Monday, 30 January 2017 00:00

እኔ፣ ሽክናና ቅኝ ግዛት

Written by 
Rate this item
(3 votes)

  ‹‹ወታደሩን በምን ያህል መጠን እናጠናክረው? ለእናት አገራችን በአስቸኳይ አንድንደርስ፣ ይሄ ቀዳዳ ሳይከፈት…ነገር ግን በሕግ አንበይናለን፤ እናስፈፅማለን እንላለን…ገና ጦር ሜዳ ሄዶ ጠላቱን አይቶ መግደሉን ወይም መሞቱን ሳያውቅ ከመኪና ላይ በራሱ እየወረደ የሚሞት ወጣት ነው ያለው፡፡ ምንድን ነው ይሄ? ከኢትዮጵያ ነው እንዴ የበቀለው?...››
አሉ አሉ ጓድ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃ/ማርያም፡፡
ከፍርሃታችን አለማፈራችን፡፡
ከእሳቸው በላይ እኔ አርሬአለሁ፡፡ ‹‹ምንድን ነው ይሄ ታለ? ከኢትዮጵያ ነው አንዴ የበቀለው?›› ብያለሁ፡፡ እሳቸው አጣለሁ ብለው ከሰጉት በላይ እኔ ሰግቻለሁ፡፡ ‹‹ፍቅራችንን በምን ያህል መጠን እናጠናክረው? ለሲፈን በአስቸኳይ እንድንደርስ፣ ይሄ ቀዳዳ ሳይከፈት…›› ብያለሁ፡፡
የቱ ቀዳዳ? መንግሥቱ እኛን የሚፈልጉን እንደ ጋሽ ሩፌ ጭቃ፣ ቀዳዳ ለመድፈን ነው እንዴ? እያነሱ ሊመርጉን፤ ትንሽ ሽንቁር ላይ ልክክ ስንል ‹‹ለእናት ሀገሩ አኩሪ መስዋዕትነት ከፍሎ…›› እንባላለን እንደ አባቴ፤ አይ ወንድ!
እነ ሸክና እኔ ቤት ሦስት ቀን አደሩ፡፡ ሽክና በእናቱ ሀገሩ እጅግ አድርጎ ተበሳጨ፤ በተለይ የጠጅ አቅርቦት ከተቋረጠ የኢትዮጵያን የሶስት ሺህ አመት ነፃነት ይገፍፋል፡፡
‹‹ተገዝተናል!›› ይላል ቀበኛ ያኘከው ጨርቅ በመሰለ ፊቱ ላይ ብስጭት እያስነበበ፡፡
ፈርተን የተሸሸግን ቢሆንም አንዳንዶች ይሄንን ሀሳብ በጀግንነት ይዋጋሉ፡፡
‹‹አሲዙ፣ እኔ እረታችኋለሁ›› ይላል ሸክና፡፡
ጨዋታ ሞቅ ሲል ሴቶቹ አብዮት ጠባቂ ከሚጠብቁበት ከዋርድያ ነቅለው ይመጣሉ፡፡
‹‹አንተ ምን ታሲዛለህ?›› ምንም እንደሌለው ያወቁ፡፡
‹‹እስክሞት ቀጥቅጡኝ›› ይላል፡፡
ሽክናን ለመምታት ሰበብ የሚፈልገው ሳኮ የመጀመሪያዋን ሃያ አምስት ሳንቲም ይጥላል፡፡
‹‹ይኸው፣ እዩ ደሞ!››
‹‹እንምርህም ግን››
‹‹አትማሩኝ››
‹‹ከሁለተኛ ፎቅ እንደመዝለል ይቆጠራል››
‹‹ንፋስ ይወስደዋላ››
ሣቅ!!
ሽክና ለውርርድ የቀረበውን ፍራንክ አይቶ ‹‹‹ለዚችማ ብዬ ውርርዴን አላበላሽም›› አለ፡፡
እልህ የያዛቸው ጨመሩ፡፡
‹‹አሁን ይቻላል! ስምንት ብርሌ ጠጅ በቂ ነው።››
‹‹በውርርዱ ካላሸነፍክ ተመላሽ ነው አትጠጣ››
‹‹ለሱ ግድ የለም፡፡›› አለና ቀጠለ፡፡ ‹‹እዚህ ሰፈር ያሉትን ስሞች ስነግራችሁ መዝግቡ››
‹‹እሺ›› መዝጋቢ ተመደበ
‹‹ሩፌ›› አለ
‹‹ሩፌ›› ተመዘገበ
‹‹ዎሌ፣ መዘገባችሁ? ቸሩ፣ ዶሪ፣ ሳኒ፣ መዘገባችሁ? ድገሙልኝ፤››
‹‹ሩፌ›› ሲሉ
‹‹ሩፍ ከሚለው እንግሊዘኛ ነው የተገኘው፡፡ ጣሪያዬ ማለት ነው››
‹‹ዎሌ››
‹‹ዎል ከሚለው እንግሊዝ ቃል የተገኘ ነው ወለሌ››
‹‹ቸሩ››
‹‹ቸር ወንበር ነው፡፡ ወንበሬ››
‹‹ዶሪ››
‹‹ዶር፤ በሪሁን ማለት ነው››
‹‹ሳኒ››
‹‹ሰን፣ ፀሀይ አይደል ፀሐዬ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ የእንግሊዝ ቅኝ ተገዢ እንደነበረች በዚህ ይታወቃል፡፡››
የሚስቀው ሳቀ፤ የሚናደደው ተከራከረ፡፡
‹‹በእንግሊዝ ቀኝ አልተገዛንም ካለች እንደ እኔ በማስረጃ ተከራከሩ››
‹‹ነው እንዴ? አንተ? እንግሊዝ ገዝታናለች?›› አለ ሳኮ፡፡ ‹‹ወይኔ የሙዜን አሰበሉኝ፣ ምን አሰዋሻቸው? ወይኔ የሻሜታዬን…››
ሽክና ጠጁን በሴቶቹ አስላከ፡፡
በሁካታ መካከል እናቴ ትመጣና አንዴ በግልምጫ ታነሳናለች፡፡ ‹‹እኔ እዚህ ነፍስና ስጋዬ ይቦጨቃል እናንተ ታወካላችሁ? እንዴት ያሉ ሀሳብ የለሾች!
ቻይና ስለእሷ የተጀመረው ወሬ እንዳይቀጥል ብቻ ለጥበቃ የተቀመጠች ይመስላል፡፡ ለመሳቅ ትሞክርና ሽክና ሲያያት ትኮሳተራለች፡፡ ያ ማር ነጋዴ ማን ይሆን? ከእኔ የባሰ ሳይፈርድበት አልቀረም፡፡ ማር የነካካ እጁን ወደኋላ አድርጎ ይሄኔ…
ምንጭ ፡- ‹‹በፍቅር ስም›› መፅሀፍ የተቀነጨበ
በደራሲ ዓለማየሁ ገላጋይ ከተፃፈው

Read 3864 times