Saturday, 17 December 2016 12:48

የኩላሊት እጥበት በጎ አድራጎት ማዕከል ለኩላሊት እጥበት 3 ሚ. ብር መደበ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(7 votes)

አባላት በሳምንት 600 ብር፣   ለስድስት ወር ይከፈልላቸዋል

      የኩላሊት እጥበት በጎ አድራጎት ማዕከል በስሩ ለሚገኙ የኩላሊት ህመምተኛ አባላቱ፣ ለኩላሊት እጥበት አገልግሎት የሚውል 3 ሚ. ብር መመደቡን አስታወቀ፡፡ ባለፈው ሳምንት በዘውዲቱ ሆስፒታል ባካሄደው ጉባኤ፤ ለህሙማኑ በሳምንት ለእያንዳንዳቸው 600 ብር በመክፈል ለስድስት ወራት ድጋፉን እንደሚቀጥልና ከስር ከስር ገቢ ለማሰባሰብ እንደሚጥር የማዕከሉ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን አሰፋ ገልፀዋል፡፡ ገንዘቡ ህሙማኑ ዲያሊሲስ ለሚያደርጉባቸው የተለያዩ ክሊኒኮች በቀጥታ እንደሚከፈልም ተናግረዋል፡፡
ህሙማኑ በጥሩ ጤንነት እንዲቀጥሉ በሳምንት ሶስት ጊዜ የኩላሊት እጥበት ማድረግ እንዳለባቸው የገለፁት አቶ ሰለሞን፤ በአንድ እጥበት ከሚከፍሉት ላይ የሁለት መቶ ብር እፎይታ ለሶስት እጥበት ደግሞ የስድስት መቶ ብር እፎይታ ያገኛሉ ብለዋል፡፡ የጉባኤው ዓላማ ማዕከሉ ለህሙማኑ የገንዘብ ድጋፍ ከማድረጉም በላይ ህብረተሰቡ በኤስ ኤም ኤስ ያዋጣው ብር የት እንደደረሰ ለማሳወቅም እንደሆነ አቶ ሰለሞን ገልፀዋል፡፡
በዘውዲቱ ሆስፒታል የእጥበት ማዕከል ለአንድ እጥበት 500 ብር ማስከፈል ተጀምሯል ያሉት ስራ አስኪያጁ፤ በሌሎች የግል ክሊኒኮች ከ800-1ሺህ ብር ለአንድ እጥበት እንደሚጠየቅ ጠቁመው በማዕከሉ ያለውን አገልግሎት የሚጠብቁ 178 አባላት ቢኖሩም ማሽኖቹ በቀን ለ20 ሰው ብቻ አገልግሎት የመስጠት አቅም እንዳላቸውና ቀሪዎቹ 156 ህሙማን ወረፋ እስኪደርሳቸው ድጋፍ እየተደረገላቸው በሌሎች ክሊኒኮች እጥበት እንዲያካሂዱ 3 ሚ ብሩ መመደቡን አቶ ሰለሞን ገልፀዋል፡፡
ህብረተሰቡ የማዕከሉን እንቅስቃሴ እያየ የባንክ ሂሳብ ቁጥር በመውሰድ የሚችለውን እያደረገ እንደሆነ የገለፁት ስራ አስኪያጁ፤ በቀጣይ ከዚህ እጥፍ የሆነ ድጋፍ እንደሚገኝ እናምናለን ብለዋል፡፡ ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም በኤስኤምኤስ ገቢ ለማሰባሰብ ማቀዳቸውንና ከሌሎች ማህበራት ጋር በመተባበር የሚሰሩ ፕሮጀክቶች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡ የኩላሊት ህመምተኞች እጥበት በጎ አድራጎት ማዕከል፤ ከ350 በላይ አባላት እንዳሉትና 187 በአባላት ከማዕከሉ ጋር በቅርበት እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ አቶ ሰለሞን ጨምረው ገልፀዋል፡፡ 

Read 4134 times