Wednesday, 25 January 2017 07:17

በሰላም አገር "ትግል" እና "መስዋዕትነት" ምን አመጣው?

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(5 votes)

 *ከሹመት በፊት "ብቃት ፈታኝ" - አፋጣጭ ጥያቄዎች ይለመዱ!
            
      ክቡር ጠ/ሚኒስትሩ ጠፍተው ጠፍተው፣(ለግል ፕሬሱ ማለቴ ነው!) ባለፈው ሰሞን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በፓርላማም ተገኝተው ለም/ቤቱ አባላት "ለስላሳ ጥያቄዎች" ማብራሪያና ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ የሰጡትን ምላሽና ማብራሪያ ስከታተል ታዲያ… አንዳንድ ያልገቡኝና መጥራት ያለባቸው "ብዥታዎች" ተፈጥረውብኛል፡፡ ምናልባት እናንተም ዘንድ ተፈጥሮባችሁ ሊሆን ይችላል፡፡ እናም ብዥታዎቹን እያነሳሁ አወጋችኋለሁ፡፡ ዓላማውም አንድና አንድ ብቻ ነው፡፡ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ ህገ መንግስታዊ መብቴን መተግበር! መጠቀም! መለማመድ! (ህገ መንግስት ውስጥ የተቀመጠ መብት፣ እንደ ባንክ ገንዘብ አይወልድም!!)
ከዚያ በፊት ግን ወደ ትራምፕ አገር ላሻግራችሁና ------ አንድ የቀናሁባቸውን ፖለቲካዊ ተሞክሮ ላካፍላችሁ፡፡ በትላንትናው ዕለት የፕሬዚዳንትነት በዓለ ሲመታቸውን ያከበሩት 45ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ለሁለት ወራት ያህል የካቢኔ አባሎቻቸውን ሲመርጡ ነበር የቆዩት፡፡ ሰሞኑን ደግሞ እሳቸው የመረጧቸው እጩዎች በሴኔት ቋሚ ኮሚቴ ሲገመገሙና በጥያቄ ሲፋጠጡ ነው የሰነበቱት፡፡ እኔ በቪዲዮ የተመለከትኩት ለመከላከያ ሚኒስትርነት የታጩትን የጀነራል ጂም ማቲሰን እና ለጠቅላይ አቃቤ ህግነት የታጩትን የጄፍ ሴሽንስ የግምገማ ሂደት ነበር፡፡ (ግምገማ ነው የወንጀል ምርመራ?) በእርግጥ ከአፋጣጭ ጥያቄዎች በተጨማሪ ለእጩዎቹ ምስክርነት የመስጠት ሂደትም አለ፡፡ ሴናተሮች ስለ እጩዎቹ ብቃት ማስረጃ እየጠቀሱ ይናገራሉ፤ያብራራሉ፡፡ ስለ ትምህርታቸው፣ ስለሚያነቡትና ስለጻፏቸው መፃህፍት፣ ስለ ሥራ ልምዳቸው፣ ስለ ህይወት ተሞክሯቸው፣ስለ ቤተሰቦቻቸው ወዘተ ----- ለቋሚ ኮሚቴው እማኝነታቸውን ይሰጣሉ፡፡ ይሄን አጠቃላይ ሂደት - Confirmation hearing ይሉታል፡፡ (እኔማ በቅናት ተንጨረጨርኩ!) አንዳንዴ እንዲህ ያሉ አሰራሮችን ለምን አንኮርጅም ብዬ አሰብኩ፡፡ እናላችሁ-----ከሹመት በፊት "ብቃት ፈታኝ" - አፋጣጭ ጥያቄዎች ቢለመዱ፣ትክክለኛ አቅምና ብቃት ያለውን እጩ ለመምረጥ በእጅጉ ይጠቅማሉ፡፡  
እኔ የምለው------"ኢህአዴግ ነፍሴ" የምርጫ ሥርዓቱን ከየትኛው አገር ነው የቀዳው? (ለወቀሳ ሳይሆን ለጠቅላላ ዕውቀት ነው!) ለነገሩ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ መስከረም ላይ ፓርላማ ሲከፍቱ፣ የምርጫ ህጉ እንደሚሻሻል ቃል ስለገቡ ብዙም አያስጨንቀንም፡፡ ከተጨነቅንም መጨነቅ ያለብን፣ እንዴት ነው የሚሻሻለው በሚለው ላይ ነው፡፡ በመጀመሪያ ክፍተቱ ያለው የቱ ጋ ነው? የሚሻሻለው ምን ውጤት ለማምጣት ነው? ምርጫ ህጉ ብቻ ነው ወይስ ምርጫ ቦርዱም መሻሻል ይፈልጋል? እኒህን ጥያቄዎች ለመመለስ ደግሞ ውይይት - ድርድር - ይፈልጋል፡፡ ደግነቱ ተቃዋሚዎች ሲወተውቱት የነበረው የድርድር መድረክ ዘግይቶም ቢሆን ምላሽ ያገኘ ይመስላል፡፡ ባለፈው ረቡዕ ሂደቱ ተጀምሯል፡፡ ውጤቱ ባይታወቅም ተስፋ ይሰጣል፡፡ እንደ በፊቱ "የሥነ ምግባር ደንብ የፈረሙ፣ያልፈረሙ" የሚል ቅድመ ሁኔታ ሳይኖር  ሁሉም ፓርቲዎች መጋበዛቸው በጎ ጅምር ነው፡፡ አሁንም ግን ከሁለቱም ወገን አስልቶ መራመድን ይፈልጋል - ጅምሩ እንዳይፈርስ፡፡ እናም ፓርቲዎች ------ እንደ ወትሮው ልዩነቶች ላይ ማተኮራቸውን ትተው፣ከእልህና ከብሽሽቅ አዙሪት ወጥተው --- ወክሎናል ለሚሉት ህዝብ በአንድ ልብ መሥራት መጀመር አለባቸው፡፡
ኢህአዴግም ሆነ መንግስት ሁሉንም ሚዲያ በእኩል ዓይን ማየት ይጠበቅበታል፡፡ ድርድሩ ባለፈው ሳምንት በተወካዮች ም/ቤት ሲጀመር፣ ፋና ብሮድካስቲንግና ኢቢሲ ሂደቱን እንዲዘግቡ ሲፈቀድላቸው፣ ሌሎች የመንግስትና የግል ሚዲያዎች ግን ተከልክለው ነበር፡፡ ሁሉንም በእኩል አለማየት ማለት ይኸው ነው፡፡ በጥልቀት መታደስ ይቺን ይቺን እንኳ ካላሻሻለማ "ታጥቦ ጭቃ" መሆን ነው፡፡ (የኋሊት ጉዞ በቃን!!)
አሁን በመንደርደሪያዬ ላይ "ብዥታዎች" ወዳልኩት ጉዳይ ልግባ፡፡ እኔ የምላችሁ ----- ኢህአዴግ ‹‹መስዋዕትነት›› የሚለው ነገር ከምር ነው እንዴ? (በሰላም አገር የምን መስዋዕትነት ነው!?) ክቡር ጠ/ሚኒስትሩ በቅርቡ በፓርላማ ሲናገሩ፤‹‹ኢህአዴግ የመስዋዕትነት ድርጅት እንደመሆኑ… ለመስዋዕትነት ዝግጁ መሆን ያስፈልጋል›› ብለዋል፡፡ (ፈጽሞ አልገባኝም!)
ከሹም ሽረቱ ጋር በተያያዘ ለጋዜጠኞች ሲመልሱም፣የመስዋዕትነትን ነገር አንስተውታል፡፡  (ተደጋገመብኝ እኮ!)
 “እጅግ አብዛኛውን አመራር እያጠቃ ያለው ለሥራ ከመትጋትና መስዋዕትነት ከመክፈል ይልቅ መዝናናትን የመምረጥ፣ ባለጉዳይን ያለማስተናገድ፣ ቢሮ ያለመገኘት፣ ወይም ዝግ መሆን፣ ከሥራ ሰዓት ውጭ ያለመስራት (“ፅድቁ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነነኝ!” አሉ)፣ እንደ ማንኛውም ሲቪል ሰራተኛ 11 ሰዓት ሲሆን ከቢሮ ወጥቶ መሄድ፣ የተለያዩ ጉዞዎችን የማብዛትና የመሳሰሉት ውጤታማ የማያደርጉ ዝንባሌዎች ይታያሉ”
ምናልባት ኢህአዴግ ------ "መስዋዕትነት" የሚለን ከ11 ሰዓት በኋላ አርፍዶ መስራትን ከሆነ፣ትክክለኛ መጠሪያው "Over Time" ይመስለኛል፡፡ እናም አስፈላጊ ሆኖ የመንግስት ሃላፊዎች ከ11 ሰዓት በኋላ አርፍደው የሚሰሩ ከሆነ፣ የትርፍ ሰዓት ክፍያ ሊከፈላቸው ይገባል እንጂ "መስዋዕትነት" የሚል መጠሪያ ሊሰጠው አይገባም፡፡
እውነቱን ልንገራችሁ አይደል … የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮች አንዳንዴ “ትግል” እና “መስዋዕትነት” የሚለውን ቃል ደጋግመው ሲጠቅሱ፣ የድሮው ትዝ እያላቸው ወይም አፋቸው ላይ እየመጣባቸው ይመስለኝ ነበር፡፡ (“ጓድ” እንደሚባባሉት!) የምራችንን ነው የሚሉ ከሆነ ግን ነገርዬው በደንብ መጥራት አለበት፡፡ (ግራ ገባና!)
ቆይ አሁን ለምሳሌ "ኢህአዴግ ነፍሴ" ለ25 ዓመታት ምን ስሰራ ኖርኩ ይላል? "ጦቢያን እየመራ ወይስ መስዋዕትነት እየከፈለ?" ሁለተኛውን የሚል ከሆነ እኮ በየሚዲያው የሚጻፈው ነገርም መለወጥ አለበት፡፡ (ታሪኩ አይደለማ!) እናላችሁ --- “ለሩብ ክ/ዘመን በስልጣን ላይ የቆየው ኢህአዴግ” የሚለው አገላለጽ ስህተት ነው ማለት ነው፡፡ እናም “ለሩብ ክ/ዘመን እየታገለና “መስዋዕትነት” እየከፈለ የቆየው ኢህአዴግ” በሚል መታረም አለበት፡፡ የምን ትግል? የምን መስዋዕትነት? ብሎ የሚጠይቅ ካለ ግን፣መልሱን የሚያውቀው ኢህአዴግ ብቻ ነው፡፡
አሁንም ነገርዬውን በደንብ እናጥራው፡፡ ኢህአዴግ ደርግን ጥሎ ስልጣን እስኪይዝ ድረስ፣ለ17 ዓመታት በ “ትግል” ላይ እንደነበር፣ብዙ “መስዋዕትነት”ም እንደከፈለ እንኳን እኛ ማንም አይክደውም፡፡ ታሪክ ነው፡፡ እኔ የምጠይቀው ግን ላለፉት 25 ዓመታት በሥልጣን ላይ ስላለው ኢህአዴግ ነው፡፡ እኔ የምጠይቀው ከዕለታት አንድ ቀን "አውራ ፓርቲ ነኝ" ብሎ ስለነገረን ኢህአዴግ ነው፡፡ (በ“መስዋዕትነት” ዙሪያ ኮንሰንሰስ ያስፈልጋል!)
እኔ የምላችሁ ግን------አንድ ሚኒስትር የተሾመበትን መ/ቤት በብቃት ከመምራት ወይም የተሰጠውን ሃላፊነት በአግባቡ ከመወጣት ሌላ የምን መስዋዕትነት ነው የሚጠበቅበት? በአገሪቱ አቅም የሚኒስትር ደሞዝ ይከፈለዋል … እንደ ደንቡ ሁለት ወይ ሦስት አጃቢ ጋርዶች (ደህንነቱን ጠባቂ) ይመደብለታል … ያማረ ቪላም ይኖረዋል …. በV8  ይፈሳል ---- (ይሄ እንዴት ነው መስዋዕትነት የሚሆነው!?) ሰሞኑን ደግሞ ከሃላፊነት ለሚነሱ ወይም የአገልግሎት ዘመናቸውን ለጨረሱ የመንግስት ሹመኞች የሚሰጡ ጥቅማጥቅሞችና የአበል ክፍያዎችን የሚያሻሽል ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ ቀርቦ፣ወደ ሚመለከተው አካል መላኩ ተሰምቷል፡፡ (ለአንጋፋ የኢህአዴግ አመራሮች “የ25 ሚ. ብር ቪላ” የተባለው ቀረ እንዴ?)  
ይታያችሁ ----- የመንግስት ከፍተኛ ኃላፊ ከአሁን በኋላ እንጃ እንጂ እስካሁን "ኃላፊነትህን በብቃት አልተወጣህም" ተብሎ የተወቀሰም የተከሰሰም የለም፡፡ “ኢህአዴግ ነፍሴ” የምን ትግል … የምን መስዋዕትነት ነው የሚያወራው? (ስልጣንና መስዋዕትነት ተምታቶበታል?) እናላችሁ------የመንግስት ሥልጣንና ሃላፊነትን እንደ መስዋዕትነትና እንደ ትግል መቁጠሩ ግራ ያጋባል፡፡ (የሥልጣን ጡር አለው!) በነገራችን ላይ የመንግስት ስልጣን እንደ መስዋዕትነት፣ ሥራው እንደ ትግል የሚቆጠርበት ብቸኛ አገር … ኢትዮጵያ… ከኢትዮጵያም ደግሞ ኢህአዴግ ብቻ ይመስለኛል፡፡ (መቼም ተቃዋሚዎች ሥልጣን መስዋዕትነት ነው አይሉም!)

Read 3669 times