Monday, 29 August 2016 10:35

ከአውራው ፓርቲ ጋር የተደረገ ምናባዊ ቃለ ምልልስ!!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(31 votes)

“አገር በደቦ ወይም በማህበር አትመራም” - ኢህአዴግ
   (በአገሪቱ ወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ዙሪያ ከአውራው ፓርቲ ኢህአዴግ ጋር የተደረገውን ምናባዊ ቃለምልልስ በጥሞና እንድትከታተሉ ተጋብዛችኋል። የገዢው ፓርቲ አመራሮች እንኳን ለእኔ ቃለ-ምልልስ የሚሰጡበት ጊዜ ቀርቶ መደበኛ ሥራቸውን የሚያከናውኑበት ጊዜ አጥተዋል፡፡ (ሥልጣን ዕዳና ስጋት መሆኑ የገባቸው አሁን ነው!) በአንድ በኩል የፓርቲው ግምገማ (ያውም የ15 ዓመት)፣ በሌላ በኩል የህዝብ የተቃውሞ መንስኤን ለማጣራት ስብሰባ (ቢያንስ ለፍረጃ እንዲመች!) በእጅጉ ወጥሯቸዋል፡፡ ነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ ላይ ናቸው፡፡
ስለዚህ በህዝባዊ ተቃውሞው ዙሪያ ትንተና፣መፍትሄ ወዘተ-----ከእነሱ ለማግኘት አይታሰብም፡፡ (ሲያውቁት አይደል?!) ለዚህ ነው አዲስ ሃሳብ አመንጭተን፣ከራሱ ከገዢው ፓርቲ ጋር ምናባዊ ቃለ-ምልልስ ለማድረግ የመረጥነው፡፡ እንግዳ ሀሳብ ቢመስልም ይለመዳል፡፡ እንደውም ከዚህ በኋላ ሚኒስትር ወይም ኮሚሽነር አሊያም ዳይሬክተር ልናነጋግር ፈልገን የማይጨበጡ ከሆኑብን ከሚመሩት መ/ቤት፣ተቋም፣ድርጅት ወዘተ ጋር ምናባዊ ቃለ-ምልልስ ማድረግ ይቻላል፡፡ (አንዳንዴ ከአመራሮቹ የተሻለ መረጃ ልናገኝ እንችላለን!) እናላችሁ-----ሁልጊዜ የመልካም አስተዳደር ችግር----ምናምን እያልን ከማለቃቀስ፣ለጊዜው የፈጠራ አቅማችንን  ተጠቅመን መፍትሄ ብናበጅ ተመራጭ ነው፡፡ ወደ ቃለ-ምልልሱ ከመግባቴ በፊት አውራ ፓርቲውን (ኢህአዴግን) በ“ሰፊው ህዝብ” ስም ላመሰግነው እወዳለሁ፡፡)
 
ፖለቲካ በፈገግታ፡- ድርጅታችሁ ያለፉት 15 አመታት የተሃድሶ ጉዞውን ከገመገመ በኋላ ባወጣው መግለጫ ላይ እንዲህ የሚል አስደንጋጭ ሃረግ አንብቤአለሁ፡- “ባለፈው ዓመት አገሪቱ የገጠማትን በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የድርቅ አደጋ ትርጉም ያለው የውጭ እርዳታ ሳይገኝ በራስ አቅም ልንቋቋም መቻላችን፣ በአገራችን ምን ያህል የተጠናከረ የኢኮኖሚ ግንባታ ሲካሄድ---” ይሄ አገላለጽ በሚሊዮን ዶላሮች አውጥተው ድርቁን እንድንከላከል ያገዙንን የምዕራብ መንግስታት አያስቀይምም? እኛንስ ውለታ-ቢስ አያሰኘንም? ምስጋናው ቢቀር እንኳን ለምን በደግነት የለገሱንን እንክዳለን?
አውራው ፓርቲ፡- እንግዲህ እንደ ደርግ ህዝብ ለህዝብ የኪነት ቡድን አደራጅተን ዓለምን እየዞርን ማመስገን አንችልም፡፡ እኛ እንደሱ ሥራ ፈት አይደለንም፤በልማት ተወጥረናል፤ለአፍታ ዞር ብንል ህዝቡ ይበላናል፡፡ ይሄው ውልፊት ሳንል እንኳን የተቃውሞ ጎርፍ ይዞን ሊሄድ ደርሶ የለም እንዴ፡፡ ደርግ የልማት በለው የማንነት አሊያም የነጻነት ጥያቄ ቀርቦለት፣ሲባል ሰምቶም አያውቅም። ኢህአዴግ ግን አርሶ አደሩን ሚሊዬነር በማድረግ ብቻ አልተወሰነም። የዲሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ጥያቄዎችን የሚያነሳ (ፖለቲካል አዌርነስ ያለው) ህገ መንግስቱን ከአርቃቂዎቹ በላይ አብጠርጥሮ የሚያውቅ ንቁ አርሶ አደርም ጭምር ነው የፈጠረው፡፡ ለዚህ ነው አሁን በመብትና ነጻነት፣በእኩልነትና በፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ጥያቄዎች የተጨናነቅነው፡፡ ተገቢውን ምላሽ የማንሰጠው ከሆነ ደግሞ #ዞር በሉልኝ! መብትና ጥቅሜን የሚያስከበርልኝ መንግስት ራሴ እሾማለሁ” ከማለት ወደ ኋላ የማይመለስ ትንታግ የኦሮሞ ወጣት ነው የፈጠርነው፡፡
በአንድ በኩል ሲታይ ህዝቡ ለመብቱ ማመጹ የኢህአዴግ የትግል ፍሬ በመሆኑ ያኮራናል፡፡ በሌላ በኩል ግን የደርግ ዓይነት #ህዝብ ለህዝብ” የኪነት ቡድን ለማደራጀትና እንዳልከው እንደ ደርግ እየዞርን ዓለምን ላደረግልን ውለታ ታንኪው ለማለት ጊዜ አሳጥቶናል፡፡ እንጂ ውለታ ለመካድ አይደለም፡፡ ይሄ የኢህአዴግ ባህርይ አይደለም፡፡
ፖለቲካ በፈገግታ፡- በየአካባቢው የሚቀሰቀሱ ተቃውሞዎች፣መንስኤያቸው ምንድን ነው   ብላችሁ ነው የገመገማችሁት?
አውራው ፓርቲ፡- በእርግጥ ግምገማችን በሂደት እየጠራ የመጣ ነው፤ተቃውሞው የተጀመረ ሰሞን በአንዳንድ አመራሮች ላይ ብዥታዎች ይታዩ ነበር። ይሄ ደግሞ ተቃውሞው በፈጠረው መደናገጥ የመጣ ነው፡፡ አሁን ባጠራነው ግምገማችን መሰረት፣ ህዝቡን ለተቃውሞ ያነሳሳው አንዳንድ የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮች ሃብት ማፍራት ወይም ኪራይ ሰብሳቢነት ነው፡፡ የተቃውሞው መንስኤ ይሄ ነው ብለን በግምገማችን አስቀምጠናል፡፡
በዚህ መሰረት፤ የህዝቡ ጥያቄ ምላሽ የሚያገኘው በፓርቲው ውስጥ የተሰገሰጉ ጥገኛ ሃብታም ባለሥልጣኖችን ወይም ኪራይ ሰብሳቢዎችን ያለ አንዳች ምህረት ጠራርገን ስናጠራ ብቻ ነው በሚለው ላይ ከስምምነት ደርሰናል፡፡ ስለዚህ በድርጅቱ ውስጥ አንድም ሰው እስኪቀር ቢሆን የማጥራት ሥራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡     
ፖለቲካ በፈገግታ፡- በሌላ በኩል ህዝባዊ ተቃውሞው በውጭ ሃይሎች እንደሚመራ ከመንግስት በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል፡፡ አሁን ከነገሩኝ ጋር እንዴት ማስታረቅ ይቻላል?
አውራው ፓርቲ፡-  ግንቦት 7 እና ሻዕቢያ በህዝቡ ተቃውሞ ውስጥ እጃቸው አለበት ማለት፣ ለእነዚህ አሸባሪ ድርጅቶች የማይገባቸውን የታጋይነት ልዕልና ወይም የትግል መሪነት ቦታ መስጠት ነው፡፡ የነጠረው ግምገማችን የሚያመለክተውም፣አንዳንድ የቀለም አብዮተኞች  በቀጥታ ሳይሆን በእጅ አዙር፣ ተቃውሞና አመጹን እንደሚቆሰቁሱት ነው፡፡ ሆኖም የእነርሱ ድርሻ እሳቱን ለማቀጣጠያ የሚሆን ነዳጅና ላምባ ገዝቶ ከማቀበል የዘለለ አይደለም፡፡ እሱም ቢሆን ቀላል ነው ለማለት አይደለም፡፡ ቢያንስ አገር ውስጥ ገብተው እሳቱን የመለኮስ፣ማገዶ የመጨመር ዕድል አለማግኘታቸው ነው ያተረፈን። ህዝቡም ደግሞ እኛን ስለተቃወመ ብቻ ለነሱ ፊት አልሰጣቸውም፤ማኩረፊያ እንጂ ለዘለቄታው እንደማይሆኑት ጠንቅቆ ያውቃል። እንደ ኢህአዴግ ያለ ህዝባዊና ልማታዊ መንግስት መቼም አያገኝም። ለዚህ ነው ኢህአዴግን እንደ ህጋዊ ሚስት፣የውጭ ሃይሎችን እንደ ውሽማ የሚቆጥረው። ውሽማን ደግሞ ሚስቴ አናዳኛለች ብለህ ወደ ቤት ይዘሃት አትመጣም፡፡ ውጭ ነው የምትጨርሰው፡፡ ትዳርህ እንዲበጠበጥ አትፈልግማ!!    
ፖለቲካ በፈገግታ፡- ተቃውሞው የራሱ የህዝቡ ነው ብላችሁ ካመናችሁ፣ለተቃውሞ አደባባይ የሚወጡ ዜጎች ለምንድን ነው የሚገደሉት? ህገ-መንግስቱን መጣስ አይሆንም እንዴ?
አውራው ፓርቲ፡- ይሄንንም ቁጭ ብለን ገምግመነዋል፡፡ ችግሩ የሚከሰተው ተቃውሞና አመጽ እያጣቀሱ መጓዝ የሚፈልጉ ወገኖች በመኖራቸው ነው፡፡ ሁለቱ ተደባልቀው በሚመጡበት ወቅት እንዳመጣጣቸው መመለስ ተገቢ ይሆናል፡፡  ለተቃውሞ አስለቃሽ ጭስ፣ ለአመጽ ጥይት፡፡ እንዲያም ሆኖ መንግስት ተመጣጣኝ እርምጃ ነው እየወሰደ ያለው። መዘንጋት የሌለበት ጉዳይ ህገ መንግስቱን በሃይል ለመናድ ከሚፈልጉ ወገኖች ለመከላከል፣ ማንኛውንም መስዋዕትነት ከመክፈል ወደ ኋላ እንደማንል ነው፡፡     
ፖለቲካ በፈገግታ፡- አንዳንድ ተቃዋሚዎች፤ ኢህአዴግ በግንቦት 2007 ምርጫ መቶ በመቶ አሸንፌያለሁ ብሎ በተናገረ ማግስት፣ በህዝብ ተቃውሞ መጥለቅለቁ ምርጫው ኢ-ዲሞክራሲያዊ እንደነበር ያሳያል ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ ለዚህ ትችት የአውራው ፓርቲ ምላሽ ምንድን ነው?
አውራው ፓርቲ፡- የእኛ አገር ተቃዋሚዎች ሁሌም ሽንፈትን በጸጋ የመቀበል ችግር አለባቸው።  በየምርጫው ለሽንፈታቸው ሰበብ አያጡለትም። የአሁኑን ትንሽ ለየት የሚያደርገው ሰበቡ የተገለጠላቸው ምርጫው ከተካሄደ ከአንድ ዓመት በኋላ መሆኑ ነው፡፡  
ፖለቲካ በፈገግታ፡- ተመድ በቅርቡ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በተከሰቱት ግጭቶች በፀጥታ ኃይሎች የተገደሉ ዜጎችን ቁጥር የሚያጣራ ገለልተኛ የሰብአዊ መብት ቡድን ለመላክ መንግስትን ጠይቆ ሳይፈቅድለት ቀርቷል፡፡ ምክንያቱ ምንድን ነው?
አውራው ፓርቲ፡- ኢትዮጵያ ሉአላዊት አገር ናት። በህዝብ የተመረጠ መንግስት የሚያስተዳድራት፣ የታፈረች የተከበረች አገር መሆኗ ሊታወቅ ይገባል። የተመድን ጥያቄ መንግስታችን ከእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ለይቶ አያየውም፡፡   የተባለውን ግድያ እኛው ራሳችን የማጣራት አቅሙም ብቃቱም አለን። የተመድ እርዳታ አያሻንም፡፡ ነገር ግን ተመድ ለሰብዓዊ መብቶች ያለውን ጥልቅ ተቆርቋሪነት መንግስታችን ሳያደንቅ አያልፍም፡፡
ፖለቲካ በፈገግታ፡- አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ በሪዮ ባሳየው ተቃውሞ ምን ተሰማችሁ? ተቃዋሚዎች በመንግስት ላይ ከፍተኛ የፖለቲካ ኪሳራ ደርሶበታል እያሉ ነው …
አውራው ፓርቲ፡- በኢህአዴግ ዘመን የተፈጠሩ አራዳ ወጣቶች “ማካበድ” የሚሉት አገላለጽ አላቸው። አትሌቱ በጣም ነው ያካበደው፡፡ የታሰረበት ቤተሰብ ይሁን ወዳጅ ዘመድ ሳይኖረው በኦሎምፒክ አደባባይ ታሰርኩ ብሎ እጁን ማጣመሩ  ትርጉሙ አልገባኝም፡፡ እሱ እኮ አትሌት እንጂ አክቲቪስት አይደለም፡፡ ወደፊት የአትሌቲክስ ቡድናችን ለውድድር ሲጓዝ፣ አክቲቪስቶች ሳይሆን አትሌቶች ይዞ መሄዱን ማረጋገጥ እንደሚገባው ያስመሰከረ ክስተት ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ የአትሌቱን የፖለቲካ አቋም እናከብርለታለን፡፡ ለዚህ ነው ወደ አገሩ ቢመለስ የተለየ ችግር እንደማይገጥመውና የጀግና አቀባበል እንደምናደርግለት በይፋ የገለጽነው፡፡
ፖለቲካ በፈገግታ፡- አትሌቱ ወደ አገሩ ቢመለስ በሚቀጥለው ኦሎምፒክ የፓራኦሎምፒክ ተወዳዳሪ ነው የሚሆነው የሚል መራራ ቀልድ በሶሻል ሚዲያው ላይ ተሰራጭቷል፡፡ ይሄ ከምን የመነጨ ነው ትላላችሁ?
አውራው ፓርቲ፡- የኢህአዴግን ዲሞክራሲያዊ ባህርይ በአግባቡ ካለመገንዘብ ወይም መገንዘብ ካለመፈለግ የሚመነጭ የፈጠራ  አሉባልታ ነው፡፡ የመንደር ወሬ !   
ፖለቲካ በፈገግታ፡- በነገራችን ላይ እናንተ ምንም የተለየ ችግር አይደርስበትም የሚል ዋስትና ብትሰጡትም አትሌቱ ግን ለደህንነቴ እሰጋለሁ በማለት የፖለቲካ ጥገኝነት ለመጠየቅ እዚያው ሪዮ ቀርቷል፡፡   
አውራው ፓርቲ፡-  መንገዱን ጨርቅ ያድርግለት!!
ፖለቲካ በፈገግታ፡- አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶች የእርቀ ጉባኤ መድረክ፣ ሌሎች ደግሞ የሽግግር መንግስት ----- በአስቸኳይ እንዲቋቋም እየጠየቁ ነው። ኢህአዴግ በዚህ ላይ ያለው አቋም ምንድን ነው?
አውራው ፓርቲ፡- ይሄ ግርግር በተነሳ ቁጥር በሃይል ወይም በአቋራጭ ሥልጣን ላይ ለመውጣት የሚፈልጉ ወገኖች ህልም ነው፡፡ በሽግግር መንግስቱ ጊዜም በአውሮፕላን በቦሌ ኤርፖርት ገብተው፣ ሥልጣን ላይ ለመውጣት ሞክረው ያልተሳካላቸው ወገኖች ነበሩ፡፡ እነዚህም ተመሳሳይ ናቸው። ህገመንግስትና የምርጫ ህግ ያላት አገር ናት፡፡ ሥልጣን የልጆች እቃ እቃ ጨዋታ አይደለም፡፡
ፖለቲካ በፈገግታ፡- ኢህአዴግ 25 ዓመት ሙሉ የህዝቡን ጥያቄ መመለስ ስላልቻለ፣ ለሚችል ሥልጣኑን ማስረከብ አለበት የሚሉ ወገኖችም አሉ ------
አውራው ፓርቲ፡- በቃችሁ የሚለን ወገን፣ በምርጫ ዘርሮ ይጣለን፡፡ ከዚያ ውጭ የሚሆነው ሁሉ ኢ-ህገመንግስታዊ ነው፡፡ ባራክ ኦባማ እንደመሰከሩት፤ ይሄ መንግስት ህዝብ የመረጠው መንግስት ነው፡፡
ፖለቲካ በፈገግታ፡- በሌላ በኩል ህዝቡ እየጠየቀ ያለው ሥርነቀል ለውጥ እንጂ እንደ ቀድሞው መጠነኛ ጥገና አይደለም የሚል ክርክር የሚያቀርቡ የፖለቲካ ሓይሎች አሉ----በዚህስ ትስማማላችሁ?
አውራው ፓርቲ፡- እኛ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ነን፣ እኛ ልማታዊ መንግስት ነን፡፡ እጃችንን ጠምዝዘው ማንነታችንን ለመለወጥ የሚሞክሩ ሃይሎችን አንቀበላቸውም፡፡ ኢህአዴግ ኒዮሊበራል ሊሆን አይችልም፡፡ ከተፈጥሮአዊ ማንነታችን ውጭ ሌሎች በሃይል የሚጭኑብንን ማንነት አንቀበልም፡፡ እንታገላቸዋለን፡፡ ህዝቡንም ጭምር!!
ፖለቲካ በፈገግታ፡- ከሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የጥምር መንግስት የማቋቋም ሃሳብስ--- ሽው ብሎባችሁ ያውቃል?
አውራው ፓርቲ፡- አገር በደቦ ወይም በማህበር አትመራም፡፡ በምርጫ ያሸነፈ ፓርቲ እየመራት ነው። ህገ መንግስቱ  የሚፈቅደው እሱን ነው፤ በደቦ አስተዳድሩ አይልም፡፡
ፖለቲካ በፈገግታ፡- የመጨረሻ ጥያቄ ነው ---- ኢህአዴግ በ25 ዓመት ሥልጣኑ የሚቆጨው ወይም የሚያሳዝነው ነገር አለ?
አውራ ፓርቲ፡- አንድ የሚገርመኝ ነገር አለ። ኢህአዴግ ዲሞክራሲያዊ መንግስት ነው - ይሄን ሁሉም ያውቃል፡፡ ልማታዊ ነው - ይሄንንም ሁሉም ያውቃል። ለ8 ተከታታይ ዓመታት ባለ ሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት አስመዝግቧል - ይሄንንም አይኤምኤፍን ጨምሮ የማያውቅ የለም፡፡
ሆኖም ማንም ተገቢውን እውቅናና ምስጋና ሰጥቶን አያውቅም፡፡ አዳሜ ለትችትና ለማሳጣት ሲሆን በሚዲያው፣በፌስቡኩ አይቀረውም፡፡ እና ይሄ ያሰቆጨናል፡፡ ኢህአዴግ በቃ ዕድለ-ቢስ ነው። ምስጋናና ውዳሴ ሳይሆን ተቃውሞና አመጽ ይወደዋል። ወደፊት ግን ከአንድ ከ40 ኣመት በኋላ  ከስልጣን ስንለቅ ህዝቡ ይቆጨዋል፡፡  
 ፖለቲካ በፈገግታ፡- ከ40 ዓመት በኋላ??! ሌላ አራት አስርት ዓመታት??! በሰው ነው በእግዜር አቆጣጠር??

Read 8449 times