Monday, 05 March 2012 14:47

ስብሃት ምናችን ነው? እኛስ ምኖቹ ነን?

Written by  ሲሳይ ብዙአየሁ
Rate this item
(0 votes)

ለፉት ሳምንታት ስለ ስብሀት መታመም በተደጋጋሚ ስሰማ ነበር፡፡ የካቲት 12 ቀን 2004 ዓ.ም የ7 ሰዓቱ የቴሌቪዥን ዜና አንባቢ “ዜና ዕረፍት” የሚለውን መርዶ ነጋሪ ዐ.ነገር ሲያሰማ የስብሀትን መርዶ ሊነግረን መሆኑን ወደ ሚቀጥለው ዐረፍተ ነገር ከመሸጋገሩ በፊት ነበር ያወቅኩት፡፡ በውስጤ የተፈጠረብኝን ስሜት ለመግለጽ አልሞክርም፡፡ እንደዚህ ዓይነት የውስጥ ስብራትን ለመግለጽ የስብሀት ብእር ያስፈልጋል፡፡ በዚያ ስሜት ላይ ሆኜ መቀመጥ አልቻልኩም፡፡ አንድ ጓደኛዬ ጋር ሄድኩ፤ ስነግረው ጠዋት እንደሰማ ነገረኝ፡፡ ጓደኛዬ ስብሀትና ስራዎቹን ያውቃል፡፡ አዝኗል ነገር ግን መረጋጋቱ አልተለየውም፡፡ ቀብሩ 10 ሰዓት ስላሴ ቤተክርስቲያን መሆኑን በዜና መስማቴን ነግሬው እንሂድ አልኩት፡፡ “አይ አልሄድም!” አለኝ “ምን ያደርጋል ሄድን አልሄድን… በቃ አለፈ” ሲለኝ እኔም ለመቅረት አሰብኩና ግን አልቻልኩም ሄድኩ፡፡

የተሳፈርኩበት ታክሲ ስላሴ ቤተክርስቲያን አካካቢ መቆሚያ እንደሌለ ነግሮኝ ታች ቤተመንግስት አውርዶኝ ሄደ፡፡ ቀሪውን መንገድ በእግሬ ዎክ ሳደርግ በሀሳቤ ስብሀት መንገድ ሲሄድ ሳልኩት፡፡ ሹራቡን አውልቆ እራሱ ላይ ጠምጥሞ፣ ወረቀቶቹን በፌስታል አንጠልጥሎ በዛ ቀጭን ሰውነቱ እጥፍ ዘርጋ ሲል ታወሰኝ፡፡ የእሪ በከንቱ መንደሮችን አሻግሬ ሳያቸው እሱኑ ያስታውሱኛል፡፡ አዲስ አበባን ሳያት አሳዘነችኝ፤ ዘማሪ ወፏን አጣች፡፡ ስላሴ ቤተክርስትያን ግቢ በሰውና በመኪና ተሞልቷል፡፡ በዛ ያሉ ጥቁር የለበሱ ሴቶች አየሁ፡፡ ስገምት ሁሉም ዘመዶቹ አይደሉም፤ አብዛኞቹ አድናቂዎቹ ሳይሆኑ አይቀሩም፡፡ አሁንም በዐይኔ ሳማትር አንዳንድ የማውቃቸው የጥበብ ሰዎች አገኘሁ፡፡ አንዳንዶቹን ጠጋ ብዬ ስለስብሀት የሚያወሩትን ለመስማት ሞከርኩኝ፡፡ አንዱ “ሌቱም አይነጋልኝ” መጽሀፍ ላይ አንድ ገጸ ባህሪ ሆኖ የምናውቀውን ሰው አየሁት፡፡ ከሁለት ሰዎች ጋር ቆሞ ያወራል፤ ጠጋ ብዬ ተቀላቀልኳቸው፡፡ ወሬያቸው ተራ ሆነብኝ፡፡ “ሌቱም አይነጋልኝ ላይኮ እንትና ያለኝ እኔን ነው” ይላል፡፡ አብሮት ያለው ሰውዬ “እኔንም አንድ ቀን እንትና ኮ አንተነህ ብሎኛል” አለው፡፡ “እራሱን አይጠብቅም ነበር” “አንዴ አለመለከፍ ነው” ምናምን… ወሬያቸው በአንዴ ስልችት አለኝና ሌላ ሄጄ የምቀላቀለው ሰው በዐይኔ እያማተርኩ ሳለ አንዱ “እንትን መጽሀፍ ላይ ያለው እንትናን ታውቀዋለህ?” ይለዋል (ያን መጽሀፍ አሮጌ መጽሀፍ ተራ አግኝቼ ገዝቼው መጽሀፉ ትንሽዬ ቢሆንም ትእግስቴን አጥቼ ሳልጨርስ የተውኩት መጽሀፍ ነው)፡፡ አሁንስ አልኩና ዝም ብዬ ሄጄ ከሌላው ህዝብ ጋር ተቀላቀልኩኝ፡፡ ለቅሶኛውን በዓይኔ ስቃኝ ከ75% በላይ (በግምት) ወጣት  ነው፤ የጠበኩትም እንደዛ ነው፡፡ ህዝቡ ውስጥም ወሬዎች ነበሩ፡ ስለስብሀት የተለያዩ መሳጭ ወሬዎች፡፡ ከቀድሞዎቹ አርቲስት ተብዬዎች ወሬ በእጅጉ የተሻሉ መሳጭ ወሬዎችን ሰምቼአለሁ፡፡ ተዋንያኖችን፣ ዘፋኞችን፣ ገጣሚያንን አይቻለሁ፡፡ ቤተክርስትያኗን የሞሉትን ዘመናዊ መኪኖች ሳይ ወንድሞቹን ብለው የመጡ ባለሥልጣናትና ባለሀብቶች ቀላል ያለመሆናቸውን ገምቼአለሁ፡፡ የሚያለቅስ ሰው ብዙ አላየሁም፡፡ የአስከሬኑ መኪና ሲመጣ፣ አስከሬኑ ከመኪና ወርዶ ወደ ቤተክርስትያን ሲገባ የአንዲት ሴት ልጁና የአንዲት ሌላ ትልቅ ሴት ለቅሶ ብቻ ነበር የሚሰማው፡፡ ለነገሩ ብዙ ዋይታና ለቅሶ አልጠበኩም፡፡ ስብሀት ከአስለቃሽነት ይልቅ አስደማሚ ሰው ነው፡፡ ስርዓት ፀሎቱን የመሩት አቡነጳውሎስ እራሳቸው ናቸው፡፡ እንዲያውም ከስርዓተ ፀሎቱ በኋላ ባደረጉት ንግግር፤ የስብሀትን ግልጽነት እውቀቱንና ለነዋይ ያለውን ግዴለሽነት ሲናገሩ በዛ እለት ካየዋቸውና ከሰማኋቸው የጥበብ ሰዎች የተሻለ ስለ ስብሀት ግንዛቤ ያላቸው እንደሆኑ ተረድቻለሁ፡፡ (መጽሀፎቹን ላያነቧቸው ቢችሉም) በዚያ ከነበረው ስነሥርዓት ሁሉ ተፈሪ አለሙ በዛ ኩልል ያለ ድምፁ የሕይወት ታሪኩን ውብ አድርጎ ማንበቡ አስደምሞኛል፡፡ ከዚያ በዚች ምድር ላይ የኖራትን እየፃፈ፣ የፃፋትን እየኖረ የሕይወትን አሰልቺነት እያለዘበልን የኖረው ስብሀት፣ በሕይወት እያለ ተረት የሆነው ስብሀት፣ በቀይ አስክሬን ልብስ በተሸፈነው ሳጥን ውስጥ ሆኖ ወደ ማረፊያው ሄደ፤ ተቀበረ፡፡ እውቀት ተቀበረ፡፡ ጥበብ ተቀበረ፡፡ ቀበርነው፡፡ ተመለስን ወደየቤታችን፡፡ ወደ ሕይወታችን፡፡ ቤቴ ገብቼ ሬድዮን ብከፍት፣ ቴሌቪዥን ብከፍት እዚች አገር ላይ ምንም እንዳልተፈጠረ የተለመደው ፕሮግራማቸውን ያስተላልፋሉ፡፡ ላምን አልቻልኩም፡፡ እውነት እነዚህ ጣቢያዎች ለግማሽ ክፍለ ዘመን በየመጽሄቱ በየጋዜጣው፣ በየመጽሀፉ ሲጽፍ ሲያዝናና ሲያሳውቀን የኖረ የእውቀት አባት፣ ጥልቅ ፈላስፋ፣ የአንባቢነት ተምሳሌት የሆነ ታላቅ ሰውን ዛሬ የቀበረችው አገር ውስጥ ያሉ ጣቢያዎች ናቸው? ስብሀት የእኛን የቀናነት እጥረት ገና ድሮ ተገንዝቦ እራሱን በመጽሀፍ ውስጥ ደብቆ ገሀነሙን ገነት በማድረግ ችሎታው፣ እኛን ቢገባንም ባይገባንም በጽሁፎቹ ውስጥ ሸንቆጥ እያደረገን ኖሮ አልፏል፡፡ “ትኩሳት” የተሰኘው መጽሀፉ ላይ ባህራም የተባለው አረብ ገጽ ባህሪ፣ አበሾች ጓደኞቹ በችግሩ ወቅት እንዴት እንደደረሱለትና ምን ያህል ጥሩ ሰዎች እንደሆኑ ሲተርክለት ያስነብበንና “ሀበሾቹ እንደዚህ ጥሩ ሰዎች መስለው የታዩት ምንኛ የዋህ ቢሆን ነው ብዬ አሰብኩ” ይለናል (ገጽ 83)

 

እድሉን ካገኘው ወደፊት ስብሀት ምን ያህል ከእኛ ክፋት ጋር እየተሸዋወደ እንደኖረ ለማየት እሞክራለሁ፡፡

ነብሱን በገነት ያኑራት!!

 

 

 

Read 15377 times Last modified on Monday, 05 March 2012 15:53