by 
Rate this item
(12 votes)

1- ኢህአዴግ ያለፉት 15 ዓመታት የተሃድሶ ጉዞውን ገምግሞ ሲያበቃ ያወጣው መግለጫ ግርታን ፈጥሯል፡፡ እርስዎስ የገዢውን ፓርቲ መግለጫ እንዴት አዩት?
ሀ) በህዝብ ተቃውሞ ከሚናጥ ፓርቲ የወጣ መግለጫ አይመስልም!
ለ) በስህተት ያለፈውን ዓመት መግለጫ ደግመውት እንዳይሆን!
ሐ)  ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ!!
መ) ኢህአዴግ ራሱን በራሱ በመሸወድ የሚደርስበት የለም!
ሠ) የሌላ አገር ፓርቲ ያወጣው መግለጫ ሳይሆን አይቀርም!
2- ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ፤ባለፈው ሳምንት የመኢአድ መሪዎችን በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ እንዳወያይዋቸው ተዘግቧል፡፡ በኢህአዴግ የ25 ዓመት የሥልጣን ታሪክ፣ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችን በቤተ-መንግስቱ ጋብዞ ሲያነጋግር የአሁኑ የመጀመሪያው ነው ተብሏል፡፡ እርስዎ ዜናውን ሲሰሙ ምን አሉ?  
ሀ) እቺ አገር ተስፋ አላት!!
ለ) ግብዣ ነው ውይይት?
ሐ) ከውይይቱ የተገኘው ውጤት አልተነገረንም!!
መ) ግን እስከ ዛሬ ለምን ዘገዩ!?
ሠ) “የቱርክ ኢንቨስተሮችን ሲባሉ ከተቃዋሚዎች ጋር ተሞዳሞዱ” በሚል እንዳይገመገሙ ሰጋሁ!
3- በሪዮ ማራቶን 2ኛ በመውጣት ድል ያስመዘገበው አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ፤ ለኦሮሞ ተወላጅ ኢትዮጵያውያን ያለውን የትግል አጋርነት ለማሳየት እጆቹን ወደ ላይ በማጣመር ተቃውሞውን ለዓለም ገልጧል፡፡ መንግስት በበኩሉ፤ አትሌቱ ወደ አገሩ ቢመለስ የተለየ ችግር እንደማይገጥመው አስታውቋል፡፡ እውነት ወደ አገሩ ቢመለስ  ችግር ሳይገጥመው በነጻነት የሚኖር ይመስልዎታል?
ሀ) ይሄን ለማወቅ ኢህአዴግን መሆን ይጠይቃል!
ለ) “አልበላሽምን ምን አመጣው?!” አለች ጦጢት!!
ሐ)መንግስት እንዳይምልለት ፕሮቶኮሉ አይፈቅድም!   
መ) ቆይ ግን ምን ፍለጋ ወደ አገሩ ይመለሳል!?
ሠ) ኢህአዴግ ገና አሁን ንግግር ተሳካለት!
4- በአማራና በኦሮምያ ክልሎች ህዝባዊ ተቃውሞ በተቀሰቀሰበት በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ ጠ/ሚኒስትር ቢሆኑ ምን ዓይነት የመፍትሄ እርምጃ ይወስዱ ነበር?
ሀ) እስካሁን በኦሮምያ ቢያንስ 4፣በአማራ 2 ህዝባዊ ውይይቶችን አደርጋለሁ!
ለ) በቀውጢ ሰዓት ጠ/ሚኒስትር መሆን አልፈልግም!
ሐ) ተቃውሞውን ተከትሎ የታሰሩ ዜጎችን በሙሉ እፈታለሁ!!
መ) ከተቃዋሚ ኃይሎች ጋር መደበኛ ውይይት እጀምራለሁ!
ሠ) “ከበሮ በሰው እጅ ሲያዩት ያምር፣ሲይዙት ያደናግር!; የሚለው ተረት ትዝ አለኝ!!
5- የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፤በህዝቡ ላይ ፍርሃት ላለመፍጠር በሚል በአተት የሞቱ ሰዎችን ቁጥር አንድም ያስተባብላል አሊያም ጨርሶ ከመናገር ራሱን ያቅባል፡፡ ይሄን የሚያደርገው ለምንድን ነው ብለው ያስባሉ?
ሀ) እንደ ኢህአዴግ የቁጥር ፎቢያ ይኖርበታል!!
ለ) ወረርሽኙ ሲቆም ለተረፍነው “ሰርፕራይዝ” ሊያደርገን ፈልጎ ነው!
ሐ) አተትም ፖለቲካ ሆናለች ማለት ነው!!
መ) የአገር ገጽታ እንዳይበላሽ ተብሎ ይሆን?
ሠ) ፍርኃት እኮ ህዝቡን የበለጠ እንዲጠነቀቅ ያተጋዋል!
(N.B- ከተሰጡት ምርጫዎች ውስጥ ለእርስዎ የሚስማማ ከሌለ፣
የራስዎትን ምርጫ (ረ) የማካተት መብትዎ የተጠበቀ ነው!!!)

Read 3889 times