Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 10 March 2012 12:00

የቀድሞው የየመን ፕሬዚዳንት የስደት አገር የት ይሆን?

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ብልጡ አምባገነን ከስልጣን የለቀቁት በድርድር ነው

የአረቡ አብዮት ማእበል ክፉኛ ካናወጣቸው አገሮች አንዷ የሆነችው የመን፣ የቀድሞ ፕሬዚደንት አሊ አብደላ ሳላህ የማታ የማታ ስልጣን በመልቀቅ፣ ከአንድ አመት ወዲህ የህዝብ አመፅ ከስልጣናቸው ያወረዳቸው አራተኛው የዓለማችን አምባገነነን መሪ ለመሆን በቅተዋል፡፡ ነገር ግን የአብደላ ሳላህ መጨረሻ በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ከነበሩ መሪዎች እጣ ፈንታ የተለየ ይመስላል፡፡ ለምን ቢሉ? ሳይወዱ በግድ በውጭ አገራት ግፊትና ተጽእኖ ሥልጣን ቢለቁም ሁሉም ነገር የተደረገው በሳቸው ይሁንታና በድርድር እንጂ በሃይል አልነበረም፡፡

እንደ ሊቢያው ሙዓመር ጋዳፊ ሃብታቸው ባለበት አልታገደም (Freeze) አልተደረገም ሳላህ ስልጣን ከለቀቁ በምትኩ ለፈፀሙት ኢ-ሰብአዊ ተግባር ክስ እንደማይመሰረትባቸው ሲነገራቸው ከመቅጽበት ስምምነት ላይ ባይደርሱም፣ ግራ ቀኙን አስተውለው “እንዳላችሁት” በማለታቸው ከግብፁ ሙባረክም ሆነ ከሊቢያው ጋዳፊ የተለየ እጣ ፈንታ እንዲኖራቸው አድርጓቸዋል፡፡ ከፍርድ ቤትም ከግድያም ለጊዜውም ቢሆን ተርፈዋል፡፡

በእርግጥ አብደላ ሳላህ እየመረራቸውም ቢሆን የተተኪያቸው በአለ ሲመት ላይ ለመካፈል ተገድደዋል ለነገሩ በምትካቸው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት፣ በእሳቸው የስልጣን ዘመን በምክትል ፕሬዚዳንትነት ያገለገሉት የመናዊ አቤድ ራቦ መንሱር ሃዲ ናቸው፡፡

ሳላህ የመጨረሻዋን የስልጣን ጊዜያቸውን ልክ እንደ ልብ አንጠልጣይ ፊልም የህዝባቸውንና የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ስሜት ሰቅዘው ይዘው ቆይተዋል፡፡ በአመፁ ወቅት በቤተመንግስታቸው ላይ በተሰነዘረ ጥቃት የቆሰሉት የቀድሞው የየመን ፕሬዚዳንት፣ ሳኡዲ አረቢያ ለህክምና በሄዱ ጊዜ ብዙዎች በዛው ይቀራሉ ሲሉ ደምድመው የነበረ ቢሆንም “የወንበሬን ነገር እስከ ደም ጠብታ” ያሉት ሳላህ ግን ወደ አገራቸው በመመለስ  ለወራትም ቢሆን እየተንገዳገዱ የስልጣን ወንበራቸውን አስጠብቀዋል፡፡

አብደላ ሳላህ ከስልጣን ከወረዱ በኋላም ሌላ ሁከት እንዳይነሳ በሚል ስጋት ከአገር ለቀው እንዲወጡ ከፍተኛ ጫና ሲደረግባቸው ቢቆይም ከየመን የወጡት ግን በቅርቡ ነው፡፡ ከየመን ከመውጣታቸው በፊት ኦማንና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶችን ጨምሮ በበርካታ አገሮች የጥገኝነት ጥያቄ ሲያቀርቡ እንደቆዩ ያልተረጋገጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡  ባለፈው ሳምንት የወጡ መረጃዎች፤ የመንን ከሰላሳ አመታት በላይ በፕሬዚደንትነት የመሯት  አሊ አብደላ ሳላህ፤ ከጥቂት የቤተሰባቸው አባላት ጋር በጥገኝነት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ ያመለከቱ ሲሆን፤ ሳላህ በመዲናዋ ዳርቻ በአንድ ቪላ ውስጥ የስደት ኑሮአቸውን እንደሚጀምሩም የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡

የቀድሞው የየመን ፕሬዚዳንት አብደላ ሳላህ ንብረቶችም በመርከብ ወደ ኢትዮጵያ መላካቸውን የዘገቡ ሚዲያዎች አልጠፉም፡፡ የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፤ አብደላ ሳላህ ጥገኝነት መጠየቃቸውን አስመልክቶ ሲመልሱ፤ “ፕሬዚዳንቱ ጥገኝነት አልጠየቁም ወደፊት ጥያቄውን  ካቀረቡ ይፋ ይደረጋል፡፡ ፕሬዚዳንት አብደላ ሳላህ የመንን ለረጅም አመት የመሩ የኢትዮጵያ ወዳጅ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያን መጎብኘት መብታቸው ነው፤ በዚህም መሰረት ኢትዮጵያ መጥተው ተመልሰው ሄደዋል” ብለዋል፡፡

የአረቡ አብዮት በተጋጋለበት ወቅት “አሰና” ከተባለ የኤርትራ መንግስት ተቃዋሚዎች የሬዲዮ ጣቢያ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፤ በሊቢያ፣ በግብፅ እና በቱኒዚያ የተቀሰቀሱ  ህዝባዊ አመፆችን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ “የግብፅ የቱኒዚያ እና በተወሰነ ደረጃ የሊቢያው አመጽ የሚያስተላልፈው መልእክት ህዝብ ተጨቁኖ ለዘለአለም እንደማይኖር ነው፡፡ ስለዚህ በተመሳሳይ ሁኔታ ያለ ህዝብ ተስፋ እንዲኖረው ያደርጋል፡፡ ስልጣን ከለቀቁት እና በመልቀቅ ላይ ካሉት መንግስታት አንዳንዶቹ አካባቢውን በማወክ ድርሻ የነበራቸው ናቸው፡፡ ከነሱ ስልጣን መወገድ ጋር ተያይዞ አካባቢውን የማወክ ስራቸው ይቆማል የሚል ተስፋ አለ፡፡ በአሉታዊ የሚገለፅ ጉዳይ ባይኖርም የምንፈራው ነገር አለ፡፡ በሊቢያ ሁኔታው ወደ ረጅም ጦርነት ከተሸጋገረና ከሃይማኖት ጋር የመያያዝ ሁኔታ ካለ ችግር ሊፈጥር ይችላል፡፡” ካሉ በኋላ  የየመን ጉዳይ አሳሳቢ እንደሆነ ሲናገሩ፤ በተለይ በየመን ላይ የመበታተን ሁኔታ ካመጣ፤ ሊያመጣ ደግሞ ይችላል፤ አካባቢያችንን ሊያውክ ይችላል፡፡ በተለይ የመን፣ በተወሰነ ደረጃ ደግሞ ሊቢያ እስከ አሁን የተፈጠረ ነገር ባይኖርም አደጋ ሊኖር ይችላል የሚል ስጋት አለ” ብለው ነበር - ጠ/ሚኒስትሩ፡፡

ኢትዮጵያ ለአብደላ ሳላህ ጥገኝነት መስጠቷንም ሆነ ለመስጠት መስማማቷን በተመለከተ ከመንግስት በኩል ይፋ የተደረገ ነገር ባይኖርም ዘገባዎቹን መሰረት በማድረግ አስተያየት የሰጡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህሩ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፤ “መንግስት ለአብደላ ሳላህ ጥገኝነት የሚሰጥ ከሆነ ህዝባቸው ያባረራቸውን አምባገነን የሚያስጠጋው ነግ በኔ ከሚል  መነሻ ካልሆነ በስተቀር ለኢትዮጵያም ሆነ ለየመን ህዝብ የሚፈይደው ነገር የለም፡፡ አብደላ ሳላህ የሰብአዊ መብት አያያዛቸው የተበላሸ፣ ህዝባቸውን ለእልቂት የዳረጉ ግለሰብ ናቸው፡፡ ለሳቸው ጥገኝነት መስጠት ለየመን ህዝበ የሚሰጥ ፍቅር ሳይሆን ለየመን አምባገነን የሚሰጥ ነው፡፡ ይህ እርምጃ በሌላ መልኩ ሲታይ ችግርን መጥራት ነው፡፡ አብደላ ሳላህ በሙስሊም ወንድማማቾች አካባቢ የሚጠሉና ኢላማ ውስጥ ያሉ ናቸው፡፡ ይህ እርምጃ በገዛ እጅ ችግርን መጥራት ይሆናል፡፡ የሳቸው ወደኛ መምጣት ለሰላምና መረጋጋታችን ችግር ፈጣሪ ሊሆን ይችላል፡፡ የእሳቸው ወደ ኢትዮጵያ የመምጣት ጉዳይ ያለቀለት ከሆነ ግን የአሜሪካ እጅ አለበት ማለት ነው፡፡ ምእራባውያኑ ለነሱ የሚመች መሪን የሰብአዊ መብት አያያዙ የተበላሸና በአገሩ የፈፀመው ወንጀል የከፋ ቢሆንም እንኳን ማረፊያ ይፈልጉለታል እንጂ ተላልፎ እንዲሰጥ አይፈልጉም፡፡”

የኢዴፓ ሊቀመንበር አቶ ሙሼ ሰሙ በጉዳዩ ላይ በሰጡት የግል አስተያየት ደግሞ፤ “መንግስት እንደዚህ አይነት ውሳኔ ሲወስንም ሆነ ወስኗል ተብሎ ሲነገር ለዜጎች ግልፅ መግለጫ መስጠት ሲገባው ምንም አላለም፡፡ ኢትዮጵያ በደርግ ጊዜም የየመን ፕሬዚደንት ለነበሩ ግለሰብ ጥገኝነት ሰጥታ ነበር፡፡ መጠጊያ ያጣን ማስጠጋት የኢትዮጵያውያን ባህል ነው፡፡ ነገር ግን ለአብደላ ሳላህ ጥገኝነት የሚሰጠው ከህዝብ ፍርድ እና ዳኝነት እንዲያመልጡ ለመርዳት ከሆነ በየመን እና በኢትዮጵያ ህዝብ መካከል ቁርሾ ይፈጥራል፤ የየመን ህዝበ ለቀሰቀሰው ህዝባዊ አመፅ ስኬት በጎ አስተዋጽኦ ያደርጋል ተብሎ የሚታሰብ ከሆነ ግን ውሳኔው ጥሩ ነው፡፡ ሌላው እና ዋነኛው ግን ከተለያዩ መረጃዎች የሚሰማው ሲሆን አብደላ ሳላህ አሜሪካ ከሄዱ በኋላ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በተደረገ ስምምነት፣ ግለሰቡ በኢትዮጵያ ጥገኝነት እንዲያገኙ ተስማምተዋል የሚል ነው፡፡

ይህ ከሆነ የአገሪቱን ጥቅም በውጭ ሀይሎች ተፅእኖ ስር የሚጥል ነው” ብለዋል፡፡አብደላ ሳላህ ኢትዮጵያ ውስጥ ጥገኝነት መጠየቅ ብቻ ሳይሆን ጥገኝነቱ እንደተሰጣቸውም የዘገቡ አንዳንድ ሚዲያዎች ቢኖሩም፣ የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ግን እስከአሁን ሳላህ ጥገኝነት አልጠየቁም፤ ከጠየቁ ግን ጉዳዩን ይፋ አደርጋለሁ ብሏል፡፡ እንግዲህ እስካሁን ባሉት መረጃዎች፣ በህዝባዊ አመጽ ከስልጣን መውረድ ብቻ ሳይሆን ከሶስት አስርት ዓመታት በላይ የገዟትን የመንን ለቀው እንዲወጡ ጫና የተደረገባቸው አብደላ ሳላህ፤ የስደት መጠጊያ እንኳን አጥተው ከአገር አገር እየተንከራተቱ ነው ማለት ነው፡፡

በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ በደርግ ጊዜ ከደቡብ የመን ፕሬዚደንት አሊ ናስር ሙሃመድ አል ሃሳኒ የጥገኝነት ጥያቄ ቀርቦላት ጥገኝነቱን ሰጥታለች፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ሰሜን እና ደቡብ የመን ተዋህደው አንድ ከመሆናቸው በፊት አብደላ ሳላህ የሰሜኑ የመን አዲስ መሪ በነበሩበት ወቅት ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር ጦርነት ውስጥ ነበረች፡፡ በወቅቱ በነበረው የሪእዮተ አለም ክፍፍል እና ጐራ ደቡብ የመን ሶሻሊስት አገር ስለነበረች የኢትዮጵያ ጦር ከሶማሊያ ጋር ያደርግ በነበረው ጦርነት ከሌሎች ሶሻሊስት አገሮች ጋር በመሆን አሊ ናስር ሙሃመድ አል ሃሳኒ ለኢትዮጵያ ጦር በመላክ ድጋፍ አድርገዋል፡፡ የአምባገነንነት መዘዝ ይሄው አይደል - በጡረታ ሰዓት እንኳን የሰላምና የእፎይታ እንቅልፍ ይነሳል፡፡

በህዝብ አመጽ ከስልጣን ለመውረድ በማኮብኮብ ላይ ያሉት የሶሪያው ፕሬዚዳንት የቢጤዎቻቸውን ዕጣ ፈንታ የሚጋሩ ከሆነ ከአብደላ ሳላህ በቀጠል አምስተኛው ከስልጣን የሚገረሰሱ አምባገነን መሪ ይሆናሉ፡፡ የሚሆነውን በእርግጥ የሚያሳየን ግን ጊዜ ነው፡፡

 

 

Read 3707 times Last modified on Saturday, 10 March 2012 12:04