Sunday, 18 December 2016 00:00

ህዝብ የማይወድ-------ወደ ሥልጣን አይጠጋ!!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(9 votes)

• ከፓርቲያቸው አገራቸውን የሚያስቀድሙ መሪዎች ያስፈልጉናል
        • የኢንተርኔት መዘጋት በቀን 500 ሺ ዶላር እያሳጣን ነው ተባለ
        • የብልሹ አስተዳደር፣የፍትህና ዲሞክራሲ መጓደል ስንት ያከስራል?!
        • የሹመት አንዱ መስፈርት - የሚንቀለቀል የአገር ፍቅር ስሜት!
                
      ህዝባዊ ተቃውሞና አመጹን ተከትሎ የተከሰተውን ሁከትና ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ለማብረድ በሚል የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ (“የመንግስት እማማት”? ወይም “ተዓቅቦ ፖለቲካ”?) ለማንሳት የግድ 6 ወር መሙላት የለበትም ብለዋል - አዲሱ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ሚኒስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ። እውነታቸውን እኮ ነው፤ የታለመለትን ግብ ከመታ በኋላ ምን ይፈይዳል፡፡ እዚህ  አገር ሁሉን ነገር ቶሎ ስለምንለምድ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁንም ለምደነው ከመመቻቸታችን በፊት በቶሎ ይነሳል፡፡ የኢንተርኔት መዘጋትን እንደለመድነው፣ የታክሲና የዳቦ ቤት ወረፋን  እንደለመድነው፣ የመብራት ባሰኘው ሰዓት መጥፋትን እንደለመድነው፣ የሙስናንና መልካም አስተዳደርን ችግር እንደለመድነው ---ማለት ነው!!! (ሙሉ አገር ወደ ኋላ መጎተት ደግሞ ሃጢአት ነው!) ለዚህ ነው የኮሙኒኬሽን ሚኒስትሩን ንግግር ወይም ምላሽ የወደድኩት፡፡
 በነገራችን ላይ የግድ ሆኖ ነው እንጂ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማንም የሚመኙት አይደለም። (የኩዴታ ማግስት ድባብ አለው!) በእርግጥ አዋጁ በተፈጥሮው መብቶችን የሚነጥቅ እንጂ የሚያጎናጽፍ አይደለም። (መብቶችን ነጥቆ፣ ሰላምና መረጋጋትን ያመጣል!) ግን አንዳንዴ ነገሮችን በንጽጽር ማየት ግድ ይለናል። ተቃውሞና አመጹን ተከትሎ  በተለይ በአማራና ኦሮሚያ ----  ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ ስደት፣ መፈናቀል፣ እስር---በእጅጉ ተበራክቶ ነበር፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከእስር በስተቀር ሌላውን አስቀርቶልናል። አዋጁ ሊታወጅ ገደማ በውጭ ኢንቨስተሮች ፋብሪካዎች፣ ኢንዱስትሪዎች፣ እርሻዎችና ሌሎች ንብረቶች ላይ የደረሰው ውድመትና ጥፋት እጅግ ብዙ ነው፡፡ አገር ውስጥ ባሉ የውጭ ኢንቨስተሮች ላይ ከሚያሳድረው የደህንነት ስጋት በተጨማሪ አዳዲስ ኢንቨስተሮችም ወደ ጦቢያ እንዳያስቡ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል፡፡ የዓለም ባንክ በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት፣ ለዓመት የዘለቀው ፖለቲካዊ ቀውስ በኢኮኖሚው ላይ ያስከተለው ጉዳት ወይም ኪሳራ አሁን ሳይሆን በቀጣዮቹ ዓመታት የሚታወቅ ነው፡፡  
የፖለቲካ ቀውሱ በሌላው ዘርፍ ላይ ያስከተለው ኪሳራ ባይታወቅም በቱሪዝም ዘርፍ ግን ቁልጭ ብሎ ነው የወጣው፡፡ የቱሪዝም ሚኒስቴር ባወጣው መረጃ መሰረት፤ በ2016 በጀት ዓመት በዘርፉ የ400 ሚ.ዶላር ኪሳራ የደረሰ ሲሆን ባለፈው ሩብ ዓመት ከዘርፉ ይገኛል ተብሎ ከታቀደው ገቢ ከ7 ሚ.ዶላር በላይ ጉድለት  ታይቷል፡፡  የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አንዳንድ መብቶችን በመገደብ በራስ ላይ ፖለቲካዊ እቀባ ለማድረግ ከማስገደዱም ባሻገር ለኪሳራ የዳረጋቸው የቢዝነስ ዘርፎች አልጠፉም። የቱሪዝም ዘርፍ ዋነኛው ነው፡፡ ለምን ቢሉ? አዋጁ በወጣ ማግስት የአሜሪካና የአውሮፓ አገራት መንግስታት፣ ዜጎቻቸው ወደ ኢትዮጵያ ጉዞ እንዳያደርጉ እገዳ ጥለው ነበር። ይሄን ተከትሎም  በርካታ ቁጥር ያላቸው ቱሪስቶች ቀድመው የያዙትን የጉብኝት ፕሮግራም ሳይቀር በመሰረዛቸው አገሪቱ ከፍተኛ ገቢ ማጣቷን (ያውም በውጭ ምንዛሪ!) የአስጎብኚ ድርጅቶች ሃላፊዎች  መናገራቸው ይታወሳል። ደግነቱ ግን አሁን ከአሜሪካ በቀር ሌሎቹ በዜጎቻቸው ላይ የጣሉትን የጉዞ እገዳ አንስተዋል። (የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መልሶ አያምጣብን!) እዚች ጋር እንዳንተላለፍ ---- በአገራችን ሁሌም ሰላምና በረከቱን ያውርድልን! ለማለት ፈልጌ መሆኑ ይታወቅልኝ፡፡  
አዋጁን ተከትሎ በተዘጋው የኢንተርኔት አገልግሎት ሳቢያ፣ (ዜጎችን ከፌስቡክና በጽንፈኝነት ከሚፈረጁ ማህበራዊ ሚዲያዎች ለጊዜው ማቀብ ብየዋለሁ!) ኢትዮጵያ በቀን 500ሺ ዶላር ገደማ እያጣች መሆኑን ግሎባል ኔትዎርክ ኢንሽዬቲቭ ከዴሎይት ጋር በመተባበር ባለፈው ጥቅምት አጋማሽ ላይ ባወጡት ሪፖርት አስታውቀዋል፡፡ በእርግጥ ለእንደኛ ያለ ድሃ አገር፣ በቀን 10 ሚ.ብር እጅግ ብዙ ነው፡፡ (እውነትም የምትታለብ ላም!) እኔ የምለው---- በኢንተርኔት መዘጋት ያጣነውን በዶላር አስልተው እንደነገሩን ሁሉ፣  በብልሹ አስተዳደር፣ በፍትህ እጦት፣ በሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ በሙስና፣ በዲሞክራሲ መቀጨጭ፣ በፖለቲካ ምህዳር መጥበብ፣ በነጻ ፕሬስ መቀንጨር ወዘተ--የደረሰብንን ኪሳራ ወይም ያጣነውን ጥቅም በዶላር አስልቶ ሹክ የሚለን ማነው??! (በዶላር ሲነገር ትኩረት ይስባል ብዬ ነው!)
ፌስ ቡክ የተዘጋ ሰሞን አንዳንድ ጓደኞቼ፣ ኢህአዴግን “ነጻነት አፋኝ” በሚል እያወገዙ ይነጫነጩብኛል ብዬ ጠብቄ ነበር፡፡ እነሱ ግን እየሳቁ  የሞባይል ካርድ ወጪያቸው በከፍተኛ መጠን እንደቀነሰላቸው ነገሩኝ፡፡  በጣም ነው የገረመኝ፡፡  (ንዴታቸውን ለመሸፈን የዘየዱት ብልሃት ይሆን?!) መገረም ብቻ ሳይሆን ፌስቡክ እንደሚወራለት የማይላቀቁት  አደገኛ  ሱስ እንዳልሆነም በጓደኞቼ  አረጋግጫለሁ፡፡ እናም ሌላ ሌላው የኢንተርኔት ጠቃሚ አገልግሎት አብሮ መከርቸሙ ነው እንጂ የፌስቡኩስ ዕዳው ገብስ ነው፡፡ (ያለ ፌስቡክም ህይወት እንደሚቀጥል ብዙዎች ተገንዝበዋል!)
በነገራችን ላይ የኢንተርኔት አፈና ወይም አገልግሎት ማቋረጥ (በተለይ ሆን ብሎ!) በብዙ የአፍሪካ አገራት እየተለመደ መጥቷል፡፡ ሰበቡ ብዙ ነው፡፡ (አፍሪካ መች ሰበብ ታጣለች!) በምርጫ ሰሞን፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት  ሲፈጠር፣ ከፈተና ስርቆት ጋር በተገናኘ ወዘተ --- የኢንተርኔት አገልገሎት ይዘጋል ወይም  ይቋረጣል፡፡ (በ97 ምርጫ ቴክስት ሜሴጅ ተቋርጦብን አልነበር!) እናላችሁ---- ዓምና  በኡጋንዳ ፕሬዚዳንታዊ  ምርጫ በተካሄደ ወቅት ለበርካታ ቀናት ኢንተርኔት ተዘግቶ ነበር። የሞባይል የገንዘብ (ክፍያ) አገልግሎትም ተቋርጧል፡፡ በውጤቱም  አገሪቱ  26 ሚሊዮን ዶላር (5.2 ቢ. ብር ገደማ!) አጥታለች  ተብሏል። (ማን ሲገደው!) በአፍሪካ የኢንተርኔት  መዘጋት ወይም መቋረጥ ከአንድ ዓመት በፊት ከነበረው በእጥፍ መጨመሩን ጥናቶች ያመለክታሉ። ይሄ ብቻ አይደለም፡፡ የዲጂታል መብትን የሚጥሱ በርካታ ህጎችና ፖሊሲዎችም ወጥተዋል፡፡ (ሌሎች ህጎችን ለማሟሟቅ  አይደለም!) ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብታቸውን የተጠቀሙ በርካታ ጦማሪያን፣ጋዜጠኞችና ዜጎች ለእስር ተዳርገዋል፡፡ (ህጎቹ ስራ ላይ ውለዋል ማለት ነው!)   
አሁንም ከአፍሪካ አልወጣንም፡፡ (አፍሪካ ችኮ ናት!) እስቲ በናይጄሪያ ትንሽ ቆይታ እናድርግ። የቀድሞው የአገሪቱ ጦር ሰራዊት አባል- ሜጀር ጀነራል ሙሃማዱ  ቡሃሪ፤ ከ2015 ጀምሮ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ናቸው። ላለፉት 19 ወራት በሥልጣን ላይ ቆይተዋል። በነገራችን ላይ ጡረታ የወጡ አንድ ጄነራል፣ በምን ተዓምር  ይሆን የተመረጡት?  ግልጽ ነው፡፡ እንደ ማንኛውም የምርጫ ተወዳዳሪ ቡሃሪም-----ያልገቡት ቃል አልነበረም፡፡ (“ተዓምር እፈጥርላችኋለሁ” ቢቀራቸው ነው!) ባራክ ኦባማ፤ የዛሬ 8 ዓመት ለፕሬዚዳንትነት ሲወዳደሩ ምን ብለው ነበር? - “Yes We Can!” አሁን ከስልጣን  ሲወርዱስ?- “No We Can’t!” በነገራችን ላይ ይሄ ለብዙዎቹ የአፍሪካ መሪዎች ይሰራል፡፡ መጀመሪያ ላይ፤ “የማናደርግላችሁ ነገር የለም” ብለው ይምላሉ ይገዘታሉ፡፡ በኋላስ? “የት እናቃችኋለን!” ይመጣል። (ኢህአዴግ ነፍሴም ተመሳሳይ ነው!) ወደ ናይጄሪያው ጀነራል እንመለስ፡፡ አንድ ዓመት ከሰባት ወር ሥልጣን ላይ ቆይተዋል፡፡ ሆኖም በተለይ በኢኮኖሚው ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ አላመጡም ተብሏል፡፡ የአዲስ ዓመት በዓል እየመጣ ከመሆኑ ጋር ተደምሮ፣ የሸቀጦች ዋጋ ሰማይ መንካት፣ ናይጄሪያውያንን ስጋት ውስጥ ከትቷቸዋል፡፡
“ለቡሃሪ ድምጼን መስጠቴ ይቆጨኛል። የፈለግነው የተሻለ ኢኮኖሚ ነበር፤ግን ነገሮች እንዳይሆኑ ሆኑ፡፡ አሁን ያለው ከበፊቱም የከፋ ነው። ድምጻችንን የሰጠንበት ለውጥ ያ አይደለም፤ ነገሮች እንዲሻሻሉ እንፈልግ ነበር፤ ሆኖም አልተሻሻሉም፤ ውሃ-የለም! መብራት - የለም!” ብሏል፤ አንድ ቡሃሪን በመምረጡ የበገነ ናይጄሪያዊ፡፡ መራጭ ህዝብ እንኳን በፈረደባት አፍሪካ ቀርቶ በአሜሪካም ጭምር መብገኑ አይቀርም፡፡ እርር ድብን ይላል፡፡ (የአፍሪካ መሪዎች ዋና ሥራቸው ምን ሆነና!) በእርግጥ ቡሃሪ ለኢኮኖሚው እንደተፈለገው  አለመሻሻል ምክንያት አላጡም፡፡ (ከምክንያት ሰበብ ማለቱ ይሻላል!) የቡሃሪ መንግስት  በቀድሞው የጉድላክ ጆናታን አገዛዝ ላይ ነው የደፈደፈው። (ኢህአዴግም እኮ በደርግ ሲያሳብብ ኖሯል!) “የናይጄሪያ ድፍድፍ ዘይት በበርሜል 100 ዶላር በሚሸጥበት ወቅት በቂ ገንዘብ ማስቀመጥ ሲችል ባለማስቀመጡ ነው” ብለዋል - ፕሬዚዳንቱ፡፡
በሱዳንም የመሰረታዊ ሸቀጦችና መድሃኒት ዋጋ መጨመር ችግር ፈጥሯል፡፡ የዋጋ መናሩ የተከሰተው ደግሞ የሱዳን መንግስት ለነዳጅ የሚያደርገውን ድጎማ ለማቆም በመወሰኑ ነው፡፡ የሱዳን ፓውንድ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ መውረዱና የአሜሪካ የኢኮኖሚ ማዕቀብ የአገሪቱን ኢኮኖሚ የበለጠ አዳክሞታል ተብሏል፡፡ የነዳጅ ድጎማው መቋረጡን  በመቃወምም  የሱዳን ተቃዋሚዎችና አክቲቪስቶች  የሁለት ቀን አገር አቀፍ አድማ ጠርተዋል፡፡ (በማህበራዊ ሚዲያ ሳይሆን አይቀርም!) ይሄኔ ነው የ72 ዓመቱ የሱዳን አምባገነን መሪ ኦማር አል-ባሺር፣ በተቃዋሚዎችና በአክቲቪስቶች ላይ የዛቱት።  አገዛዛቸው በማህበራዊ ሚዲያና በአክቲቪስቶች የሚገረሰስ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ በምስራቃዊ የአገሪቱ ክፍል በምትገኘው የከሳላ ከተማ ለደጋፊዎቻቸው ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንቱ፤ “አገዛዙን መጣል ከፈለጋችሁ ፊት ለፊት ጎዳና ላይ ተጋፈጡን። ወደ አደባባይ እንድትወጡ እንፈልጋለን። ግን አትወጡም፡፡ ምክንያቱም ባለፈው የሆነውን ታውቁታላችሁ። ሥርዓቱ በኪቦርድና በዋትስ አፕ አይወድቅም!” ብለዋል። (አል-ባሺር፤  ታንክና ፌስቡክ ሲገጥሙ ማን እንደሚያሸንፍ አይጠፋቸውም!) ሥራቸው እጅግ አድካሚ እንደሆነ ለቢቢሲ የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፤ በ2020 ዓ.ም ከሥልጣናቸው እንደሚወርዱ አስታውቀዋል፡፡ ችግሩ ግን ያመናቸው የለም፡፡ ከዚህ ቀደም እንዲሁ ብለው ቃላቸውን አጥፈዋል። (ሙጋቤም ከሥልጣን እወርዳለሁ እያሉ ስንት ዘመናቸው!) በቅርቡ ምርጫ ባካሄደችው የምዕራብ አፍሪካዋ አገር ጋምቢያ የተከሰተውን ሳትሰሙ አትቀሩም፡፡ ገዢው ፓርቲን ወክለው የተወዳደሩት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት በምርጫው ሲሸነፉ፣ በቀጥታ የተቃዋሚ ፓርቲ አሸናፊው ጋ ደውለው፤” ኮንግራጁሌሽንስ!” አሉ፡፡ (አሜሪካኖቹ ሲባባሉ ሰምተው መሆን አለበት!) አለም ሁሉ ሳይደነቅ አልቀረም፤ አፍሪካ በለውጥ ጎዳና ላይ ናት በሚል። የጋምቢያው የቀድሞ መሪ፣ አድናቆቱ ከሳምንት በላይ እድሜ እንዲኖረው አልፈለጉም። በአገሪቱ ቴሌቪዥን ቀርበው ምርጫው ችግር ስላለበት በድጋሚ መካሄድ አለበት አሉ፡፡ (የተጭበረበረ ምርጫ! የተጭበረበረ ኮንግራጁሌሽን! የተጭበረበረ መንግስት! የተጭበረበረ አገር! የተጭበረበረ ህዝብ! የተጭበረበረች አፍሪካ!)  
ወደ ሱዳን ልመልሳችሁ፡፡ በሄግ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት በዘር ማጥፋት ወንጀል የሚፈለጉት  አል-ባሺር፤ በተገኙበት እንዲያዙ ማዘዣ ከተቆረጠባቸው ወዲህ እንዳሻቸው  መንቀሳቀስ አልቻሉም፡፡ በሌላ በኩል አገራቸው በአሜሪካ በተጣለባት የኢኮኖሚ ማዕቀብ መከራዋን ስትበላ ከርማለች፡፡ ለዚህ ሳይሆን አይቀርም የሱዳኑ መሪ፣ የአሜሪካውን አዲስ ተመራጭ ፕሬዚዳንት- ዶናልድ ትረምፕን ድንገት ተነስተው ማወደስ የጀመሩት፡፡ “ትረምፕ ከሌሎቹ ጋር ሲነጻጸር የሚፈልገውን በቀጥታና በግልጽ  የሚናገር ሰው ነው” ያሉት አል-ባሽር፤ ”ከሱ ጋር መነጋገር ከባድ አይሆንም” ሲሉ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡ “የቢዝነስ ሰው ነው፤ የሚደራደራቸውን ወገኖች ጥቅም ከግንዛቤ ያስገባል፤ ትኩረቱ የአሜሪካ ዜጎች ጥቅም ላይ ነው፤ ስለ ዲሞክራሲ፣ ሰብኣዊ መብትና ግልጽነት ከሚደሰኩሩት የተለየ ነው፡፡” ብለዋል - የሱዳኑ ፕሬዚዳንት፡፡ ትረምፕን በትክክል ያወቋቸው አይመስሉም፡፡ እርግጥ ነው የንግድ ሰው ናቸው፡፡ ነገር ግን አል-ባሽር  የአሜሪካ ሌሎች ፕሬዚዳንቶች ሲጨቀጭቋቸው ስለነበሩት የዲሞክራና ሰብአዊ መብቶች ጉዳይ አያነሱብኝም ብለው ካሰቡ በትልቁ ተሳስተዋል። (ትረምፕ ስለ ኩባ ያሉትን አልሰሙ ይሆናል?) የሆኖ ሆኖ የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ከትረምፕ የሚፈልጉት አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ አሜሪካ በአገራቸው ላይ የጣለችው የኢኮኖሚ ማዕቀብ በሚነሳበት ጉዳይ ላይ ውይይት መጀመር!! ክፉ ሃሳብ አይደለም። ሆኖም ማዕቀቡ ከተጣለ አንስቶ አል-ባሽርና መንግስታቸው በዲሞክራሲና በሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ ምን ለውጥ አስመዝግበዋል? የሚለው ጥያቄ ከትረምፕም ሆነ ከታዛቢ ወገን መነሳቱ አይቀርም፡፡ እስከዛው ግን እድሜ ለአንዳንድ የአፍሪካ አምባገነን መሪዎች--- አል ባሻር ከአገራቸው  ሹልክ ብለው ወጥተው፣ ሹልክ ብለው ይመለሳሉ፡፡ (ኢህአዴግም ዋና ወዳጃቸው ነው!) ሁሌም የምንናፍቀው ግን አፍሪካ ከአምባገነን መሪዎች ተላቃ፣ የህዝቦቿ ነጻነት--መብትና ሰብዓዊ መብቶች----የሚከበሩባት፤ የዕውቀት፣ የብልጽግና፣ የሰላም፣ የሥልጣኔ፣ የሃብት ----- ምንጭ ሆና ማየት ነው፡፡ (“እኛን ነው ማየት” አለ ዘፋኙ!)
እስካሁን ያወጋነውን ጠቅለል አድርገን ስናየው------አገር ለማስተዳደር፣ ህዝብ ለመምራት፣ የመንግስት ሥራዎች ለማከናወን፣ማህበረሰቡን ለማገልገል------ከፍተኛ ፍላጎት አለን የሚሉ ሰዎች-----ከትምህርት ዝግጅታቸውና ከብቃታቸው በተጨማሪ የአገር ፍቅር ስሜታቸውም በጥልቀት  መመርመር  እንዳለበት ያሳየናል፡፡ ህዝብ እመራለሁ ብሎ ሥልጣን የያዘ ግለሰብ፣ ፓርቲ፣ ምሁር--- ወዘተ አገሩንና ህዝቡን ከልቡ መውደድ አለበት፡፡ ህዝቡን ሳይወዱ ------የአገር ፍቅር ስሜት ሳይኖር----- የተዋጣለት ፕሬዚዳንት፣ ጠ/ሚኒስትር፣ ዳይሬክተር፣ ኮሚሽን፣ ገዢ፣ ሃኪም፣ ኢንጂነር፣ መምህር፣ ሳይንቲስት፣-----ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ አገሩንና ህዝቡን የሚወድ ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣን፣ በሙስና ተዘፍቆ የግል ጥቅሙን አያባርርም፡፡ (ህግ ፈርቶ ብቻ አይደለም፤ ህሊናው አይፈቅድለትም!) ከሚወዳት አገሩና ከሚያከብራቸው ህዝቦቹ --ወርቅና ገንዘብ፣ ፎቅና መሬት፣ ሃብትና ንብረት ----እየዘረፈ ለራሱ ከማከማቸት የላቀ ህልምና ራዕይ እንደሚኖረው አያጠራጥርም፡፡ ኢትዮጵያና ህዝቦቿ  የዛሬ 5----10----15-----20-----30---- ዓመት የት ይደርሳሉ? ብሎ የሚያስብ፣ የሚያሰላስል፣ ዕቅድና ግብ የሚነድፍ፣ ለስኬቱም እንቅልፍ አጥቶ የሚተጋ ነው፡፡
ነቢይ በአገሩ አይከበርም እንዲሉ ------ጣል ጣል ያደረግናቸው ቀዳማዊ ኃይለስላሴ፤ ለአገራቸው ያልሙ ይመኙ የነበረውን ከመሰረቷቸው ዩኒቨርሲቲዎች፣ ባንኮች፣ ወታደራዊ ተቋማት፣ አየር መንገድ፣ ትያትር ቤቶች፣ ሲኒማ ቤት፣ ቤተ-መንግስት-----ተነስተን ለማወቅ፣ ለመገንዘብ እንችላለን። ብዙዎቹ በድጋሚ እንኳን አልተሰሩም። ዛሬም ከ50 ዓመት በኋላ ብቸኛ አገልግሎት ሰጪ፣ የአገር ሃብትና ኩራት ሆነው ቀርተዋል። አገሩን የሚወድ፣ህዝቡን የሚያከብር መሪ----መንግስት----ፖለቲከኛ-----ፓርቲ-----ይሄንን  ነው የሚያደርገው፡፡ ኢትዮጵያችን--- የምሁራን ሚኒስትሮች፣ በዶክተሮች የተሞላ ካቢኔ፣ ሙስናንና በስልጣን መባለግን የሚጠየፉ የመንግስት ሃላፊዎች----እንደሚያስፈልጋት አያከራክረም፡፡ ሁሉም ግን ህዝቡን የሚወዱ መሆን አለባቸው፡፡ ከፍተኛ የአገር ፍቅር ስሜት ሊኖራቸውም ግድ ይላል፡፡ (የማይወደን አስቀድሞ ለምን ወደ ሥልጣን ይመጣል!?)
ባለፈው ወር በአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ላይ ዶናልድ ትረምፕ ማሸነፋቸው በተሰማ ማግስት፣ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በውጤቱ ለፈነደቁም ለደነገጡም፣  አንድ የማረጋጊያ ንግግር አድርገው ነበር፡፡ ለእኛም በእጅጉ ይጠቅመናል፡፡ ኦባማ እንዲህ ነው ያሉት፡- “ዲሞክራትና ሪፐብሊካን ከመሆናችን በፊት ሁላችንም አሜሪካውያን ነን!!” (ደስ የሚል ፈዋሽ እውነት!) እዚህም ታዲያ፤ “ኢህአዴግ ወይም መድረክ አሊያም ኢዴፓ ከመሆናችን በፊት ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ነን!!” ብለው የሚናገሩ፣ ብለው የሚያስቡ፣ ከፓርቲያቸው በፊት አገር የሚያስቀድሙ  መሪዎች ያስፈልጉናል!!! (የሁሉም ነገር ማቀፊያ ኢትዮጵያ ናት!)
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!!

Read 4523 times