Saturday, 17 December 2016 12:49

“ለቤዛ የስነ- አዕምሮ ልዩ ክሊኒክ” ተመርቆ ተከፈተ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(5 votes)

 በሱስ ሳቢያ የሚመጡ የአዕምሮ ህመሞችንና ሌሎችንም የአዕምሮ በሽታዎች ለማከም የተቋቋመው ለቤዛ የስነ አዕምሮ (ሳይካትሪ) ልዩ ክሊኒክ፣ ባለፈው ሳምንት ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡
ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ‹‹ለቤዛ የስነ-ልቦና ማማከር አገልግሎት›› በሚል የማማከርና የስልጠና አገልግሎት ሲሰጥ የነበረው ድርጅቱ፤ በአዕምሮ ህመም ላይ ያለውን የህክምና ክፍተት ለመሙላት ታስቦ መቋቋሙን የክሊኒኩ ዋና ስራ አስኪያጅ ዶ/ር አስመረት እንደ ብርሀን በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ተናግረዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በግል የተከፈተ ሶስተኛው የስነ አዕምሮ ክሊኒክ መሆኑንና ከዚህ ቀደም “አቢቹ ልጁ መታሰቢያ ክሊኒክ” እና “ስጦታ ማዕከል” የተባሉ ሁለት የግል ክሊኒኮች ብቻ እንደነበሩ ዶክተሯ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከጫት፣ ከሲጋራ፣ ከአልኮልና እንደ ማሪዋና ካሉ እፆች ጋር በተያያዘ በሚመጣ ሱስ ብዙዎች ለአዕምሮ ህመም እየተዳረጉ መሆናቸውን የገለፁት ዶ/ር አስመረት፤ ክሊኒካቸው ይህንን ክፍተት ለመሙላትና በተመጣጣኝ ዋጋ አገልግሎት ለመስጠት መከፈቱን ተናግረዋል፡፡ ከኡራኤል ቤተክርስቲያን ዝቅ ብሎ በሚገኘው ፕላዛ ሆቴል ጀርባ የተከፈተው “ለቤዛ የስነ-አዕምሮ ልዩ ክሊኒክ”፤ ከተመላላሽ ህክምና በተጨማሪ የአስተኝቶ ማከም አገልግሎት እንደሚሰጥና እስካሁንም ስምንት አልጋዎችን ማዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡
3 እና 4 ሚሊዮን ህዝብ በሚኖርበት አዲስ አበባ ከተማ፤ ሦስት የግል የስነ አዕምሮ ክሊኒኮች ብቻ መኖራቸው ከሚፈለገው መጠን በታች እንደሆነ የገለፁት ዶ/ር አስመረት፤ መካከለኛ በሆነ ክፍያ የአገልግሎት ክፍተቱን እንሞላለን ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የአዕምሮ ህመም በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የተጠና ጥናት ስለመኖሩ ከአዲስ አድማስ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ ከባድ የአዕምሮ ህመም 1 በመቶ፣ በጫት ሱስ የሚመጣ እንደየአካባቢው 60 በመቶ በአልኮል ሱስ የሚመጣ፣ 30 በመቶ እንደሆነ ጥናቶች እንደሚያሳዩ ገልፀው በተለይ በሀይስኩል ተማሪዎች ማሪዋና የተሰኘው አደንዛዥ እፅ በስፋት እየተዘወተረ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡
ድርጅቱ እንደ የሁኔታው የ50 በመቶ ቅናሽና ነፃ ህክምና የሚሰጥበት አሰራር ማመቻቸቱን ገልፀው አንድ ሳይካትሪስት 10 ህመምተኞችን ባከመ ቁጥር አንድ ሰው በነፃ እንደሚያክምና አንድ ታካሚ እየታከመ ቆይቶ በማገገሚያው ሰዓት ገንዘብ ካጠረውና ሀኪሙ ካመነበት የ50 በመቶ ቅናሽ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡
ክሊኒኩ እግረ መንገዱን ማህበረሰቡ ስለ አዕምሮ ህመም ያለውን አመለካከት እንዲለውጥ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ጎን ለጎን ይሰራልም ተብሏል።
ክሊኒኩን ለማደራጀትና ውስጡን ለህሙማን ምቹ ለማድረግ ከ300 ሺህ ብር በላይ መውሰዱን የገለፁት ዶ/ር አስመረት ለዚህም አቢሲኒያ ባንክ ላመቻቸላቸው ብድር አመስግነዋል፡፡ 

Read 6032 times