Monday, 09 January 2017 00:00

በአሜሪካ - “የቢሊየነሮች ካቢኔ”፣ በጦቢያ - “የምሁራን ካቢኔ”!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(10 votes)

*አዲሶቹ ምሁር ሚኒስትሮች ህልማቸውን ይንገሩን!!
                  *ባራክ ኦባማን ያየ፤ ‹‹ሌጋሲ አታሳጣኝ››ብሎ ይጸልያል!
                  *ፖለቲከኞች ከጨዋታ ውጭ እየሆኑ ነው!
                    

        ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ 130 ግለሰቦችና ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፌደራል ፖሊስ ነግሮናል፡፡ አሁን እንግዲህ ስንቱ እንቅልፍ እንደሚያጣ ገምቱ፡፡ (“ምን ያለበት----ምን አይችልም አሉ”!) ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ከመንግስት ዕቃ ግዢ፣ ከቤቶች ልማት፣ ከመሬት ልማት፣ ከባንክ ስራዎችና ከአክስዮን ኩባንያዎች፣ ከታክስ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ ነው ተብሏል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ፤ በገዥው ፓርቲ የግምገማ መድረኮች የማይጋለጡ ውስብስብ የሙስና ወንጀሎችን በልዩ ጥናት ፈትሾ እንደሚያወጣ የጠቆመ ሲሆን፤“በጥልቀት የመታደስ ዘመቻው በጥሩ ሁኔታ በመተግበር ላይ ነው” ብሏል። (Better late than never - አለ ፈረንጅ!) ጨርሶ መቅረትም ሊያጋጥም ይችላል፡፡ አሁን እንግዲህ መጀመሩን ሰምተናል - በጥልቀት የመታደስ ዘመቻው!! በህክምና ቋንቋ በሽተኞች ተመርምረውና ደዌያቸው ታውቆ፣ ሃኪም ያዘዘላቸውን መድሃኒት እየወሰዱ ነው፡፡ ከደዌያቸው ጨርሶ እንዲፈወሱ ግን መድሃኒታቸውን በአግባቡ ወስደው መጨረስ አለባቸው፡፡ እነሱ ተፈወሱ ማለት ሌላ በሽተኛ የለም ማለት ግን አይደለም፡፡ (ከጤነኛው የታወከው ባይበልጥ ነው!!) እናም ሃኪም ሥራውን ይቀጥላል፡፡ አገር ጤነኛ እንድትሆን በሽተኞችን ያክማል፡፡ ዘመቻ የሚያስፈልገው አተት (የሙስና ኮሌራ) ሲገባ ብቻ ነው፡፡ በሰላሙ ጊዜ ሃኪሙ የመከላከል ህክምና ላይ ያተኩራል፡፡ (“ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ!”እንዲሉ!!)
በነገራችን ላይ ልማታዊው መንግስታችን፣ ከስህተቱ ተምሮ ከዛሬ ነገ ለውጥና መሻሻል ያመጣል ብለን በጉጉት እየጠበቅን ነው፡፡ (“ጠዋት ከቤትህ ስትወጣ ያደናቀፈህ ድንጋይ፣ ማታም መልሶ ካደናፈቀህ ድንጋዩ አንተ ነህ!”) ድንቅ ናት - እንቅፋቷ ሳትሆን አባባሏ!! ደጋግሞ እንቅፋት የሚመታን ተመሳሳይ ድንጋይ መሆኑን አስተውላችኋል? (ድንጋዩን ስለማናነሳው እኮ ነው!) እናላችሁ ------ ከ25 ዓመት በላይ በሥልጣን ላይ ከቆየው አውራው ፓርቲው፤አሁን ብዙ እንጠብቃለን፡፡ ዕድሜም ልምድም ያበስለዋል ብለን እኮ ነው፡፡ ግን ከፈለገ ብቻ ነው፤ ፍላጎቱ ከሌለው ዕድሜም ልምድም የሚፈይዱት ነገር የለም፡፡ የ92 ዓመቱ አዛውንት የዚምቧቡዌ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ፣ከ35 ዓመት አምባገነናዊ አገዛዝ በኋላ ለምርጫ እንደሚወዳደሩ ስትሰሙ፣ ተስፋ ትቆርጣላችሁ፡፡ (ንስሃ በመግቢያ ዕድሜያቸው እኮ ነው!)
እኔ የኢህአዴግ ደጋፊ አይደለሁም፡፡ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ አድናቂም አይደለሁም። (እንኳን ላደንቀው አይገባኝም!) ግን እንደ አንድ ለአገሩ ተቆርቋሪ ዜጋ፣ የገባኝን ያህል እናገራለሁ። ኢህአዴግ መራሹ መንግስት አንዱ ችግሩ፣ ሁሉን ነገር በቡድን ወይም በደቦ ---ማሰብ፤ መመልከት፤ መወሰኑ ነው፡፡ (የፓርቲው ስታይል መሰለኝ!) የግለሰቦች ጥረትና ችሎታን አያደንቅም፡፡ የቡድን ስኬት ነው የሚወደው፡፡ የኢህአዴግ አመራሮች ስለ ራዕይ፣ ህልም፣ ዕቅድ---- ሲጠየቁ፣ ወደው አይደለም የኢህአዴግን የሚዘረዝሩት፡፡ ቅድሚያ ለፓርቲ ነው፡፡ ጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ሥልጣን የያዙ ሰሞን የአልጀዚራ ጋዜጠኛ ስለ ራዕያቸው ጠይቃቸው፤” እኔ የፓርቲውን ራዕይ ነው የምፈጽመው፡፡” ብለው ነበር፡፡ ጠ/ሚኒስትር ሆነው መሾማቸውን በተመለከተ፤ እንደ ስልጣን ሳይሆን እንደ ትግልና መስዋዕትነት እንደሚቆጥሩት መናገራቸውን አስታውሳለሁ፡፡ ስለ ጠ/ሚኒስትሩ ያነሳሁት፣ እግረ መንገድ እንጂ ዋና ጉዳዬ አይደለም።  እናላችሁ ---- ኢህአዴግ ለግለሰቦች ጥረት ትኩረት ስለማይሰጥ ነው የተሾመበትን መ/ቤት በአስደናቂ ሁኔታ አሻሽሎ፣ ተዓምረኛ ለውጥ የሚፈጥር ሚኒስትር፣ ዳይሬክተር፣ ሥራ አስኪያጅ፣ዋና ሥራ አስፈጻሚ-----የሌሉት፡፡ ችሎታ ወይም ብቃት ያለው ሹመኛ ጠፍቶ አይደለም፡፡ ፓርቲው አያበረታታም፡፡ ኢህአዴግ መራሹ መንግስት፣ ለውጥ ወይም ውጤት የሚሻ ከሆነ ግን የአመራር ስታይሉን መቀየር አለበት፡፡ ሚኒስትሮችና ሌሎች የመንግስት ሃላፊዎች የሚመሩበት መንገድ መለወጥ ይኖርበታል፡፡ እያንዳንዱ ሚኒስትር ለሚመራው መ/ቤት ስኬትም ሆነ ውድቀት መሉ ሃላፊነቱን ሊወስድ ይገባል፡፡ ስኬት የሚያሸልም፤ ውድቀት የሚያስወቅስና የሚያስጠይቅ መሆን አለበት። ሽልማትም ቅጣትም የሌለበት የሥራ ሃላፊነት ለማይሰሩ ሰዎች ይመቻል፡፡ የአመራሮች ጉልህ አሻራ (ብቃትም ጉድለትም!) የሚታይበት አሰራር መፍጠር የግድ ይላል፡፡ እስቲ አዳዲሶቹ ሚኒስትሮች ------- ህልማቸውን ይንገሩን፡፡ (ገና ሲሾሙ መሆን የነበረበት እኮ ነው!) ለምሳሌ አዲሱ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ሚኒስትር በ5 ዓመት የሥልጣን ዘመናቸው ምን ሊሰሩልን፣ ሊለውጡልን አስበዋል? ሌሎቹስ ሹመኞች? ከቀድሞዎቹ ሚኒስትሮች በምንድን ነው የሚለዩት? ለውጥ የሚያመጡት እንዴት ነው? “የኢህአዴግን ፕሮግራም፣የመንግስትን ዕድቅ----- አስፈጽማለሁ” የሚለው ሽሽት እንጂ መልስ አይደለም፡፡ (እኔም ብሾም እለዋለሁ!) አዲሶቹ ሚኒስትሮች ቴክኖክራቶች እንጂ ፖለቲከኞች አይደሉም ተብሏል፡፡ ግን ለውጡን የምናውቀው ውጤት ሲመጣ ነው፡፡
በነገራችን ላይ ዘመኑ ለፖለቲከኞች ብሩህ አይመስልም፡፡ ፖለቲከኞች ከማውራት ውጭ ጠብ የሚላቸው ነገር እንደሌለ ህዝብ ከርሞ ከርሞ የገባው ይመስላል፡፡ እዚህ ጦቢያ ምድር ላይ ብቻ እንዳይመስላችሁ፡፡ በሰለጠነችውና በበለፀገችው ታላቋ አሜሪካም ጭምር ነው፡፡ ቢሊዬነሩ ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት፤ “የአሜሪካ ህዝብ ከዲስኩር በቀር ተግባር ላይ በሌሉበት የዋሺንግተን ፖለቲከኞች አንጀቱ መቃጠሉን፣ ጨጓራው መብገኑን---” ደጋግመው ተናግረዋል። (አልተሳሳቱም!) የእሳቸው መመረጥ በራሱ ላለመሳሳታቸው በቂ ማስረጃ ነው፡፡ በመንግስት አስተዳደርና ፖለቲካ ምንም ዓይነት ልምድ የሌላቸው የሪል እስቴቱ ከበርቴ ትራምፕ፤ከ30 ዓመት በላይ በፖለቲካና በመንግስት አስተዳደር በቂ ልምድ ካካበቱት የ69 ዓመቷ ሂላሪ ክሊንተን ልቀው የ2016 የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አሸናፊዋ ሆነዋል፡፡
ትራምፕ ያዋቀሩት ካቢኔም ከፖለቲካ ይልቅ ቢዝነስን (ፋይናንስ፣ ኢኮኖሚክስና ማኔጅመንት) አብጠርጥሮ የሚያውቅ ነው። አብዛኞቹ ሹመኞችም የዎልስትሪት የቢዝነስ  ባለቤቶችና ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች የነበሩ ናቸው። በአሜሪካ ዘመናዊ ታሪክ ሚሊየነሮችና ቢሊየነሮች የሞሉበት የመጀመሪያው ካቢኔ መሆኑን የገለጸው ፎርብስ፤ የትራምፕ ካቢኔ 4.5 ቢ ዶላር ሃብት እንዳለው ጠቁሟል፡፡ (የነጋዴዎች ካቢኔ ነው? የመንግስት ካቢኔ?)
ከሁለት ሳምንት በኋላ ፖለቲከኞች ከዋይት ሀውስ ተጠራርገው ወጥተው የቢዝነስ ሰዎች ይተካሉ፡፡ (ዋሽንግተን ሌላ ዎልስትሪት ልትሆን ነው!) አገር በናጠጡ ነጋዴዎች አትመራም፣ የሚል ጥልቅ እምነት ያላቸው ሰዎች የትራምፕ ካቢኔ ሊያሰጋቸው ይችላል፡፡ ይሄን የመረጠው ግን ሌላ ሳይሆን የአሜሪካ ህዝብ ነው - በድምፁ!! አሜሪካውያን ትራምፕን የመረጡት በሁለት ምክንያቶች ሊሆን ይችላል፡፡ አንድም በምርጫ ቅስቀሳቸው አምነውና ተደምመው አሊያም በኦባማ ዲሞክራቲክ ፓርቲና በልሂቃን ፖለቲከኞች ላይ ያላቸውን ቁጣና ንቀት ለመግለፅ ነው - እንደ ተቃውሞ!! (በ97 ምርጫ ህዝብ ድምጹን ለቅንጅት የሰጠው ኢህዴግን ለመቃወም ነው ሲባል ነበር!)
ሃቁ ግን፤ ትረምፕ የተመረጡት የተራ ተርታውን አሜሪካዊ ችግር፣ ፍርሃት፣ ስጋትና ተስፋ መቁረጥ በራሱ ቋንቋ ስላስተጋቡለት ነው፡፡ (ስስ ብልቱን አግኝተውታል!) መፍትሄውም እንዳላቸው ትራምፕ ተናግረዋል፡፡ ግብር እቀንሳለሁ … ኢኮኖሚውን አሳድጋለሁ … በውጭ ያሉ የአሜሪካ ኩባንያዎች አገር ውስጥ እንዲገቡ አደርጋለሁ … ህገ ወጥ ስደተኞችን አባርራለሁ … አይሲስ ላይ የማያዳግም እርምጃ እወስዳለሁ ወዘተ….በማለት፡፡ በሌላ በኩል ፖለቲካውን አብጠርጥረው ያውቁታል የሚባሉት ሂላሪና ፓርቲያቸው የአሜሪካን ህዝብ አንገብጋቢ ፍላጎት ማስተጋባት አልቻሉም፡፡ እናም ዱብዕዳ ለሆነባቸው ሽንፈት በቁ፡፡ (What a pity!)  
ለዚህ ነው ዘመኑ ለፖለቲከኞች ብሩህ አይመስልም ያልኩት፡፡ ወደኛ አገር ስንመጣም ተመሳሳይ ሁኔታ እናስተውላለን፡፡ ባለፈው ጥቅምት ጠ/ሚኒስትሩ ያቋቋሙት አዲስ የሚኒስትሮች ካቢኔ እንደ ትራምፕ የባለጸጎች ስብስብ ባይሆንም ብዙ ፖለቲከኞች ያሉበት አይደለም፡፡ ይልቁንም በምሁራን (ቴክኖክራት) የተዋቀረ ካቢኔ ነው ማለት ይቻላል፡፡ አንዳንድ ተቃዋሚዎች፤ ‹‹የምሁራን ካቢኔ›› ማለታቸው ትዝ ይለኛል፡፡ (ትችት ነው ሙገሳ?) የዩኒቨርሲቲ ሴኔት ይመስላል ያሉም አልጠፉም! በአማራና ኦሮሚያ ክልሎችም በተመሳሳይ ካቢኔያቸውን በምሁራን ነው ያዋቀሩት። የትግራይ ክልላዊ መንግስት ባካሄደው የስልጣን ሹም ሽር ብዙ የዶ/ር ስያሜ ያላቸው ምሁራንን በመሾሙ ‹‹የዶክተሮች ካቢኔ›› ተብሎ ነበር፡፡ (የባሰባቸው አሽሙረኞች ደግሞ “ትግራይ ታማለች ወይ?›› ብለዋል) ዶክተሮች በዙ ለማለት ነው!
እናላችሁ … እዚህም እኛ አገር፣ ገዢው ፓርቲ/መንግስት ባደረገው ሹም ሽረት እንኳን ፊቱን ከፖለቲከኞች ወደ ምሁራን አዙሯል፡፡ (የፖለቲካ ስትራቴጂ ነው ወይስ የጥልቅ ተሃድሶ ውጤት?!) በሌላ በኩል ባለፈው ዓመት በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በተቀሰቀሰው የህዝብ ተቃውሞና ቁጣ፣ ፖለቲከኞች ከጨዋታው መገለላቸውን በግልፅ ታዝበናል፡፡ ወደ 70 ገደማ የሚደርሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳሉ በሚነገርባት ጦቢያችን፤ ህዝባዊ አመፁ መሪ አልባ ነበር፡፡ በተደራጀ የፖለቲካ ፓርቲ አለመመራቱና ባለቤት አልባ መሆኑ ከመንግስትም ከተቃዋሚም በኩል ስጋት ፈጥሮ ነበር፡፡ (ግዴላችሁም ዘመኑ የፖለቲከኞች አይደለም!)
ወደ ትራምፕ አገር ልመልሳችሁ፡፡ ለነገሩ አሜሪካ ለኢትዮጵያውያን እንደ ሁለተኛ አገር ናት፡፡ መኖሪያም መበልጸጊያም መሰደጂያም! ከአገራቸው መንግስት ጋር ዓይንና ናጫ የሆኑ አያሌ ጋዜጠኞች፣ ፖለቲከኞች፣ አክቲቪስቶች-------ወዘተ የከተሙባትና ነጻነታቸውን ያወጁባት አገር ናት - አሜሪካ፡፡ የኢኮኖሚም የፖለቲካም ነጻነት!! የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች ወደ አገር ቤት ለወዳጅ ዘመድ በሚልኩት ከፍተኛ ገንዘብ፣ መንግስትም ጭምር የዶላር ነጻነቱን በከፊል መቀዳጀቱ አልቀረም። (ቁ-1 የውጭ ምንዛሪ ምንጩ ነው!) እናላችሁ….ስለ ትራምፕ አገር ብናወራም ያምርብናል፡፡ (ባለ ድርሻ አካል ነን!)
በመጪው ጃንዋሪ 20, 2017 ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት፤ ‹‹ፖለቲከኞቹ›› እነ ኦባማ ከዋይት ሃውስ ይወጡና፣ ቢሊየነሮቹ የትራምፕ ካቢኔ አባላት አሜሪካን ይረከባሉ፡፡ (‹‹የፖለቲከኞች ምንቸት ውጣ! የቢሊየነሮች ምንቸት” ግባ! እንደማለት!) በነገራችን ላይ … የአሜሪካ ዲሞክራቶች እንደ ዘንድሮ በምርጫ መሸነፍ ሞት መስሎ የታያቸው ጊዜ የለም። (‹‹ከአንቺ መለየቱ ሞት መስሎ እየታየኝ›› አለ የሙዚቃ ንጉሱ!) እናም እስከ ምርጫ ውጤቱ ድረስ ዲሞክራሲን … ነፃና ፍትሃዊ ምርጫን … ውጤቱን በፀጋ መቀበልን… ወዘተ ሲሰብኩ የከረሙት ሂላሪ ክሊንተንና ፓርቲያቸው፤ ያልተጠበቀ የሽንፈት ዜናቸውን በሰሙ ማግስት አቋማቸው ተከረበተ፡፡ (ለማሸነፍ ብቻ ነበር የተዘጋጁት!) ዓለም ግን የአሸናፊነት መድረክ ብቻ ሆና አታውቅም፡፡ ለሽንፈታቸው ያልደረደሩት ሰበብ የለም፡፡ የፌስቡክ ፌክ ኒውስ … የፎክስ ኒውስ ቴሌቪዥን በየባሩ መሰቀል … የሩሲያ መንግስት (ፑቲን) በሃኪንግና ሊኪንግ ትራምፕ እንዲያሸንፍ ተጽእኖ ማድረግ------ወዘተ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ በዚህ ብቻ ግን አላበቁም፡፡ ምርጫው መጭበርበሩ በማስረጃ ሳይረጋገጥ በተለያዩ ግዛቶች ዳግም የድምፅ ቆጠራ እንዲካሄድ … አቧራ አስነስተዋል፡፡ (የገንዘብ ማሰባሰቢያ ስልት ናት ተብሏል!) ውጤቱስ ምን ሆነ? ዶናልድ ትራምፕ ተጨማሪ ድምፅ አገኙ። ከእነዚህ ሁሉ ሙከራዎች በኋላ ነው ኦባማ ድንገት ተነስተው፤ ‹‹በ2016 ምርጫ እኔ ብወዳደር ኖሮ ትራምፕን በዝረራ አሸንፈው ነበር›› ያሉት፡፡ የሚገርመው ደግሞ ኦባማ ስልጣን ከያዙ አንስቶ ባለፉት 8 ዓመታት ውስጥ ዲሞክራቶች ከ1ሺ በላይ መቀመጫዎችን አጥተዋል ተብሏል፡፡
ዓለም በእርጋታቸው የሚያውቃቸው የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፤ በ11ኛው የሥልጣናቸው ሰዓት ላይ መልካም ስምና ዝናቸውን ለማጥፋት እሽቅድምድም የገቡ መሰሉ፡፡፡ በ8 ዓመት የፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው ያላደረጉትን ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አሳክተዋል፡፡ አገራቸውን ከእስራኤልና ከሩሲያ ጋር ቅራኔ ውስጥ የሚከት አስከፊ ውሳኔና እርምጃ ወስደዋል፡፡ (ሌጋሲ ማስቀጠል ይሄ ነው እንዴ?)
በአሜሪካ የቀድሞ የተወካዮች ም/ቤት አፈ-ጉባኤና ደራሲ ኒውት ጊንግሪች፤ ከ‹‹አዲሱ የትራምፕ አስተዳደር ምን ይጠበቃል?›› በሚል ከፎክስ ኒውስ የቴሌቪዥን ጣቢያ በቅርቡ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፤ ‹‹… አስተዳደሩ ዋይት ሃውስ እንደገባ የመጀመሪያ ሥራው 60 ወይም 70 በመቶ የሚሆነውን የኦባማ ሌጋሲ መሻር ነው›› ብለዋል፡፡
ከጠቅላላ ሌጋሲያቸው ውስጥ 70 በመቶ ከተሻረ ምን ቀራቸው? (“ሌጋሲ አታሳጣኝ” ማለት ይኼ ነው!) በነገራችን ላይ ኦባማ፣በሂላሪ የምርጫ ዘመቻ ላይ ሲቀሰቅሱ፣ ደጋፊዎቻቸውን በሌጋሲያቸው አስፈራርተው ነበር;፡- “It is an insult to my legacy if we lost” በማለት፡፡(አልቀረላቸውም እንጂ!) የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ መሬት ይቅለላቸውና … ያረፉ ሰሞን፣ “ሌጋሲያቸውን እናስቀጥላለን” የማይል አልነበር! (የሚያዋጣው ሁሉም የራሱን ድርሻ ቢወጣ ነው!)
በመጨረሻ “የኦባማ ሌጋሲ ምን ሊሆን ነው?” ብላችሁ አጥብቃችሁ ከጠየቃችሁ፣ መልሱ “የዕዳ ክምር” የሚል ነው (“አጥብቆ ጠያቂ የእናቱን ሞት ይረዳል” አሉ!) እ.ኤ.አ በ2009 ኦባማ በፕሬዚዳንትነት ዋይት ሀውስ ሲገቡ፣ የአገሪቱ ጠቅላላ ዕዳ 10.6 ትሪሊዮን ዶላር እንደነበር ያስታወሰው ዘ ዋሽንግተን ታይምስ፤ ከሥልጣን የሚወርዱት አገሪቷን ለ20 ትሪሊዮን ዶላር ዕዳ ዳርገው ነው ብሏል፡፡ የኦባማ ሌጋሲ - የ20 ትሪሊዮን ዶላር ዕዳ ነው  ማለት ነው፡፡ (ከዕዳ ሌጋሲ ይሰውረን!)
ፀሎት ወይም ምኞት ብቻ ግን ዋጋ የለውም። በዕውቀት አስልቶ መራመድን ይጠይቃል። ዕውቀት ብቻ ሳይሆን ታላቅ ስነ ምግባርንም ይፈልጋል። የመንግስት የውጭ ዕዳ በ10 ዓመት ውስጥ ከ2 ቢ.ዶላር ወደ 22 ቢ.ዶላር ተመንድጓል። ያስፈራል! ህልም ተፈርቶ ሳይተኛ አይታደርም እንዲሉ --- ከልማት መታቀብ አይመከርም። ልማታዊ መንግስታችን እየተበደረ ማልማቱም ክፋት የለውም፡፡ ዋናው በግልጽነትና በተጠያቂነት ነው ወይ ፕሮጀክቶች የሚከናወኑት የሚለው ነው። ወደ 77 ቢ. ብር ወጥቶባቸው ለአስር ዓመት ያልተንቀሳቀሱት የስኳር ፋብሪካዎች እምን ደረሱ? ለእስካሁኑ ጥፋት ምን እርምጃ ተወሰደ? በጠቅላላ ምን ያህል ገንዘብ ከሰረ? ለመዘግየቱና ለኪሳራው ተጠያቂው ማን ነው? ከመንግስትም ሆነ ከጠ/ሚኒስትሩ ደፋር ውሳኔና እርምጃ ይፈልጋል፡፡ (ያለዚያ ነገም ይቀጥላል!) የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ኸርበርት ሁቨርት ስለ አገር የገንዘብ ዕዳ ሲናገሩ፤ - “ወጣቱ ትውልድ የተባረከ ነው፤ ዕዳን ይወርሳልና” ሲሉ ቀልደዋል፡፡ (ቀልዱ ግን ብዙ ጊዜ እውነት ይሆናል!)

Read 4693 times