Saturday, 10 March 2012 09:28

ሕፃናትን ከወሲብ ንግድ ማን ይታደጋቸው?

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

ለመጀመሪያ ጊዜ አዲስ አበባን የረገጠችበት አመሻሽ እስካሁን አለቀቃትም፡፡ገና በ17 ዓመቷ የፒያሳ ጎዳናዎችን በምሽት ከእርቃን ባልተናነሰ አለባበስ ወዲያ ወዲህ ትልባቸዋለች፡፡ከአዲስ አበባ 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው የሰሜን ሸዋ ዞን ሰላሌ አካባቢ ተወልዳ ያደገችው ብርቱካን ቤተሰቦቿ በግብርና ሥራ የሚተዳደሩ ነበሩ፡፡አባቷ በበግብርና ሥራቸው ላይ ንግድን ደርበው እየሠሩ የስምንት ልጆቻቸውን ፍላጎት ለማሟላት ቢጥሩም ስኬታቸው እምብዛም ነበር፡፡ይባስ ብሎም ህይወታቸው በማለፉ የብርቱካን  እና  ቤተሰቦቿ ህይወት አደጋ ላይ ወደቀ፡፡ የቤት እመቤት የነበሩት እናቷ ወትሮም ያልሞላው ጓዳቸውን ማቅናት ስለተሳናቸው፣ የበኩር ልጃቸው ብርቱካን ወደ አዲስ አበባ ልትሰደድ የግድ ሆነ፡፡

አዲስ አበባ ለወራት በቤት ሠራተኝነት ያገለገለችው ብርቱካን፤ አሠሪዎቿ በተደጋጋሚ ደሞዟን ሊከፍሏት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው በወቅቱ የነበራትን ብቸኛ አማራጭ ለመጠቀም ተገደደች፡፡ ያውም በለጋ ዕድሜዋ፡፡

የሴተኛ አዳሪነት ህይወቷን ሀ..ሁ ያለችባቸውን የመጀመሪያ ቀናት ዘግናኝ ትውስታዋ ናቸው፡፡  የሴትነት ክብሯን ያሳጣት የመጀመሪያ ደንበኛዋ ለሰጠችው “አገልግሎት” የከፈላት ስድስት ብሮችን ብቻ ነበር ለቀናት አላራምድ እያለ ከፈተናት የህመም ስሜቷ እንዳገገመች “ለሥራ” ጐዳና ላይ ወጣች፡፡

ልጅነቷንና ትኩስ ገላዋን የተመኙ ሁሉ ጥቂት ቀያይ ብሮችን እያስጨበጡ የፍላጐታቸውን ፈፀሙባት፡፡“በዕድሜ ከእኔ ከሚያንሱ ልጆች ጀምሮ አያቴ እስከሚሆኑ አዛውንት ድረስ ደንበኞች ነበሩኝ፡፡ አብዛኞዎቹን ደንበኞቼን የማገኘው ጐዳና ላይ ነው፡፡ የሚፈልገውን አድርጐ የጠየኩትን ሂሣብ ከፍሎ የሚያሰናብተኝ እንዳለ ሁሉ አስገድዶ ደፍሮኝ የያዝኩትን ነጥቆ የሚያባርረኝም አለ፡፡ ያለ ፍላጐቴና ከኮንዶም ውጪ ግንኙነት እንዳደርግ ተገድጃለሁ፡፡ ለዚህ ሁሉ ሥቃይና እንግልት የበቃሁት ከቤተሰቦቼ ተነጥዬ ከተማ በመምጣቴ ነው››የምትለው ብርቱካን ዛሬ የልጅነት ወዘናዋ ጠፍቶ የተለያዩ ሱሶች ተጠቂ ሆና በአነስተኛ ክፍያ የወሲብ ንግድ ሥራውን ቀጥላበታለች፡፡

ሕፃናቱ ከየት መጡ?

በሕፃናት ሴተኛ አዳሪነት ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት በኢትዮጵያ እንደ አዲስ አበባ የሕፃናት ሴተኛ አዳሪነት የተስፋፋበት ከተማ የለም፡፡ በተለይ ደግሞ የተሻለ ሕይወት ፍለጋ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የነገዋ ተስፋችን ወደሚሏት አዲስ አበባ የሚጎርፉት አብላጫውን ቁጥር ይይዛሉ፡፡በአዲስ አበባ ጀንበር ዘቅዘቅ ሲል እንደ ፒያሳ፣ ካዛንችስ፣ ሃያ ሁለት ፣ ጨርቆስና መርካቶ አካባቢዎች ያሉ ጎዳናዎች በነዚህ ታዳጊዎች ይወረራሉ፡፡ ለአካለ መጠን ያልደረሱ፤ የምሽቱን ቅዝቃዜ መቋቋም ያቃታቸው፤ ምን ያጋጥመኝ ይሆን በሚል ጥርጣሬና ስጋት ውስጥ እንዳሉ ፊታቸው የሚያሳብቅ ታዳጊዎች ከምሽቱ አንድ ሰአት አንስቶ ወዲህ ወዲያ ይላሉ፡፡

በእነዚህ ምሽቶች እና ሌሊቶች እንደ 17 ዓመቷ ብርቱካን ለአዲስ አበባ እንግዳ የሆኑት ታዳጊዎች፤ በብርሃን በደመቁትና በአቅራቢያቸው ባሉ የምሽት ክበቦችና ጎዳናዎች በብዛት ይታያሉ፡፡

እ.ኤ.አ በ2010 ዓ.ም በዴንማርክ የሕፃናት አድን ድርጅት(Save the Children, Denmark) የተደረገው ጥናት እንደሚያሳየው፤ ከ100 ታዳጊ ሕፃናት ሴተኛ አዳሪዎች 56ቱ ከአዲስ አበባ ውጭ ተወልደው አድገው ወደ ከተማዋ ግን በደላሎችና በተለያዩ ሌሎች ምክንያቶች የገቡ ናቸው፡፡  44ቱ ደግሞ አፍላ የልጅነት ዕድሜያቸውን በአዲስ አበባ ያሳለፉ ናቸው፡፡ በትውልድ ቀዬአቸው አፍ በሚያስከፍት ትረካ፤ በልጅነት አእምሮ ውስጥ ተቀርፆ በሚቀር ውብ ምስል የቀረበችላቸው አዲስ አበባን ለማየት እግራቸውን ባነሱና ተወልደው አድገውባት መልካም ፍሬዋን ባላቀመሰቻቸው ሕፃናት የተሞሉ ናቸው - አብዛኛዎቹ የአዲስ አበባ ምሽቶች ፡፡

ለምን ወደ ስቃይ?

ዴንማርክ የሕፃናት አድን ድርጅት የተደረገው ጥናት እንደሚያረጋግጠው፤ ሕፃናቱ  ወደ አዲስ አበባ  የመጡት በአራት ዋና ዋና ምክንያቶች ነው፡፡43 በመቶ የሚሆኑት በድህነት ተማረው የተሻለ ሕይወትና ሥራ ፍለጋ አዲስ አበባ የከተሙ ናቸው፡፡ቀሪዎቹ ከወላጆቻቸው ጋር  ባለመስማማታቸው የሚፈጥሯቸው የቤተሰብ ግጭቶች፣ በልጅነት መዳርና የእናት ወይም የአባት ሞት ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ወደ ከተማ የሚያመጧቸው ደላሎች በዋነኛነት ልጆቹንም ሆነ ቤተሰቦቻቸውን የሚያገጉት፣ ልጆቹ አዲስ አበባ ቢመጡ መማር እንደሚችሉና ሰው ቤት ትንሽ ሠርተው በርካታ ገንዘብ እንደሚያገኙ ደጋግመው ስለሚነግሯቸው ነው፡፡

ነገር ግን ከሕፃናቱ መካከል የትምህርት ዕድል ያገኙት በጣም ጥቂቶቹ ሲሆኑ እነርሱም ቢሆኑ የአንደኛ ደረጃ ትምህርትን እንኳን በቅጡ አላገባደዱም፡፡እናም ሕፃናቱ ተስፋ ያደረጓት አዲስ አበባ ፊቷን ስታዞርባቸው፣ የልጅነት ህልማቸው እንደ ጉም ሲበን ብቸኛ አማራጫቸው የሴተኛ አዳሪነት ሕይወትን መቀላቀል ይሆናል፡፡እንደውም ጥናቶቹ እንደሚያሳዩት፤60 በመቶ ያህሉ ይህንን አስከፊ የሴተኛ አዳሪነት ህይወት 15 ዓመት ሳይሞላቸው ይጀምራሉ፡፡

አዲስ አበባ ተወልደውና አድገው፣ በለጋ ዕድሜያቸው የሴተኛ አዳሪነት ሕይወትን የተቀላቀሉት ሕፃናት ላይ የተደረገ ጥናት እንደሚያመለክተው፤ታዳጊዎቹ ለሴተኛ አዳሪነት የሚዳረጉበት ዋነኛ ምክንያት ድህነትን ለማሸነፍ በሚደረግ ትግል በሚያጋጥማቸው  የፈተናዎች መደራረብ ነው፡፡አዲስ አበባ ተወልደው ያደጉትም ቢሆኑ  አብዛኛዎቹ ከድሃ ቤተሰብ የተገኙ ሕፃናት መሆናቸውን ጥናቱ ያስረዳል፡፡ ከተለያዩ ክልሎች ለሚመጡትም እንደ መንስኤ ይቀመጥ እንጂ በተለይ በአዲስ አበባ ሕፃናትን በየመንደሩና በትምህርት ቤቶች አካባቢ በሚያሳድዱ ደላሎች ተታለው፣ ወደ አስከፊው ሕይወት የሚገቡ ሕፃናትም አሉ፡፡ እነዚህ ደላሎች ገንዘብ፣ አልባሳትና ጌጣጌጦችን መደለያ በማድረግ፣ ሕፃናቱን ያለ ዕድሜያቸው ወሲባዊ ግንኙነት እንዲፈፅሙ የሚጎተጉቱና አልፎ ተርፎም በማታለል፣በአልኮልና በአደንዛዥ ዕፅ በማስከር፣ በሕፃናቱ ላይ ወሲባዊ ጥቃት እንዲፈፀም ያደርጋሉ፡፡ይህ ደግሞ ሴት ሕፃናቱ በለጋ ዕድሜያቸው ወደማይቋቋሙትና ሊወጡ ወደማይችሉት ቀውስ እንዲያመሩ ያደርጋቸዋል፡፡

በተለይ አዲስ አበባ የትውልድ ቀያቸው ለሆኑት ሕፃናት ሊጠቀስ የሚችል ተጨማሪ ምክንያት ቢኖር የጓደኞች ግፊት ነው፡፡ ይህም ቢሆን ግን ከፍተኛ ድርሻ ያለው አይደለም፡፡ በሕፃናት የሴተኛ አዳሪነት ሕይወት ላይ በአዲስ አበባ የተደረጉት በርካታ ጥናቶች፣ የሴተኛ አዳሪነት ሕይወት አስከፊ ስለመሆኑ በጥቅሉ ይስማማሉ፡፡ አሁን በዚህ ህይወት ውስጥ ከሚገኙት 100 ታዳጊ ሴቶች ዘጠና ዘጠኙ “ያለነው የሚያንገሸግሽ ሕይወት ውስጥ ነው” ብለዋል፡፡

አስከፊው ህይወት

ምሽቱ በሙዚቃ፣ በደማቅ መብራቶችና በአልኮል መጠጦች በተሞሉበት የአዲስ አበባ መንደሮች ካሉ ወጣት ሴተኛ አዳሪዎች ባልተናነሰ የ17 አመቷ ብርቱካን የዕድሜ እኩዮች የዝሙት ንግዱ ተዋናዮች ናቸው፡፡ሥራውን የሚጠሉት በርካታውን ቁጥር የሚይዙት ቢሆኑም ጀንበር ማዘቅዘቅ ስትጀምር የዕለት ጉርሳቸውን ለመሸፈን ሲሉ መፍትሄ ወዳሉት የሴተኛ አዳሪነት ሕይወት በሁኔታዎች አስገዳጅነት ይዘፈቁበታል፡፡

እነዚህ ታዳጊዎች ገላቸውን ለመሸመት የሚመጣውን ወንድ የሚያገኙት በመጠጥ ቤቶች አልያም በጎዳናዎች ላይ ነው፡፡ በእነዚህ ስፍራዎች መሆን ደግሞ ሕፃናቱን ገና በለጋ ዕድሜያቸው ለደባል ሱሶች እንዲጋለጡ በር ይከፍታል ፡፡ወደ አልባሌ ሱስ ሳይወዱ በግድ እንዲዘፈቁም ያስገድዳቸዋል፡፡ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ሕፃናቱን በሱስ ከሚያስሯቸው ልማዶች ውስጥ የአልኮል መጠጥ፣ ሲጋራ ማጨስና ጫት መቃም ጉልህ ስፍራ ይይዛሉ፡፡ እነዚህ ነገሮች የሚጀመሩት በለጋ ዕድሜ ላይ በመሆኑ በታዳጊዎቹ ላይ የሚያሳድሩት የጤና ቀውስ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ይሄም ሳያንሳቸው እርጅና የተጫናቸው ወላጆቻቸውንና ቤተሰቡን  የማስተዳደር ኃላፊነት ያለባቸው ደግሞ በምሽቱ አስከፊ የሴተኛ አዳሪነት ሕይወት በለስ ካልቀናቸው ለረሃብ ይጋለጣሉ፡፡

የሴተኛ አዳሪነት ሕይወትን በለጋ ዕድሜያቸዉ የተቀላቀሉ ሕፃናት ለተለያዩ ሱሶች ተጋላጭ ከመሆናቸውም በተጨማሪ አሳዛኝ ወሲባዊ ጥቃቶችንም ያስተናግዳሉ፡፡ገና ከመነሻው የሕፃናቱ ገላ ለወሲባዊ ግንኙነት ያልጎለበተ ከመሆኑ ባሻገር ሕፃናቱ ገንዘብ ከፍሎ አብሯቸው ከሚተኛው ወንድ በአካል ስለሚያንሱ ጥንቃቄ የጎደለው የግብረስጋ ግንኙነትን ለመከላከል የሚቸገሩባቸው አጋጣሚዎች በርካታ ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ ካልተፈለገ እርግዝና በተጨማሪ ለተለያዩ የአባላዘር በሽታዎችና እንደ ኤችአይቪ/ኤድስ ላሉ የጤና ቀውሶች ተጋላጭ ያደርጋቸዋል፡፡ ጥናቶች የሚያረጋግጡትም፤ ከመቶ ታዳጊ ሴተኛ አዳሪ ሕፃናት ውስጥ 47ቱ ቢያንስ አንዴ አስገድዶ መደፈር አጋጥሟቸዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ ግማሾቹ ደግሞ በተደጋጋሚ በወንዶች የተደፈሩ ናቸው፡፡ከወሲባዊ ጥቃቶቹ ባለፈ ሕፃናቱ ተደጋጋሚ ድብደባና ዘረፋ የዕለት ሕይወታቸው አካል ነው፡፡ እናም ገና 18 ዓመት ካልሞላቸው ሴተኛ አዳሪ ሕፃናቱ መካከል 25 በመቶ የሚሆኑት ህመም እንደሚሰማቸው ይናገራሉ፡፡ የ17 ዓመቷ ብርቱካን እንደምትናገረው፤አንድ ዓመት በቆየችበት የሴተኛ አዳሪነት ሕይወት ያለ ኮንደም የግብረ ስጋ ግንኙነት እንድታደርግ ተገዳለች፣ በተደጋጋሚ ተደፍራለች፣ በተደጋጋሚ ገንዘብና ንብረቷን ተዘርፋለች፡፡

በለጋ ዕድሜያቸው ሳይወዱ የሴተኛ አዳሪነትን ሕይወትን ለመግፋት የተገደዱት ሕፃናት፤ ገላቸውን ሸጠው እንኳ ኑሮአቸው አልተቃናም፡፡ አብላጫዎቹ ኑሮን ለማሸነፍ የጋራ ቤት ተከራይተው የሚኖሩ ናቸው፡፡

ምን ይሻላል?

ግንቦት 1997 ዓ.ም የተሻሻለው የኢትዮጵያ ወንጀለኛ መቅጫ ሕግ አንቀጽ 634 ላይ እንደተጠቀሰው፤18 ዓመት ያልሞላቸው ታዳጊዎችን ለወሲባዊም ሆነ ለሌላ የግዳጅ አካላዊ በደል ያጋለጠ ከፍተኛ ቅጣት ይጠብቀዋል፡፡የሠራተኛ ሕጉም ቢሆን ታዳጊዎች መሥራት ስለሚገባቸው ሥራዎች በግልፅ ያስቀምጣል፡፡ በተለይ ሕፃናትን በግዳጅም ሆነ በማታለል ለወሲባዊ ጥቃት ያጋለጠ በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ መሰረት እንደሚዳኝ ይዘረዝራል፡፡ በተጨማሪም ኢትዮጵያ የፈረመቻቸው የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መብት ኮንቬንሽንና የዓለም አቀፉ የሥራ ድርጅት አነስተኛ የሥራ ዕድሜ ድንጋጌዎች ለሕፃናቱ ከለላ መሆን አልተቻላቸውም፡፡

ለዚህ ደግሞ ዋነኛ ምክንያት ተደርጎ የሚቀመጠው ከማታለልና ከኃይል ማስገደድ ባልተናነሰ የኑሮ ሁኔታና ድህነት፣18 ዓመት ያልሞላቸውን ሕፃናት ወደ ሴተኛ አዳሪነት ሕይወት እንዲገቡ እያስገደዳቸው መሆኑ ነው፡፡

ከሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የወጣው ጥናት፤‹‹ወላጆች፣ የአካባቢው ማኅበረሰብና እንደ እድር ያሉ ማኅበራዊ የትስስር ተቋማትና ኃይማኖታዊ ድርጅቶች፣ሕፃናት ከማኅበረሰቡ ተገቢውን እገዛና ድጋፍ ማግኘታቸውን የማረጋገጥ ኃላፊነት አለባቸው ይላል፡፡ ሕፃናት ከቤታቸው ቀጥሎ ሰፊውን ጊዜ የሚያሳልፉበት ስፍራ በመሆኑ በዚህ ጉዳይ ላይ የትምህርት ቤቶችና የመምህራን ድርሻም ቀላል አይሆንም፡፡

አሁን ባለው ተጨባጭ እውነታ ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት ያልዘለለ ሕፃናት በድህነት አስገዳጅነት በሴተኛ አዳሪነት ሕይወት ውስጥ ተሰማርተዋል፡፡ በአብላጫው እነርሱም ሆኑ ወላጆቻቸው የተማሩ አይደሉም፡፡

የሴተኛ አዳሪነት ሕይወቱ አስከፊነት ከለጋ ዕድሜያቸው ጋር ተዳምሮ የሕፃናቱን ሕይወት ሲኦል አድርጐባቸዋል፡፡ የሴተኛ አዳሪነት ሕይወት እጅግ አስከፊ ነው የምትለው የ17 ዓመቷ ብርቱካን፤ ‹‹ይህን ሕይወት ለታናናሾቼ አልመኘውም፤ እኔም ሆንኩ ጓደኞቼ ከዚህ ሕይወት የሚያወጣን እንፈልጋለን›› ብላለች ፡፡

ታዳጊዋ የንግዱን ዓለም የመቀላቀል ምኞት ቢኖራትም አሁን ያለችበት ህይወት አንድም እርምጃ የሚያራምድ አልሆነላትም፡፡

እናም ብርቱካን ‹‹ጥሩ ሰዎች ባገኘሁና ምናለ ወደ ቤት ሠራተኝነቴ በተመለስኩ›› በማለት ትመኛለች፡፡

 

 

Read 18810 times Last modified on Saturday, 10 March 2012 12:55