Print this page
Saturday, 17 March 2012 09:23

የጨጓራ በሽታ - የታዳጊ አገር ህዝቦች ችግር

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(10 votes)

ቅመም፣ ቅባትና በርበሬ የበዛባቸው ምግቦች የጨጓራ በሽታን ሊያባብሱ ይችላሉ…

አዲሱ ቴክኖሎጂ በሽታውን የመጠቆም አቅሙ አስተማማኝ ነው…

ሰውነቷ በላብ ተዘፍቋል፡፡ አናቷን እየወቀረ ከሚያሰቃያት ራስ ምታት ፋታ ለማግኘት፣ ራሷ ላይ ያሰረችውን ጨርቅ ፈታ ጣለችው፡፡ ሽቅብ ሽቅብ እያለ ከሚታገላት የማስመለስ ስሜት ትንሽ ፋታ አግኝታለች፡፡ የእናቷን ትከሻ ደገፍ ብላ ከተቀመጠችበት ተጠጋኋት፡፡ የህመም ስሜቱ ከጀመራት ሳምንታት ቢቆጠሩም እንዲህ የባሰባት ግን ሰሞኑን መሆኑን እናቷ ነገሩኝ፡፡

ለህክምና ያልሄደችበት ሆስፒታል፣ ያልረገጠችው የሃኪም ደጅ የለም፡፡ ጨጓራ፣ የአንጀት ቁስለት፣ የምግብ መመረዝ፣ ለበሽታዎቹ ከሃኪሞች የተሰጡ ስያሜዎች ናቸው፡፡ ከየሄደችባቸው የህክምና ቦታዎች የሚታዘዙ መድሃኒቶችን ቤተሰቦቿ ገዝተው ለማቅረብ ባይሰንፉም፣ ለእሷ ግን ውጤት አላመጡላትም፡፡ ዕለት ከዕለት የበላችው አልረጋ እያላት ክፉኛ ተቸግራለች፡፡

በዩኒቨርሳል ክሊኒክ ያገኘኋት ወጣት በቅርቡ ወደ አገር ውስጥ ገብቶ አገልግሎት መስጠት በጀመረው የጨጓራ ህመም መመርመሪያ መሣሪያ ለመታየትና ከደዌዋ ለመዳን በመጓጓት ነው ወደ ክሊኒኩ የመጣችው፡፡ በአንድ የግል ድርጅት ውስጥ በፀሐፊነት ተቀጥራ የምትሠራው የ24 አመቷ ወጣት፤ አልፎ አልፎ ጨጓራዬን ያመኛል ከማለቷ በስተቀር የከፋ ህመም እንደሌላት ያጫወቱኝ እናቷ፤ የሁዳዴ ፆም ከገባ ወዲህ ግን ህመሙ እየበረታባትና ዕለት ተዕለት እያሠቃያት እንደሆነ ነግረውኛል፡፡ በየጊዜው ህክምና የሚያደርጉላት ሃኪሞች የአመጋገብ ሥርዓቷን እንድታስተካክልና በሰዓቱ እንድትመገብ ቢነግሯትም በጄ አላለችም ይላሉ - እናቷ፡፡

በሥራዋ ምክንያት ቤተክርስቲያን ሄዳ ማስቀደስ ባትችልም፣ ምግብ የምትበላው ግን ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ እንደሆነ ይናገራሉ - የህመሙ መባባስ ሰበቡ የአመጋገቡ ስርዓቷ መዛባት ሊሆን እንደሚችል በመጠርጠር፡፡

የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስትና በዩኒቨርሳል ከፍተኛ ክሊኒክ ቴዎድሮስ ቅርንጫፍ፣ ሜዲካል ዳይሬክተርና ሐኪም የሆኑት ዶ/ር ምክሩ ታረቀኝ፤ ስለ ጨጓራ በሽታ ምንነት፣ መንስኤዎችና ህክምናው እንዲነግሩኝ ጠየኳቸው፡፡

ኤች ካይሎር ወይም ኤሌክትሮፖክትራ ካይሎር የተባለው ባክቴሪያ፣ ለጨጓራ በሽታ መንስኤ ሲሆን ባክቴርያው በታዳጊ አገር በሚኖሩ ህዝቦች ላይ ከፍተኛ ስርጭት እንዳለው ዶ/ር ምክሩ ይናገራሉ፡፡ የታዳጊ አገር ህዝቦች የአኗኗር ሁኔታና የንፅህና ጉድለት ባክቴሪያው ከፍተኛ ስርጭት እንዲኖረው ማድረጉን የጠቆሙት ሃኪሙ፤ የባክቴሪያው ስርጭት በአደጉ አገሮች እየቀነሰ መምጣቱን ገልፀው በታዳጊ አገሮች ላይ ግን አሁንም ከፍተኛ መሆኑንና ዘጠና በመቶዎቹ የታዳጊ አገር ህዝቦች የዚህ ባክቴሪያ ተሸካሚ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡

ሁለተኛው የጨጓራ በሽታ መንስኤ ከአሲድ መጨመር ጋር ተያይዞ የሚመጣ ችግር ሲሆን ይሄውም ከተለያዩ መድሃኒቶች በተለይም ለህመም ማስታገሻ እየተባሉ በሚወሰዱ መድሃኒቶች ምክንያት የሚመጣው የጨጓራ ቁስለት እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ ጨጓራችን ለሚያከናውነው ምግብ የመፍጨት ሂደት አስፈላጊ የሆኑ ተፈጥሮአዊ የአሲድ መጠን በተለያዩ ሁኔታዎች ሊጨምር ይችላል፡፡ ለምሣሌ በተለያዩ ሆርሞናል ችግሮች፣ ልዩ ልዩ ከፍተኛ በሽታዎች የሚፈጥሩት ጫናዎች ለአሲድ መብዛት አስተዋፅኦ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ ከአልኮል መጠጣትና ከሲጋራ ማጤስ ጋር ተያይዞ የሚመጡ ችግሮችም ለጨጓራ ቁስለት ሊዳርጉ ይችላሉ፡፡

የጨጓራ ቁስለት በአብዛኛው ዕድሜያችን ከፍ እያለ ሲሄድ እየጨመረ የሚሄድ ችግር ነው፡፡ በሽታው እንደየደረጃው ለተለያዩ የጤና ጠንቆች የሚዳርግ ሲሆን አልሰር የሚባለው ደረጃ ላይ ሲደርስ የጨጓራ ግድግዳ ሊደማ ይችላል፡፡ ይህ ደግም አጣዳፊ ሞትን ሊያስከትል እንደሚችል የህክምና ባለሙያው ይናገራሉ፡፡ የጨጓራ ግድግዳ ሙሉ በሙሉ ሊበሣ እንደሚችል የሚናገሩት ዶ/ሩ፤ “ይህም የተለያዩ ኬሚካሎች ወደ ነፃው የሆዳችን ክፍል እንዲገቡ በማድረግ ለኢንፌክሽንና ፔሪቶራይትስ ለሚባለው ለሞት የሚዳርግ የበሽታ ዓይነት ሊያጋልጥ ይችላል፡፡ አንዳንድ ጊዜም የጨጓራ ጠባሣ በመፍጠር ከጨጓራ ወደ አንጀት የሚያስተላልፈው ቱቦ እንዲዘጋ ስለሚያደርግ የምንመገበው ምግብ እንዳያልፍና የተለያዩ ንጥረ ነገሮች ለሰውነታችን እንዳይደርሱ በማገድ፣ ለንጥረ ነገር እጥረት በሽታዎች እንድንጋለጥ ያደርገናል” በማለት አብራርተዋል፡፡

አንዳንድ የጨጓራ አልሰሮች የካንሰር ባህርይ ይኖራቸውና ካንሰር ሆነው ለሞት ሊዳርጉን ይችላሉ - ብለዋል ባለሙያው፡፡

የጨጓራ በሽታ የህመም ስሜት ወጥ የሆነና በሁሉም ህሙማን ላይ የሚከሰት ስሜት እንዳልሆነ የሚናገሩት ዶ/ሩ፤ ለአንዱ የጨጓራ በሽታ ታማሚ የማይስማማው የምግብ አይነት ለሌላው ሲስማማው፣ በአንድ ወቅት የተስማማው የምግብ አይነት ለዚያው ታማሚ በሌላ ጊዜ ላይስማማው ይችላል በማለት የምግብ አይነት ለበሽታው መባባስ ምክንያት ሊሆን ይችላል የሚል ድምዳሜ ላይ መድረስ አለመቻሉን ተናግረዋል፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ ግን ቅመም፣ ቅባትና፣ በርበሬ የበዛባቸው ምግቦች የጨጓራ በሽታን ሊያባብሱ እንደሚችሉ ጥናቶች ማረጋገጣቸውን ጠቁመዋል፡፡

ሁለት አይነት የጨጓራ አልሰር ችግሮች መኖራቸውን የጠቆሙት ዶ/ር ምክሩ፤ እነዚህም ጋስትሪክ አልሰርና ዲኦዲን አልሰር እንደሚባሉና ጋስትሪክ አልሰር ምግብ በሚመገቡበት ጊዜ የህመም ስሜቱ የመቀስቀስ ባህርይ ሲኖረው፣ ዲአዲን አልሰር የሚባለው ደግሞ ምግብ ሲመገቡ የህመም ስሜቱ እንደሚጠፋና ለህመምተኛው እረፍት እንደሚሰጠው ይገልፃሉ፡፡

የጨጓራ በሽታ በርካታ ሰዎችን የሚያጠቃ በሽታ ቢሆንም በህክምና መፍትሔ እንዳለውና ተስፋ ሣይቆርጡ ክትትል ካደረጉ ሙሉ በሙሉ ከህመሙ ሊፈወሱ እንደሚችሉም ዶክተሩ ይናገራሉ፡፡ ቀደም ሲል የበሽታውን መንስኤ ለማወቅ የተለያዩ የምርመራ ዘዴዎችን ይጠቀሙ እንደነበረ የተናገሩት ዶክተሩ፤ የደም ምርመራ፣ ኢንዶስኮፒና የሰገራ ምርመራ እንደሚገኙበት ገልፀዋል፡፡ እነዚህ የምርመራ ዘዴዎች የጨጓራ በሽታ አምጪ ባክቴሪያው መኖር አለመኖሩን ከመጠቆም የዘለለ ጥቅም የሌላቸው ከመሆኑም በላይ በሽታው ከጠፋም በኋላ አለ የሚለውን አመላካች ነገር በማሳየት ህመምተኛውን ለአስፈላጊ ወጪና ለመድሃኒት ተጋላጭነት እንደሚዳርገው ይናገራሉ፡፡ አሁን ግን ይህንን የሚያስቀር አዲስ ቴክኖሎጂ ወደ አገራችን ገብቷል፡፡  በዚህ አዲስ ቴክኖሎጂ አማካኝነትም ህክምናውን ለህሙማን በመሥጠት ላይ እንደሆኑ ባለሙያው ተናግረዋል፡፡

ችግርን ማወቅ የመፍትሔ ግማሽ አካል ነው እንደሚባለው፣ አዲሱ የምርመራ ቴክኖሎጂ ለበሽታው አምጪ ባክቴሪያ ከፍተኛ የሆነ Sensitivity እና Specifty  (ትክክለኛውን የመንስኤ ሁኔታ የመናገር ወይም የመጠቆም አቅም) እንዳለው ተገልጿል፡፡

በዚህም ቀደም ሲል ከነበሩት የምርመራ ዘዴዎች የተሻለና ወደ መቶ ፐርሰንት ሊጠጋ የሚችል አስተማማኝነት ያለው የምርመራ አይነት እንደሆነም  ዶክተሩ ይናገራሉ፡፡

በአደጉት አገራት ቴክኖሎጂውን ላለፉት ሰባትና ስምንት አመታት ሲጠቀሙበት የነበረ ሲሆን ባለፈው ወር መጨረሻ አካባቢ ወደ አገራችን ገብቶ ህክምናው በመሰጠት ላይ መሆኑን ባለሙያው አክለው ተናግረዋል፡፡

ዩሪያ ፕሬስ ቴስት /በትንፋሽ የመመርመሪያ መሣሪያ/ ምርመራ ከመካሄዱ በፊት ህመምተኛው አሲድ ቀናሽ ከሆኑ መድሃኒቶች ቢያንስ ለሁለት ሣምንት፣ ለኢንፌክሽን ከሚወሰዱ አንቲባዮቲክ መድሃኒቶች ቢያንስ ለአንድ ወር መታቀብ እንደሚገባውና በምርመራው ዕለትም ምግብ ሣይመገብ ወደ ክሊኒኩ በመሄድ ህክምናውን ለማግኘት እንደሚችል ዶክተር ምክሩ ተናግረዋል፡፡

ለዚህ ምርመራም 490 ብር እንደሚከፈልና እስከ አሁን ድረስ ከ150-200 የሚደርሱ ሰዎች የህክምናው ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉ ገልፀውልናል፡፡

 

 

Read 16001 times Last modified on Saturday, 17 March 2012 11:51