Sunday, 25 December 2016 00:00

በአዲስ አበባ በየዕለቱ እስከ 100 ከረጢት ደም ይሰበሰባል

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(7 votes)

 - ፍላጎቱና አቅርቦቱ ፈፅሞ አልተመጣጠነም ተባለ
                         - ከ80 በላይ የ”ሞሃ” ሠራተኞች የደም ልገሳ አድረጉ
                         
      በአዲስ አበባ ከተማ በየዕለቱ ከ40 እስከ 100 ከረጢት ደም የሚሰበሰብ ቢሆንም የደም ፍላጎቱ በየቀኑ ከ100-300 ከረጢት እንደሚደርስና ፍላጎቱና አቅርቦቱ ፈፅሞ ሊጣጣም አለመቻሉ ተጠቁሟል፡፡  
በሌላ በኩል፤ ከትላንት በስቲያ ከ80 በላይ የሞሃ የለስላሳ መጠጦች ኢንዱስትሪ ሰራተኞች፣ የደም ልገሣ ያደረጉ ሲሆን ድርጅቱ በተጨማሪ ለብሔራዊ ደም ባንክ የድንኳን፤ ወንበሮችና ጠረጴዛዎች ድጋፍ አድርጓል፡፡
በብሔራዊ ደም ባንክ በመገኘት የደም ልገሳ ያደረጉት የሞሃ ሰራተኞች፤ “የሚለገሰው እያንዳንዱ ከረጢት ደም፣ የወገኖቻችንን ህይወት ለማትረፍ የሚያስችል በመሆኑ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶናል” ብለዋል፡፡  ሞሃ የለስላሳ መጠጦች ኢንዱስትሪ፤ ለደም ባንኩ በስጦታ ያበረከተውን 10 ድንኳኖች፣ 200 ወንበሮችና 30 ጠረጴዛዎች ለደም ባንኩ ኃላፊዎች ያስረከቡት የሞሃ ለስላሣ መጠጦች ኢንዱስትሪ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጌታቸው ቢርቦ በሥነስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ “ድርጅቱ ከደም ባንኩ ጎን በመቆም ለወገኖቻችን የሚደረገውን ሰብአዊ እርዳታ ከልብ በመደገፍ፣ ሁልጊዜም ከጎናችሁ ይቆማል” ብለዋል፡፡ በዕለቱ ድርጅቱ በቁሳቁስ ካበረከተው ድጋፍ ይልቅ ሠራተኞቹ ባደረጉት የደም ልገሣ በእጅጉ ኮርቻለሁ ያሉት ዋና ስራ አስፈፃሚው፤ በቀጣይም ድርጅቱ ለብሄራዊ ደም ባንኩ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግ ገልፀዋል፡፡
የብሔራዊ ደም ባንክ ተ/ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሃብተማርያም ደሞዝ በበኩላቸው፤ “ሞሃ የለስላሳ መጠጦች ኢንዱስትሪ ሁልጊዜም ከብሔራዊ ደም ባንክ ጎን በመቆም ለሚያደርግላቸው ድጋፍ አመስግነው፣ የወገኖቻቸውን ህይወት ለማዳን ደም ለመለገስ ፍቃደኛ የሆኑት የድርጅቱ ሰራተኞችም ሊመሰገኑ ይገባል፤ አርአያነታቸውም የላቀ ነው” ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በየዕለቱ ከ40 እስከ 100 ከረጢት ደም እንደሚሰበሰብ የጠቆሙት ዶ/ር ሀብተማርያም፤ የደም ፍላጎቱ በየዕለቱ ከ100-300 ከረጢት እንደሚደርስና አቅርቦቱና ፍላጎቱ ፈፅሞ ሊጣጣም አለመቻሉን ገልፀዋል፡፡ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ደም ለጋሾች ተማሪዎች ናቸው ያሉት ተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተሩ፤ በበዓላት ወቅትና በክረምት ወራት የደም ለጋሹ ቁጥር እንደሚቀንስ ተናግረዋል፡፡ ባለፈው ዓመት 140 ሺህ ከረጢት ደም መለገሱንም ዶክተሩ ጨምረው ገልፀዋል፡፡

Read 2848 times