Saturday, 10 March 2012 11:13

“ዶ/ር ከበደ ሚካኤልን መክሬ ችግሩ እኔም ጋ ደረሰ” ደራሲና ተርጓሚ ማሞ ውድነህ

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(0 votes)

ሰው ወደ ላይ ወጣ

መልሶም ወረደ

ቁልቁለት ሳይገታው

የሰው ልጅ ወረደ - ወረደ ነጐደ

አቀበት የወጣው

ጉልበቱ ደከመ - ሕይወቱ በረደ፡፡

ስለ ሞት የሚገልፁት እነዚህ ስንኞች በ1960 ዓ.ም ባሳተሙት መፅሐፍ ውስጥ የሚገኝ ነው፡፡ ውልደትና ሞት እንደ አንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ የማይለያዩ ቢሆንም ሰው ሁሉ በመወለዱ እኩል ሆኖ፣ ሞቶ ሲቀበር ግን አንዱ ከሌላው ይለያል፡፡

በድህነት የመጨረሻው ወለል ላይ የሚገኝ የጐዳና ተዳዳሪ ባንቀላፋበት በረንዳ ላይ እስትንፋሱ ቢቋረጥ፤ በማዘጋጀ ቤት አስፈፃሚነት በመንግሥት የቀብር ቦታ አስከሬኑ እንዲያርፍ ይደረጋል፡፡

አኗኗራቸው በድህነት የሚፈረጁት ቢሆኑም፣ መኖሪያ ቤት ጐረቤትና ቤተ-ዘመድ ኖሯቸው እድር ባይኖራቸው፣ የእለት እርዳታ ተለምኖ ሳጥኑም፣ ንፍሮውም እንዳቅሙ ተዘጋጅቶ “ነግ በኔ” ባሉ ቀባሪዎች ወደ ግብአተ መሬት ይሸኛሉ፡፡

ወዳጅ፣ ሀብትና ንብረት፣ እድሩም… ያለው ደግሞ መቀበሪያ ቦታ ተመርጦለት፤ ሀዘኑ በድግስ ተንበሽብሾ፣ “ኖረው ካለፉ አይቀር እንዲህ ነው” በሚያሰኝ ሁኔታ ሞተው ተቀበሩ ሳይሆን፣ በከርሰ ምድር በኩል ወደ መንግሥተ ሰማያት የተላኩ ይመስልላቸዋል፡፡

ከእነዚህ የተለየ የቀብር አይነትም አለ፡፡ ሟቹ ሀብትና ንብረት ሊኖረውም ላይኖረውም ይችላል፡፡ እድር ኖረው አልኖረው የሚያስጨንቅ ጉዳይ አይሆንም፡፡ በቀብሩ ላይ ቤተ ዘመዶቹ ኖሩ አልኖሩ ያን ያህል ለውጥ አያመጣም - ቀብሩን ለማሳመርና ለማድመቅ፡፡ የቀባሪዎች ቁጥር አነሰም በዛ ሟቹን ለመቅበር የሚመጡት ግን በአብዛኛው ሟቹ የማያውቃቸው፤ ቀባሪዎቹ ግን የሚያውቁት ሰዎች ናቸው፡፡ የእንዲህ አይነቱን ሟች ቀብር ለማሳመር ሕዝብ ብቻ ሳይሆን መንግሥትና የተለያዩ ተቋማትም የየራሳቸውን አስተዋፅኦ ያበረከታሉ፡፡

የካቲት 12 ቀን 2004 ዓ.ም በደራሲ ስብሃት ገብረእግዚአብሔር ቀብር ላይ የተገኘ አንድ ወጣት የቀብሩ ሥነ ስርዓት ላይ እንዴት እንደተገኘ ተጠይቆ ሲመልስ:-

“ጋሽ ስብሃት በየጋዜጣው ላይ ደጋግሞ እንደፃፈው፤ ደራሲ ሲፅፍ አንባቢያን አጠገቡ አይኖሩም፡፡ ተደራሲያን የደራሲውን ሥራ ሲያነሱ ደራሲው አጠገባቸው አይኖርም እንደሚለው፣ እኔም የጋሽ ስብሃትን ሥራዎች ላንብብ እንጂ እሱን ግን በቅርበት አላውቀውም፡፡

“በአንድ ወቅት በአንድ ጋዜጣ ላይ ለወጣቶች ምን ትመክራለህ? የሚል ጥያቄ የቀረበለት ጋሽ ስብሃት ጊዜ ካላቸው ያንብቡ፣ ሃሳብ ከመጣላቸው ይፃፉ፣ በቅድሚያ ግን የዕለት እንጀራ የሚያገኙበትን ሥራ ያስቀድሙ የሚል ምላሽ ሰጠ፡፡ እኔ ያንን ካነበብኩ ጀምሮ አባባሉን የህይወቴ መመሪያ አድርጌ ስለተከተልኩት ተጠቅሜበታለሁ፡፡ በጋሽ ስብሐት ቀብር ላይ የተገኘሁት በእነዚህ ምክንያቶች ነው” ብሏል፡፡

አገርና ትውልድ የሚጠቀምበት ቋሚ ሥራ መስራት መቻል እንዲህ አይነት ክብር ያስገኛል፡፡ ባለፈው የካቲት ወር በአንድ ሳምንት ልዩነት ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ደራሲ ስብሃት ገ/እግዚአብሔርና ደራሲና ተርጓሚ ማሞ ውድነህ፤ በሕዝብና በአገር ደረጃ አክብሮት የማግኘታቸው ምክንያቱ ይኸው ነው፡፡ ይህንን ማየት አስደሳች ነገር ቢሆንም ዓመታት ባለፉ ቁጥር ብዙ ባለታሪኮች በሚዘነጉበት አገር፣ የእነዚህስ ሥራ ከዓመታት በኋላ የሚታወስበት እድል ይኖራል ወይ? የሚለው ጥያቄ ግን ሊያነጋግር ይችላል፡፡

ብዕርና ቀለም

ወረቀትና ጣት

ከጥንት ጀምሮ

የቀረፁት ሐውልት

አይነቃነቅም

ነፋስ አይጥለውም

የመሬት መንቀጥቀጥ

የሰው ልጆች ቅጣት

የውቅያኖስ ሙላት

ምን ቢሆን አይጥለው

“ብዕር እንደዋዛ!” በሚለውና ለመፅሐፉ ርእስ በሆነ ግጥም ደራሲ ማሞ ውድነህ ቋሚ ነገር መሥራት የቻለ ሰው ሞቶ አይሞትም፤ ተረስቶ አይረሳም ያሉ ይመስላል፡፡ ትውልዱና ዜጋው የደከሙበትን ሥራ በቅርስነት የማኖር የዳበረ ልምድ በሌለበት አገርስ ታሪክ ሰሪዎች የመረሳት፣ የመዘንጋት እጣ አይደርስባቸውም ወይ?

ሐምሌ 24 ቀን 1999 ዓ.ም የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ “የኢትዮጵያ ታሪክ ከንግሥተ ሳባ እስከ አድዋ ጦርነት” መፅሐፍ በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት አዳራሽ በተመረቀ እለት፣ በደራሲያንና ሥራዎቻቸው ዙሪያ በተነሳ ውይይት ላይ “ከመታተማቸው በፊት ወጣቶች እየተቀባበሉት ያነበቡት የደራሲ ስብሃት ገብረእግዚአብሔር “ሌቱም አይነጋልኝ”ና ሌሎች ረቂቅ የእጅ ፅሁፎች የት ነው የሚገኙት? ዋጋና ክብር ያላቸው እንዲህ አይነት ሥራዎች ለኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ቢሰጡ በቅርስነት ለትውልድ ይተላለፋሉ…” የሚል ጥቆማ ከዶ/ር ፈቃደ አዘዘ ቀርቦ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡

ዶ/ር ጌታቸው ተድላ “የሕይወት ጉዞዬና ትዝታዎቼ” በሚል ርእስ ያሳተሙትን መፅሐፍ ታህሳስ 21 ቀን 2004 ዓ.ም በጣሊያን ባህል ተቋም ባስመረቁ እለት፣ በክብር እንግድነት ከተጋበዙት አንዱ ደራሲ ማሞ ውድነህ ነበሩ፡፡ የምረቃው ሥነ ስርዓት ከተጠናቀቀ በኋላ በሻይ ቡና ወቅት፣ አንድ ሰው ለደራሲ ማሞ ውድነህ ያቀረበው ጥያቄና መልሳቸው ከላይ ያነሳሁትን ሃሳብ በተሻለ ይገልፀዋል፡፡

“የመፃሕፍቶችዎ ቁጥር ስንት ደረሰ?” የሚል ጥያቄ ነበር ለደራሲ ማሞ ውድነህ የቀረበላቸው፡፡ በምላሻቸውም 53ቱን ለአንባቢያን እንዳደረሱ፣ 54ኛውን ማተሚያ ቤት እንዳስገቡና የቀረኝ የሚሉት አንድ ሃሳብ ላይ 55ተኛ መፅሐፋቸውን እያዘጋጁ መሆኑን “ጊዜን ለመቅደም እየፈጠንኩ ነው” የሚል ቀልድ አክለው ነበር ምላሽ የሰጡት፡

ይህ ምላሻቸው ያስገረመው ሌላ ሰው “ሁሉም መፃህፍትዎ በእጅዎ ይገኛሉ ወይ?” የሚል ጥያቄ ሲያስከትል፣ የደራሲ ማሞ ውድነህ መልስ “እነ ዶ/ር ከበደ ሚካኤልን ሥራዎቻችሁን አሰባስባችሁ ለመያዝ ሞክሩ እያልኩ እመክር ነበር፡፡ ችግሩ ዞሮ እኔም ጋ ደርሷል፡፡ ከድርሰቶቼ ጥቂቱ በእጄ የሉም” የሚል ነበር፡፡ ደራሲው ይህንን ምስክርነት በሰጡ በሁለተኛው ወር ለጊዜ አሸናፊነት እጅ ሰጥተዋል፡፡ ይህንን ደግሞ ቀድመውም ያውቁታል፡፡ ከላይ በተጠቀሰው የግጥም መፅሐፋቸው በገፅ 58 የጊዜን ቀድሞ ሟችነት አመልክተዋል:-

ሄደች ኮበለለች

ያች ቀን ያች ሰዓት

ሮጠች ውዲቱ ያች የምንወዳት

አመለጠች ቀረች እኛን ትታ ሄደች

ዛሬ ሞቶ ነገን እንደሚተካው ሁሉ ልጅነት ወጣትነትን፣ ጉልምስና ሽምግልናን እየተካው ሰው ሁሉ በሞት ፍፃሜው ላይ ይደርሳል፡፡ “ሳሉ ልጆቻችን አንሞትም እኛ” እንዳለው ድምፃዊ የወለደ አልሞተም ካልተባለ በስተቀር፣ ሟችን ሕያው ለማድረግ ታሪክ ሰሪነት ተመራጭ ነው፡፡

ይህ እውነታ እንደሚያከራክር ብዙ ማሳያዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ “የእሳት ልጅ አመድ” እየሆነ የቤተሰቦቻቸውን ወይም የወላጆቻቸውን ታሪክ በማጥፋት የሚታወቁ ልጆች፣ በሁሉም አገርና ዘመን ይኖራሉ፡፡ አሉም፡፡ ነበሩም፡፡ በፍልስፍና እውቀቱ በዓለም ሁሉ የሚታወቀው ሶቅራጥስ ባለትዳርና የልጆች አባት ነበር፡፡ በዚህ ዘመን የእርሱ ዘር ነኝ የሚል ማንም የለም፡፡ እውቀቱ፣ ሥራውና ተግባሩ ግን ዘመናት ተሻግሮ መዘከሪያው ሆኗል፡፡

በቅርቡ በሞት የተለዩን የአገራችን ሁለት ታላላቅ ደራሲያን ለዘመናት መዘከሪያ ሊሆናቸው የሚችል ሥራ ሰርተው አልፈዋል፡፡

ሆኖም ግን በተመሳሳይ መልኩ በየዘርፉ ታሪክ መሥራት ችለው ከዘመናት መለዋወጥ ጋር ከተዘነጉ ኢትዮጵያዊያን ጋር እየተረሱ እንዳይመጡ ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? ደራሲ ማሞ ውድነህ ፈልጌ አጣሁት ያሉት የድርሰት ሥራቸው ማን ጋ ይገኝ ይሆን? የታላላቆቻችንን ክቡር ሥራ ለትውልዱ ለማቆየት እንትጋ!!

 

 

Read 19868 times Last modified on Saturday, 10 March 2012 12:58